August 30, 2011

“የሚሌኒየሙ አዳራሽ ጉባኤ ገንዘብ ደብዛው ጠፍቷል” (ነጋድራስ ጋዜጣ)

(ነጋድራስ፣ ቅጽ 08 ቁጥር 293፤ ዐርብ፣ ነሐሴ 20 ቀን 2003 ዓ.ም/ READ IN PDF)፡- “ገቢው ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናትና ጠዋሪ ቀባሪ ለሌላቸው አረጋውያን መርጃ” በሚል ታኅሣሥ 25 ቀን 2002 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደገባ አለመታወቁን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወቃል፡፡ የ(ነጋድራስ)ጋዜጣው ዘጋቢ በጉዳዩ ላይ ያሰባሰባቸውን መረጃ ይዞ ይመለከታቸዋል የተባሉ ወገኖችን ለማነጋገር ባደረገው ጥረት፣ በወቅቱ “ቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ” በመባል ይታወቅ የነበረው ማኅበር ተነሣሽነቱን መውሰዱን አረጋግጧል፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያክ ልዩ ጽ/ቤትም በቀን 07/03/2002 ዓ.ም በቁጥር ል/ጽ/141/2002 ለሚሌኒየም አዳራሽ የጻፈው ደብዳቤ ለማኅበሩ ትብብር እንዲደረግለት ይጠይቃል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ምንጮች ለዘጋቢው እንደጠቆሙት፣ ከተጠቀሰው ማኅበር አመራር አንዳንዶቹ ታዋቂ ዘፋኞችን ዱባይ እየወሰዱ ሲያዘፍኑ የቆዩ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ በመዝሙር ተደማጭነት ያገኙ አንዳንድ ዘማርያንን ስፖንሰር በማድረግ ከፍ ባለ [ፕሮሞሽን] ቢዝነስ ውስጥ የቆዩ መሆናቸውን ነው ያወሱት፡፡

ማኅበሩ ታኅሣሥ 25 ቀን 2002 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ ጉባኤ ከማካሄዱ በፊት ለቅዱስ ፓትርያሪኩ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች፣ ቅድሚያ ለማኅበሩ ዕውቅና በሚሰጥበትና የማኅበሩ መቋቋሚያ ሰነድ በፓትርያኩ ልዩ ጽ/ቤት ጸድቆ እንዲፈቀድ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት በቀን 23/02/2002 በቁጥር ል/ጽ/103/2002 የፓትርያክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በጻፉት ደብዳቤ ማኅበሩ የሚተዳደርበት ደንብ ተጠብቆ እንዲሠራበትና ይኸውም በቅዱስ ፓርያኩ መፈቀዱን የሚገልጽ ነው፡፡

“ስማችንና የሥራ ሓላፊነታችን አይገለጽ፤ ነገር ግን የተጠቀሰው ማኅበርና አመራሮቹ በቤተ ክርስቲያኗ ስም የሰበሰቡት ገንዘብ ለተቸገሩ ወገኖች ገቢ አልተደረገም፤ የሚመለከተው ሕጋዊ አካል ጥቆማችንን ይከታተል” ያሉት የጋዜጣው ምንጮች፣ በእጃችን የሚገኘው ሰነድ የማያወላዳ በመሆኑ ለሚጠይቁን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን እያሉ ነው፡፡

እንደነዚሁ ምንጮች ከሆነ፣ በሚሌኒየም አዳራሽ ይካሄዳል ከተባለው ጉባኤ በፊት በጉባኤው አዘጋጆች ማንነት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች እንደነበሩ ነው ያብራሩት፡፡ ይኸውም በወቅቱ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የማይታወቁ [ዕውቅና የሌላቸው] ወገኖች፣ በከተማው ባሉ አንዳንድ አዳራሾች በቤተ ክርስቲያኗ ስም ስብሰባ እና ገቢ የሚያስገኙ መርሐ ግብሮችን ያዘጋጁ ስለነበር፣ ይህ ማኅበርም መስመር የለቀቁ ሰባክያን እንደሚገኙበት በመጥቀስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሓላፊ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ማስጠንቀቂያ እንደሰጡ ታውቋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ በቀን 06/04/2002 ዓ.ም በቁጥር ስ/ወ/65/2002 ለመንበረ ፓትርያኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት በደብዳቤ እንዳሳወቁት፣ “… ስብከተ ወንጌል መሰበክ ያለበት መዋቅሩን ጠብቆ መሆን እንዳለበት በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን በስብከተ ወንጌል ዙሪያ በትጋት በዕቅድ እየሠራን ቢሆንም፣ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ስም ታኅሣሥ 25 ቀን 2002 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ መስመሩን በለቀቁ ሰባክያን ትምህርተ ወንጌል እንደተዘጋጀ ለማወቅ ችለናል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዐይነቱ ቤተ ክርስቲያን የማታውቀው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ስለሚፈታተን አርኣያነቱም መልካም ስላልሆነ መመሪያ እንዲሰጥበት በአክብሮት እንጠይቃለን፤” ብለው ነበር፡፡

ይሁንና ለፓትርያኩ ቅርብ የሆኑ ግለሰቦች /አንዲት ሴትን ጨምሮ/ ማሳሰቢያውን ወደ ጎን በማለት፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓለፊ ከሆኑት ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ ጋራ ባደረጉት ስብሰባ፣ በጉባኤው ስለሚመደቡ መምህራንና በዕለቱ የሚገባውን ማንኛውም ገቢ ስለማሳወቅ ተስማምተው፣ ይህንንም በቃለ ጉባኤ አስፍረው መለያየታቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው፡፡

እንደተባለውም ታኅሣሥ 25 ቀን 2002 ዓ.ም፣ ጉባኤው ከተካሄደ በኋላ የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር፣ በቀን 14/05/2002 በቁጥር 1035/02 ለስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በዝግጅቱ ላይ የጠገኘውን ገቢ በሚመለከት ተከታዩን ዝርዝር አሳውቆ ነበር፡፡
  • የታተመ ትኬት ብዛት 50,000፣ የአንዱ ዋጋ 30.00፣ ጠቅላላ ዋጋ 1,500,000፤
  • ያልተሸጠ ትኬት ብዛት 21,000፣ የአንዱ ዋጋ 30.00፣ ጠቅላላ ዋጋ 600,000
  • ተሸጦ ገቢው የተሰበሰበ 15,000፣ የአንዱ ዋጋ 30.00 ጠቅላላ ዋጋ 450,000
  • በሰው እጅ ያለ (ያልተሰበሰበ) 14,000፣ የአንዱ ዋጋ 30.00፣ ጠቅላላ ዋጋ 420,000
ሲሆን የገቢ ዝርዝሩ፡- በቼክ የተሰበሰበ 3,000.00፣ በዕለቱ የተሰበሰበ 24,998.00፣ በጥላ የተሰበሰበ 70,784.40፣ በዶላር የተሰበሰበ 101 ዶላር፣ ጠቅላላ ድምር 98,782.40 እንዲሁም በዕለቱ ቃል ተገብቶ “አልተሰበሰበም” በሚል 606,631.00 መሆኑን በማኅበሩ ሊቀ መንበር ኤፍሬም ኤርሚያስ (ከወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋራ የሕገ ወጥ ሰባክያንንና ዘማርያንን እንቅስቃሴ በማስተባበር የሚታወቅ፣ ለዚህም ተግባሩ በአዲስ አበባ ቦሌ የሚገኘውን “ፊደል” የተባለ ሬስቶራንቱን በማደራጃነት የሚጠቀም፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በጋሻው ደሳለኝ በእነ መ/ር ዘመድኩን በቀለ እና ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ላይ ለመሠረተው ክስ ተፈጻሚነት የትራንስፖርት ድጋፍ የሰጠ፣ ሁለቱ መምህራን በፖሊስ ጣቢያ በቀረቡበት ወቅት ሁኔታውን ለመከታተል በመጡት የሰባክያን ጥምረት አመራሮች ላይ የዛቻና ማስፈራሪያ ቃል የሰነዘረ፣ በዱባይ የሙዚቃ ፕሮሞሽን ሥራ ላይ ተሠማርቶ የነበረ) የተፈረመው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ይሁንና የተጠቀሰው ገንዘብ እንደተገኘ ከማሳወቅ ውጭ እስካሁን ድረስ ገቢ አለመደረጉ ጉዳዩን የተከታተሉ ወገኖች እየተናገሩ ነው፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)