August 27, 2011

ፓትርያርኩ ዱባይ ናቸው

(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 27/2011, READ IN PDF)፦ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከሐሙስ ጀምሮ ዱባይ ገብተዋል፤ በዱባይ ከኤምሬትባለሥልጣናት ጋራ ይወያያሉምእመኑንም አግኝተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሊባኖስ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ፈቃድ ሳይገኝና በሊቀ ጳጳሱ ሳይባረክ በባር ዱባይ በቅዱስ ሚካኤል ስም ‹‹ቤተ ክርስቲያን አቋቁሜያለሁ›› ያለው ሕገ ወጥ ቡድን አገልጋይ የሆነ ቀሲስ ተስፉ እንዳለ የተባለ ካህን በዱባይ-ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ምእመናን በደረሰበት ተቃውሞ ከቤተ መቅደ መከልከሉ እና ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያንም እንዲወጣ መደረጉ ተገለጸ፡፡


ቀሲስ ተስፉ እንዳለ
ቀሲስ ተስፉ የምእመናኑ ግልጽ ተቃውሞ የተሰነዘረበት በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሊባኖስ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት የሚገኙትን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያክ አቡነ ጳውሎስን ተከትሎ ወደ ዱባይ-ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለመግባት በሞከረበት ወቅት ነው፡፡ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ጥያቄ መምጣቸውን የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ ዱባይ የገቡት ሐሙስ ማምሻውን ሲሆን ዐርብ ጠዋት በየሳምንቱ ዐርብ በሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሚደረገው መደበኛ የጸሎት መርሐ ግብር ላይ ተገኝተዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱን ሥልጣን በመናቅ እና ሊቀ ጳጳሱን በመዝለፍ የሚታወቀው የሕገ ወጥ ቡድኑ ተቀጣሪ ቀሲስ ተስፉ ፓትርያኩን ተከትሎ በቅጽሩ አልፎ ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት ሲያመራ በፍራው የነበሩ በርካታ ምእመናን ‹‹ተሐድሶ ይውጣልን!!›› እያሉ አሰምተው በመናገር ተቃውመውታል ተብሏል፡፡ የምእመናኑን የተቃውሞ ጩኸት ከቁም ነገር ባለ መቁጠር እያለፈ ወደ ቤተ መቅደሱ በር ሲደርስ ግን ሥነ ሥርዐት አስከባሪዎች የቤተ መቅደሱን በር በመዝጋት እርሱን በውጭ ለይተው አስቀርተውታል፡፡ ይሁንና ቀሲስ ተስፉ ካህን ነኝ፤ መግባት እችላለሁ እያለ መወራጨቱን በመቀጠሉና ለጠብም በመጋበዙ ከምእመናኑ መካከል የወጡ ጎበዞች አንከብክበው የከፋ ትርምስ ሳይፈጠር ከቅጽሩ በአፍዓ አስወግደውታል ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጥቅም እና የኑፋቄ ቡድኑ አቀንቃኝ የሆኑ ግለሰቦች በዱባይ አየር ማረፊያ ጀምሮ ለፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ በተደረገው አቀባበል ላይ በመታየት ከዱባይ ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተለይተው ያለ ሊቀጳጳሱ ፈቃድ በቅዱስ ሚካኤል ስም አቋቁመናል ያሉትን ሕንጻ እንዲጎበኙላቸው መጠየቃቸው ታውቋል፡፡ ቀደም ሲል ቀሲስ ተስፉን ጨምሮ በስም የተጠቀሱት ግለሰቦች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከሥርተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ከቃለ ዐዋዲው በተፃራሪ የፈጸሙትን ተግባር በአባቶች ቡራኬ ሕጋዊነት ለማልበስ ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም እንዳልተሳካላቸው ታውቋል፡፡ እንዲያውም በወቅቱ ወደ ፍራ ተሰማርቶ የነበረ ልክ ጉዳዩን አጣርቶ ለሲኖዶሱ ባቀረበው ሪፖርት ቅዱስ ሲኖዶስ ድርጊታቸውን ክፉኛ በመኮነን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የተላለፈባቸውን ውግዘት አጽንቶባቸዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያአርብ ጠዋት በደብሩ በቤተ ክርስቲያኑ በነበራቸው ቆይታ ለምእመናኑ የሰጡት አውላላ ሜዳ ላይ በራሳቸው የሚጮኹትን አትስሟቸው፤ አትከተሏቸው የሚለው ቃለ ምዕዳንም ይህንኑ ውሳኔ የሚያስረግጥ ነበር ተብሏል

ከቅዱስነታቸው ዑደት በፊት የፀረ-ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት አባላት በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጥሪና በቀናዒ ምእመናን ትብብር ወደ አካባቢው ተደጋጋሚ ስምሪት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በአገልግሎታቸውም ጉባኤ ምእመናንን እስከ መክፈል የደረሰውን የጥቅመኞች እና መናፍቃን ቡድን ሤራ በማጋለጣቸው በአሁኑ ወቅት በባር ዱባይ የሚገኘው ምእመን ልቡን እንደ ቀደመው ወደ ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የመለሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የምእመናኑ ግፊት የበረታበት የጥቅም እና ኑፋቄ ቡድኑም ያቋቋመውን አጥቢያ አስተዳደር እንደ ያዘ በሀገረ ስብከቱ ሥር ለመሆን ሊቀ ጳጳሱን መማፀን ግድ ሆኖበታል፡፡

በፍትሕ ነገሥቱ ድንጋጌ መሠረት በኤጲስ ቆጶስ ባልተባረከ ቤተ ክርስቲያን የሚቀድስ ካህን ከክህነቱ የሚሻር በመሆኑ ሥልጣነ ክህነቱ አጠያያቂ የሆነው ቀሲስ ተስፉ ቀድሞ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመርቆ በማኅበረ ቅዱሳን የመጽሐፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ በመደበኛ አገልጋይነት ተቀጥሮ ይሠራ እንደ ነበር ተገልጧል፡፡ ይሁንና በዱባይ በወ/ሮ መንበረ መለስ ቤት ተጠንስሶና ወደ አዳራሽ አምርቶ፣ የሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ጉባኤ ምእመናንን በመክፈል ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በተቋቋመው ‹ሕንጻ› የግል እና የቡድን ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ግለሰቦች ምንደኛ ሆኖ ወደዚያው አምርቷል፡፡ ቀሲስ ተስፉ በውስጥ አገልግሎት ሊጠነቅቃቸው የሚገቡ ምሥጢራትን ይሁነኝ ብሎ በመተላለፍ፣ በተለይ በግል ቀርበው ጥያቄ በሚያቀርቡለት ምእመናን ልቡና ላይ ጥርጥርና ክሕደት በመዝራት ይታወቃል ተብሏል፡፡ ለአብነት ያህል፣ ሴቶች በልማድ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ሊገቡና ሊቆርቡም ይችላሉ፤ እኛ ኦሪታውያን ስለሆን እንጂ ይሄም አያስፈለግም፤ ቅዱሳንን የምናከብራቸው ግብፃውያን የጫኑብን ጣጣ ስለሆነ እንጂ አያስፈልገንም የሚሉት ስሑት ትምህርቶቹ ይጠቀሳሉ፡፡

የዱባይ-ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና ሥር ከሚገኙት ሦስት አብያተ ክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኘው ከአኀት አብያተ ክርስቲያን አንዷ በሆነችው በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ በሆነ ሕንጻ ውስጥ ነው፡፡ የአሁኑ የፓትርያኩ ዑደት ከዱባይ ከተማ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከኤምሬትሱ ፕሬዝዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ጋራ በሚደረግ ውይይት ቤተ ክርስቲያናችን መሬት አግኝታ የራስዋን ሕንጻ - ቤተ መቅደስ የምትሠራበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የታቀደበት ነው ተብሏል፡፡

አርብ ጠዋት በሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ጸሎት እና የእመቤታችን ወርኀዊ በዓል ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ ወደ አቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም እና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ተጉዘው የዕለቱን ጸሎተ ቅዳሴ መርተው ማከናወናቸው ተዘግቧል፡፡Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)