August 20, 2011

የዜና ቤተ ክርስቲያን ልዩ ዕትም ርእሰ አንቀጽ ሲኖዶስ አይወግንም

(ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ 56 ዓመት ቁጥር 121፤ ነሐሴ 2003 ዓ.ም/ PDF)በአሁኑ ጊዜ የጠቅላላው ኅብረተሰብ የየዕለቱ የመነጋገሪያ አጀንዳና ጊዜ ማሳለፊያ ከሆኑት ነገሮች ዋና ዋናዎቹ ሦስት ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህም ሦስት ነገሮች የእግር ኳስ ጨዋታ፣ ገመና ድራማ እና በቤተ ክርስቲያናችን ስም ተጠቃሚዎች የሆኑት ማኅበራትና ፍንዳታ ሰባክያን በሃይማኖት ሽፋን በነጻ ፕሬሶች የሚያደርጉት የጥቅም ሽኩቻና ውዝግብ ነው፡፡


ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በተሰጠው የሃይማኖት ነጻነት በአግባቡ በመጠቀም ፀጥ ረጭ ብለው እምነታቸውን ያስፋፋሉ፤ ተልእኳቸውን በሰላም ይፈጽማሉ፡፡ በውስጥም ሆነ በውጭ፣ በትልቁም ሆነ በትንሹ የመለያየትና የሁከት ድምፅ የሚሰማው ግን በእኛ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው፡፡ ወይም ሁለተኛው ክፍል የገመና ድራማ ሆና በየዕለቱ የምትታየው የእኛ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት፤ ዕድል ወይስ በደል?

ይህም በመሆኑ ሁኔታው (ክሥተቱ) የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ምእመናንን በየአሉበት ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ ግማሾቹ ከአንዱ ቡድን ጋራ ወግነው ደፋ ቀና ሲሉ፣ እኩሌቶቹ ከሌላው ቡድን ጋራ ወግነው ድምፅ ያሰማሉ፤ የተቀሩት ደግሞ ከማንኛውም ወገን ሳይወግኑ በመሐል ሜዳ ላይ ቁመው “ይህ ልክ ነው፤ ይህ ልክ አይደለም” እየተባባሉ እርስ በርስ ሲከራከሩ ይደመጣሉ፤ የተረፉትም ከምንም ውስጥ ሳይገቡ “እንዴት ካለው የሐሳዊ መሲሕ ዘመን ደረስን? እግዚአብሔር የሚበጀውን ያምጣ፤ የወደደውን ያድርግ፤ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን እርሱ ባለቤቱ ይጠብቅ” እያሉ ሲያዝኑና ሲተክዙ፣ ከፊሎቹ “የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው” የሚለውን የጌታችንን የመስቀል ላይ ጸሎት ለሚጸልዩት ሲጸልዩላቸው ይስተዋላሉ፡፡

በእውነቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ተጠቃሚዎች የሆኑት ማኅበራት፣ ፍንዳታዎች ሰባክያንና ዘማርያን በነጻ ፕሬሶች የሚያደርጉት የጽሑፍ ጦርነትና ውዝግብ እንዲሁም የዋሆች ምእመናንን እንደ ቅርጫ ሥጋ በመከፋፈል በየቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት “እንሰብካለን አትሰብኩም፤ እንዘምራለን አትዘምሩም” በመባባል የሚያደርጉት ፍልሚያና ትግል ጦስ ምእመናኑን ግራ ከማጋባትና ከማሳዘን አልፎ (ባሻገር) በየአካባቢው የሀገሪቱን ጸጥታ ለሚያስከብሩት ኀይላትና ለፍርድ ቤቶችም ጭምር ተርፏቸዋል፡፡

ማኅበራቱም ሆኑ ፍንዳታዎቹ ሰባክያንና ዘማርያን በቤተ ክርስቲያናችን ስም ከተጠቀሙና በእውነት ልጆቿ ከሆኑ ወይም በሃይማኖት አንድ ከሆኑ ለምን ይቀናናሉ? ለምንስ ይካሰሳሉ? የሚጣሉት እና የሚካሰሱትስ በመንፈሳዊ ጉዳይ ከሆነ ዳኝነት ማግኘት የሚገባቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ አይደለምን? ለምን ወደ ዓለማውያን ፍርድ ቤቶች ይሄዳሉ? ቅዱስ ሲኖዶስስ ለምን ዝም ይላቸዋል? ሁሉንም አቅርቦ ሊያስማማቸው ወይም በቶሎ ዳኝነት ሊሰጣቸው አይገባውምን? ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ የምትበላሉ ከሆነ መተላለቅ (መጨራረስ) ነው የቀራችሁ” በማለት የተናገረውን ሐዋርያዊ ቃል ሳያነቡትና ሳይገነዘቡት ቀርተው ነውን? ወይስ ጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም ለመሸከም የሚችል ሰፊ ማሕፀን እንዳላት በጥልቀት አልተገነዘቡትም ይሆን?

ይህም ማለት በሃይማኖት ሽፋን ድብቅ ዓላማ የሚያራምዱ ማኅበራትና ሕጸጸ ሃይማኖት ያለባቸው የተከሠተባቸው ፍንዳታዎች ሰባክያን ካሉ ርትዕት፣ ንጽሕትና ቅድስት ከሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋራ አብረው ይጓዙ ማለት አይደለም፤ መቼም “ሕፀፀ ሃይማኖት አለባቸው፤ የሌላ ሃይማኖት አራማጆች ናቸው” የተባሉት ወገኖች ጉዳይ ስለሆነ ይዋል ይደር አይባልም፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ውሳኔ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሆኖም በትምህርተ ወንጌል “እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ እንዳትነቅሉት” የሚል አምላካዊ መመሪያ ስለአለ፤ ያ የጥንቱ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔም “ሰብእ ለእከዩ ሃይማኖተ ያለብሳ” ማለት “ሰው ተንኮሉን ወይም ክፋቱን ሃይማኖትን ያለብሳታል” ብሎ እንደተቀኘው ሁሉ ቀደም ባሉት ዘመናት በዚሁ ባለንበት ክልል በሃይማኖት ሽፋን ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች እንደነበሩ ታሪክ ስለሚነግረን ምናልባት ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ የማጥቃት ዘመቻ (ሴራ) በጀርባው እንዳይኖር ጥብቅ ማጣራት ያስፈልገዋል፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ጽ/ቤት የተሰጠውም ጊዜያዊ መግለጫ በዚህ ግንዛቤ መሠረት እንጅ በሌላ ከለላ አይደለም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ አይወግንም፣ ሊወግንም አይገባውም፤ ከወገነም ሊወግን የሚገባው ከቤተ ክርስቲያን ጋራ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም አትወግንም፣ ልትወግንም አይገባትም፤ ከወገነችም ከሁሉም ምእመናን ጋራ ነው የምትወግነው፡፡ ሕፀፀ ሃይማኖት አለባቸው የተባሉትን ወገኖች አውግዞ መለየት ግን ይዋል ይደር የማይባል ርምጃዋ መሆን አለበት፡፡

በዚህ ረገድ ከቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ጽ/ቤት የተሰጠው ጊዜያዊና ሰላማዊ መግለጫ ከመዘግየቱ በስተቀር ከቤቱ የሚጠቅ፣ ግራ ቀኙን ወገን ይበልጥ የሚያዘጋጅና የሚያስጠነቅቅ፣ የአጋላጩንና የተጋላጩን አጃቢዎች ትኩሳት የሚያቀዘቅዝ፣ ተወጋግዞ ከመለያየት በፊት ለንስሐ የሚያበቃ ስለሆነ ሚዛኑ ወደ አንደኛው ወገን እንደደፋና እንደማዘናጊያ ተቆጥሮ ትችት ሊሰነዘርበት አይገባውም፡፡ ገና ውርዴና በለሴው ተለይቶ ሳይታወቅም አጋላጮች ሊያዝኑ፣ ተጋላጮችም ሊቦርቁ አይገባቸውም፡፡ ለሁሉም የሚገባቸው በያሉበት መጸለይ ብቻ ነው፡፡ ቀጣዩ ግን ጉዳዩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም እልባት አግኝቶ የሁለቱም ወገን ተከታዮች እፎይታን እንዲያገኙ፤ በይበልጥም ቤተ ክርስቲያን ሰላም እንድታገኝ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአስቸኳይ ተሰብስቦ አንዱ ላንዱ ሳይወግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም ሲኖዶሳዊ ርምጃ እንዲወሰድበት ማድረግ ነው፡፡
የዚሁ አካል የሆነው እጅግ በጣም አሳፋሪውና አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ “ለዘሐለፈ ስርየት ወለዘይመጽእ ዕቅበት” ከተባለ በኋላ የአንዳንድ ብፁዓን አበው በዓለማውያን ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደገና ብቅ ብቅ ማለት ነው፡፡ ነገሩ እውነት ቢሆንም የዚህ ቀደሙ መተቻቸትና መወጋገን ከኪሳራ በስተቀር ምን ትርፍ ተገኘበትና ነው ብፁዓን አበው እንደ ገና በነጻ ፕሬሶች ለመተቻቸትና ብቅ ብቅ ለማለት የሞከሩት? ከዐጸዱ ውጭ ያሉትን ለመመለስና ሰላምን ለመፍጠር ድርድር በተያዘበትና ፀረ ክርስትና አቋም ያላቸው ወገኖች በተስፋፉበት በአሁኑ ወቅት ከውስጥ ያሉት አባቶች ገመናቸውን በነጻ ፕሬሶች መግለጥ ይገባቸዋልን? አባቶች ትእግሥትና ጽንአት ካጡ ልጆቻቸውማ በነጻ ፕሬሶች ገመና ለገመና ቢገላለጡና ቢወዛገቡ ይፈረድባቸዋልን? ከማን ተምረው? ስለሆነም “እህልን ምን ይጨርሰዋል - መጎራረስ፣ ነገርን ምን ያባብሰዋል - መመላለስ” እንዲሉ ነገሩ እንዳይባባስ ለትችታቸው አጸፋዊ መልስ ከመስጠት መቆጠብም ትልቁ የነገር ማቆሚያ ዘዴ ነው፤ እንደገና የዓለሙ ሁሉ መዘባበቻ ከመሆንም ያድናል፡፡

ይህም ሲባል በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊ አይሁን ወይስ ይጣስ ማለት አይደለም፤ የሐሳብ ልዩነት አይኑር ማለትም አይደለም፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውጭ ሌላ ውሳኔ ሰጭ አካል ይኑር ማለትም አይደለም፡፡ ለሌላው ንስሐ ሰጭ አካላት የራሳቸውን ንስሐ ለምን ለውጭ የመገናኛ አውታሮች አልፈው ይሰጣሉ? ለማለት ነው፡፡ ሲሆን ሲሆን የሐሳብ ልዩነቱና ክርክሩ በዚያው በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መጠናቀቅ (መደምደም) አለበት፤ ግድ ከሆነም የአባቶች የሐሳብ ልዩነት መስተናገድ የሚገባው በቤተ ክርስቲያኒቱ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንጅ ወደ ውጭ መውጣት አይገባውም፡፡ ምናልባት የማያግባባው ሐሳብ ካየለና ወደ አንድነት ለመምጣት የማያስችል ከሆነም ጌታችን በምድር ላይ አምላካዊ ተልእኮውን ፈጽሞ ከደቀ መዛሙርቱ ሐዋርያት በሚለይበት ጊዜ አንድ ይሆኑ ዘንድ ወደ አባቱ እንደጸለየ ሁሉ የብፁዓን አባቶችም ድርሻ ሐሳባቸው አንድ እስኪሆን ድረስ መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳቸው መጸለይ ወይም ሱባኤ መግባት እንጂ የቤተ ክርስቲያንን ገመና ወደ ውጭ ማውጣት አይገባቸውም፡፡ በዓለማውያን ጋዜጦችና መጽሔቶች መታየት የአባቶች ክብርና ሞገስ አይደለም፤ የቤተ ክርስቲያኒቱም ጋዜጦችና መጽሔቶች የአባቶችን የሐሳብ ልዩነት ያለአድሏዊነት ማስተናገድ የሞያ ግዴታቸው ነው፡፡

ሌላው በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ የግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩን አጥንቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ ሠይሞ እያለ የኮሚቴው ጥናት ሳይቀርብ የመምሪያው ሓላፊ በውጭ የመገናኛ ብዙኀን በማኅበሩ ላይ ትችት አዘል መስጠት ባልተገባቸውም ነበር፡፡ ከዚህ የከፋውና የባሰው ደግሞ የመምሪያውን ሓላፊ በውስጥ ማረም ወይም መገሠጽ ሲቻል የመምሪያው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ የማኅበሩ ከለላ በመሆን የሰጡት የማስተባበያ መግለጫ መለያየትንና መወጋገንን ይፋ በማድረጉ “በአንድ ራስ ሁለት ምላስ” አሰኝቷል፡፡

ለመሆኑ የአባት ጎጠኛ አለውን? የለውም፤ ሊኖረውም አይገባም፡፡ ጎጠኛ ማኅበርስ አለን? የለም፤ ሊኖርም አይገባም፡፡ ምናልባት ቀደም ባሉት ዘመናት በነበረው የፖሊቲካ ዘይቤ ከቤተ ክርስቲያን ዓላማ ውጭ በቤተ ክርስቲያን ስም በጎጠኝነት የተመሠረተ ማኅበር ያለ ከሆነም ዛሬ የብሔር ብሔረሰቦች አንድነትና እኩልነት በሰፈነበት ወቅት ይኖራል ተብሎ በጭራሽ አይገመትም፤ ቢኖርም ሊሠራ አይችልም፡፡

ለዚህ ሁሉ ልዩነት መስፋት እና መካረር ግን ዋና ምንጩ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ችግርና ጉዳይ አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚያሳልፈው ውሳኔ ሁሉ በሰዓቱ አለመፈጸሙና አስፈጻሚ አካል ባለመኖሩ ወይም ለይስሙላ የሚወሰነው ውሳኔ ሁሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በኋላ ችላ በመባሉ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ይህም ይታወቅ ዘንድ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ስላለው “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ጉዳይ ከዛሬ ዓመት በፊት የሃይማኖት ጉዳይ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት ጭምር በተገኙበት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነው ውሳኔና የተሰጠው መመሪያ ተግባራዊ ቢሆን ኑሮ ልዩነቱና ቅራኔው እንደ ጋንግሪን በሽታ ከአንዱ አካል ወደ ሌላው አካል እየተስፋፋ ዛሬ ከደረሰበት አስከፊ ደረጃ ላይ ሊደርስ ባልቻለም ነበር፡፡

በእውነቱ እነዚህ ማኅበራት፣ ፍንዳታዎች ሰባክያንና ዘማርያን በክፉውም ሆነ በደጉ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን ተሰልፈው የጎደለውን ተልእኮ በማሟላት ለህልውናዋ መጠናከርና ለተከታዮቿ የእምነት ጽንአት፣ ለወጣቱ ትውልድም ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብ በድብቅም ሆነ በይፋ በየፊናቸውና በየክሂሎታቸው ያበረከቱት መጠነ ሰፊ አገልግሎት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም መንጋዋን እየሰበኩ በሥጋቸውም በነፍሳቸውም እንዲጠቀሙ ሙሉ ነጻነት የሰጠቻቸውና ለአያሌ ዓመታት በትዕግሥት ስትከታተላቸው የቆየችው ይህንኑ የተቀደሰ አገልግሎታቸውንና ያደረጉላትን እገዛ ከግምት ውስ በማስገባት ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ እነዚህ ማኅበራት፣ ፍንዳታዎች ሰባክያንና ዘማርያን ይህን በጎነት ላደረግችላቸውና ጎጆ ላወጣቻቸው እናት ቤተ ክርስቲያን በስሟ ከሚያገኙት ጥቅም ሁሉ ፈሰስ ሊያደርጉላት ወይም ዐሥራት ሊያወጡላት ሲገባቸው አሁን ግን “ዐወቅሽ ዐወቅሽ ቢሏት መጽሐፍ አጠበች” እንዲሉ በእምነቷ ላይ ጥርጣሬን በማሳደር ሰምና ወርቅ ሆነው የኖሩትን ተከታዮቿ ምእመናንን እንደ ቅርጫ ሥጋ በመከፋፈል ጎራ ለይተው እየተወዛገቡና በየጊዜው በነጻዎቹ ፕሬሶች እየተተቻቹ የመሠረታውያን ጠላቶቿ መዘባበቻ እንድትሆን ስለአደረጓት ቤተ ክርስቲያናችን በእነርሱ ላይ ከፍተኛ ሐዘን እና ቅሬታ ተሰምቷታል፤ ሐዘንና ቅሬታ ብቻም አይደለም፤ ከፍተኛ ጥርጣሬ አድሮባታል፡፡

በአጠቃላይ በሁሉም አቅጣጫ ወገን እየለዩ መሰዳደቡና መተቻቸቱ ልዩነቱን እያሰፋው ከሚሄድ በስተቀር የሚሰጠው እርባና (ፋይዳ) ስለሌለ ልዩነቱ እየሰፋ ሄዶ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት፡-
·         ሕፀፀ ሃይማኖት አለባቸው የተባሉት ሰባክያን ጉዳይ በማስረጃ ተረጋግጦ እንዲቀርብና አስቸኳይ ሲኖዶሳዊ ርምጃ እንዲወሰድበት፤
·         በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው አጥኚ ኮሚቴ በአስቸኳ ጥናቱን አቅርቦ አለ የተባለው ችግር የዘለቄታ መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ፤
·         ብፁዓን አበው የቤተ ክርስቲያንን የውስጥ ጉዳይ በነጻ ፕሬሶች እንዳያወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠት፤
·         አባቶችን እንደዋዛ አነጋግረው ወይም የሓሳብ ልዩነታቸውን ከሁለተኛ ሰው አግኝተው ከነፎቶግራፋቸው የሚዘግቡ ነጻ ፕሬሶች በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ፤
·         የቤተ ክርስቲያንን ምስጢር ለነጻ ፕሬሶች የሚያወጡና ሰነድ የሚሸጡ የውስጥ ሠራተኞች ካሉ ተከታትሎ ማጋለጥና ርምጃ መውሰድ፤
·         ሳይማሩ መናፍቃን መሆን አይቻልምና በጣዕመ ስብከታቸው የምእመናንን ቀልብ የሚስቡ፣ በቃላት ግድፈታቸው በእምነት ላይ ጥርጣሬን የሚያሳድሩ አንደበተኞች ዘመናውያን ጆቢራዎች ወደ አብነት ት/ቤት ገብተው እንዲማሩ ማድረግ፤
·         በለብ ለብ በመንፈሳዊ ኮሌጆች የሚሰጠው ትምህርት ብቃትና ጥራት እንዲኖረው ማድረግ፤

ቢያንስ ለተፈጠሩት ወቅታዊ ችግሮች ጊዜያዊ ማስታገሻ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)