August 12, 2011

የጠ/ቤተ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ መልእክት፤ እንወያይበት


(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 12/2011/ READ IN PDF)፦ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በቅርብ ወራት ከሾማቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ የሆኑት  አቶ ልዑልሰገድ ግርማ (ሥልጣነ ክህነት ካላቸው አቶ በማለታችን ይቅርታ፣ ስላላወቅን ነው) ሰሞኑን በድረ ገጽ ባወጡት በሚከተለው ጽሑፋቸው ብዙ የመወያያ ነጥቦችን አንስተዋል። በተለይም በቤተ ክህነቱ ውስጥ ስለተንሰራፋው ብልሹነት በአለፍ ገደም ለመጠቃቀስ ሞክረዋል። እስቲ አንብቡና እንወያይበት። ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ቁጭት በቤተ ክህነት
(ልዑልሰገድ ግርማየጠቅላይ ቤተ ክህነት /ዋና ሥራ አስኪያጅ)፦ ቅዳሜ ግንቦት 27 ቀን 2003 . የግንቦት 20 20 ዓመት የድል በዓል ማጠቃለያ በሚሌኒየም አዳራሽ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በተገኙበት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል፤ በዚሁ መድረክ ላይ የተላለፈ አንድ መልእክት ደግሞ እጅግ አስደምሞኛል፡፡ የዘንድሮው የግንቦት 20 በዓልን ያጀበውን የታላቁን የህዳሴ (የዓባይ ግድብን) የተመለከተ ነበር መልእክቱ፡፡ ‹‹ድሮ ድሮ የዓባይ ገባሮች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ አሁን ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡ ሕፃን፣ ወጣት፣ ዐዋቂ ሳይል ሁሉም ለግድቡ የሚችለውን በማዋጣትና ቦንድ በመግዛት ገባርነቱን እየገለጸ ይገኛል፡፡ የድሮዎቹ ገባሮች የኢትዮጵያን ለም ዐፈር እየጠራረጉ ለባእዳንና ለሜዲትራኒያን ባሕር እየገፉ ወስደዋል፡፡ ያሁኖቹ ገባሮች ግን ተመሳሳይ ተግባርን የሚያበረታቱ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት የሚገባ ውጤትን የሚያመጡ ናቸው›› የሚል ነበር መልእክቱ፡፡ እኔ ድንቅ መልእክት ብየዋለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ከሲኖዶስ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ባላት መዋቅር ለተመሳሳይ ጉዳይ የራሷን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች፡፡ ይኸውም በቦንድ ግዢና በመዋጮ ይገለጻል፡፡ ይህም ተገቢና ወቅታዊ አስተዋጽኦ ነው፡፡

የደርግ መንግሥት ግብዓተ መሬት ከተፈጸመ ዕለት ጀምሮ በሀገራችን በርካታ ለውጦችን እያየን ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተገቢውንና ትክክለኛውን ዕውቅና የሚሰጥና በዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች ውስጥ የተካተቱ ሰብዓዊና ዴሞክራሰያዊ መብቶችን ሊያስከብር የሚችል ሕገ-መንግሥት ጸድቋል፣ ታላላቅ የልማት አውታሮች ተገንብተዋል፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት ጨምሯል፣ ዴሞክራሲያዊነትን የተላበሱ አገር አቀፋዊና አካባቢያዊ ምርጫዎች ተካኺደዋል፣ በርካታ የሆኑ ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲዎች በአገሪቱ ጉዳይ ድምፃቸውን አሰምተዋል፣ በርካታ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተገንብተዋል፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ /ቤቶች ተስፋፍተዋል፣ የሴቶች እኩልነት ተከብሯል፣ ድህነትና ረሃብን ለማጥፋት ጥረት ተደርጓል፣ ወዘተ. አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን ወደሌላ ደረጃ ለማሸጋገር የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ታቅዶና ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ተመክሮበት ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡ በቤተ ክህነታችንስ?

ቤተክህነታችንም ጥንታዊቷንና ታሪካዊቷን ቤተክርስቲያናችንን በማስጠበቅና በማስቀጠል ሃይማኖታችንን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚያስችል በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የእግዚአብሔር እጆች ያረፉባቸውን ተአምራዊ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ታሪካዊ ቦታዎችንና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለመጠበቅ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርታለች፡፡ የውጭ ግንኘነት ሥራዎቿ በእጅጉ አድገዋል (ይህም በመሆኑ ቅዱስ አባታችን የዓለም አብያተ ክርስቲያንት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም ምክር ቤት የክብር ፕሬዚዳንት ሆነዋል) ከተለያዩ ዓለማት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን የሚስቡ የአደባባይ ሃይማኖታዊ በዓሎች በደመቀ ሁኔታ ተከብረዋል፤ በወገኖቻችን ላይ አደጋ በደረሰ ጊዜ የውስጥና የውጭ ለጋሾችን በማስተባበር ለመታደግ ተችሏል፣ ኤች.አይ./ኤድስን ለመከላከል ከፍተኛ የሚባል ሃይማኖታዊ ሥራ ተሠርቷል፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን በማዳረስ ጤናው የተጠበቀ ትውልድ እንዲፈጠር ጥረት ተደርጓል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በስነ ምግባር ታንጸው ለሀገራቸው ጠቃሚ ዜጐች እንዲሆኑ ሃይማኖታዊ ሥራ ተሠርቷል፣ እንዲሁም ለሃይማኖቱ መስፋፋትና መጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ዘመናዊ ኮሌጆች ተከፍተዋል፡፡ ሌላስ?

አገራችን በበርካታ ጉዳዮች ወደኋላ ስለቀረች አሁን ያለው ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት በሚያደርገው ያላሰለሰ የልማት ጥረት በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ የተጫረው የቁጭት ስሜት የሚገርም ነው፡፡ የህዳሴ ጉዞው ማቀጣጠያ ነዳጅ ቁጭትና እልህ ነው ብሎ ለመደምደምም ያስችላል፡፡

በቤተክህነታችን ያለው የቁጭት መጠን ግን አጠያያቂ ነው፡፡ እንዲያውም ከዘመኑ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን አስተሳሰብ ጋር መሄዱ ያጠራጥራል፡፡ በእርግጠኝነትም እንደጥንቱ እየተጓዝን ነው ማለት ይቻላል፡፡ በድሮ በሬ ማረስ አሁንም አልቀረም፡፡ ዘመናዊ አስተሳሰብና አሠራር አልዳበረም፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን በማስተባበር በልማቱና በመልካም አስተዳደሩ ዘርፍ የሚታይና የሚዳሰስ ሥራ በመሥራት ፈንታ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድገት ወደሚገታ አቅጣጫ የማምጣቱ ሥራ ሕጋዊ በሚመስል መልኩ ይከናወናል፡፡ እዚህ ላይ ቅዱስ አባታችን ጥቅምት 3 ቀን 2003 . ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ያደረጉትን ንግግር ማስታወስ ተገቢ ይሆናል፡፡

ቅዱስ አባታችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭ መሆኗን አስታውሰው የነበራት ሥልጡን አሠራር ከተቀበረበት ወጥቶ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የሚራመድ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው ብለው ነበር፡፡ በተጨማሪም ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በዚሁ ቀን እንደተናገሩት ሠራተኞችን አክብሮና የዘመኑን አሠራር የሚያሠራና የቤተ ክርስቲያናችንን ለልማት የምታበረክተውን አስተዋጽኦ የሚደግፍ አመራር እንፈጥራለን ማለታቸው ይታወሳል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት /ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በበኩላቸው የቤተ ክርስቲያናችንን ዕድገት የሚደግፉ ተጨማሪ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል ብለው ነበር፡፡

ይህ አባባላቸው የቅዱስነታቸውንና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመለወጥ ያነሳሳቸውን ቁጭት ከመግለጹም ባሻገር ለለውጥ ያላቸውን ተነሳሽነት ቁልጭ አድርጐ ያሳያል፡፡ ተግባራዊነቱ ግን በርካታ ፈተናዎች አሉበት፡፡ እነዚህን ፀረ-ለውጥ ፈተናዎችና የፈተና መነሻዎችን ታዲያ አመራሩ ብቻ ሳይሆን መላው ሠራተኛ በግልጽ ሊቃወማቸውና ከለውጥ አስተሳሰብ ጐን ሊሰለፍ ግድ ይለዋል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት አንድ ድርጅት (ተቋም) ስኬታማ የሚሆነው ለውስጥና ለውጭ ለውጦችና ፈተናዎች የማያቋርጥ መልስ ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው እስትራቴጂዎች ሲነደፉ፣ አቅምና ችሎታ ሲያድግና መዋቅሮችና ሲስተሞች ያለማቋረጥ ሲስተካከሉ ብቻ ነው፡፡

በፍጥነት እያደገ ያለውን የዓለማችንን የቴክኖሎጂ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ መከተል የሚቻለው ከላይ የተጠቀሰውን በማከናወን ብቻ ነው፡፡ ለውጥን የማያቋርጥ የሕይወታችን አካል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ደግሞ የማይቀየረው ሃይማኖታዊ ዶግማውና ቀኖናው እንጂ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥራው አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ትርጉም ያለውን ምእመናኗን ይዛ ለልማት ማነሳሳት የምትችለው በአመለካከትና በክህሎት የበለጸገ አሠሪና ሠራተኛ ሲኖራትና የዘመኑ አሠራር የሆነውን የስትራቴጂክ እቅድ ይዛ ስትነሳ ብቻ ነው፡፡

ይህንን በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ለማረጋገጥም በመንፈሳዊ ትምህርት የበለጸጉና ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ ሠራተኞችና ምእመናን እንደ አሏት እርግጥ ነው፡፡ ትልቁ ሥራ የሚሆነው ግን ይህንን እጅግ ትልቅ የሆነ የሰው ኃይል በማሰተባበር የአስተሳሰብንና የአሠራር ለውጥን ማምጣት ነው፡፡

በእስትራቴጂክ ዕቅድ የማይመራ ድርጅት ማንነቱን፣ አቅሙንና ችሎታውን፣ ምን ምን ችግሮችን እንደሚፈታ፣ ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚያመጣ፣ ተጨባጭ ሁኔታዎችንና ሀብቱን እንዴት ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ አያውቅም፡፡ በአጠቃላይም ራዕዮቹን፣ ግቦቹንና ዓላማዎቹን ፈጽሞ አያውቅም፡፡ ይህ አካሄድ መለወጥ አለበት፡፡ አካባቢያችን እንዴት እየተለወጠ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

እስትራቴጂክ እቅድ አካባቢያችን ያሉ ፈተናዎችንና ሥጋቶችን ለይቶ ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ልንጠቀምባቸው የሚገቡ ዕድሎችንም ፍንትው አድርጐ ያሳየናል፡፡ ጥንካሬያችንንና ድክመታችንን እንለያለን፡፡ በአጠቃላይም ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ለአገራችን ዕድገት አስተዋጽኦ እናበረክታለን፡፡ የማይለወጠውን ሃይማኖትና ሕዝብ ይዘን አገራችንን ዘመኑ በሚጠይቀው ልማታዊ ጉዞ ማስጓዝ እንችላለን ይገባናልም፡፡

በሠራተኞችና በአለቆች መካከል ያለው ፍጹም የሆነ አለመናበብ መወገድ አለበት፤ ለዚህም የሠራተኛ አስተዳደር ሥርዓቱን ፍጹም መለወጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለሙስና እጅግ የተጋለጠውን የሙዳየ ምጽዋት አሰባሰብ፣ የበጀት አቀራረጽና አፈጻጸም እንዲሁም ያረጀውና ያፈጀው የፋይናንስ ሥርዓት እንደገና መታየት ይኖርበታል፡፡ በየአቅጣጫው የሚፈጠሩ ውዝግቦችን በቀላሉና በመግባባት ለመፍታት ዘመናዊ የሆነ የግጭት አለመግባባትና አፈታት እንዲሆን ትራንስፎርሜሽን ትምህርት በስፋት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ጸጋና ጥበብ አባቶቻችን ለዚሁ ዓላማ በይበልጥ ሊያውሉት ይገባል፡፡ አባቶችን በማዋረድ ሥራ የተጠመዱትን እኩያንን ጸጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በማያገባቸው እዛም እዛም የሚገቡትንና የግል ጥቅማቸውን ብቻ የሚያሳድዱትን ልበ ጥቁሮች እንዲመለሱ ካልሆነም እንዲወገዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የራሳቸውን ዓላማ ብቻ ለማሳካት በመላ አገሪቱ የሚገኙትን መዋቅሮች በሪሞት ኮንትሮል የሚቆጣጠሩና ውዝግብን በመፍጠርና ለውጥ እንዳይከሰት በየዕለቱ እየዶለቱ የሚገኙ ግብረ ሠይጣኖችን ትጥቃቸውን ማስፈታት ያስፈልጋል፡፡ የወጣቱን ኃይል በሚገባ መጠቀምም በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይም ቁጭት ወይም እልህ በውስጣችን ሊፈጠር ይገባል፡፡ ቁጭት ሳያድርብን ቀርቶ ዓባይ በርካታ ነገሮችን ጠራርጐ ወስዶ ለባዳ አስረክቦብናል፡፡ ቁጭት በቤተክህነት ባለመፈጠሩም ሙስናና ብልሹ አሠራር ተንሰራፍቷል፤ እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ የሚሉ አምባገነኖች በርትተዋል፤ በሐሜት ቤቱን የሚያምሱ ሰዎችን ያሻቸውን አውርተው ያሻቸውን ሲያደርጉ ዝም ብለን አይተናቸዋል፡፡ ለሥራ በአዲስ መንፈስና ጉልበት የተነሱ ሰዎች እንዲመቱ ተደርጓል፡፡ ጣልቃ ገብነት በርትቷል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ በሀገረ ስብከቶች ጡረታ ላለመውጣት የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ነው፡፡ ይኸው ትግል ዶክመንት ከመሠረዝና ከመደለዝ አንስቶ እስከ ስወራ ይደርሳል፡፡ ከፍተኛ ሀብት እያስገኙ ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች ማስረጃዎቻቸው በግለሰቦች እጅ ይገኛሉ፡፡ ይህ ምንን ያመለክት ይሆን? ጠዋት ፊርማ ፈርመው እንዴት አደራችሁ ብለው ወደቤታቸው የሚመለሱ ሠራተኞች በርክተዋል፡፡ ምንም አስተዋጽኦ ሳይኖራቸውና ቤተ ክርስቲያናችንን በሐሜትና በፈጠራ ወሬ ውዥንብር እየፈጠሩና እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ ጨምረው የደመወዝና የደረጃ ዕድገት የሚጠይቁ እየበዙ መጥተዋል፡፡ አንዳንዶች ለሥራ የተነሡ ሰዎችን ጥላሸት መቀባት ዋናው ሥራቸው አድርገውታል፡፡ ሥጋት የመሰላቸውን ለብልሹ አሠራራቸው ተባባሪ ያልሆናቸውን ሰው ለማስወገድ ሌት ተቀን ሲባዝኑና ሲማስኑ ይታያሉ፡፡ አሁን በቤተክህነት ያለው የዲፖርትመንቶች ተቀናጅቶ መሥራትና የአስተዳደር ጉባኤ አሠራር መሠረታዊ ለውጥ የሚያሻው ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ሕጐች መሠረት ዕውቅና ያገኙ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ቆይተዋል፡፡ ይህ አካሄድ ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሀገራችን አይበጅም፡፡ አሁን የተፈጠረው የህዳሴ ጉዞ የእኛም ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ በአፋችን የጀመርነውን ቁጭት በተግባር ዛሬውኑ እንጀምረው፡፡ ቁጭትን ለልማት እንጠቀምበት ቁጭትን አባቶችን ለማሳሳትና ልማትን ለማደናቀፍ አንጠቀምበት፡፡ የህዳሴውን ጠበል እንጠመቀው በትራንስፎርሜሽኑ እቅድ በተግባር እንሳተፍ፡፡

በእርግጥ መሠረታዊ ለውጥ በአንድ ጀምበር የሚከሰት አይደለም፡፡ በመንፈስ የተመራ ሳይንሳዊ አሠራር በሆነ መንገድ ደረጃ በደረጃ ሊኬድበት ይገባል፡፡ የመጀመሪያውና ዋነኛው ጉዳይ ተነሳሽነት ነው፡፡ እስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ ማቀድ ደግሞ ቀጣዩ ሥራ ነው፡፡ እቅዱን ወደተግባር ለመተግበር የሚደረግ ቁርጠኝነት ደግሞ ወሳኝ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የጥንቱን ሥልጣኔዋን በመመለስና ጥንታዊነቷንና ታሪካዊነቷን በመጠበቅ በእልህ ወደፊት መጓዝ ይጠበቅባታል፡፡ ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይቀይር ሁሉ ዶግማችንና ቀኖናችን በፍጹም አይለወጥም፡፡ የሚለወጠው አሠራር ብቻ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ዋና ዓለማ ምእመናን የእግዚአብሔርን ቃል እየተመገቡና መልካሙን ሁሉ እየሠሩ የምድር ቆይታቸውን ሲያበቁ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንዲችሉ ማብቃት ነው፡፡ ለዚህም ምእመናን እርስ በርስ ተከባብረው በመንፈስ እየተመሩ የዓለምን እንቅፋቶች ሁሉ እያስወገዱ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስረክቡትን ሥራ እየሠሩ እንዲኖሩ ማስተማርና ማብቃት ደግሞ ሁለተኛ ተግባሯ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ስንፍናን፣ አለመከባበርን፣ ሙስናንና ሌሎች ኃጢአቶችን የሚጸየፍ ትውልድ የመፍጠር ሓላፊነት አለባት፡፡ አርአያ መሆንም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ምን ላይ ነው ያለነው? ቁጭቱ ዛሬውኑ መጀመር አለበት፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)