August 6, 2011

የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬና ነገ ያካሂዳል

  • “ጽሑፉ ዲያቆን ዳንኤልን በሕግ የሚያስጠይቁ እና ከአባልነት እንዲወገድ የሚያደርጉ ጉዳዮች የተነሡበት ቢሆንም ወንድማችን ነው፤ አሳልፈን አንሰጠውም” (/ን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም)
  • በማኅበሩ የአዲስ አበባ ማእከል ከሐምሌ 29 - ነሐሴ አንድ ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የሦስት ቀን ጸሎተ ምሕላ ታውጇል፤
  • ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የሰሜን አሜሪካ ቆይታውን አቋርጦ ተመልሷል፤
 (ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 6/2011/ READ IN PDF)፦ ቀደም ሲል በዕቅድ ከተያዘለት ጊዜ (ነሐሴ 23 - 24 ቀን 2003 ዓ.ም) ቀደም ብሎ በአስቸኳይ እንደተጠራ የተገለጠው የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር ጉባኤ ጠቅላላ ስብሰባ ዛሬ ሐምሌ 30 እና ነገ እሑድ ነሐሴ አንድ ቀን 2003 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ “የንኡሳን ማእከላት ተወካዮችን የሚያጠቃልል የሥራ አመራር ጉባኤ ጠቅላላ ስብሰባ በየስድስት ወሩ አንድ ጊዜ በዋናው ማእከል ጽ/ቤት ይደረጋል” በሚለው መሠረት በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲሰበሰብ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 15/ዠ ያዛል።  


ስብሰባው ከተያዘለት የጊዜ መርሐ ግብር ቀደም ብሎ የተጠራበት ምክንያት፣ “ከማኅበሩ መሥራቾች አንዱና የረዥም ዘመን መደበኛ አገልጋይ የሆነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ዋና ጸሐፊው ዲያቆን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም ለ‹ዕንቊ› መጽሔት ሰጠው ቃለ ምልልስ መነሻ አድርጎ ከማኅበሩ አመራር ጋራ በአቋም ተለየባቸው ስትራቴጂያዊ አካሄዶች እና አፈጻጸሞች ላይ ያለውን ቅሬታ ይፋ በማድረጉ፣ ያንንም ተከትሎ የሥራ አመራር ጉባኤ ዲ/ን ዳንኤልን ከአባልነትና ከማንኛውም የማኅበሩ አገልግሎት የማገድ ርምጃ መውሰዱ፤ ጠቅላላው ጉዳይም ማእከላትን፣ አባላቱ እና አመራሩ ውጥረት ውስጥ በመክተቱ ነው” ተብሏል፡፡

ትናንት አርብ ማምሻውን ጉባኤው በጸሎት ሲከፈት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም፣ “ማኅበሩ በአገልግሎት የሚከሠቱ ግድፈቶችንና ስሕተቶችን የሚያርምበት የውስጥ አሠራርና ቁጥጥር ሥርት ያለው በመሆኑ የጉባኤው አባላት በመደማመጥ፣ በአትሕቶ ርእስ፣ በመከባበርና በመተማመን በነጻነት እንድንነጋገር አደራ እላለሁ” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ከሐምሌ 20 ጀምሮ አሜሪካ የነበረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ቆይታውን አቋርጦ ትናንት ጠዋት ወደ አዲስ አበባ የተመለሰ ሲሆን በጉባኤው ላይ በአስረጅነት ይገኝ ወይም አይገኝ የታወቀ ነገር የለም፡፡

መቀመጫውን በዋናው ማእከል አዲስ አበባ ላይ ያደረገውና 17 አባላት ያሉት መደበኛው የሥራ አመራር ጉባኤ ሐምሌ 19 ቀን 2003 ዓ.ም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ የላከው ጽሑፍ በተስተናገደ በ36 ሰዓታት ውስጥ (ሐምሌ 20 ቀን 2003 ዓ.ም እኩለ ሌሊት) ነበር በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ የእግድ ውሳኔውን ያስተላለፈው፡፡ የማኅበሩ ምንጮች እንደሚያስረዱት፣ ቀደም ሲል ረቡዕ ሐምሌ 20 ቀን 2003 ዓ.ም የሥራ አመራር ጉባኤው እንዲነጋገርበት ተይዞ የነበረው አጀንዳ ዲያቆን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም ለ‹ዕንቊ› መጽሔት የሰጠውን ቃለ ምልልስ አዳምጦ፣ በቃለ ምልልሱ ላይ የታዩ ግድፈቶችንና ስሕተቶችን ለይቶ እርማት ስለሚሰጥበት ሁኔታ መወሰን ነበር፡፡

ይሁንና ሐምሌ 19 ቀን 2003 ዓ.ም በ‹ደጀ ሰላም› ላይ በተስተናገደው የዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ ሳቢያ አዳዲስ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ለሐምሌ 20 ቀን ተይዞ የነበረው አጀንዳ የዋና ጸሐፊው ቃለ ምልልስ ወዳስከተለው የዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍና በዲያቆን ዳንኤል ላይ መወሰድ ስለሚገባው ርምጃ መለወጡ፣ ቀደም ብሎ የተያዘው አጀንዳም በልዩነት ለሐምሌ 22 ቀን 2003 ዓ.ም ማደሩ ተዘግቧል፡፡
“ጽሑፉ ዲያቆን ዳንኤልን በሕግ የሚያስጠይቁ እና ከአባልነት እንዲወገድ የሚያደርጉ ጉዳዮች የተነሡበት ቢሆንም ወንድማችን ነው፤ አሳልፈን አንሰጠውም” (/ን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም)
የዕለቱ የሥራ አመራር ጉባኤ ስብሰባ በተጠቀሰው መልኩ የዋና ጸሐፊውን ቃለ ምልልስ አጀንዳ ያደረገው መጽሔቱ ከወጣ ከአንድ ወር በኋላ መሆኑ ከፍተኛ ትችት እንዲሰነዘርበት አድርጓል፡፡ ሐምሌ 20 ቀን ማምሻውን ተጀምሮ እኩለ ሌሊትን አሳልፎ የተጠናቀቀው የሥራ አመራሩ ስብሰባ በውጥረት የተሞላ እንደነበር የስብሰባው ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ የዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ በሚበዙት የሥራ አመራር አባላቱ ዘንድ፣ ጽሑፉ “የማኅበሩን ህልውና እና አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል፣ ለአራረ ቤተ ክርስቲያን አጋልጦ የሰጠ፣ ከመንግሥት እና ከሰንበት ት/ቤቶች ጋራ የሚያጋጭ ስም አጥፊ” እንደሆነ ግንዛቤ ቢወሰድም ዲ/ን ዳንኤል ላይ መወሰድ ያለበትን ርምጃ አስመልክቶ አምስት ያህል አቋሞች መንጸባረቃቸው ተመልክቷል፡፡

“ጽሑፉ ዲያቆን ዳንኤልን በሕግ የሚያስጠይቁ እና ከአባልነት እንዲወገድ የሚያደርጉ ጉዳዮች የተነሡበት ቢሆንም ማኅበሩን ለረዥም ዘመን ያገለገለ ወንድማችን ነው፤ አሳልፈን አንሰጠውም፤ በመጪው የሥራ አመራር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አቅርበን እንጠይቀዋለን” የሚለው በዋና ጸሐፊው ዲያቆን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም የተራመደ አቋም ነበር ተብሏል፡፡ ሌሎች የሥራ አመራር አባላት ጽሑፉ የዲያቆን ዳንኤል ስለመሆኑ፣ ለምንና እንዴት ወደ ውጭ እንዳወጣው በዝርዝር ቀርቦ እንዲጠየቅ እስከዚያው ድረስ ከአባልነት መብቶችና ከማንኛውም አገልግሎት ታግዶ እንዲቆይ ሐሳብ ሲያቀርቡ ጥቂቶችም ጨርሶ በአስቸኳይ እንዲሰረዝ አቋም በመያዝ የተሟሟቀ ክርክር ተደርጓል፤ በጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይታለፍ ያሉም ነበሩ፡፡ “ከዋና ጸሐፊው ቃለ ምልልስ ጋራ የተያያዙ ውዝግቦችን ለአንድ ወር ባስታመምንበት፣ ከወራት በፊት ሥራ አመራሩ ያቋቋመው ኮሚቴ ከዲያቆን ዳንኤል ጋራ በዐበይት የልዩነት ጉዳዮች ላይ የጀመረውን ውይይት በአግባቡ አለመፈጸሙን በታገሥንበት ሁኔታ በዲያቆን ዳንኤል ላይ ለመወሰን መብከንከናችን አግባብ “fair” አይደለም” በሚል ከውሳኔ ለመታቀብ የተሟገቱም ነበሩ፡፡


የሆነው ሆኖ በመጨረሻ የሥራ አመራር አባላቱ “ዲያቆን ዳንኤል በማኅበር አባልነቱ ትችት ለመሰንዘር ያለውን ተቀባይነት ያሳጣዋል፤ ከጀመረው አሉታዊ የጽሑፍ ዘመቻ እንዲታገሥ ያደርገዋል፤ የአባላትንና የማእከላትን ጫና ያሣድርበታል” የተባለው “ከማኅበር አባልነትና ማንኛውም አገልግሎት እንዲታገድ” የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ሊወሰን መቻሉን ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡

በዚህ የእግድ ውሳኔ መሠረት ጉዳዩ  በሥራ አመራሩ ጉባኤው ትእዛዝና በሥራ አስፈጻሚ ጉባኤው በተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ተጠንቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጠው ድረስ ዲያቆን ዳንኤል በማኅበሩ ስም፣ በማኅበሩ መዋቅር ውስጥና በማኅበሩ መርሐ ግብሮች ላይ አገልግሎት እንዳይሰጥ የሚከለክለው ይሆናል፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤው በምክትል ዋና ጸሐፊው መ/ር አንዱአምላክ ይበልጣል የሚመራ በአጠቃላይ አራት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡

መቀጠልም የሥራ አመራር ጉባኤው ሐምሌ 22 ቀን 2003 ዓ.ም ስብሰባው በጽሑፍና በድምፅ የቀረበውን የዋና ጸሐፊውን ቃለ ምልልስ መርምሮ የመወሰን አጀንዳ አጽድቆ ተወያይቷል፡፡ በዕለቱ ማምሻውን የተጀመረው ስብሰባ እስከ ሌሊቱ 10፡00 ድረስ ቀጥሎ ከፍተኛ የሐሳብ ግብግብ ተካሂዶበታል፡፡ በውይይቱ ዋና ጸሐፊው “አብዛኛው የማኅበሩ አባላት የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ስለመሆናቸው”፣ የማኅበሩ ኤዲቶሪያል አገልግሎት ከሴንሰርሽፕ ጋራ የተነጻጸረበት “ሕገ መንግሥቱ ስለመጠቀሱ”፣ በጋሻው ደሳለኝ በቂ ትምህርት የሌለው መሆኑ ከሰንበት ት/ቤቶች አኳያ የተነሣበት ሁኔታ፣ ዲያቆን ዳንኤል ከማኅበረ ቅዱሳን ከማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልግሎት ስለነበረው ሓላፊነትና ስለለቀቀበት ሁኔታ፣ በአንድ ወቅት የማኅበሩ ሥራ አመራር አባል የነበረው ቀሲስ ሰሎሞን ሙሉጌታ ከሕገ ወጥ ሰባክያን ጋራ ስለሚሠራበት ሁኔታ የተመለከቱ ነጥቦች ተነሥተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው”አብዛኛው የማኅበሩ አባላት የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ስለመሆናቸው” ማለቱን በተመለከተ በዋናነት “እንደዚያ ባይል (ባይናገር) ጥሩ ነበር፤ ከተናገረውም ፋክት (እውነት) ነው፤” የሚሉ እና “ዋና ጸሐፊው ይህን ለመናገር የሚያበቃ ሥልጣንም ማስረጃም የለውም፤ ስሕተት ነው፤ በግልጽ መታረም ይገባዋል” በሚሉት ሐሳቦች ላይ ክርክር ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም በማኅበሩ አንቀጽ አምስት “ማኅበሩ በማንኛውም የፖሊቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ ገብነት እንደማይኖረው” የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ እና ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ የማኅበሩ ሚዲያዎች አዘጋጆችና ሪፖርተሮች፣ የማኅበሩ (ሰባክያነ ወንጌል) መምህራንና የማእከላት ሰብሳቢዎች የማንኛውም ፖሊቲካ ፓርቲ አባላት መሆን እንደማይችሉ በ1998 ዓ.ም የተላለፈውን መሪያ መሠረት በማድረግ በዋና ጸሐፊው የተነገረው ስሕተት መሆኑ ተገልጦ መታረም እንደሚገባው ከስምምነት ላይ ተደርሷል ተብሏል፡፡ ይህም እርማት የዋና ጸሐፊው ቃለ ምልልስ በተስተናገደበት መጽሔት እንዲወጣም ተወስኗል። ማስተካከያው ማኅበሩ ለዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ ከሚሰጠው የጽሑፍ ምላሽ ጋራ በአንድነት ሆኖ”፣ የለም በተናጠል መሆን ይገባዋል በሚለው ላይ ግን የአካሔድ ልዩነት እንደታየበት ተመልክቷል፡፡

በተያያዘም፣ ከትንት በስቲያ በማኅበሩ ሰብሳቢ ፊርማና በማኅበረ ቅዱሳን ማኅተም በወጣው “በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ማብራሪያና መግለጫ” የዋና ጸሐፊው ቃለ ምልልስ በዋናነት እንዲያተኩር የተፈለገው በማኅበሩ የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ እንደነበር ተገልጧል፡፡ ቃለ ምልልሱን ምክንያት በማድረግ በዲያቆን ዳንኤል የወጣው ጽሑፍ አሉታዊ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፣ ዋና ጸሐፊው በማኅበሩ የፖሊቲካ ሱታፌ ላይ የተናገረው በሥራ አመራር አባላቱ በጋራ ያልተያዘ፣ በግል ግንዛቤው/እምነቱ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድቷል፡፡

እንደ መግለጫው ማብራሪያ ከሆነ፣ የማኅበሩ ኤዲቶሪያል አገልግሎት የሳንሱር ጠባይ ያለው እንደሆነ፣ ሕገ መንግሥትን አስመልክቶ በዋና ጸሐፊው ንግግር ውስጥ ያልነበረና በ“ዕንቁ” መጽሔ ዝግጅት ክፍል ኤዲቲንግ የተጨመረ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ሰንበት ት/ቤትን በተመለከተ በጋሻው በሰንበት ት/ቤት በተወሰነ ደረጃ የነበረው ተሳትፎ “በቂ ዕውቀት እንደማይሰጠው” እንጂ በመጽሔቱ ላይ እንደተገለጸው “ከሰንበት ት/ቤት ያላለፈ ዕውቀት ነው ያለው” የሚል ቃል በዲ/ን ሙሉጌታ ንግግር ውስጥ እንደሌለ ተገልጧል፡፡

የማ/ቅዱሳን አባላት በሰንበት ት/ቤቶች እና/ወይም በሰበካ ጉባኤ ውስጥ ገብተው የማገልገል እና የመገልገል ግዴታ እንዳለባቸው ሕገ ማህበሩ የሚያዝ ከመሆኑ አንጻር ዋና ፀሐፊው ሰንበት ት/ቤቶች በመናቅ መልክ የተናገረ መስሎ የቀረበው ቃለ ምልልስ በርግጥም ከዋና ፀሐፊው መቅረቡ ላይ ብዙዎች ጥርጣሬ ነበራቸው - ከመጀመሪያውኑ። እንደተገመተውም ዲ/ን ሙሉጌታ አሉታዊውን አባባል እንዳልተናገረው መታወቁ ማኅበሩ ከሰንበት ት/ቤቶች ጋር ያለው የጠነከረ ግንኙነት ምንም ነቅ ሳያገኘው እንዲዘልቅ ያደርገዋል።

ዲያቆን ዳንኤል በመደበኛ አገልግሎት በነበረው ድርሻ የሚዲያ ሓላፊ እና የልማት ተቋማት ማኔጂንግ ዳይሬክተር እንደነበር በዋና ጸሐፊው ምላሽ የተጠቀሰ ሲሆን ከሥራ አመራሩ ጋራ በተፈጠረው ልዩነቱና ከመደበኛ አገልጋይነት በለቀቀባቸው ጉዳዮች ላይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተነጋገረ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡ ነገር ግን መግለጫው በሥራ አመራር ጉባኤው በጋራ በተደረሰበት ውሳኔ መሠረት የተዘጋጀ ባለመሆኑ ዛሬና ነገ በሚካሄደውና የማእከላት ተወካዮች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አስተያየት ሊሰጥበት እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

የዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ በደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ ለአጭር ጊዜ ወጥቶ ከወረደ ጀምሮ በአንዳንድ የማኅበሩ አባላት መካከል ተጠናክሮ ቀጠለው የማጥቆር እና ፀረ ማጥቆር እንቅሰቃሴ እንዲገታ፣ ችግሩም ከመሠረቱ ተቀርፎ የብዙኀን ተስፋ የሆነው ማኅበር ታላቅ ትምህርት በሚያገኝበት አኳኋን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው እንደሚፈታው ተስፋ ተደርጓል፡፡

ጽሑፉ ደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ ለአጭር ጊዜ ወጥቶ እንዲወርድ የተደረገው ልዩነቱ በማኅበሩ የውስጥ አሠራር እንዲፈታ ዕድል ለመስጠት መሆኑን መግለጻችን ይታወሳል። ሐዋርያውተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 426) ያለውን በማስታወስ ደጀ ሰላም ለጉባኤው በስኬት መጠናቀቅ ያላትን መልካም ምኞት ትገልጻለች፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)