August 3, 2011

አቡነ ጳውሎስ "ተሐድሶ" ላይ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲደረግበት መመሪያ ሰጡ

  • ዛሬ በመንበረ ፓትርያኩ አዳራሽ የተሰበሰቡ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አለቆች፣ ጸሐፊዎችና የስብከተ ወንጌል ተጠሪዎች በሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ንባብ መመሪያውን እንዲሰሙት ተደርጓል፤ ጥያቄ ለማቅረብና አስተያየት ለመስጠት ተከልክሏል፤ መመሪያው በተመለከተ የሚዘግብ የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ልዩ እትም ከዋና አዘጋጁ ዕውቅና ውጭ እየተሰናዳ መሆኑም ተሰምቷል፡፡
  • “ቤተ ክህነቱ እንደቀድሞው ዘመን ለችግሩ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ የችግሩ አካል ወደሆነበት ጊዜ መድረሳችን ፈተናውን አክብዶታል፡፡ ሲኖዶሱ የተሐድሶ ችግር ስለ መኖሩ በመረጃ ከተረዳ በማስተካከል፣ በማውገዝና በመለየት መፍትሔ ማበጀት ይገባዋል፡፡. . .ችግሩ በማእከላዊ አካሄድ የማይፈታ ከሆነ ምእመኑ በተናጠል ወደ መፍትሔ ፍለጋ ያመራል፡፡ ይህ ደግሞ በጣም መጥፎና አደገኛ አካሄድ ይሆናል፡፡” (ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለ‹ዕንቊ› መጽሔት)
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 3/2011/ READ IN PDF)፦ ከወርኀ ጥቅምት 2003 ዓ.ም አንሥቶ በስፋት ተጀምሮ ጥልቀት እያገኘ በቀጠለውና ምእመኑ ከዳር እስከ ዳር በሃይማኖታዊ ቀናዒነት የተደራጀበት የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ እንቅስቃሴ፣ “የቤተ ክርስቲያንንና የሀገርን ሰላም ለማወክ የሚካሄድ” እንደሆነና ይህም “በስም አጥፊነት በሕግ ከማስጠየቅ ያለፈ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም” ሲሉ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አስጠነቀቁ፡፡
“ሥርዐትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ የሚቀርብ ማስረጃ ካለ እንደ ጌታችን ትምህርት ተደጋጋሚ ምክር፣ ትምህርትና ተግሣጽ መስጠቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ የማይታረምና የማይመለስ ሆኖ ሲገኝ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከመስጠት ወደኋላ እንደማይል ሁሉም ሊረዳው ይገባል በማለት ያስታወቁት አቡነ ጳውሎስ፣ በፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ከማድረግ ጋራ “ምእመናን ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በሰባክያነ ወንጌል አማካይነት ተከታታይ ትምህርት እንዲሰጥ” መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡


ይሁን እንጂ አስተያየት ሰጪዎች፣ የፓትርያርኩ መመሪያ ዋነኛ መንሥኤ ሰሞኑን በፀረ-ተሐድሶ ጥምረቱ ለኅትመት በበቁት መጻሕፍት እና ሲዲዎች አማካይነት በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ላይ የተጠናከረው እንቅስቃሴ እንደሆነ በመግለጽ በቢሮክራሲያዊ አሠራር ንቅናቄውን ለማዳፈን በሰርጎ ገብ አማካሪዎቻቸው የታቀደ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡


ተዋሕዶ የሐዋሳውያኑ ቁ. 2 ቪሲዲ፣ በረከት በእርስዋ ላይ አለና አታጥፋት” የመ/ር በላይ ወርቁ ቪሲዲ፣ “የሰባኪው ሕጸጽ” የዲ.ን ደስታ ጌታሁን መጽሐፍ ፣ “በጋሻው ኦርቶዶክሳዊ ነውን?”  የመ/ር ሣህሉ አድማሱ መጽሐፍ፣ “ውሾች ከበቡኝ” የሊቀ ትጉሃን ወንድወሰን አዳነ መጽሐፍ፣ “የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ” መጽሐፍ እና ቪሲዲ በማኅበረ ቅዱሳን በከፍተኛ ሁኔታ መሰራጨታቸው በሥራዎቹ ውስጥ አስተሳሰባቸው፣ ድርጊታቸውና ስማቸው በተገለጹት ግለሰቦች ላይ በየስፍራውና በየአጋጣሚው ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ/ አባ ሰረቀ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ ጥያቄ እንዲቀርብ ጭምር/ ምክንያት ሆኗል፡፡

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ለ‹ዕንቁ› መጽሔት የሰጡትና ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለንባብ የበቃው ቃለ ምልልሳቸው ያገኘው ከፍተኛ ተቀባይነትና የፈጠረው መነሣሣት ፓትርያርኩንና በዙሪያቸው የተሰለፉትን ጥቅመኞችና ሕገ ወጦች ማበሳጨቱም ሌላው ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡

በቁጥር ል/ጽ/592/1639/03 በቀን 25/11/2003 ዓ.ም በፓትርያርኩ ተፈርሞ ከጽ/ቤታቸው የወጣውና በአድራሻ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተለያዩ አካላት የተላከው ይኸው ደብዳቤ፣ “ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና እና ሥርዐት ውጭ በሆነ ሁኔታ እገሌ ተሐድሶ ነው፤ እገሌ መናፍቅ ነው” የሚል ጽሑፍ እየተበተነ፣ ካሴትና ሲዲ በመሳሰሉት መሣሪያዎች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት በማእከል ደረጃ በተሠየሙ ሊቃውንት እየተተረጎሙና የምሥጢራቸው ጥልቀትና ምጥቀት በሚገባ እየታዩ መሰራጨታቸው፣ ሰባክያንም ሆኑ የጉባኤ መምህራን በሚያስተምሩት ትምህርት የምስጢር መዛባትና የትርጉም ስሕተት እንዳይፈጠር ምንጊዜም እርማት የሚያደርጉ ሊቃውንት በጠቅላይ ቤተ ክህነት በጉባኤ እንዲሠሩ መደረጋቸው እንዲሁም እስከ ኮሌጅ ድረስ ት/ቤቶች መክፈታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና ሥርዐት ለመጠበቅና ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያሳይ ደብዳቤው ያትታል፡፡
ደብዳቤው አያይዞም የሃይማኖት ሕጸጽ ሲያጋጥም ስለ እውነትነቱ በሕጋዊ ማስረጃ የተደገፈ ጽሑፍ ቀርቦ፣ በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮና ተጣርቶ ትክክለኛ መሆኑ ሲረጋገጥ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ ማግኘት እንዳለበት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መታዘዙን አውስቷል፤ ሕግን፣ ሥርዐትንና የሥልጣን ገደብን ጠብቆ የማይፈጸም ድርጊት የምእመናንን ኅሊና በማሻከር፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ሥርዐትና በሀገሪቱ ሰላም ላይ ዕንቅፋት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚደረግ ሙከራ መስሎ ስለሚታይ ጎጅነቱ ቀላል እንዳልሆነም አሳስቧል፡፡ በመሆኑም “የእምነት ሕጸጽ በትክክል አጋጥሞ ከሆነና በቂ ማስረጃ አለኝ የሚል ካለ በግል ስሜት ብቻ ተገፋፍቶ ቀኖናው በማይፈቅደው አካሄድና በሌለው ሥልጣን ራሱ ወስኖ ከመሮጥ ይልቅ አለኝ የሚለውን ማስረጃ ቀኖናው በሚፈቅደው መርሕ መሠረት ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ እንደሚኖርበት” አስታውቋል፡፡

ይህን የፓትርያርኩን መምሪያ የያዘው ደብዳቤ ዛሬ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አዳራሽ ስብሰባ ለተጠሩትና ቁጥራቸው እስከ 200 ለሚደርሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች እና የስብከተ ወንጌል ተጠሪዎች በንባብ ተሰምቷል፡፡ ስብሰባው በዋናነት “ለታእካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም የቀሳውስትና መምህራን ማሠልጠኛ እድሳት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ለማቋቋምና በመጪው እሑድ በሚጀመረው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲሰጥ ለማሳሰብ” የተጠራ ነው ተብሏል፡፡ ለማሠልጠኛው ድጋፍ የሚያሰባስብ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

በስብሰባው መጨረሻ ላይ አሁን የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ሓላፊ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ የፓትርያርኩ መመሪያ የሰፈረበትን ደብዳቤ “በዝግታ እና ሳያሳስቱ” በንባብ ለጉባኤው እንዲያሰሙ በአቡነ ጳውሎስ ታዝዘዋል፡፡ ደብዳቤው ከተነበበ በኋላ ግን በርካታ እጆች ለጥያቄና አስተያየት የተነሡ ቢሆንም ፓትርያርኩ ዕድል አለመስጠታቸው ተነግሯል፡፡

መመሪያው በተሰጠበት አዳራሽ ከወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋራ እንደ አሰግድ ሣህሉ፣ ፍጹም ታደሰ (ፍጹም ሰይጣን ይሉታል)፣  ትዝታው ሳሙኤል፣ ናትናኤል ታምራት (“ዛሬ ከክርስቶስ ጋራ እናስተዋውቃችኋለን” ብሎ ያስተማረ)፣ ዕዝራ ኀይለ ሚካኤል፣ አሮን በረከት፣ ታምራት ኀይሌ፣ ቅድስት ምትኩ፣ ሐዋዝ (“ጌታ ሆይ፣ የአንተን ክብር ለእናትህ በመስጠቴ አጥፍቻለሁ፤ ይቅር በለኝ፣ መጥቻለሁ” ለፕሮቴስታንቶች የተናዘዘ) ያሉት ሕገ ወጦችና የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኞች እንዲገኙ መፈቀዱ የመመሪያውን ተጠቃሚዎች ማንነት የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡

ከስብሰባው በኋላ እነ አባ ሰረቀ፣ አሰግድ ሣህሉ፣ ፍጹም ታደሰ እና ትዝታው ሳሙኤል ደብዳቤውን ለማሰራጨት ሲራወጡ ታይተዋል፡፡ ይህም ቀድሞም ቢሆን የመመሪያው መውጣት የእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ ጌታቸው ዶኒ፣ በጋሻው ደሳለኝና የራሳቸው አባ ሰረቀ ከፍተኛ ግፊት እንዳለበት የተነገረውን ከጥርጣሬ በላይ የሚያስረዳ አድርጎታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ አበው ካህናትና ምእመናን በፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ዙሪያ ተሰብስበው ሰፊ ንቅናቄ በፈጠሩበት ሁኔታ የመመሪያው ፋይዳ እነ አባ ሰረቀንና መናፍቁ ጌታቸው ዶኒን ለመከላከልና ለሕገ ወጥ ሰባክያን ስምሪት ሽፋን ለመስጠት የታሰበ ስለመሆኑ የተሰማውን ጥርጣሬ የሚያጎላ ሆኗል፡፡

ከዚህም በላይ የመመሪያው መነሻ ሐሳብ አቡነ ጳውሎስ በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ላይ ያላቸውን ግዕዘ ኅሊና እና አቋም ገልጦ የሚያሳይ እንደ ሆነ ተዘግቧል፡፡ ፓትርያርኩ በመቐለ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ በተካሄደው የዘንድሮው የደቀ መዛሙርት ምረቃ በዓል ላይ “ተሐድሶ፣ ተሐድሶ እያሉ ለሚያስቸግሯችሁ እንደ አጋቶን ድንጋዩን ከአፋችሁ አውጥታችሁ የለም በሏቸው” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ በጋሻው ደሳለኝ ከምሥጢረ ሥላሴ እና ምሥጢረ ተዋሕዶ አስተምህሮ አኳያ ሕጸጽ የመላበት ንግግሩን ደጋግሞ በመናገር እያረጋገጠ ባለበት ሁኔታ፣ “ካላቸው የሙያ ብቃት፣ ፍላጎትና ዝንባሌ አንጻር እንደ ሌሎቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሠራተኞች የሥራ መደብና የስብከተ ወንጌል ፈቃድ እንዲሰጣቸው ታደርጉ ዘንድ እናስታውቃለን” የሚል ደብዳቤ ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጽፈዋል፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እንደተጻፈ የሚመስለው ደብዳቤው የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ያላረጋገጡት (ፓራፍ ያላደረጉበት) በውጭ የተረቀቀ የተጭበረበረ ደብዳቤ መሆኑ ታውቋል፤ በቀጣዩ የሲኖዶሱ ስብሰባም ሙከራው በአጀንዳነት ቀርቦ ፓትሪያሪኩ እንደሚጠይቁበት ተዘግቧል፡፡

በጋሻው በ”የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች”፣ “የጋግራን እሪታ” እና በቪሲዲ ባስተላለፋቸው መልእክቶች የሠራቸው ግድፈቶች “የጊዜ እና የዕድሜ አለመብሰል በፈጠሩት ጫና” የተነሣ “አላስፈላጊ የተግባር እንቅስቃሴ” ሲያደርግ መቆየቱን ደብዳቤው ያስረዳል፡፡ ለዚህም ግለሰቡ የካቲት 11 ቀን 2001 ዓ.ም ሊቃውንት ጉባኤ ፊት ቀርቦ ከእንባ ጋራ በተናገረው የመፀፀት ቃል ይቅርታ እንዲደረግለት በመጠየቁ መጋቢት 21 ቀን 2001 ዓ.ም ሊቃውንት ጉባኤው ቅዱስ ሲኖዶስ የበጋሻውን የይቅርታ ቃል እንዲቀበለው የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡ ተገልጧል፡፡ ግንቦት 11 ቀን 2001 ዓ.ም የተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም የሊቃውንት ጉባኤን የውሳኔ ሐሳብ በመቀበል፣ “መጋቤ ሐዲስ በጋሻው የሥራ ጓደኞቻቸውን ይዘው ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርቡና ይቅርታ እንዲደረግላቸው ውሳኔ ሰጠ፤” ይላል - ፎርጅዱ ደብዳቤ፡፡ አስከትሎም በእነበጋሻው የተረቀቀው ፍሮጅዱ ደብዳቤ፣ “የመጋቤ ሐዲስ በጋሻው ደሳለኝ የሥራ አፈጻጸም ጉዳይ…በቅዱስ ሲኖዶስ እልባት ካገኘ በኋላ በአፈጻጸም ችግር እስከ አሁን ድረስ መቆየት እንዳልነበረበት” በመተቸት ግለሰቡ ካለው “ሞያና ብቃት፣ ፍላጎትና ዝንባሌ አንጻር የሥራ መደብና የስብከተ ወንጌል ፈቃድ እንዲሰጠው” አስታውቋል፡፡

ፓትርያርኩ ደብዳቤውን ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ከመሩት በኋላ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መምሪያዎች፣ ሰባክያነ ወንጌልንና በተለይ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶችን በማስቆጣቱ በአስቸኳይ ተመላሽ እንዲደረግ ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡ ግለሰቡ “በጥፋቱ የተጸጸበት”ና “ይቅርታ ተደርጎለታል” የተባለበት አግባብና እውነታ አጠያያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ “ይቅርታ ተደርጎለታል” ከተባለ በኋላ በፈጸማቸውና በቅርቡ ስለተጋለጡት ሕጸጾቹ ሐምሌ 11 ቀን 2003 ዓ.ም በፓትርያርኩ ተጽፏል የተባለው ደብዳቤ ያመለከተው ነገር የለም፤ የዛሬው የፓትርያርኩ መመሪያም እነ በጋሻው በሚዲያ እየቀረቡና በቪሲዲ በግልጽ እያስተላለፉት ያለውን ስሕተት በጸና መሠረት ላይ በቆመው ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት መቃወምን በመከላከል የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር እየተነገረ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ሰሞኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተነግረው የሰማናቸው የብፁዓን አባቶች ትምህርት ከዛሬው የፓትርያርኩ መመሪያ ይዘትና አፈጻጸም ጋራ በቀጥታ የሚጋጭ መሆኑ ሲታይ፣ ፓትርያርኩ በቅዱስ ሲኖዶስ አብረዋቸው በሚሠሩ አባቶች ምክርና ውሳኔ ሳይሆን ሥነ አእምሯቸውን በተቆጣጠሩ ሕገ ወጦች ዱለታ የሚመሩ ስለመሆኑ ግልጽ አስረጅ ሆኗል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የሃይማኖት ጉዳይ እንዳያነሡ መከልከላቸውን ለ‹ዕንቊ› በሰጡት ቃለ ምልልስ ያጋለጡት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እንዲህ ብለዋል - “እኔ በአሁኑ የሃይማኖት አያያዛችን ደስተኛ አይደለሁም፡፡ በሃይማኖት ጉዳይ ለብታው በዝቷል፤ ለብታ አለ፤ ለብ ብለናል፤ በዚህ ለብታ የሃይማኖት አስተምህሮ መበላሸቱን እየሰማን ነው፡፡ በዚህ ሰሞን የተሠራጨ ሲዲ አለ፤ ‹ኢየሱስ በሉ እንጂ እግዚአብሔር አትበሉ› ይላል፤ ይሄ የንስጥሮስ ትምህርት ነው፡፡ ‹ይሄ የእኛ ሃይማኖት አይደለም› ተብሎ ቢያስፈልግ በዐዋጅ ወይ በሬዲዮ እርማት ሊደረግ ይገባል፡፡ ከእኔ ጀምሮ እያንዳንዳችን ሊቃነ ጳጳሳት አንድም በሲኖዶስ ሁለተኛም በየሀገረ ስብከታችን ሓላፊነት አለብን፡፡ በሃይማኖት ዝምታ ካለ ከእኛ ከጠባቂዎቹ በኩል ችግር አለ ማለት ነው፤ ‹ኢየሱስና እግዚአብሔር የተለያዩ ናቸው› የሚለውን ሰው ዝም ማለት ብቻ ሳይሆን ከተከባከብነው፣ ሥራ ከሰጠነው አቋሙን እንጋራለን ማለት ነው፤ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ አንድምታው ብዙ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ያለ ችግር እየተስፋፋ ነው።”

ሐምሌ 19 ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ትምህርት የሰጡት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስም፣ “. . .በሰማይም በምድርም የማምላችሁ ‹ተሐድሶ› የሚባሉ መጥተዋል፤ እነርሱን እንዳትከተሉ፣ እንዳትሰሙ ያስፈልጋል፤ የእኛ ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነው፤” ምእመናኑን አስጠንቅቀዋል፡፡ አገልግሎታቸውን አስመልክቶ ምዕዳን ለመቀበል በቢሯቸው ለተገኙት ሰባክያንም፣ “ጠንክራችሁ ተቋቋሟቸው፤ ሕዝቡ ከእናንተ ጋራ ነው፡፡ እኔም የሚጠበቅብኝን አድርጋለሁ፡፡ አይቀጠሩም፣ አይቀጠሩም፣ አይቀጠሩም!! አይሆንም፣ አይሆንም፣ አይሆንም!! ሕገ ወጥ ናቸው፣ ሕገ ወጥ ናቸው፣ ሕገ ወጥ ናቸው!!በማለት ውሳኔያቸውን አረጋግጠውላቸዋል፡፡ በዚሁ ዕለት በተለያየ ቦታ በስብከተ ወንጌል ላገለገሉ ሰባክያን መምሪያ የሰጡት ብፁዕ አቡነ ማርቆስም. “ይህ ሰውዬ ቢቀጠር ባሕታዊ ነው የምሆነው፤ መጀመሪያ የምቃወመው እኔ ነኝ፤ ስም እየጠቀሳችሁ ክሕደታቸውን ግለጡ፤ ምእመኑ ግራ አይጋባ፡፡” በማለት ማበረታታቸው ተዘግቧል፡፡

የፓትርያርኩ መመሪያ በሰፈረበት በዛሬው ደብዳቤ የተገለጹት የትምህርት ተቋማት፣ ሊቃውንት ጉባኤውም ሆነ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በአስተዳደር፣ በበጀትና በሰው ኀይል ምደባ ተሽመድመደው በሥልጣን እንዳይሠሩና እንዲዳከሙ የተፈረደባቸው በመሆኑ በመመሪያው የተገለጸውን የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዐት የማስጠበቅ ተግባር በሚፈለገው መልኩ መከላከል ስለመቻላቸው የብዙዎች ስጋት ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖቱን ከቀሳጥያን ለመጠበቅ በፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አጀንዳ ዙሪያ የተሰባሰበው ምእመንና አገልጋይ ከማንም ያልተሰወረ እንቅስቃሴም ‹የሀገርን ሰላም በማደፍረስ› መፈረጁም “የመንግሥት ያለህ” የሚያሰኝ ነው፡፡ 


 

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)