August 2, 2011

(ሰበር ዜና) ማኅበረ ቅዱሳን በአባ ሰረቀ ላይ የመሠረተው ክስ ለጊዜው እንዲቋረጥ ታዘዘ

  • ትእዛዙ ፓትርያርኩ ለፍትሕ ሚኒስቴር የጻፉትን ደብዳቤ መነሻ ያደረገ ነው::
  • የማኅበሩ የሕግ አገልግሎት የፍርዱ ሂደት የሕግ የበላይነትን በሚያስከብር አኳኋን የሚቋጭበትን መንገድ እያጤነ ነው::
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 2/2011/ READ IN PDF):- በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል በፈጸሙት የስም ማጥፋት ድርጊት የመሠረተባቸው ክስ እንዲቋረጥ የፍትሕ ሚኒስቴር አዘዘ፡፡ ትናንት ለዐቃቤ ሕግ በተጻፈውና በሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፣ “አባ ሰረቀ ብርሃን በተከሰሱበት የስም ማጥፋት ወንጀል ማጣራት የምንፈልገው ስላለ ክሱ ለጊዜው ተቋርጦ መዝገቡ እንዲላክልንሲል ትእዛዝ መሰጠቱን ያስረዳል፡፡


ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ለፍትሕ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ፡- አባ ሰረቀ መጋቢት 30 ቀን 2003 ዓ.ም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች ስለ ማኅበሩ የሰጡት መግለጫ ባለባቸው የሥራ ሓላፊነት አግባብ የተነገረ እንጂ የስም ማጥፋት ድርጊት አለመሆኑን፣ የክሱ ፍሬ ነገር ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት እየተመለከተ ባለበት ሁኔታ በተፈጠረ ግጭት ላይ የተመሠረተና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን፣ እንዲህ ዐይነት የውስጥ ጉዳዮች ወደ ክስ ማምራታቸው ለሌሎቹ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካላት መጥፎ አርኣያ ሊሆን እንደሚችል በማስረዳት ክሱ እንዲቋረጥ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡

ሚኒስቴሩ በፓትርያርክ ደረጃ የቀረበውን አቤቱታ መሰል ጥያቄ መታየት እንዳለበት በማመን የክሱ ሂደት እንዲቋረጥ ቢያዝም፣ አቤቱታው በክሱ ከተመለከተውና አባ ሰረቀ በሰው ምስክር፣ በሰነድ እና በምስል ወድምፅ ከቀረበባቸው ማስረጃ ጋራ ያለውን አግባብነት ከትክክለኛ የፍትሕ አሰጣጥ አኳያ እንደሚመረምረው ተስፋ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የማኅበሩ የሕግ አገልግሎት በበኩሉ ክሱ ለጊዜውም ቢሆን እንዲቋረጥ የተደረገበትን መነሻ በመፈተሽ የፍርዱ ሂደት የሕግ የበላይነትን በሚያስጠብቅ አኳኋን እንዲቋጭ ብርቱ ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2003 ዓ.ም አባ ሰረቀ በዐቃቤ ሕግ የቀረቡባቸውን የሰው ምስክር፣ የሰነድና የምስል ወድምፅ ማስረጃዎች እንዲከላከሉ በታዘዙት መሠረት ያስረዱልኛል ያሏቸውን 12 ምስክሮች አቅርበው እንዲያሰሙ የታዘዙበት ቀጠሮ ነበር፡፡ ዐቃቤ ሕጓ ክሱ ለጊዜው እንዲቋረጥ ከሚኒስትሩ የተሰጣቸውን ደብዳቤ በማስረዳት ወደፊት መዝገቡን የማንቀሳቀስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ይጠይቃሉ ተብሏል፡፡

ጉዳዩን የሚከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ የአባ ሰረቀ ተጠሪነት ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እንደመሆኑ በፓትርያርኩ የቀረቡት አቤቱታዎች በእርሳቸው ዕውቅና እና የሓላፊነት ደረጃ መቅረብ ይገባው እንደ ነበር በመጥቀስ የጥያቄውን አቀራረብ ይተቻሉ፡፡ በዛሬው ጊዜ-ቀጠሮ አባ ሰረቀ ምስክሮቼ ባሏቸው ክሱን እንዲከላከሉ ተደርጎ ሂደቱ ወደ ብይን መቀጠል ይገባው እንደነበር የሚናገሩ ተቺዎች በበኩላቸው፣ የመጨረሻ ውሳኔ እስካልተሰጠ ድረስ ሂደቱ በተገለጸው መልኩ ሊቋረጥ የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም ማኅበረ ቅዱሳን ጠበቃ በማቆም እንዲቀጥል ለማድረግ የሚችልበት አግባብ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

አባ ሰረቀ ማኅበረ ቅዱሳን በመምሪያ ከቀረበለት ጥያቄ ለመሸሽ ታላላቅ አባቶችን በፍርድ ቤት መክሰሱን፣ ይህም የጥቂት አመራሮች ፍላጎት መሆኑን በመግለጽ የማኅበሩ ብዙኀን አባላት ለማነሣሣት እየሞከሩ ነው፡፡ ሰሞኑን ወደ አደባባይ የወጣውን በማኅበሩ ውስጥ የተከሠተ አለመግባባት የተመሠረተባቸውን ክስ ለማድበስበስ ሊጠቀሙበት እየጣሩ ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡ ከዚህ አኳያ አባ ሰረቀ የውስጠ-ማኅበር አለመግባባቱን ከዐውድ ውጭ እየወሰዱ በመበዝበዝ የማኅበሩን አባላት ልብ ለመብላት የሚሞክሩበት ከፋፋይና የአዛኝ ቅቤ አንጓች ፕሮፓጋንዳ እንደማይሠራላቸው የማያሻማ መልእክት ሊተላለፍላቸው እንደሚገባ ደጀ ሰላም ታምናለች፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)