August 1, 2011

የዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ርእሰ አንቀጽ


የነጻነት በዓለ ሢመት (ርእሰ አንቀጽ)
/ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ 56 ዓመት ቁጥር 121፤ ሰኔና ሐምሌ 2003 ዓ.ም, READ IN PDF/፦ የአምስተኛው ፓትርያሪክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 19 ዓመት የፓትርያሪክነት በዓለ ሢመት የአንድ ግለሰብ የሥራ ፍሬ የሚገለጥበት፣ ክብርና ዝናው የሚንጸባረቅበት ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያናችን ለ1600 ዘመናት ያህል በግብጻውያን የአገዛዝ ቀንበር ሥር ስትማቅቅ ኑራ ነጻ የወጣችበት ዘመን የሚታሰብበት በዓለ ሢመት ነው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ እመርታን ያስገኘችበት በዓለ ሢመት በመሆኑ መንፈሳዊ ነጻነትን ሙሉ በሙሉ የተጎናጸፍንበትን ይህን የነጻነት በዓለ ሢመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ብቻ ሳንሆን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት የሆን በሙሉ በታላቅ መንፈሳዊ ሐሤትና በታሪካዊ ትዝታ ልናከብረው ይገባናል፡፡

ከዚህ በላይ እንደተገለጸው የጥንቶቹ ግብጻውያን ‹‹ኢትዮጵያውያን ከዐዋቂዎቻቸው መካከል ጳጳሳትን መሾም አይገባቸውም›› ይል በነበረው በሥርዋጽ ባስገቡት አጉል ዘይቤ በመመራት ባደረሱብን ተጽዕኖ ጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ነጻነቷን ተገፋ የኖረችበት ዘመን ሩቅ አይደለም፡፡ ታዲያ ይህን መንፈሳዊ ነጻነት ለማግኘት የቀድሞ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥትም ጭምር ብዙ ደክመውበታል፤ በልኡክነት ተልከው ሲሄዱም የግብጽ በርሓ የበላቸው ወገኖቻችን ብዙዎች ናቸው፡፡

በዚህ ጉዳይ ከደከሙትም ኢትዮጵያውያን አበውና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መካከል የስብከተ ወንጌል ማኅበር በማቋቋም ትምህርተ ወንጌል በመላ ኢትዮጵያ እንዲዳረስ ያደረጉትና የገቢ ምንጭ የሚሆኑ ሕንጻዎችን በማሠራትም ሆነ በፓትርያሪክነቱ በር ከፋች የሆኑት የመጀመሪያው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም ቃለ ዐዋዲ የተሰኘውን መተዳደሪያ ደንብ አውጥተው በመላዋ ኢትዮጵያ ሰበካ ጉባኤን ያቋቋሙት፣ የካህናት ማሠልጠኛዎች ተከፍተው የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ካህናት ከጊዜው ጋራ የተገናዘበ ዕውቀት እንዲያገኙና ወጣቶች በሰንበት ት/ቤቶች አማካይነት እንዲደራጁ ያደረጉት ሁለተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ በዓለ ሢመቱ ይህን መሳይ ቋሚ ሥራ ሠርተውልን ያለፉትን እነዚህን የመሳሰሉትን ቅዱሳን አባቶች ሁሉ እንድናስባቸው ያስገድደናል፡፡

ከዚህም ሌላ በገዳማዊ ሕይወታቸውና በፍጹም አባትነታቸው የመላውን ዓለም ትኩረት የሳቡትና የሰበካ ጉባኤን በመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ግምገማ ያጠናከሩት መናኙና ፍጹሙ ሦስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሊወሱ የሚገባቸው በዚሁ በዓለ ሢመት ነው፡፡ ዛሬ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ከአድማስ እስከ አድማስ እንደልባቸው ለመንቀሳቀስ ያስቻለቸውንና ከላይ እስከ ታች ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሠራተኞችም በቂ ወርኀዊ ደመወዝ ሊያገኙ የቻሉትም በየጊዜው በተሾሙትና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገትና ብልጽግና ቅድሚያ ይሰጡ በነበሩት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች ከፍተኛ ጥረትና በየወቅቱ በነበሩት ሠራተኞች መሥዋዕትነት በመሆኑ እነርሱም በዚህ በዓለ ሢመት ሊታሰቡ ይገባቸዋል፡፡

እነሆ ለአሁኑ የአገልጋዮች ካህናት የተሻለ አኗኗርና ለምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት መመቻቸት የሰበካ ጉባኤን ከመሐል ኢትዮጵያ እስከ ጠረፊቱ ኢትዮጵያ በማቋቋም፣ የገቢ ምንጮቻችን የሆኑትን ሕንጻዎች አሠሪና ተቆጣጣሪ እየሆኑ ጦም ውለው፣ ጦም አድረው በማሠራት፣ የስዕለት ገቢዎችንና የሙዳየ ምጽዋት ገንዘቦችንም የእግዚአብሔር ገንዘቦች እንደሆኑ ተገንዝበው በጥንቃቄና በፈሪሃ እግዚአብሔር በመያዝ እነርሱ እየተራቡ ያቆዩት ገንዘብ ነው፤ ዛሬ የበላውንና ያልበላውን የሙስና ዱላ ሲያማዝዝ የሚስተዋለው፣ ማጣቱ ሳያወዛግብና ዱላ ሳያማዝዝ ማግኘቱ፣ ማወዛገቡና ዱላ ማማዘዙ ግን እጅግ የሚያስገርምና የሚያሳዝን ነው፡፡

ዛሬ ሁሉም እንደ ልቡ የሚዝናናበትና ለድንገተኛው ሁሉ ብር በቁና እየተሰፈረ የሚገኘው እነዚያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራና ሁለንተናዊ በየዘርፉ ሲደክሙ እንደተራቡ የሞቱት ሐቀኞች ሠራተኞች ሊበሉት ይገባቸው የነበረ የሙታን ውዝፍ ደመወዝ መሆኑንም ሁላችንም በጥልቀት ልንገነዘበው ይገባል፡፡ ከተገነዘብነውም ዘንድ በዓለ ሢመቱ የእነሱም የመታሰቢያ በዓል መሆኑን አንርሳው፤ ካረሳነውም በሥራችን ሁሉ እንደ እነርሱ ሐቀኞች ለመሆን እንጣጣር፤ በሐቅና በፈሪሃ እግዚአብሔር የተሰበሰበውንም ገንዘብ ያለሐቅ ስንበላው ደይንና መቅሰፍት እንደሚሆንብን እንረዳ፡፡

ወደ አሁኑ ስንመጣም የመንፈሳዊ ኮሌጆች መከፈት፣ በየአህጉረ ስብከቱ የካህናት ማሠልጠኛዎች መዋቀር፣ የቅርሳ ቅርስ መጠበቂያና መከባከቢያ ሙዝየሞች መሠራት፣ ተወርሰው የነበሩት ሕንጻዎች መመለስ፣ የጽርሐ መንበረ ፓትርያሪክ የአባቶች ማረፊያ ቤት መሠራት እንዲሁም የሠራተኛው ዘመናዊ ቢሮ ግንባታና የደመወዝ ስኬል መሠረት መጣል 19ው ዓመት የፓትርያሪክነት በዓለ ሢመት የሚከበርላቸው የአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና በየተራቸው አብረዋቸው በሥራ አስኪያጅነት የሠሩት የብፁዓን አበው ጥረት ውጤትና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ጭምር ታክሎበት የተፈጸመ በመሆኑ በበዓለ ሢመቱ ይህ ሁሉ ተጠቃሎ ሊታሰብና ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል፡፡

የአሁኑ የግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ያሳለፋቸው አንዳንድ ውሳኔዎችም በተግባር ከተተረጎሙና የሚገፋባቸው ከሆነ ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ የሚታይባቸው ስለሆኑ የበዓለ ሢመቱ ዋዜማ ፍሬዎች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊውን ነጻነት ሙሉ በሙሉ ከተጎናጸፈች ወዲህም ቢሆን የወርቅ ኢዮቤልዩን ጨርሳ የአልማዝ ኢዮቤልዩን የተያያዘችው ስለሆነ ከጊዜው ርዝመትና ከብፁዓን አባቶች መበራከት አንጻር ሲታይ ተመጣጣኝ ሥራ ተሠርቷል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፤ የሥራ ውጤቱ ብዙ የሚያወላዳ አይደለም፡፡

ስለሆነም ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፊት ተደቅነው ይታያሉ፤ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ብንጠቅስ፡-
  •  በአዲስ አበባም ሆነ በአህጉረ ስብከት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገትና ብልጽግና የሚረዱ የማምረቻ ተቋማትን ከፍቶ በካህናት ስም በየቤተ ክርስቲያኑ ያለውን የሠራተኛ ክምችትና የቦዘነ ጉልበት ወደየማምረቻ ተቋማቱ ማሰማራት፤
  •  የሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ጥራትና ብቃት እንዲኖረው በየደብሩ የተመደቡት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ከጊዜው ጋራ እንዲገናዘቡ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች እየገቡ እንዲሠለጥኑ ማድረግ፤
  •  በየገዳማቱና በየአድባራቱ የሚሾሙት አስተዳዳሪዎች ‹‹ለእኛ ይመቹናል፤ ይታዘዙናል›› በሚለው ዘይቤ ሳይሆን ለእግዚአብሔርና ለቤተ ክርስቲያኑ ይመቿቸዋል፤ ይታዘዟቸዋል፤ ዕወቀታቸውና ግብረ ገብነታቸውም ምእመናንን ያንጻል በሚለው ዘይቤ እየተፈተሹ ሊሾሙ ይገባቸዋል፡፡
  • በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ዋና መምሪያና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የተነሣው ውዝግብ የዘለቄታ መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ፤
  • ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ ጥቅመኞች በየነጻ ፕረሱ የፈጠሩት የተሐድሶ ውዝግብና ውዥንብር ንጹሐን ምእመናንን ግራ ያጋባና የሌላው እምነት ተከታዮች መዘባበቻ ያደረገ ስለሆነ አንዱ የአንዱ ቡድን ደጋፊ፣ ሌላው የሌላው ቡድን አቀንቃኝ በመሆን የላይ ፈሪ የታች ፈሪ እያሉ ማባባሱን አስወግዶ መከፋፈልና የከፋ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የማያዳግም እልባት እንዲያገኝ ማድረግ፡፡


ይህ ሲሆን ብቻ ነው ሙስና የሚቀነሰውና የእግዚአብሔር ገንዘብ ለእግዚአብሔር የሚሆነው፤ ብሎም የእግዚአብሔር በረከት የሚትረፈረፈውና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያኒቷ የ20ው ዓመት የነጻነት በዓለ ሢመት የቤት ሥራ(ጥናትና ዕቅድ) ሊሆን ይገባዋል፡፡

በአጠቃላይ በዓለ ሢመቱ የሚያስታውሰን ባለፈው የተሠራውን ሥራ ብቻ ሳይሆን ያለፉት አባቶች የሠሩትን ሥራ ዛሬ እኛ እየሠራነው ካለው ሥራ ጋራ በማወዳደር ቀጣዩ ትውልድ እኛንም በሥራችን እንዲያስበን ልንሠራው የሚገባንንም ያሳስበናል፡፡ ቀደም ብሎ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው በዓለ ሢመቱ ያለፉት አባቶቻችን ብዙ የተጋድሎ ሥራ የሠሩበትና አያሌ መሥዋዕትነትን የከፈሉበት የነጻነት በዓለ ሢመት ስለሆነ እንደ ግለሰብ በዓል ሳንቆጥረው እንደ ሁላችን በዓል አድርገን በታላቅ መንፈሳዊ ስሜትና ሐሤት ልናከብረው ይገባናል፡፡

(መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ፤ ዋና አዘጋጅ)

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)