July 28, 2011

የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች ታሪካዊ መግለጫ አወጡ፤ ተሐድሶን ተቃወሙ


(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 28/2011/ READ IN PDF):-  የሰ/አሜሪካ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ ኑፋቄ በመቃወም ታሪካዊ መግለጫ አወጡ በአዲስ አበባ የሚገኙ ወንድሞቻቸው እህቶቻቸው የሰንበት ት/ቤቶች አባላት ያሳለፉትን ውሳኔ ደገፉ። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ሰፍሯል።
 
 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 
ሥራ አስፈጻሚ  የተሰጠ መግለጫ

ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም።  1ኛ ቆሮ 311

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  ጥንታዊት ታሪካዊትና ብሔራዊት  እንደመሆኗ መጠን በዓለም አቀፍ  ደረጃ ሳይቀር በከፍተኛ አድናቆት ከሚጠሩት የእምነት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኗ ይታወቃል።  ቤተክርስቲያናችን ሐዋርያዊት የተባለችውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማራቸው ሐዋርያት በጉባኤ ወስነው ፤ በቃል አስተምረው ፤በጽሁፍ አስቀምጠው በሰጡን ዶግማና ቀኖና  መሠረት የምትመራ መሆኗን ለመመስከርና ይህንን መሠረት ጠብቆ ማገልገልና መገልገል የሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን መንፈሳዊ ግዴታ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው ። ይህም ታላቅ መንፈሳዊ አደራና  ኃላፊነት በብዙ መስዋዕትነትና ተጋድሎ ከትውልድ  ወደ ትውልድ  ሲተላለፍ ቆይቶ ተረኛ እና ባለ አደራ ለሆነው ለዚህ ትውልድ ደርሷል ። ይህም ትውልድ አባቶች እንዳስረከቡት የቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጠብቆ፤ ጊዜው የጠየቀውን መስዋዕትነት ከፍሎ፤ የሃይማኖት ጽናትን በቃልና በተግባር  በማሳየት በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ  (መዝ4516) የተባለው አምላካዊ የተስፋ ቃል ዛሬም እየተፈጸመ መሆኑን በተግባር መግለጽ ይኖርበታል።

ከቤተ ክርስቲያን  ታሪካዊ እና ሐዋርያዊ ጉዞ እንደምንረዳው አጽራረ ቤተ ክርስቲያንና አላውያን ነገሥታት  በክርሰቶስ ደም የተመሠረተችውን ቤተክርስቲያን ቢቻላቸው መሠረቷን ለማናጋት፤ በቻሉት አጋጣሚ ሁሉ እምነት ዶግማና ቀኖናዋን ለማፋለስ  ያላቸውን ሥልጣንና ገንዘብ በመጠቀም  ክርስቲያኖችን  በማታለል፤ በማስፈራራትና በማሰቃየት ብዙ መከራ በክርስቲያኖች ላይ ቢያደርሱም እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” (ሐዋ420) ብለው የተናገሩትን የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ሞትን ሳይፈሩ ጸንተው በመመስከር ሰማዕትነትን ተቀብለው ታሪካቸውን ጠብቀው ለትውልድ አስረክበው አልፈዋል። በዚህ ሁሉ ፈተና ግን ቤተ ክርስቲያን የበለጠ እየተስፋፋች መሄዷን ስንለመከት  በየዘመኑ የነበሩት አባቶችና ምእመናን  የነበራቸው እንደ ብረት የጠነከረ አንድነትን እና መንፈሳዊ ቅናት  ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ትልቁ ድርሻ እንደነበረው እንረዳለን። በዓለም አቀፍ ደረጃ  በኒቅያ፤ በኤፌሶን እና ቁስጥንጥንያ በተደረጉት ጉባኤያት የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ትምህርት ለማዛባት እና የሐዋርያትን ቀኖና ለማፋለስ ለተነሱት መናፍቃን  ሁሉ  ስህተታቸውን በመናገር እውነትን የመሰከሩት፤  ቅዱስ አትናቴዎስን የመሰሉ አባቶች  ለስደት የተዳረጉት የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት ጠብቆ ለትውልድ ለማስረከብ ጽኑ መንፈሳዊ ቅናት እንደሆነ ይታወቃል ።

ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ብለው አበው በብሂል እንደሚናገሩት የቤተ ክርስቲያንን ባለቤት እግዚአብሔርን በመናቅ  ለሃይማኖታቸው ለሥርዓታቸው የሚቆጬ አባቶችና ምእመናን የሌሉ በማስመሰል በቤተ ክርስቲያን ላይ የድፍረት እጃቸውን የዘረጉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆች በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የክህደት መርዛቸውን ለማስፋፋት ደፋ ቀና ሲሉ በማየታችን የተኛን ሁሉ ነቅተን ጉዳዩን በዝርዝር መርምረን ለእውነትና ለምስክርነት በአንድነት መቆም እንዳለብን  ተረድተናል። ይህንን ለማድረግ የማንነሳ ከሆነ ግን የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ አደራ ብሎ የሰጠንን አምላካችንን ቃል በመዘንጋት በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ በሰው ፊት ለሚክደኝ ሁሉ በሰማዩ አባቴ ፊት እክደዋለሁማቴ 1032-33 ብሎ በተናገረው  መሠረት  የምንመዘን መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል፤ በተጨማሪም  ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው፤ በእንተ ስማ ለማርያም ብለው ተምረውና አስተምረው  ሰማዕትነትን ተቀብለው በአደራ ያስረከቡን የአባቶቻችን ታሪክም ይፋረደናል።

በአጠቃላይ ከቀደመው ታሪክ የምንማረው ለሁላችንም ክብር መሠረቱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓት መከበርና መጠበቁ ነው። ዛሬ በታላቅ ክብር የምናነሳቸው የሃይማኖት አባቶቻችንም የተከበሩት የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በማክበራቸው በእውነት በመሄዳቸው ነው። ዛሬም ቢሆን የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን የሚከበሩት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ሥርዓት ሲያከብሩ ነው። የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ሥርዓት የሚንቅ ሁሉ  በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ያለውን ክብር ማጣቱ የማይቀር ነው። የታሪክ ምስክርነት እንደሚያረጋግጥልን ቤተ ክርስቲያንን ያከበሩ ተከብረዋል ቤተ ክርስቲያን  የእግዚአብሔር ቤት መሆኗን ዘንግተው የራሳቸውን ስሜት እና ፍላጎት ለማርካት ሲሉ  ትምህርቷንና  ሥርዓቷን ለማፍረስ የሞከሩ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ ተዋርደው፤ ከክብር ሲያንሱ ታይተዋል። በዚህ መልኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ በታላቅ ተጋድሎ ሲተላለፍ የቆየው እምነታችንና ሥርዓታችን በእኛ ዘመን ቅጥ አጥቶ ሥርዓት ተዛብቶ እምነት ተፋልሶ ለማየት መቼም ቢሆን አንፈልግም ።

ሐዋርያት በቀኖና ያስቀመጡት ሥርዓት ቀስ በቀስ ችላ እየተባለ በመምጣቱ በምንኖርበትም በሰሜን አሜሪካ ጭምር የሚያሳዝን ተግባር ሲከናወን  ይታያል።  በተለይም  አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን  አባቶች የተሰጣቸውን ክብርና  ኃላፊነት መሠረት በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በመጠበቅ ለሰንበት ት/ቤቶች አባላትና ለምእመናን ምሳሌ መሆን ሲገባቸው የቤተክርስቲያንን ሥርዓት በቀላሉ ሲተላለፉ በማየታችን መንፈሳዊ ሐዘን ተሰምቶናል። ለምሳሌ ያህል ብንመለከት የቤተ  ክርስቲያን  ቀኖና እንደሚያዘው  አንድ ሊቀ ጳጳስ ወደ ሌላ ሀገረ ስብከት ሲሄድ በቅድሚያ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እያዘዘ ወደ ሰሜን አሜሪካ  በቅርቡ የመጡ አንድ ሊቀ ጳጳስ ግን ይህንን ሥርዓት ከመጠበቅና ለሌሎች ምሳሌ ከመሆን ይልቅ በራሳቸው አካሄድ በመጓዝ በተጨማሪም  በሀገረ ስብከቱ መዋቅር ውስጥ  ባልተካተቱ እና ራሳቸውን ገለልተኛ ብለው በሚጠሩ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ቀኖናን ተላልፈው የሚመለከታቸው ሊቀ ጳጳስ እያሉ ሥልጣነ ክህነት በመስጠት የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ሲተላለፉ በማየታችን የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ እኒህ አባት መመሪያ እያከበሩ እና እየጠበቁ ስለመሆናቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መነጋገር እንደሚገባው ተረድተናል።

ቅዱሳን አባቶቻችን ቆመው የሃይማኖት ምስክርነትን የሰጡበት የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምህረት  ያለውን ክብር ካለመረዳት እና በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ግፊት በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ሥርዓት የሚቃወም፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን ግራ የሚያጋባ፣ የሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን መሠረት የሚያናጋ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ቦታ እያገኘ መምጣቱን ሁሉም እያስተዋለው የመጣ እውነታ ነው። ቁጥጥርና ክትትል የማይደረግባቸው ሕገ ወጥ ሰባኪያን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ከማጠናከር ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም በማሳደድ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ የፈለጉትን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተመልከተናል። የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሳይመለከቱት እና ቤተ ክርስቲያንን የሚወክል ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሳይሰጥበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ደንብና እና ሥርዓት የጠበቀ በማለት ትውልዱን የሚያሰናክል የትምህርትና የመዝሙር ካሴቶች መሠራጨታቸው እና የመናፍቃን የክህደት ትምህርቱን በቃልና በጽሁፍ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ለማስፋፋት እድል ማግኘታቸውን ስንመለከት እውነትን የሚናገር ሰው ጠፋ ወይ?” የሚያስብል ከመሆኑም በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን መብት የማስጠበቅ ጉዳይ ወቅታዊ ተግባር መሆኑን አስገንዝቦናል።

ከዚህም  በተጨማሪ ከእግዚአብሔር በነጻ የተሰጣቸውን የማስተማርና የመዘመር ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ብለው  ማገልገል እንደሚገባቸው የቤተክርስቲያን ትምህርት እየገለጸ ፤ የሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም ሕይወት ይህንኑ እየመሰከረ ፤ ይህንን ተላልፈው ትምህርታችንንና መዝሙራችን ግዙ እያሉ  በእግዚአብሔር ቃል መነገድን ሥራየ ብለው የተያያዙትን  አሳዛኝ ተግባር እየተመለከትን ሲሆን ይህ ከፍተኛ ወንጄል በቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ማየታችን  የእግዚአብሔርን ቤት የንግድ ቤት  አድርጎ በንቀት መመልከት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ። ይህ ተግባር  ሊወገዝ የሚገባው ከመሆኑም በተጨማሪ  እያወቁ እንዳላወቁ ሆኖ ወይም የጥቅም ተካፋይ ሆኖ ዝም ማለት ግን ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁትሉቃ 1946  ብሎ በተናገረው አምላካዊ ቃል መሠረት  ሁላችንም  ለዚህ ጉዳይ በምንሰጠው ተግባራዊ ምላሽ የምንመዘን መሆኑን ያመለክተናል ።  ይህ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በካህናትና በምእመናን ዘንድ ይበቃል መቆም አለበት አሁን ካልተባለ የእግዚአብሔርን የቁጣ በትር ማስነሳቱ የማይቀር ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን የምትገኝበትን አጠቃላይ ሁኔታና በተለይም የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-እንቅስቃሴን ጉዳይ  በቅርበት እየተከታተለ የሚገኘው የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ይህ ወቅታዊ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እና ተግባራዊ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ተረድቷል። በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች ይህንን የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ለመግታትና ከቤተ ክርስቲያን ለማጽዳት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ብንረዳም የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ደረጃውን ያልጠበቀ፤ የቅዱስ ሲኖዶስን የበላይነት የናቀ፤ ምእመናንን ለብጥብጥ ማነሳሳትን ትኩረት ያደረገ ተሐድሶየሚባል የመናፍቃን እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የለም በማለት ኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያንን ለማፈራረስ ለተነሡ መናፍቃን ሽፋን በመስጠት ላይ መገኘታቸውን ተረድተናል። በተቀደሰው የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትም ላይ  ሥላሴ አትበሉ፤ እግዚአብሔር አትበሉ፤ ምንድን ነው ፍርሃት ዙሪያ ዙሪያውን መሸሽ፤ ኢየሱስ ብቻ በሉየሚሉ መልእክት ያላቸውን  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ እና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ  ያለውን አንድነት የሚለዩ የኑፋቄ ትምህርቶች መስማታችን በቂ ማስረጃ ነው ።ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን በየዐውደ ምሕረቱ ሕዝቡን እንዳያሰናክሉ ውሳኔ ያስተላለፈ ቢሆንም ይህንን ውሳኔ ችላ በማለት እና የቤተ ክርስቲያንን መድረክ ከሥርዓት ውጭ ለዓላማቸው እንዲጠቀሙበት  አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል  እና መሰሎቻቸው በሚሰጡት ደረጃውን ያልጠበቀ መመሪያ ምእመናን እንዲበጠበጡ፤ አባቶች በንቀት እንዲታዩ የማድረግ ዘመቻ  የማን አለብኝነት መገለጫ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ሆኗል።

ለዚህም በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ በአዲስ አበባ ደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን፣ በደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንና በዲላ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን  የተከሰቱት ችግሮች በቂ ግብዛቤ ሰጥተውናል። ይህንን ችግር በመረዳት  የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ሕገ ወጥ ሰባኪያንና መዘምራን የሚፈጥሩትን ችግር ለማስቆም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እየወሰደ እንዳለው ተግባራዊ ምላሽ ሌሎች አህጉረ ስብከትም በተመሳሳይ መልኩ ቁርጥ አቋማቸውን በማሳየት የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት የማስጠበቅ ተግባር ይሰራሉ ብለን በተስፋ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። ይህ እየተከሰተ ያለው ችግር ከአሁኑ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው የሁሉንም ሰላም የሚረብሽና ወደ አልተፈለገ ብጥብጥ  የሚገፋፋ በመሆኑ ጉዳዩን የሰሙና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የቤተክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅና ሰላምን ለማረጋገጥ ተገቢው ምላሽ እና እርምጃ  ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተጠናክሮ መሰጠት ይገባል እንላለን።

ይህንን ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር በጥልቀት ከመረመረ በኋላ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
1.   ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል እንደመሆኑ መጠን የቤተ ክርስቲያንን ህልውና መጠበቅ ባለበት ኃላፊነት መሠረት  ከዚህ በፊት ሕገ ወጥ ሰባኪያነ ወንጌልና መዘምራንን በተመለከተ ባስተላለፈው ውሳኔ ከፍተኛ መንፈሳዊ ደስታ የተሰማን ቢሆንም ውሳኔው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር በጠበቀ መልኩ  በየደረጃው የሚገኙ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን እንዲመለከት በመጠቆም ይህንን ሂደት ለማሳካት  የሰንበት ት/ቤቶች አባላት ሊኖረን  የሚገባው ድርሻ በግልጽ መመሪያ እንዲሰጠን እንጠይቃለን ።
2.   የተሰጣቸውን ኃላፊነትና አደራ በመዘንጋት  ደረጃውን ያልጠበቀ መመሪያ በማስተላለፍ  የሰንበት ት/ቤት አባላትን የናቀ እና ወደ ብጥብጥ የሚመራ ተግባር በመፈጸም ላይ የሚገኙት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል  አሁን እያደረጉ ያሉት ተግባር እንዲገመገምና የባሰ ችግር በቤተክርስቲያን ላይ ከማስከተላቸው በፊት የተሻለ ብቃት እና መንፈሳዊነት ባላቸው ኃላፊዎች እንዲተኩ እንጠይቃለን ።
3.   የወቅቱን የቤተ ክርስቲያንን ችግር መሠረት በማድረግ የአዲስ አበባ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በቅርቡ ያወጡትን መግለጫ ሙሉ በሙሉ የምንደግፈውና እኛም የሚጠበቅብንን ሁሉ ከወንድሞቻችን ጋር በመሆን ለማድረግ ያለንን መንፈሳዊ ቁርጠኝነት እንገልጻለን።
4.   በሕገ ወጥ  ሰባኪያንና ዘማርያን ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ የማያድም እርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን።
5.   የቤተ ክርስቲያንን  መዋቅር ባልጠበቀ መልኩ ወደ ሰሜን አሜሪካ በሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት የሚከናወኑ ተግባራት   የባሰ እና የተወሳሰበ ችግር ከማስከተሉ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ  መመሪያ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን።
 6.   ቤተ ክርስቲያን አሁን ያለችበት ደረጃ አሳሳቢ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን በመምራት ላይ የሚገኙ አባቶች ከምእመናንና ከሰንበት ት/ቤቶች አባላት ጋር ግንዛቤንና መፍትሔን በሚያመለላክቱ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ለመወያየት እንዲቻል አስፈላጊውን ሁኔታወች እንዲያመቻቹና ሁሉም በአንድነትና በመግባባት ድረሻውን የሚወጣበትን መንገድ እንዲመቻች እንጠይቃለን።
7.  የቤተ ክርስቲያን ታማኝ አገልጋይ የሆንን ሰንበት ት/ቤት አባላት በሙሉ በንቃትና በትጋት ባለንበት ቦታ ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችንን ከመናፍቃን እና ከመሰል ሰዎች ለመጠበቅ አስፈላጊውን ምክክር ከአባቶችና ከምእመናን ጋር በማድረግ የሁሉም ግንዛቤ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ አጠናክረን በመቀጠል ታሪካዊና መንፈሳዊ አደራችንን እንድንወጣ እናሳስባለን ።

የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን እንዲጠብቅልን አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያስታግስልን ለእኛም ጽናትን እንዲሰጠን ፈቃዱ ይሁንልን ።
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን ።
ሐምሌ 19 2003 .
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ስራ አስፈጻሚ
ሰሜን አሜሪካ
ግልባጭ:
·   ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ፣
·    ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት 
·    ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት  
·    በሰሜን አሜሪካ ላሉ ሶስቱም አህጉረ ስብከት
·    ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት በያሉበት ፣
·    በጠቅላይ ቤተክህነት ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
·    በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፣
·    በካናዳ  በአፍሪካና በአውሮፓ ለሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች13 comments:

Anonymous said...

በአጠቃላይ ከቀደመው ታሪክ የምንማረው ለሁላችንም ክብር መሠረቱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓት መከበርና መጠበቁ ነው።
I love this.... Bertu Eski...
Tilik Yetwuld Dirsha Ena Halafinet yemewotat Guzo...

123... said...

It is great!!! Thank to Almighty God. YE BETEKRSTYAN GUDAY HULUM ENDIH KETESATEFE TILIK SIRA YSERAL.WAGACHHUN EGZYABHER YKFELACHIHU.

Anonymous said...

+++
እግዚአብሔር ይጠብቅቻሁ እስኪ በርቱ::
እግዚአብሔር ቤ/ን ይጠብቅ::

Anonymous said...

Egziabher yemesgen.
Ahunim 1 yadergen.
Betam des belonal wendemna ehetochachin.
Ateru kewest kewech ketenekere telatin mekotater yechalal.amlake kedusan yerdan.
ke ager bet

Anonymous said...

this is a great job you did nassu keep continue doing ////

Anonymous said...

God bless you all it is one of relieve for me OH my God thank you soo much! Egiziabeher kehulachn gari yihun!

Anonymous said...

good job.

Anonymous said...

We support both the US and Addis Sunday School Positions.

I feel we need to correct our say about "Silase atibelu...Eyesus Belu"

The statement as said should be understood in context. His intention should be understood from his whole preach.

We know these people are detroying the order but lets mention whats wrong and right.

Anonymous said...

Bertu !

Anonymous said...

It is a great declaration. Particularly, I like the opposition agaisnt making the church a place of business. Zeben and his likes have trying to profit from thier position as preachers and singers. Every servant should be compensated according to the law, but not be allowed to make the church a place of business.

On the other hand, I have the following questions.

1. We hve hundreds of EOTC churches in NA. Which churches are included in the declaration? Why did not they sign it?

2. The declaration is similar to the one by AASSU. Is there any coordinating body to make this happen?

3. The declaration fully reflects and supports the voices of DS/MK. So, what is the role of DS/MK in prepring the declaration?

God bless.

Anonymous said...

For the Anonymous who commented about Zebene
What is the intention of your comment? is it really necessary to mention names of the real tewahedo brothers. The issue was how we should fight tehadeso menafikans that are trying to destroy our church, not our tewahedo brothers who work hard for the church. Memher Zebene is one of the many real tewahedo brothers who build a church in rural area not destroy.

Anonymous said...

Thanks GOD bertu nassu we allways with you hulunem maderg makenawen yemechelew AMLAK mechereshawen yasamerlen AMEN

Anonymous said...

12 ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።

13 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)