July 31, 2011

“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን የዘገበውን ዜና ቀጥሎ ያንብቡ

የእርስ በርስ ቀውስ - በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
  • የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር ከፓትርያሪኩ ጋራ ሳይወያዩ ቀሩ፤ ጉዳዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋራ ደርሷል
(አዲስ አድማስ፣ ሐምሌ 24 ቀን 2003 ዓ.ም፤ ጁን 30/2011፤ ቅጽ 10 ቁጥር 602/ READ IN PDF)፦ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የ131 አድባራት እና ገዳማት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር ከፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ጋራ በትላንትናው ዕለት እንደሚያካሂዱ የተጠበቀው ውይይት ሳያሳካ ቀርቷል፡፡

ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ በመሆን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በተለያዩ ጊዜያት ያስተላለፋቸው እና የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እንዲከበሩ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኀን የሰጧቸው መግለጫዎች ይፋዊ ማስተካከያ እንዲሰጥበት፣ በሕገ ወጥ ዘማርያን ላይ ተገቢው እና ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ፣ ምእመናን በንቃት ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ በአፋጣኝ እንዲሠራ፣ ከቤተ ክርስቲያኗ ዕውቅና ውጭ በቤተ ክርስቲያኗ ስም ‹‹ኢቢኤስ›› በተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሚሠራጨው ፕሮግራም እንዲቆም እና በቤተ ክርስቲያኗ ስም ከቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ውጭ እየታተሙ የሚሠራጩ የኅትመት፣ የምስል እና የድምፅ ውጤቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ድረ ገጽ ላይ እንዳይወጡ እንዲታገዱ ደብዳቤ በግልባጩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤትን ጨምሮ ለተለያዩ የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያኒቷ አካላት ጽፈው ነበር፡፡

ምንጮች እንደሚሉት ይህንኑ ደብዳቤ መሠረት በማድረግ በትላንትናው ዕለት ፓትርያሪኩ ሊያነጋግሯቸው እንደሚፈልጉ ተገልጦላቸው 131 ያህል የሰንበት ት/ቤት ሓላፊዎች ቢገኙም ከመንበረ ፓትርያሪኩ ግቢ ተገድደው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ጠርተው ውይይቱ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ነግረው እንደሸኟቸው ታውቋል፡፡…..
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም ለ‹ዕንቊ› መጽሔት ቃለ ምልልስ ሲሰጡ ያስተላለፉትን መልእክት በመቃወም መልስ የጻፉት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከማኅበሩ አባልነትና ከማኅበሩ አገልግሎት ታገዱ፡፡ ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፣ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ.ን ሙሉጌታ ‹ዕንቊ› ለተባለ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ በአሁኑ ወቅት ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው የሚወጡ አብዛኞቹ ተማሪዎች የኢሕአዴግ አባል መሆናቸውን፣ በመንግሥት መሥ/ቤት የሚመደቡትም እነዚሁ ተማሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የማኅበሩ አባላት የሚሆኑትም ከነዚህ ተማሪዎች ውስጥ ከሆነ አብዛኛው የማኅበሩ አባላት የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፤ አያይዘውም ‹‹በእውነቱ ለመናገር ግን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው የሚባለው ፕሮፓጋንዳ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ስለ ዲያቆን ዳንኤል ሲናገሩም ከማኅበሩ ምሥረታ ጀምሮ የነበሩ መሆናቸውን የልማት ተቋማት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ ሥራው የሚፈለገውን ያህል ሊንቀሳቀስ ባለመቻሉ በገዛ ፈቃዳቸው እንደ ለቀቁ በመጥቀስ ዲያቆን ሙሉጌታ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የዲያቆን ሙሉጌታ ቃለ ምልልስ ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ ምንም ዐይነት መረጃ በሌለበት፣ ‹‹በአብዛኛው የማኅበሩ አባላት የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው›› ማለታቸው ስሕተት መሆኑንና እርሳቸው ከማኅበሩ መደበኛ አገልጋይነት የለቀቁበትን ምክንያት በሚመለከት የተሰጠው መረጃ ትክክለኛ አለመሆኑን በመግለጽ ማኅበሩ በአደባባይ ማረሚያ እንዲያወጣ የሚጠይቅ ጽሑፍ እንደጻፉ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የማኅበሩ ምንጮች እንደሚያስረዱት የማኅበሩ አመራር አባላት በዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጽሑፍ በሚዲያ ላይ መውጣት መነሻነት ስብሰባ በማድረግ፣ ‹‹አብዛኛውን አባላት በመወከል የተሰጠው አስተያየት ትክክል አይደለም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ቁጥር በተበራከተበት በአሁኑ ወቅት ሐሰት ነው ለማለት ይከብዳል፤ የዲ.ን ዳንኤል ክብረት አስተያየት መነሻ ነጥቦች ግላዊ ናቸው፤ በዚህ ሁኔታ ማስተባበሉስ ምን ያስከትልብናል?›› የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ቢቆዩም አደባባይ የወጣ ነገር እንዳልነበር ምንጮቹ ያስረዳሉ፡፡

የማኅበሩን ሥራ አመራር ምላሽ ለአንድ ወር ሲጠብቅ የነበረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም በበኩሉ፣ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ በአደባባይ ሠርተውታል ላለው ስሕተት በአደባባይ ትችት ለመስጠት መገደዱን በመግለጽ ወደ 15 ገጽ በሚጠጋ ጽሑፍ የማኅበሩ አመራር አባላትን ወቅሷል፡፡ ይኸው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጽሑፍ በ(ደጀ ሰላም) ዌብሳይት ከወጣ በኋላ የሥራ አመራሩ አስቸኳይ ስብሰባ ተደርጎ የወጣው ጽሑፍ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት መሆኑ ተረጋግጦ ለጻፈው ጽሑፍ በይፋ ይቅርታ እስኪጠይቅ ድረስ ከማኅበሩ አባልነትና አገልግሎት ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑ ታውቋል፡፡ የማኅበሩ አመራር አባላት ስብሰባ ላይ በመሆናቸውና ዲያቆን ዳንኤል ከሀገር ውጭ በመሆኑ ያላቸውን ምላሽ ማስተናገድ አልቻልንም፡፡ Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)