July 28, 2011

“ማኅበረ ቅዱሳን የውይይት እና የምክክር ባሕሉን ይቀጥል” (ደጀ ሰላም)


(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 28/2011/ READ IN PDF):-  የዲ/ን ዳንኤል ክብረትን ጽሑፍ ካስነበበንበት ወቅት ጀምሮ ብዙ ደጀ ሰላማውያን እጅግ በጣም ገንቢ ሐሳቦችን፣ ምክሮችን እና ቁም ነገሮችን ለግሳችሁናል። ብዙዎቻችሁ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት “የዓይናችን ማረፊያ” ያላችሁትን የማኅበረ ቅዱሳንን “ገመና” እና መለያየቱን በአደባባይ ማቅረባችን ትልቅ ሐዘን እንደፈጠረባችሁ ገልጻችሁልናል። አንዳንዶቻችሁም በሥራችን መከፋታችሁንከፍተኛ ቁጭት እና ሐዘን እንደፈጠረባችሁ ደጀ ሰላም ተረድታለች

በጽሑፉ የተዘረዘሩ ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች በውስጠ-ማኅበር ልዩነት ላይ የተወሰኑ መሆናቸውን በመገንዘብ፣ የማኅበሩ አባላትና ሌሎች አንባብያንም ልዩነቱ ውስጣዊ በመሆኑ ለአፈታቱ ዕድል እንዲሰጠው ማሳሰባቸውን በመቀበል፣ ደጀ ሰላምንና ማኅበረ ቅዱሳንን እንዲሁም ዲ/ን ዳንኤልን አምርረው የሚጠሉና የሚቃወሙ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አራማጅ ብሎጎች ጽሑፉን ከዐውዱ ውጭ ላልተገባ ጥቅም ማዋላቸውን በመረዳት ጽሑፉ የወጣው የማ/ቅዱሳንንም ሆነ የፀሐፊውን የዲ/ን ዳንኤል ስምና ዝና እንዲሁም ያላቸውን ተቀባይነት ለመጉዳት ባለመሆኑ፣ ጽሑፉ በሌሎች እጅ እንደገባ ብናውቅም የዲ/ን ዳንኤል እና እርሱ አባል የሆነበት ማበር የሐሳብ ልዩነት ራሳቸው በሚያደርጉት ውይይት እንዲፈታ እንደምንፈልግ ለማሳየት ደጀ ሰላም ኤዲቶሪያል የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጽሑፍ ከጡመራው መድረክ ላይ እንዲነሣ ወስኗል፡፡


በአጠቃላይ ግን ይህንን ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦች እና አስተያየቶች በመሰንዘር ላይ ናቸው። የማኅበሩ የተለያዩ ማእከላት “አብዛኞቹ የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ አባላት ተበድያለሁ ካለ አባል ጋር ወግነው አቤቱታ ሰሚ ሆነው አልተገኙም፤ ችግሩን ለመፍታት ያሳዩት ዳተኝነት አለመግባባቱን አባብሶታል፤ ዲ.ን ዳንኤልም ጥያቄውንና ቅሬታውን ለማኅበሩ መዋቅሮች በየደረጃው በማቅረብ እስኪፈታ መታገሥ ነበረበት፡፡ ጽሑፉ የማኅበሩን የውስጥ ችግሮች ለመፍታት በጀመርነው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው” ሲሉ ያስረዳሉ። የማኅበሩ አባላትና ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ “ዲ.ን ዳንኤል ክብረት እንዲህ መጻፍ አልነበረበትም፤ ዲ.ን ሙሉጌታም ኀይለ ማርያምም እንዲህ መናገር አልነበረበትም፤ ሁለቱም ይፋዊ ይቅርታ ጠይቀው የተዘረዘሩት ውስጣዊ ችግሮች በማኅበሩ የውስጥ አሠራር መሠረት ይፈቱ፤ ዋና ጸሐፊው በሰጡት ቃለ ምልልስ ስለ ማኅበሩ አባላት ፖለቲካዊ ሱታፌና ሰንበት ት/ቤቶችን በተመለከተ የተጠቀሰው” ማብራሪያና ማረሚያ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን” ይላሉ።

በተያያዘ መልኩ የፀረ-ተሐድሶ-ሰባክያን ጥምረት አባላት በበኩላቸው ዲ.ን ዳንኤል በጽሑፉ “አባቶች፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ ሰባክያንና ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የፈጠሩበት የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ እንቅስቃሴ ‹የማኅበረ ቅዱሳን ውስጣዊ ችግር ማስቀየሻ ስልት› ነው” ሲል በገለጸው ሐሳብ ላይ ማብራሪያና ማረሚያ እንዲሰጥ በጥብቅ ጠይቀዋል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም ለ‹ዕንቊ› መጽሔት፣ አራተኛ ዓመት ቁጥር 46 እትም በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በተነሡ አነጋጋሪ ነጥቦች መንሥኤነት ከአንድ ወር በፊት ተቀስቅሶ በቆየው አለመግባባት፣ ይህንንም ተከትሎ የማኅበሩ መሥራችና የቀድሞው የማኅበሩ የልማት ተቋማት አስተዳደር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጽሑፍ አዘጋጅ ‹ዕንቊ› መጽሔትና ለደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ በላከው አስተያየና ጽሑፉ በጡመራ መድረካችን ከወጣ በኋላ በተፈጠሩት ስሜቶች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

የማኅበሩ የቅርብ ምንጮች እንደሚያስረዱት የዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ በደጀ ሰላም ከመስተናገዱ በፊት ችግሩ በአስቸኳይ እንዲፈታ የሚያሳስቡ ጽሑፎች በተወሰኑ የማኅበሩ አባላት መካከል የኢ-ሜይል ልውውጥ ሲደረግባቸው ሰንብቷል፡፡ የዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ በደጀ ሰላም ከተስተናገደ በኋላ በርካታ የማኅበሩ አባላት “ጉዳዩ በሥራ አመራር ጉባኤውና በዋና ጸሐፊው የአካሄድ ችግር ባይዘገይ ኖሮ ጽሑፉ ወደ ውጭ አይወጣም ነበር” በማለት አመራሩን ለችግሩ ተባባሪ በማድረግ ሲወቅሱ ሌሎች ደግሞ “የዲያቆን ዳንኤል ክብረት የአስተያየት መነሻ ነጥቦች ግላዊ ናቸው” ከማለት ጀምሮ በማኅበሩ የውስጥ መዋቅሮች ያሉትንና አመራሩን ሊያስገድዱ የሚችሉ የቅሬታ ማቅረቢያ መድረኮችን አሟጦ እንዳልተጠቀመ በመጥቀስ በገመና ገላጭነት፣ በእከብር ባይነትና በውዳሴ ከንቱ ፍለጋ ይወቅሱታል፡፡ እንደነዚህ ወገኖች መረጃ ከሆነ የዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ በደጀ ሰላም ላይ መጦመሩና ማኅበሩን በሚከሱ ብሎጎች ላይ መታየቱ በግል ተነሣሽነታቸው የሥራ አመራሩንና የሥራ አስፈጻሚውን ጽ/ቤት በመጠየቅ ለመፍትሔ የተጉትን አባላትና ከስድስት የማያንሱ ማእከላት /ቅርንጫፎች/ በየበኩላቸው ዋናውን ጽ/ቤት በማሳሰብ ባደረጉት ጥረት ላይ “ውኃ የሚቸልስ፣ አንጀት የሚበጥስ” ነው ተብሏል፡፡

ሌሎች ጥቂት አባላት በበኩላቸውም “ማኅበረ ቅዱሳን የማይሳሳት፣ የማይተች አይነኬ እንዳልሆነ” በማብራራት መፈተሽ የሚገባቸው በዲያቆን ዳንኤል የተዘረዘሩት የማኅበሩ ድክመቶች ሐቀኝነት ብቻ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ እኒህን ወገኖች ቅር የሚያሰኛቸው ግን ዲያቆን ዳንኤል የውስጠ - ማኅበር ልዩነቶችን እንዲህ በገሃድ ለማውጣት “ተገቢውን ጊዜ አለመጠበቁ” ነው። ቃለ ምልልሱ በመጽሔቱ ታትሞ ለንባብ ከበቃበት ቀን ጀምሮ በማኅበረ ቅዱሳን አባላት መካከል የተለያየ አቋም ተይዞ የሐሳብ ግብግብ እየተካሄደበት ይገኛል፡፡ ውይይቱና ክርክሩ በዋናነት በነገሩ ርግጠኛነት (Facticity) እና አግባብነት (Appropriatness) ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡

ከሥራ አመራሩና ከሥራ አስፈጻሚው አባላት የተወሰኑቱ ዋና ጸሐፊው የተናገረው “ፋክት ነው” በሚል ሲሟገቱ የተቀሩት ደግሞ “የማናውቀው የአባልና አባልነት ቅጽ ተሞልቶ ካልሆነ በቀር ፋክት ለመሆኑ የምናረጋግጥበት ምንም ዐይነት ዳታ የለንም፤ ቢኖረንም ዋና ጸሐፊው ስለ አባላቱ ፖሊቲካዊ አቋም ይህን ዐይነቱን ፖሊቲካዊ ምልከታ ያለው ማስረገጫ /assertion/ መስጠት አይችልም” የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ሌሎች ወገኖችም በገዥው ፓርቲ እንደሚባለው ከአውራ ፓርቲ ሥርዐት መገንባት እና በተቃዋሚው ወገን ደግሞ ጠቧል ከሚባለው ፖሊቲካዊ ምኅዳር ጋራ በማያያዝ ዋና ጸሐፊው “አብዛኛው የማኅበረ ቅዱሳን አባል የኢሕአዴግ አባልና ደጋፊ ነው” ቢል ስሕተት አይሆንም ባይ ናቸው የማኅበሩ አባላት የሕዝቡ አካል ከመሆናቸው አኳያ ያሉበትን ሥርዐት ጠቅላይ ባሕርይ በሌላ መጽሔት የሚያሳይ ወይም የሚያስረግጥ ዘይቤያዊ አገላለጽ አድርገው የቆጠሩትም አልታጡም፡፡ ሐዘኑ ግን “ፖሊቲካዊ አቋማችንን በውጭ ትተን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት ነው የተሰበሰብነው” ለሚሉት አባላቱ ማኅበሩ እንዲህ ያሉትን አወዛጋቢ ጉዳዮች በፍጥነት ለመፍታት የሚያስችል፣ ራሱን በውስጣዊ መዋቅሩ የሚያርምበት አስገዳጅ አሠራር የሌለው መምሰሉ ነው፡፡ በአንዳንዶች አነጋገር ደግሞ ማኅበሩ “የፓርቲዎች ልዩነት /በተለይም የገዥው ፓርቲ/ መናኸሪያ እንዲሆን” የተደገሰለት ይመስላል፡፡ 

ከቅርብ ምንጮች እንደተሰማው በዋና ጸሐፊው ቃለ ምልልስ “ሳናውቀውና በሌለንበት ፖሊቲካዊ ካምፕ ውስጥ ተፈርጀናል” የሚሉ አባላት ጉዳዩ በአመራሩ ላይ ያላቸውን አመኔታ የሚያጠፋ የሕገ ማኅበር ጥሰትና በተለይም በውጭ አገር በሚገኙ የማኅበሩ አባላት አገልግሎት ላይ ይፈጥረዋል ከሚባለው ጫና አኳያ ማኅበሩ አስቸኳይ ማብራሪያ /Clarification/ እንዲሰጥበት የሚሹ አባላት ግፊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ነው ስድስት የማኅበሩ ማእከላት እና የዋናው ማእከል ሦስት ዋና ክፍሎች መደበኛ አገልጋዮች የሚመለከተው የዋናው ማእከል ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይሰጣቸው ዘንድ በደብዳቤ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ በአንጻሩ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይሁን ማረሚያ መስጠት “ላልታሰበ ከባድ ችግር ይዳርገናል” የሚሉ ተሟጋቾች “አቧራ ለማስነሣት ካልሆነ በቀር ጉዳዩን አጀንዳ ማድረግ አስፈላጊ አይደለም” የሚል አቋም መያዛቸው ተሰምቷል፡፡

በየ15 ቀኑ ታትሞ ለሚወጣው ‹ዕንቊ› መጽሔት በዋናነት በወቅታዊው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ምንነት፣ ማኅበሩ ከኑፋቄው አደጋ አኳያ እያደረገ ስላለው የመከላከል እንቅስቃሴና እንቅስቃሴውን ተከትሎ ከተከሠቱት ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር ምላሽ የሰጡት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው፣ “ስለ ማኅበሩ አባላት ፖሊቲካዊ ሱታፌ የተናገርሁት በዐይነታዊ መረጃዎች /Qualitative facts/ ላይ ባለኝ ግንዛቤ የተመሠረተ ነው” በሚል ለሥራ አመራር ጉባኤው ማስረዳታቸውን የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡ “የዳንኤል እይታዎች” በተሰኘው የጡመራ መድረኩ የምናውቀውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ ስማችን በቃለ ምልልሱ ውስጥ አላግባብ /አሉታዊ በሆነ መንገድ/ ተጠቅሷል የሚሉትን የቀድሞው የማኅበሩ ሥራ አመራር አባልና አሁን በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ውስጥ በሓላፊነት የሚሠሩት ቀሲስ ሰሎሞን ሙሉጌታን ዋና ጸሐፊው በግላቸው በማነጋገር ቅሬታቸውን አዳምጠው እንዲፈቱ በሥራ አመራር ጉባኤው ታዝዘው እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ይሁንና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጁን 20/2011 በአድራሻ ለጡመራ መድረካችን በላከውና በጡመራ መድረካችን ላይ ተጦምሮ ለአጭር ጊዜ በቆየው ጽሑፉ ላይ እንዳመለከተው፣ ዋና ጸሐፊው የሥራ አመራር ጉባኤውን ትእዛዝ በተሟላ መንገድ ተግባራዊ አላደረጉም፤ ለውይይትም ፍላጎት አላሳዩም ተብለዋል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ራሱ በስልክ እንዳወያዩት የጠቀቸው የማኅበሩ ሰብሳቢም የዋና ጸሐፊው ቃለ ምልልስ ‹በይዘቱ አዎንታዊና ይህን ያህል አነጋጋሪ ሊሆን የማይገባ› የሚል አቋም መያዛቸውን ጠቅል፡፡ ይህም ስለ ራሱ ስለ ዲያቆን ዳንኤል ይሁን ስለ ማኅበሩ ዋና ፀሐፊው በአደባባይ ሠርተውታል ለሚለው ስሕተት በአደባባይ ማረሚያ ለመስጠት እንዳስገደደው ነበር በጽሑፉ ያስረዳው፡፡

የደጀ ሰላም ማጠቃለያ በዚህ ጉዳይ፦

ማኅበረ ቅዱሳን ሊመሰገንባቸው ከሚገባቸው ጠባያት መካከል የውይይት እና የምክክር ባሕሉ አንደኛው መሆኑን በየአገልግሎት ክፍሎቹ  ውስጥ እንዲሁም በመላው ዓለም በሚገኘው መዋቅሩ የሚያገለግሉ አባላቱ የሚያደርጉትን ጠንካራ የስብሰባ ዘይቤ የሚያውቁ ይመሰክራሉ። አባላቱ በአገልግሎት ላይ በሚነሱ አጀንዳዎች ዙሪያ በግልጽነት እና ፊት ለፊት በመወቃቀስ እና በመተራረም ላይ የተመረኮዘ ማኅበረ ቅዱሳናዊ የአገልግሎት ይትበሀል እንዳዳበሩ ይነገርላቸዋል። አሁን በዲ/ን ዳንኤል ፀሐፊነት በደጀ ሰላም ላይ የወጣው ሐተታ ይህንን የሥራ ይትበሀል እንደማያቀጭጨው እና በሌሎቹ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ውስጥ የምናየው ዓይነት ሐሳብን የመፍራትና የመሸሽ፣ ሐሳብ አንጪዎችንም የማግሸሽ ጠባይ ይከሰታል ብለን አንገምትም። የማኅበሩ የውይይት እና የምክክር ባሕል ይቀጥል እንላለን።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)