July 21, 2011

የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ታሪካዊ መግለጫ አወጡ፤ ተሐድሶን እና አባ ሰረቀን ተቃወሙ


  • ከአዲስ አበባ ውጪ በየአህጉረ ስብከቱ ያሉትም ይደግፏቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፤
  • በሰሜን አሜሪካ ያለው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አጋርነቱን ይገልጻል ተብሎ ይጠበቃል፤
(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 20/2011/ READ IN PDF):-  በፕሮቴስታንታዊ - ተሐድሶ - ኑፋቄ ላይ ውስጥ ውስጡን እየተቀጣጠለ የሚገኘው የምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ቁጣ ፈንድቶ አስከፊ ጉዳት ከመድረሱ በፊት አስፈላጊው የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ጠየቁ። ፌዴራል ፖሊስ በሰንበት ት/ቤቶቹ የቀረበው አቤቱታ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊን አሳስቧል ተብሏል:: “ለሰንበት ት/ቤቶች የሚጠቅም አንዳችም ተጠቃሽ ሥራ አላበረከቱም” የተባሉት ዋና ሓላፊው አባ ሰረቀ ስለ ተሐድሶ መናፍቃን የሰጡት መግለጫ ሰንበት ት/ቤቶችን አይወክልም፤ መግለጫው በመምሪያ ሓላፊነታቸው እንዳይታመኑ የሚያደርግና በብዙኀን መገናኛ ተገቢው ማስተካከያ ሊሰጥበት የሚገባ እንደሆነ ተመልክቷል።


ሰንበት ት/ቤቶች የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-መናፍቃን እንቅስቃሴን ለመግታትና ከቤተ ክርስቲያን ለማጽዳት የሞት ሽረት ትንቅንቅ በሚያደርጉበት በአሁኑ ወቅት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል መዋቅሩን ሳይጠብቁ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በሚሰጧቸው አደናጋሪ መመሪያዎች ጥረቱን እያደናቀፉ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አስታውቀዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ 131 አድባራት እና ገዳማት ሰንበት ት/ቤቶች ሥራ አመራሮች ትናንት ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ ሥርዓተ  ቤተ ክርስቲያንን ሳይጠብቁ በከፍተኛ ሁኔታ የሚስፋፉት ስብከት እና መዝሙር ተብዬዎች የሰንበት ት/ቤቶችን ህልውና በመፈታተን ላይ ይገኛሉ፡፡ “ሕገ ወጥ ሰባክያን የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ለሆኑት ሰንበት ት/ቤቶች ያላቸው ንቀት ጫፍ ከመድረሱ የተነሣ ትምህርተ መለኮትን በማምታታት ‹ሥላሴ አትበሉ፤ እግዚአብሔር አትበሉ፤ ምንድን ነው ፍርሃት ዙሪያ ዙሪያውን መሸሽ፤ ኢየሱስ ብቻ በሉ፤› በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ እና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ በሥልጣን ያለውን አንድነት የሚለይ የኑፋቄ ትምህርታቸውን ካስተላለፉ በኋላ “ይህን ታላቅ ምስጢር ሰንበት ት/ቤት ገብታችሁ ተማሩ” ያለው የሰንበት ት/ቤቶቹ መግለጫ ሕገ ወጥ ሰባክያኑ በሰንበት ት/ቤት ስም መነገድ እንደማይችሉ ያሳስባል፡፡

አባ ሰረቀ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሐላፊነት ከተሾሙበት ጊዜ አንሥቶ እስከዛሬ ድረስ ለሰንበት ት/ቤቶች አንዳች የሚጠቅምና የሚጠቀስ ሥራ አለመሥራታቸውን ያወሱት ሰንበት ት/ቤቶቹ፣ ዋና ሓላፊው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ነባራዊ እውነታነት በመቀበል ረገድ ያላቸው ውግንና “እጅግ በጣም አስደንጋጭና አሳዛኝ” ከመሆኑም በላይ በእርሳቸው ላይ እምነት እንዳይኖራቸው እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ መልኩ አባ ሰረቀ ለተሐድሶ መናፍቃን እየሰጡት ያለው ሽፋን ምእመናንን በከፍተኛ ሁኔታ በማስቆጣቱ በየቦታው ሁከት እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ ለዚህም በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ በአዲስ አበባ ደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን፣ በደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንና በዲላ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን የተጠቀሰውን ችግር መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን በየዐውደ ምሕረቱ ሕዝቡን እንዳያሰናክሉ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያን ችግሩ እስከ አሁን ቀጥሎ እንደሚገኝ ያመለከተው መግለጫው፣ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሩ በፖሊስ ጥበቃ ይከናወን የነበረበት የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ በሀገረ ስብከቱ በሳል ውሳኔ መፍትሔ የተሰጠው በመሆኑ ሀገረ ስብከቱን አመስግኗል፡፡ ሕገ ወጥ ሰባክያንንና ዘማርያንን ለማስቆም ደረጃውን ጠብቆ የተጻፈው ደብዳቤም እጅግ የሚያስመሰግን ነው፡፡

ነገር ግን መፍትሔ ሰጭውን አካሄድ ለማጽናት ከፍተኛ ሥራ ሊሠራ በሚገባበት ሰዓት በተለያየ አካባቢ ለተከሠተው ችግር ተዋንያን በመሆን የሚታወቁ ግለሰቦችን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የተለያዩ መምሪያዎች ላይ በሓላፊነት የማስቀመጥ ሂደት እየተፈጸመ ስለመሆኑ መረጃዎች እንደሚያሳዩ መግለጫው ጠቁሟል፡፡ ይህም ሂደት የከፋ ችግር ስለሚያስከትል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

በመሆኑም በተሐድሶ ኑፋቄና ለዚህ መሣሪያ በሆኑ ሕገ ወጥ ሰባክያን ላይ ውስጥ ውስጡን የተቀጣጠለው የምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ቁጣ ፈንድቶና ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ በቤተ ክርስቲያንና በሀገር ላይ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ሕጋዊና ተገቢ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ የሰንበት ት/ቤቶቹ የጋራ የአቋም መግለጫ በአጽንዖት ጠይቋል፡፡

ይኸው ባለስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ - ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው ያስተላለፋቸውና የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እንዲከበሩና እንዲተገበሩ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ግንቦት 23 ቀን 2003 ዓ.ም በጽ/ቤታቸው ስለ ተሐድሶ የሰጡትን መግለጫ ሰንበት ት/ቤቶቹ የማይቀበሉት በመሆኑ በብዙኀን መገናኛ ማስተካከያ እንዲደረግበት፤ ዐውቀውም ይሁን ሳያውቁ የተሐድሶ መናፍቃንን ጉዳይ በማስፈጸም ላይ የሚገኙ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን በየትኛውም ዐውደ ምሕረት ላይ እንዳይቆሙ፣ ከአጥቢያ ጀምሮ በየደረጃው በሓላፊነት ተመድበው ለተመሳሳይ ዓላማ በሚንቀሳቀሱት ላይ የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድ፣ ራሳቸውን ባሕታውያንና አጥማቅያን ብለው የሠየሙና ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያንና ከመንግሥት ጋራ የሚያጋጩት አካላትም ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው፤ የቤተ ክርስቲያን ብዙኀን መገናኛዎች የተሐድሶ መናፍቃንን ምንነትና ዓላማ ለምእመኑ በማጋለጥ በተዋሕዶ እምነቱ የሚያጸናና የሚያረጋጋ፣ በንቃት እየተሳተፈ ቤተ ክርስቲያኑን ተግቶ እንዲጠብቅ የሚያደርግ አቅጣጫ እንዲሰጣቸው፣ ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጭ በኢ.ቢ.ኤስ ቻናል “ታኦሎጎስ” በሚል ስያሜ የሚተላለፈው ፕሮግራም ምእመናንን ግራ እያጋባ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ስም መሸቀጡን እንዲያቆም ወይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደማይወክል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን በብዙኀን መገናኛ እንዲገለጽ ተጠይቋል፡፡የሰንበት ት/ቤቶቹ መግለጫ በአድራሻ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በግልባጭ ደግሞ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትና ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ጀምሮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ፣ ለፌዴራልና እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተሰራጭቷል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ መግለጫው እንደደረሳቸው ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ችግሩን በትክክለኛ ገጽታው ተመልክቶ ከመፍታት ይልቅ ሕገ ወጥ ሰባክያንን በቢሯቸው ሰብስበው የተቃውሞ አቤቱታውን ያነሣሣሉ ያሏቸውን አካላት (እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ) በመጥቀስ ሲወነጅሉ እንደነበር የዜናው ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ዋና ሐላፊው ሰንበት ት/ቤቶቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ከሚደቅኑት የጸጥታ ስጋት አንጻር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ፌዴራል ፖሊስ ለአባ ሰረቀ አሳስቧቸዋል ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት ነገ ኀሙስ ሐምሌ 14 ቀን 2003 ዓ.ም እና ቅዳሜ ሐምሌ 16 ቀን 2003 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት 10 አመራር አባላት እና የአምስቱ (የሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች) የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በሀገረ ስብከቱ አማካይነት ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ጋራ እንደሚወያዩ እየተጠበቀ ነው፡፡

የመግለጫውን ሙሉ ቃል ለማግኘት ይህንን  PDF ይጫኑ!

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)