July 17, 2011

እነበጋሻው “የምእመናንን ተቃውሞ የሚያበርድ” ያሉትን አዲስ ቪሲዲ እያዘጋጁ ነው


  • የቅጥር ማመልከቻቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሠራተኞች አስቆጥቷል
(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 17/2011/ TO READ IN PDF)፦ በጋሻው ደሳለኝን እና አጋሮቹ ራሳቸውን “ፍፁም ኦርቶዶክሳዊ” መሆናቸውን ለማሳየት ያዘጋጁት ነው የተባለ  ቪሲዲ በቅርቡ ለመልቀቅ ዝግጅት ላይ መሆናቸው ታውቋል። ቪሲዲው እነበጋሻው እንባቸውን እንደ ማየ ክረምቱ ሲያንዠቀዥቁ የሚያሳዩበት እንደሆነም ተነግሮለታል። በካሜራ ፊት በደቦ የተደረገ የልቅሶ ትዕይንት የሆነው የዚህ ቪሲዲ ተዋንያን በጋሻው ደሳለኝ፣ ትዝታው ሳሙኤል፣ ያሬድ አደመ፣ ዕዝራ ኀይለ ሚካኤልና ምርትነሽ ጥላሁን ሲሆኑ ልቅሶውን በመሪ ተዋናይነት በመምራት የሚያላቅሳቸው /አስለቃሹ/ ደግሞ በሪሁን ወንደወሰን ነው ተብሏል፡፡
በልቅሶ ዜማ ግጥም እንደ ዶፍ የሚወርደው ቃለ ተውኔትም የሚከተለው ቀለም ዐይነት መልክ እንዳለው የቅርብ ምንጮች ተናግረዋል፤
             “እኛ ተሐድሶ አይደለን
              እከክም የለ በጀርባችን
              በሃይማኖታችን ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለን
              እባካችሁ አትረበሹ ምእመናን
              ውጊያው ነው የሰይጣን፡፡
             
              እንኳን እኛ ወንጌል የሰበክናችሁ፣
              እናንተም አትለውጡትም ሃይማኖታችሁን፤
              እጅግ ሃይማኖታችንን እንወዳታለን፤ እናፈቅራታለን፡፡
              ሕልሙም የለም፣ ሐሳቡም የለም
              ቢሆን ደስ ይላቸዋል እነሱ ቢሆን፤
              ምእመን ሆይ፣ ሲቆራረጥ /ቪሲዲውን/ ጠርጥር፤
              በገንፎ ውስጥም አይጠፋም ስንጥር
              ሙሉ ሲዲዬ ወደፊት ስለሚናገር”

በአለቃ ኪዳነ ወልድ አገላለጽ እንባ /እንብ/ የልቅሶ ፍሬ፣ የሐዘን ጠበል ካይን የሚፈልቅ፣ የሚፈለፈል፣ የሚፈላ የሚገነፍል ነው፤ ዐይነቱም ሁለት ወገን ነው - አንብዐ ሥጋ እና አንብዐ ጸጋ ወይም ሥጋዊና መንፈሳዊ ተብሎ ይታወቃል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችንም የጽድቅ መሠረት የሆነው ጾም የእንባ መፍለቂያ ምንጭ እንደሆነ ተምረናል፤ ቅዱሳን አባቶቻችን የራሳቸውንና የወገኖቻቸውን ኀጢአት፣ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ የተቀበለውን መከራና በደሙ በዋጃት ቤተ ክርስቲያን ላይ አረማውያን፣ ከሐድያንና መናፍቃን ስለሚያደርሱት ጥፋት እንባቸው አልቆ እዥ፣ እዡ አልቆ ደም እስኪወጣቸው አንብተዋል፡፡ የእነበጋሻውን “የእንባ/ የልቅሶ ርእይ” የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ይመስላል እንዳንለው አንብዐ ንስሐ ሳይሆን የዐይኔን ግንባር ያድርገው ሽምጠጣ ነው፤ ቀድሞ የተወገዙት ወገኖቻቸው መስቀል ይዘው፣ መጽሐፍ ቅዱስ መተው፣ ምለው ተገዝተው በተከሰሱበት የተሐድሶ ኑፋቄ እንደሌሉበት ሲናገሩ የዐባይ ዐባዩን እያወረዱት ነበር - ቆይቶ ለየላቸውና ከዱ እንጂ!!

“እኛም የምናጋልጠውን በቪሲዲ እናወጣለን” በማለት በማኅበረ ቅዱሳን፣ በሰባክያን ፀረ ተሐድሶ  ጥምረት አባላትና በሐዋሳ ምእመናን ላይ ሲፎክሩ የከረሙት እነበጋሻው ይህን የልቅሶ ቪሲዲ ለማውጣት ያስገደዳቸው በየስፍራው የተጠናከረባቸው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ የቀናዒ አገልጋዮችና ምእመናን የተባበረ ርምጃ ነው፡፡ ተቃውሞው የተደራጀና የተጠናከረ ስለመሆኑ ሰሞኑን በገዛ አንደበታቸው የሰጡት ምስክርነት ተጠቃሽ ነው - በጋሻው “የተደራጀ ኀይል ኀይሉን በጣም አጠናክሮ የመጣ ይመስላል” ያለ ሲሆን ዘማሪ እስጢፋኖስ ሣህሌ (ቄሴ) ይቅርታ በመጠየቅ እነርሱን ስላጋለጠበት ምስክርነቱ የተጠየቀው ትዝታው ሳሙኤል ደግሞ “በተክልዬ ቤተ ክርስቲያን የተከሠተው ሁኔታ አሁን ካለው ችግር ጋራ በርግጥም ይገናኛል፡፡ በነገራችን ላይ በዛ ብቻ ሳይሆን በተቀናጀ ሁኔታ ሥራው እየተሠራ እንዳለ የምታውቀው በቃሊቲ ገብርኤል፣ በቅድስት ልደታ ሜክሲኮ፣ በቅዱስ ዑራኤል እንዲሁም ክፍለ ሀገር በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በናዝሬት፣ በዲላ፣ በሐረር ወዘተ ሆን ተብሎ ገንዘብ ተመድቦለት እንደ ፕሮጀክት እየተሠራበት ነው” ብሏል፡፡

የሕገ ወጥ ቡድኑ አባላት የሆኑት እነ አሸናፊ ገብረ ማርያምና ምርትነሽ ጥላሁን በግንቦት ወር መጨረሻ በደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ብርቱ ተቃውሞ ካጋጠማቸው ወዲህ ተቃውሞው ሰንሰለታዊ መልክ ይዞ ቀጥሏል፡፡ ግንቦት 21 ቀን 2003 ዓ.ም በአሸናፊ ገብረ ማርያም፣ ተረፈ አበራ፣ ያሬድ አደመና በጋሻው ደሳለኝ አጋፋሪነት ጋብቻዋን ፈጽማ ግንቦት 27 ቀን በደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጉሸማ የደረሰባት ምርትነሽ ጥላሁን፣ ግንቦት 28 ቀን 2003 ዓ.ም ለሠርጉ መልስ ባመራችበትና ተወልዳ ባደገችበት ይርጋዓለም ቅዱስ ዐማኑኤልም የጠበቃት ተመሳሳይ ተቃውሞ ነበር፡፡

በዕለቱ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ታላቅ ጉባኤ ተዘጋጅቶ ዙሪያው ከተፈቀደላቸው አገልጋዮች ውጭ ረብሻ የሚፈጥሩ ሕገ ወጦችን በሚከላከል የፖሊስ ኀይል የጥበቃ ወረዳ ሥር ነበር፡፡ ካባዋን ለብሳ በእነ ተረፈ አበራና ትዝታው ሳሙኤል ታጅባ ወደ አጥቢያው ለመግባት የመጣችው ምርትነሽም “ተሳልማ ከመመለስ ውጭ ምንም ዐይነት መዝሙር ማድረግ እንደማትችል” ተነግሯት ተመልሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ሰኔ 11 ቀን አሰግድ ሣህ የሚያሽከረክራት መኪና ወደ ሜጋ ቅዱስ ሚካኤል ለመድረስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀር ተገልብጦ ጉዳት የደረሰባት፡፡ “ግጥምና ዜማ እሰጣችኋለሁ” በሚል በበጋሻው ደሳለኝ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚደረግባት ምርትነሽ ጥላሁን ከሌሎቹ የሕገ ወጥ ቡድኑ አባላት ቢያንስ አጽዋማትን በማክበር /በመጠበቅ/ እንደምትለይ ይነገርላታል፡፡

በጋሻው ደሳለኝ በግንቦት ወር አጋማሽ በአንድ ነጋዴ ወዳጁ ጠሪነት “አስተምራለሁ” ብሎ ከሄደበት ከናዝሬት ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪውና በስብከተ ወንጌል ኮሚቴ አባላቱ ርምጃ በምእመናን ፊት ከዐውደ ምሕረት እንዲባረር ተደርጓል “ቁጭ ብለህ ተማር አልያ ውጣ” የተባለው በጋሻው በቤተ ክርስቲያኗ ቅጽር ላይ ቆሞም የአዞ እንባውን ረጭቶ ወደመጣበት ተመልሷል ለሰኔ 12 የቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ወደ ክብረ መንግሥት ሲያመራም አለታወንዶ ላይ በፖሊስ ተይዞ እንዲመለስ ተደርጓል ለጉባኤው ማስታወቂያ ይሆን ዘንድ ከተማው በቅስቀሳ “እንዲቀወጥ” የመከረበት የድምፅ ማስረጃም ለደጀ ሰላም ደርሷል፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር የማያርመው በጋሻው ከሁለት ዓመታት ባላነሰ ከፈነጨበት ከደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የታገደው፡፡ ከሰሞኑም ከእነ ትዝታው ሳሙኤልና ተረፈ አበራ ጋራ “ርስታችን ነው፤ ማኅበሩን ነቅለን አባረንበታል፤ ጽ/ቤቱን አዘግተነዋል” በሚል ለመበጥበጥ ካቀዱበት ዲላ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በምእመናኑ ተቃውሞ የተነሣ በፖሊስ ተይዘው እስከ ሌሊቱ አምስት ድረስ በቁጥጥር ሥር እንደ ቆዩ ተዘግቧል፡፡

“ቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር” በሚል ራሱን የሚጠራው ቡድን ሰብሳቢ ፍጹም ታደሰ በአዲስ አበባ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ሰንበት ት/ቤት ከነበረው የሰንበት ት/ቤት መምህርነት በሰንበት ት/ቤቱና የስብከተ ወንጌል ክፍል አባላቱ ተቃውሞ ከመድረክ ታዶ በመቆየቱ በሥራ ገበታው ላይ እንዳልተገኘ በቁጥር 979/14/2003 በቀን 27/10/2003 ዓ.ም በደብሩ አስተዳደር የተጻፈለት ደብዳቤ ያመለክታል፡፡ ግለሰቡ ቀደም ሲል ከእነ አሸናፊ ገብረ ማርያም ጋራ በመሆን በባሌ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶችን በማወክ ጽ/ቤቶቻቸውን እስከማዘጋት መድረሱ ተጠቁሟል፡፡ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በነበረበት ወቅት የዜና አበው /ፓትሮሎጂ/ መምህር የነበሩት ዶ/ር ፓኒከርም ክፋቱን በማየት “ፍጹም ሰይጣን” በማለት ይጠሩት እንደነበር አንድ የኮሌጁ ደቀ መዝሙር ያስታውሳል፡፡

በተያያዘ ዜና አሰግድ ሣህሉ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የአባ ሰረቀ ረዳት፣ በጋሻው ደሳለኝና መሰሎቹ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሥር በተዘዋዋሪ ሰባኪነት ለመቀጠር አቅርበውታል የተባለው ማመልከቻ በተጠቀሱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ነው፡፡ ከትንት በስቲያ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አምስት የማኔጅመንት አባላት በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት እንዳደረጉ የተዘገበ ሲሆን ከዋና ሓላፊው አባ ሰረቀና ከምክትላቸው ውጭ ሌሎቹ ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማታቸው ታውቋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ማመልከቻውን እንደማይቀበሉ ቢያስታውቁም ፓትርያኩ በትንትና ዕለት በአባላቱ አለመሟላት ሳይካሄድ በቀረው የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ ጉዳዩን አጀንዳ ለማድረግ አቅደው እንደነበር ተዘግቧል፡፡ የአቡነ ጳውሎስ ቤተ ዘመዶች ሳይቀር ተቃውሟቸውንና ምክራቸውን ለፓትርያኩ አቅርበውበታል የተባለው የሕገ ወጦቹ ማመልከቻ የፀረ ተሐድሶው እንቅስቃሴ ያነሣሣውን የምእመኑን ቁጣ ሊያባብሰው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ 

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)