July 13, 2011

አባ ሰረቀ ፍ/ቤት ቀረቡ


  • ፍ/ቤቱ አባ ሰረቀ የብር 4000 ዋስትና አስይዘው ሰኞ ሐምሌ 11 ቀን እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል::
  • ኢ.ቢኤስ ቴሌቪዥን የአዲስ አበባ ቢሮ እነበጋሻው ደሳለኝ ለስድስት ተከታታይ ሳምንታት ባስተላለፉት ፕሮግራማቸው ማኅበረ ቅዱሳንን በስም ጠርተው የተናገሩት ውንጀላ እንዳይደገም ማሳሰቢያ ሰጠ፤ ትዝታው ሳሙኤል “የተሐድሶ ምንጩና መፍለቂያው ማኅበረ ቅዱሳን ነው” ሲል የተናገረው ስላቅ ከሕግ ዐይን አኳያ እየተጤነ ነው::
(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 12/2011; TO READ IN PDF)፦ በቅርቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ብዙኀን መገናኛዎችን በጽ/ቤታቸው ጠርተው ባዘጋጁት ጋዜጣዊ ጉባኤ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ በሰጡት መግለጫ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ሐምሌ 4 ቀን 2003 ዓ.ም ረፋድ ላይ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀረቡ፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫቸው ስለ ማኅበሩ የተናገሩት ነገር “ሊያስከስሰኝ አይችልም” በማለት በጠበቃቸው አማካይነት ያስረዱት ዋና ሓላፊው በሦስት ቅጂ ያዘጋጇቸውንና ከ50 - 60 ገጽ የሚሆኑ ዶሴዎችን ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡ የዶሴው አንድ ቅጂ በችሎቱ የተሰጣቸው ዐቃቤ ሕጓም “ሰነዱ አሁን የደረሰን በመሆኑ አስተያየት ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን” ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ችሎቱ ዋና ሐላፊው አባ ሰረቀ ያቀረቡትን ሰነድ ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠትና በከሳሽ በኩል የቀረቡ አራት ምስክሮችን ቃል ለመስማት ለቀጣይ ሳምንት ሰኞ፣ ሐምሌ 11 ቀን 2003 ዓ.ም ቀጠሮ በመስጠት ተነሥቷል፡፡

አባ ሰረቀ ግንቦት 23 ቀን 2003 ዓ.ም በቢሯቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ “ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቷ ስም የከፈታቸው ልዩ ልዩ የንግድ ተቋማትና የገቢ ማስገኛ ማእከላት ለ19 ዓመታት ግብርና ቀረጥ ያልተከፈለባቸው ከፍተኛ የቢዝነስ ሥራ ይሠራል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ኦዲት የማይደረገው ብቸኛው ተቋም ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ነው፤ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በሆነ መንገድ በራሱ ፈቃድ በሚያደርጋቸው ገለጻዎች ሲኖዶሳዊ አካሄድን ንዷል/የስም ማጥፋት ውንጀላ ይፈጽማል/ ያሻውን ያወግዛል፤ የማኅበሩ አባላት ለማኅበሩ እንጂ በሰበካ ጉባኤና በሰንበት ት/ቤት አባላት ሆነው ለቤተ ክርስቲያን የሚገባውን አስተዋፅኦ ስለማያደርጉ በቤተ ክርስቲያን ላይ አስተዳደራዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ እያደረሰ ነው፤” ብለው መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ የአባ ሰረቀን መግለጫ አስመልክቶ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮና ከአገር ውስጥ ብዙኀን መገናኛ በወቅቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በማኅበሩና በመምሪያው መካከል ስላለው ችግር አጣሪ ኮሚቴ ባቋቋመበት ሁኔታ መግለጫው መሰጠቱ ሕገ ወጥ እንደሆነ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡ ማኅበሩ በተመሰከረላቸው የውጭና የውስጥ ኦዲተሮች ሒሳቡን እንደሚያስመረምርና በየስድስት ወሩና በየዓመቱ ለመምሪያው ሪፖርት እንደሚያቀርብ፣ በስፋት እየተካሄደ በሚገኘው የተሐድሶ ኑፋቄን የመከላከል ጥረትም የችግሩን ምንነትና አደጋ ከማስገንዘብ ውጭ በስም ጠርቶ የወነጀለው ግለሰብ አለመኖሩን፣ ይሁንና ጉዳዩን ለረጅም ጊዜ የተከታተለውና በማስረጃ ያረጋገጠው መሆኑን፣ የማኅበሩ አባላትም በሰንበት ት/ቤትና በሰበካ ጉባኤ አባል በመሆን በሞያቸውና በገንዘባቸው ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ መሆኑን በማስረዳት ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ የማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስም አባ ሰረቀ ለሚዲያ ስለ ሰጡት መግለጫ ተጠይቀው፣ የውስጥ ጉዳይ በውስጥ አሠራር ማለቅ እንዳለበት፣ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳ ተይዞ ሳለ መግለጫ እንዲሰጥ ሳይወሰንና መግለጫም የሚሰጠው አካል ሳይለይ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ አግባብነት እንደሌለው ገልጸው ነበር፡፡

በተያያዘ ዜና “ታኦሎጎስ” በተሰኘውና ከኢ.ቢ.ኤስ የሳተላይት ቴሌቪዥን በገዙት የአየር ሰዓት ከአንድ ሳምንት በፊት ባስተላለፉት ፕሮግራማቸው “የሐዋሳውን ቪ.ሲ.ዲ ያዘጋጀው ማኅበረ ቅዱሳን ነው - ሄደህ፣ ሄደህ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ላይ ነው፤ እነሱ ናቸው በይዞታው፤ ምን ዐይነት ሐሳብ ውስጥ እንደገቡ አላውቅም፤…” ሲል በጋሻው ደሳለኝ በተናገረው ክስ መነሻነት ማኅበረ ቅዱሳን ለቴሌቪዥኑ የአዲስ አበባ ቢሮ የቃልና የጽሑፍ አቤቱታ ማቅረቡ ታውቋል፤ የቢሮው ሓላፊም “በጣቢያው የአየር ሰዓት የሚሸጥላቸው የሃይማኖት ተቋማት ስለ ራሳቸው እምነት ከማስረዳት በቀር የሌላውን አካል አቋም እየጠቀሱ እንዲነቅፉ እንደማይፈቅድ” አቤቱታቸውን ላቀረቡት የማኅበሩ ተወካዮች አስረድተዋል፤ ይኸው ፖሊሲው የተጣሰበት የፕሮግራም ስርጭት በወቅቱ ሪፖርት ከተደረገላቸውም በደንቡ መሠረት ርምጃ እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡

ስለተባለው የፖሊሲ ጥሰት የስድስት ሳምንት የእነ በጋሻው ፕሮግራም ይዘት ዝርዝር ማብራሪያ የተሰጣቸው የቅርንጫፍ ቢሮው ሓላፊ፣ ከብሮድካስት ጋዜጣዊ ሞያና ከኢትዮጵያ ሕግ አንጻር ማኅበሩ ስሙ ተጠቅሶ ስለ ተሰራጨበት ጉዳይ በሚዛናዊ ዘገባ አሠራር አግባብ አቋሙን የመጠየቅና በተመጣጣኝ የአየር ሰዓት ማስተባበያ የመስጠት መብት እንዳለው ተነግሯቸዋል - ለአብነትም የአባ ሰረቀ ሕገ ወጥ ጋዜጣዊ መግለጫ የማኅበሩ አስተያየት ባልተጠየቀበት ሁኔታ እንዳለ መተላለፉ በማሳያነት ተጠቅሷል፡፡ ማኅበሩ ለስድስት ሳምንታት ስሙ እየተጠቀሰ ሲወነጀል ዝምታን መምረጡ ድክመት መሆኑንና ቢሮውም አፋጣኝ የማስቆም ርምጃ እንዳይወስድ እንዳደረገው ሓላፊው የተቹ ሲሆን በቀጣይ የተባሉትን የስድስት ሳምንታት ፕሮግራሞች ይዘት በጥንቃቄ አይተው የተባለው የፖሊሲ ጥሰት ተፈጽሞ ከሆነ በኢ.ቢ.ኤስ ሳተላይት ቴሌቪዥን ስም ለማኅበሩ የይቅርታ ደብዳቤ እንደሚጽፉ አስታውቀዋል፡፡ ሓላፊው ለተወካዮች በገቡት ቃል መሠረት ለሁለት የፕሮግራሙ ባለቤቶች ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ትዝታው ሳሙኤል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለኅትመት በዋለውና በገንዘብ እንደሚደጉሙት በሚነገረውና ማራኪ ለተሰኘው የሃገር ውስጥ መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ፣ “የተሐድሶ ምንጩና መፍለቂያው ማኅበረ ቅዱሳን ነው” በሚል የተናገረው ቃል በማኅበሩ የሕግ ባለሞያዎች እየተጤነ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ “በቃሊቲ ገብርኤል፣ በቅድስት ልደታ ሜክሲኮ፣ በቅዱስ ዑራኤል እንዲሁም ክፍለ ሃገር በድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ናዝሬት፣ዲላ ሐረር፣ ወዘተ…” የተቀናጀና ጠንካራ መከላከል እየገጠማቸው እንዳለ ያመነው ትዝታው ዘወትር ሲናገር እንደሚደመጠው ከባድ የአስተሳሰብ ችግር እንዳለበት የሚያመለክቱ ገለጻዎችን በቃለ ምልልሱ ተናግሯል - “ለብዙ ዘመናት የተሐድሶ እንቅስቃሴ አለ እያለ በጎላ መልኩ የሚያስተጋባው ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ተሐድሶ የሚለው ቃል ራሱ ፌመስ ሆኗል፡፡ ምናልባት ቃሉ እንደሚገባኝ ሕዳሴ ከሚለው ቃል ጋራ አንድ ዐይነት ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ለእኔ ተሐድሶም ሆነ ከቤተ ክርስቲያኗ ተከፍለው የወጡ ተቋማት አንድ ናቸው፡፡”

በተቺዎች አስተያየት ትዝታው በዚህ ገለጻው ብዙ ነገሮች ገና እንዳልገቡት አሳብቋል፤ አልያም ሆ ብሎ ለማምታት ሞክሯል፡፡ በመጀመሪያ ስለ አንድ አደጋ ደጋግሞ ማሳሰብ፣ ማስጠንቀቅ የአደጋውን መንሥኤነት ያመለክታል ከተባለ ስለ ወንጀል ባሕርያትና ክሥተት ኅብረተሰቡን ሠርክ የሚያስጠንቅቀው ፖሊስ፣ ስለ ሰብአዊ መብት ጥሰት እና ስለ ሽብርተኝነት ስጋት የሚያወሩ ተቋማት እና መንግሥታት ምን ሊባሉ ኖሯል? ይህም ሆኖ ትዝታው ማኅበሩ ስለ ‹ተሐድሶ› በደንብ እንደሚያውቅ መናገሩ ማኅበሩ በተለያየ ጊዜ ከሚሰጣቸው መግለጫዎች አኳያ ሐቅ ነው፡፡ ይሁንና “በሊቀ መንበርነት ማኅበሩን ሲመሩ የነበሩና ‹ተሐድሶ› በሚል ፈሊጥ ማኅበሩን ጥለው ወጥተው በይፋ አቋማቸውን የገለጹትን ግለሰቦች” ገልጦ ቢናገር ለሁሉም መልካም ይሆን ነበር፡፡

ማለፊያ! ተሐድሶና ሕዳሴስ ምንና ምን ናቸው? ከወቅቱ መንፈስ አኳያ ትዝታው ሕዳሴንና ተሐድሶን በትርጉም አንድ በማስመሰል ሊጫወት ያሰበውን “የማዕድቤት ፖሊቲካ” ወጊድ እንበለውና ‹ተሐድሶ› እና ሕዳሴን በትርጉም አንድና ያው ያደረጋቸው እንደምን እንደሆነ ትንሽ ቢያብራራ የግንዛቤው ውስንነት የት ጋራ እንደሆነ ለመለየት በተቻለ ነበር፡፡ ሁለቱ ቃላት በቋንቋዊ መሠረታቸው (linguistically) ከመታደስ፣ ከመለወጥ፣ ዐዲስ ከመሆን፣ ከማጥናት፣ ከማበርታት አንጻር ተመሳሳይና አዎንታዊ ትርጉም ቢኖራቸውም በዓለም የአስተሳሰብ ታሪክ አስተምህሮ ግን ‹ሕዳሴ› (Renaissance) ለ‹ተሐድሶ› (Reformation) መቅድም የሆነ፣ በዋናነት ከግሪኮችና ሮማውያን የሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥነ መንግሥት፣ ፍልስፍና እና ታሪክ ሥልጣኔ ዳግም መወለድ (Rebirth of the old Roman and Greek Civilization) ከሳይንሳዊ ምርምሮች መስፋፋት ጋራ የተቆራኘ፣ በሀገርም ደረጃ ውጥኑ በተበታተኑት የኢጣልያ ግዛቶች ውስጥ ነበር፡፡ ወቅቱም ከመካከለኛው (የጨለማው) ክፍለ ዘመን በኋላ ከ1300 - 1600 ዓ.ም የቆየ ነው፡፡

ማርቲን ሉተር ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ (protestant reformation) የ“ጥበብ ዳግም ልደት” /ሕዳሴ/ ዘመንን ተከትሎ በሰሜናዊ አውሮፓ የተከሠተ ሲሆን ዋና ትኩረቱም በሮም ካቶሊክ እምነትና አስተዳደር ውስጥ የነበረው ቀውስ ነው፤ ቦታውም ጀርመንና ኔዘርላንድስ ነው፡፡ በርግጥ ሃይማኖትን መነሻው ያደረገውን ተምህሮነት (Scholasticism) በመቃወም ግለኝነትን (Individualism) የትክክለኝነት መሠረት የተደረገበት “የጥበብ ዳግም ልደት /ሕዳሴ/” ዘመን ለሉተር ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ አንዳንዶች የሉተርን ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ “የሰሜን/ሰሜናዊ ሕዳሴ” (The Northern Renaissance/ በማለት ይጠሩታል፡፡ ነገር ግን ለሳይንስ አብዮትና ለዘመነ አብርሆ ዋዜማ የሆነው “ጥበባዊው ሕዳሴ” ከእምነትና ሃይማኖት ውጭ በርካታ የጥበብ ደብሮችን የሚከብ እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም በማጠቃለል ሲታይ “ተሐድሶ” መናፍቅነትና ክሕደት መሆኑ ግልጽ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ብዙዎች “Renaissance” ለሚለው አጠራር የሚግባቡበት “ሕዳሴ” የሚለው ፍች ከተሐድሶ ጋራ በተለይ በታሪካዊ ትርጉሙና መንፈሱ አንድ ነው ሊባል አይችልም፡፡ በጉዳዩ ላይ ደጀ ሰላማውያን ሊወያዩበት ይችላሉ፡፡  

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)