July 6, 2011

የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሕገ ወጥ ሰባክያንን አገደ

  •  የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአጥቢያውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተመለከተ ‹‹በበላይነት መምራትና ማስተዳደር አልቻለም›› ባለው የደብሩ አስተዳደር ጽ/ቤት ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስጠንቅቆ ነበር
  • ሰንበት ት/ቤቱ በሕገ ወጥ ሰባክያኑና የእነርሱ ተባባሪ በሆኑት የአጥቢያው ስ/ወንጌል ሓላፊዎች የሚመራው የስብከተ ወንጌል አካሄድ ‹‹ወዳልተፈለገ ግጭት›› እንደሚያደርስ በመጥቀስ ለሀ/ስብከቱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር
  • በሙሰኛነቱና ባለበት የሥነ ምግባር ችግር ተቃውሞ የተነሣበት ናሁ ሠናይ ነጋ የተባለው የአጥቢያው ስብከተወንጌል ሓላፊ የእገዳውን ምክንያትና ፋይዳ ለማስተባበል እየተፍጨረጨረ ነው
  • ሥላሴ አትበሉ ብያለሁ፤ ሥላሴን አትመኑ ግን አላልሁም” (በጋሻው ደሳለኝ- በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)
(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 6/2011, Read in PDF.)፦ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጽ/ቤት በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና በሀገረ ስብከት ያልተፈቀደላቸው ሰባክያን ከሰኔ 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በአጥቢያው እንዳይሰብኩ መታገዳቸውን አስታወቀ፤ ጽ/ቤቱ ይህን ያስታወቀው የእገዳውን ውሳኔ ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ የደብሩ ስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ለሆኑት መ/ር ናሁ ሠናይ ነጋ እና መ/ር ታሪኩ አበራ በቁጥር 6020/03 በቀን 28/10/03 በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡
የሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት በቁጥር 4561/71/03 በቀን 24/10/03 የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለደብሩ አስተዳደር የጻፈውን ትእዛዝ በመጥቀስ በጥብቅ እንዳስታወቀው ውሳኔው በደብሩ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት መመሪያ መሠረት አስተዳደራዊ ርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ አስጠንቅቋል፡፡

በዚህ የእገዳ ውሳኔ መሠረት ላለፉት ሦስት ዓመታት የደብሩን አስተዳደር በተለያዩ መንገዶች ባዳከሙት የአጥቢያው ስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ተባባሪነት የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ምንደኛ እና ጥቅመኛ በሆኑት በእነበጋሻው ደሳለኝ ሕገ ወጥ ስምሪት ሥር የቆየው የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮስፍ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ትላንት ማክሰኞ፣ ሰኔ 28 ቀን 2003 ዓ.ም ኣርነት(ሓራ) መውጣቱ ተረጋግጧል፤ በዚህም ሕገ ወጥ ሰባክያኑ እና ዘማርያኑ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያሏቸውን የመጨረሻ ምሽጎች እያጡ ስለመሆናቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ ሆኗል፡፡


ይሁንና የደብሩ ስብከተ ወንጌል ሓላፊ የሆነው ናሁ ሠናይ ነጋ በሕገ ወጥ ሰባክያኑ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊነት በተረጋገጠበት በትላንቱ የሠርክ ስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ላይ፣ ‹‹ምእመናን፣ ከባድ ፈተና ገጥሞናል፤ ወንድሞቻችን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብሰባ ላይ ስለሆኑ ነው ያልመጡት›› በሚል የመታገዳቸው ውሳኔ በግልጽ ከማሳወቅና በተለይ በጋሻው ደሳለኝ በየሳምንቱ ማክሰኞ ከሚገኝበት መድረክ የመወገዱን ምክንያት ለማስተባበል ሲሞክር ታይቷል፡፡ ቀደም ሲል በነበረባቸው የጎፋ ካምፕ ኪዳነ ምሕረት እና የገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ክፍሎች ቆይታው ወቅት ከእነ አሰግድ ሣህሌ ጀምሮ ዛሬ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ከሚገኙት የለየላቸው የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞች ጋራ በሚያደርገው ጥብቅ ግንኙነትና እስከ አስገድዶ መድፈር ድረስ በተረጋገጠበት የሥነ ምግባር ችግር የሚታወቀው ይህ የደብሩ የስብከተ ወንጌል ሓላፊ በቤተ ክርስቲያን ያለው ትምህርት ያልተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ወደ ደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ሲመጣ የመቃብር ስፍራዎች ተቆጣጣሪ ነበር፡፡

ቀስ በቀስ የደብሩ ስብከተ ወንጌል ሓላፊ እስከ መሆን ደርሶ የአጥቢያውን ጠቅላላ አስተዳደር በቁጥጥሩ ሥር ስለማስገባቱ የሚነገርለት ግለሰቡ በጋሻው ደሳለኝ ከሁለት ዓመታት በላይ በሕገ ወጥ መንገድ ተሰማርቶ ከቆየበት ዐውደ ምሕረት ቢታገድ ቤተ ክርስቲያኑን ከሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ተገንጥሎ በቦርድ እንደሚተዳደር እስከመዛት ደርሶ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በመዝገብ የሚታወቀው ወርኀዊ የገቢ አቅሙ ከሚፈቅደው በላይ የአንድ ትልቅ ቪላ ቤት፣ የአንድ የቤትና የሥራ መኪና ‹ባለቤት› ስለመሆኑ የሚነገርለት ‹ናሁ ሠናይ› በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር የእግረኞች መረማመጃ በሸክላ አሠራለሁ በሚል ከዋጋው ውጭ እስከ ብር ዘጠኝ መቶ ሺሕ ውጪ እንዲደረግ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የደብሩ ስብከተ ወንጌል ምክትል ሓላፊ የሆነው መ/ር ታሪኩ አበራ፣ ‹‹ተሐድሶ የለም፤ በተሐድሶ ስም የወንድሞቻችን ስም እየጠፋ ነው፤ ምእመናን ተረጋጉ፤ የበጋሻውን ዐሥሩንም ቪሲዲ አይቸዋለሁ፤ አንዳችም አላገኘሁበትም›› በሚለው የተለመደ መወራጨቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በበርካታ መድረኮችና አጋጣሚዎች በተለያዩ መምህራንና ምእመናን ምክርና ማሳሰቢያ ሲሰጠው ቆይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ሥር የሚገኙ ንኡሳን ክፍሎች በቃለ ዐዋዲው ሕግና ደንብ መሠረት እንዲሠሩ፣ የደብሩ ሰባክያነ ወንጌልም ከደብሩ አስተዳደር ጽ/ቤትና ሰንበት ት/ቤት የሥራ አመራር አመራር አባላት ጋራ በመመካከርና በመግባባት የበላይ አካል መምሪያ በመጠበቅ እንዲሠሩ ማስጠንቀቂያ በሰጠበት ደብዳቤ ላይ እንደተመለከተው፣ ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ የደብሩ ስብከተ ወንጌል ምክትል ሓላፊ የሆነው መ/ር ታሪኩ አበራ ‹‹ያልተፈቀደላቸውን መምህራን በዐውደ ምሕረት በመጋበዝ፣ በዐውደ ምሕረት ላይ ያልተፈለጉ ቃላትን በመናገር፣ በቃለ ዐዋዲው ሕግና ደንብ በተቋቋመው ሰንበት ት/ቤት ውስጥ ጠብና ክርክር እንዲፈጠር›› ምክንያት በመሆኑ ተጠያቂ አድርጎታል፡፡ በቅርብ ምንጮች መረጃ ከሆነ መ/ር ታሪኩ የአቋም መሻሻል ምልክቶች እያሳየ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የደብሩ አስተዳዳሪና ጽ/ቤትም ‹‹የቤተ ክርስቲያኑን ዐውደ ምሕረት በቸልተኝነት በመመልከትና ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያልተፈቀደላቸው ሰባክያነ ወንጌል በመድረክ እንዳይሰብኩ የተላለፈውን መመሪያ ባለማስከበራቸውና በወቅቱም አስተዳደራዊ መፍትሔ ባለመስጠታቸው›› ከተጠያቂነት እንደማይድኑ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አመልክቷል፡፡

የእነበጋሻው ሕገ ወጥ ቡድን የታገደበት ርምጃ የተወሰደው ሰኔ 20 ቀን 2003 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የደብሩ አስተዳዳሪና ፀሃፊ፣ የደብሩ ሰባክያነ ወንጌል፣ የደብሩ ሰንበት ት/ቤት አመራር አባላት፣ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነትና የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት አመራሮች በተገኙበት ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጋራ በተደረገው ውይይትና በተደረሰበት የጋራ ስምምነት መሠረት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስና የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ፈቃድ ባልተሰጣቸው ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ላይ የእግድ መመሪያ ካስተላለፈበት ከየካቲት ወር 2001 ዓ.ም አኳያ የደብሩ ርምጃ በእጅጉ የዘገየ ቢሆንም የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ምንደኞች በአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ደረጃ ያላቸውን የመጨረሻ ምሽግ/መሠረት እያጡ መሆኑን እንደሚያመለክት አስተያየት እየተሰጠበት ይገኛል፡፡

ንት በዐውደ ምሕረቱ በየሳምንቱ ማክሰኞ የለመደውን ፕሮግራም ማካሄድ ያልተቻለው በጋሻው በግንቦት ወር አጋማሽ ከናዝሬት ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ያለስብከተ ወንጌሉና አስተዳደሩ ዕውቅና ከተጠራበት ጉባኤ በምእመናን ፊት ዐውደ ምሕረት ተባሯል፡፡ ለሰኔ 12 የቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ወደ ክብረ መንግሥት እያመራ ሳለ አለታ ወንዶ ከተማ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውሎ የተቆጣው ምእመን ብትር ሳያርፍበት በመጣበት እግሩ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ካለፈ ድርጊት የመማር ሰብአዊ/ኣእምሯዊ ችሎታ የጎደለው በጋሻው ግን በሳምንቱ መጨረሻ በተላለፈው አንድ ‹ቃለ ምልልሱ› ‹‹ሥላሴ አትበሉ ብያለሁ፤ ሥላሴን አትመኑ ግን አላልኩም፤. . .ከልጅነታችን ጀምሮ ስለ ሥላሴዎች ስንማር ነው ያደግነው…..›› እያለ ከመወሻከት አልታቀበም፡፡ እየገጠመው ያለው ተቃውሞ የተደራጀና በመጠናከር ላይ ስለመሆኑ ያመነው በጋሻው ከዚህ በኋላ ለሚነሣበት ተቃውሞ ሁሉ በቪሲዲ ምላሽ መስጠትን ተግባሩ እንደሚያደርግ ዝቷል!!!
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)