July 3, 2011

“ጳጳሶቹ አይረቡም … (ቤተ ክህነቱ) ወደ ሞት አፋፍ እየሄደ ነው” (አቦይ ስብሐት ነጋ)


(ደጀ ሰላም፤ ላይ 1/2011, To Read in PDF, click HERE)፦ የሕወሐት/ኢሕአዴግ የፖለቲካ መሐንዲስ መሆናቸው የሚነገርላቸው አረጋዊው አቶ ስብሐት ነጋ ስለ ቤተ ክህነት በሰጡት ግልጽ አስተያየት ላይ “ጳጳሶቹ አይረቡም”፣ ቤተ ክህነቱም “ወደሞት አፋፍ እየሄደ ነው” ሲሉ ተናገሩ። ዛሬ አርብ ሰኔ 24/2003 ዓ.ም በወጣው “ፍትሕ” ጋዜጣ ላይ ረዥም ጽሑፍ ያስነበቡት አቶ ስብሐት ነጋ (በተለምዶ አቦይ ስብሐት ይባላሉ) ስለ ቤተ ክህነቱ በከፋ አስተዳደራዊ ብልሽት ውስጥ መውደቅ ምክንያቱ “ራሱ ቤተ ክህነቱ” እንጂ መንግሥት አለመሆኑን አብራርተዋል። 


ባለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 17/2003 ዓ.ም ወጥቶ በነበረው የፍትሕ ጋዜጣ ላይ አቶ ተመስገን ደሳለኝ የተባሉ ግለሰብ ለሰጡት አስተያየት መልስ በሆነው በዚህ የአቶ ስብሐት ማብራሪያ ቤተ ክህነት ከጥንት ዘመን ጀምሮ ከመንግሥት ጋር ተጣብቃ እንደኖረች፣ አጼ ኃ/ሥላሴ “ቅዱስ ተብለው ታቦት ተቀርጾላቸው እንደነበር”፣ ለዚህ ደግሞ በዋነኛነት ተጠያቂው ቤተ ክህነቱ ራሱ መሆኑን ዘርዝረዋል። “ኦርቶዶክስ ከመንግሥት ሳይለያይ ለመቆየቱ ዋናው ተጠያቂዎች የቤተ ክህነት ኃላፊዎች የነበሩ ሰዎች ናቸው። መንግሥታቱ በሁለተኛ ደረጃ ይጠየቃሉ። ‘ፕሮፌሰሮቹ (እነ ፕሮፌሰር መስፍንን ለማለት ይመስላል) እና ሌሎች አማኞች ያን ጊዜ ባለመናገራቸውና ባለመጻፋቸው በምን ደረጃ ይጠየቃሉ?’ የሚል ጥያቄም ሊነሣ ይገባዋል” ሲሉ ጽፈዋል።

“ዋናው ነገር ቤተ ክህነት ከመንግሥት ተጣብቆ በመቆየቱ፣ የሃይማኖት ተቋምነቱ እየወደቀ መጥቷል። አሁንስ ሃይማኖትና ፖለቲካ በሕገ መንግሥቱ ደረጃ በጽኑ እምነት ከተለየበት ወዲህ (ቤተክህነቱ) ከደረሰበት ድቀት እያንሰራራ ነው ወይስ በነበረበት ጉዳት ደረጃ ነው ያለው? የአሁኑ ፓትርያርክ ሥራ ከጀመሩ ጀምሮ ስለ ቤተ ክህነቱ የሚወራው እጅግ በጣም ዘግናኝና አሳፋሪ የአስተዳደር ጉድለት ተነሥተን ወደ ሞት አፋፍ እየሄደ ነው የሚያሰኝ ነው” ብለዋል።

በመቀጠልም “የቤተ ክህነቱ አስተዳደር ብልሽት የሚባሉ ዘርፈ ብዙ ናቸው። አማኝ ሐቁን የመስማት መብት ያለው ይመስለኛል። ሌሎች ሃይማኖቶች እንደ ቤተ ክህነት ለምን ክፉ ወሬ አይወራባቸውም። በራሱ ውስጣዊ ድክመት እየተጎዳ የመታ ቢሆንም ኦርቶዶክስቤተ ክርስቲያን በታሪኩ የሀገር ፀጋ ሆኖ ነበር የቆየው፤ ፀጋነቱ በዚህ ደረጃ መውደቅ የለበትም ነው የምለው በዚህ አጋጣሚ” ሲሉ አበክረው አሳስበዋል።

ብዙ ጊዜ እንደሚነገረው “የቤተ ክህነቱ አሳዛኝ ቦታ መውደቅ ተጠያቂው መቶ በመቶ ራሱ (ቤተክህነቱ)ነው። ሕገ መንግሥት ከፖለቲካ ነጻ አድርጎት እያለ ለምን?” ሲሉ ይጠይቁና “ባይኖርስ (ከፖለቲካ ነጻ ባይሆንስ?) ለእምነታቸው ለምን አይሠሩም? ጳጳሳቱ አይረቡም ያልኩበት ምንክንያት ከዚህ አጠቃላይ መርሕ ብቻ ተነሥቼ አይደለም። አብዛኞቹ ከድሮ ጀምረው በአቡነ ጳውሎስ አስተዳደር እንደሚያለቅሱ አውቃቸዋለሁኝ። ነገር ግን ትርጉም ያለው ሥራ አልሠሩም። ለዚህ ነው አይረቡም ያልኩበት ምክንያት። አሁንም ልጨምርበትና ለእምነታቸው አልረቡም።” ብለዋል።

ስለ ማ/ቅዱሳንም እግረ መንገዳቸውን ያነሡት አቶ ስብሐት “እኔ እንደሚመስለኝ፣ ባለኝ ቀጥተኛ ትዝብትም፣ ማህበረ ቅዱሳን የቤተ ክህነት እዳ ነው። ቀጥተኛ ትዝብቴ፣ የቤተ ክህነትን አስተዳደር ለማሻሻል መጠነኛ እንቅስቃሴ ሲጀመር ገንቢ ተራ (ገንቢ ሚና) ከመጫወት አፍራሽነት ይበዘበታል። አልፎ አልፎም ብልሽት እያዩ ዝምታ ይበዛል። የተቃዋሚ ፖለቲካ መድረክነትም እንዳለበት ይወራል። ይህ ትክክል ከሆነ እጅግ በጣም የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የሃገር ስርዓት ማለት ህገ መንግስት የመጣስ ክህደት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ቤተ ክህነት የራሱን ድክመት እንዳያይ ማድረግ … ቤተ ክህነቱንም በጣም ይጎዳል። …  ቤተ ክህነትን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነው የመዳከምህ ምክንያት አንበለው። ድክመቱ የራሱ የውስጡ ሁለገብ አስተዳደራዊ ብልሽት ነው። ተደጋግሞ አቤቱታ ቀርቦለት ያላጣራው ከሆነ  አሁንም ብልሽቱ የራሱ ነው።” ሲሉ አብክረው ገልጸዋል።Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)