July 14, 2011

እነሆ 19 ዓመት ሆነ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 12/2011/ READ IN PDF)፦ አምስተኛው ፓትርያርክ በመንበረ ፕትርክና ከተቀመጡ እነሆ ዛሬ 19 ዓመት ሆናቸው። እርሳቸው ወደዚህ ሥልጣን ሲመጡ ቤተ ክህነቱ የተለያዩ ችግሮች ነበሩበት። ከ19 ዓመታት በኋላ ስንመለከተው እነዚህ ችግሮች አድገውና ሰፍተው፣ ዓይነታቸውም ተበራክቶ፣ ይልቁንም ይህንን ችግር ይቀርፋሉ የተባሉ ርዕሰ ቤተ ክርስቲያን የችግሩ ፊት-አውራሪ ሆነዋል። 19 ዓመት የአንድ ወጣት ዕድሜ ነው። ለተሳሳተ ሰውም ለመመለስ 19 ዓመት ረዥም ጊዜ ነበር። ከጥፋት ከመመለስ ይልቅ በበደል ላይ በደል መጨመርን ተካኑበት እንጂ። ከዚህ በታች ያለውና (ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 5/2009) ያወጣችው ጽሑፍ ምን ማለታችን እንደሆነ የበለጠ ይገልጸው ይሆናል።
 
ይህ አጭር ጽሑፍ የተወሰደውየኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ዋና አንገብጋቢ ችግሮች እና መፍትሔዎች፦ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻከሚል በግንቦት 2001 . ተዘጋጅቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ቀርቧል ከተባለ ዘገባ ላይ ነው። የዶኩመንቱ አዘጋጅ ስም፣ ለምን ዓላማ እንደተዘጋጀ፣ በማንና ለማን ወይም ለነማን እንደቀረበ አይጠቅስም። ይሁን እንጂ ከያዘው መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አንጻርስለ ቅዱስ ፓትርያርኩየሚናገረውን ብቻ ቀንጭበን አውጥተነዋል።

መልካም ንባብ፤
ደጀ ሰላም

+++
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጸሟቸው ዐበይት ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፦

1.
ለዘመናት በአንድነቷ የምትታወቀው ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ፓትርያርኩ ለግል ዝናና ስልጣናቸው ሲሉ በእልህ በሚፈጽሙት ድርጊት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት ተከፍላለች፡፡ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በሚገኙ ምዕመናን መካከል ከፍተኛ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ በአባቶች መካልም በጥርጣሬና በጥላቻ ከመተያየት ባሻገር መወጋገዝን አስከትሏል፡፡ ይኸውም ዛሬ ከፈጠረው ችግር ባሻገር ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ የሚተርፍ ከፍተኛ ፈተና ነው፡፡ ለዚህም አንዱና ዋናው ምክንያት ቅዱስ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት የእርቅና የስምምነት በር እንዳይከፈት በማድረግ ወይም በመዝጋት እርቅ እንዳይመጣ ሰላምም እንዳይወርድ አፍነው በመያዛቸው ነው፡፡ ለምሳሌም በጥቅምት ወር 2000 . የቀረበውን የእርቅ ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡

2.
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት /ቤት የሥራ አስፈጻሚነትና የአስተዳደር ሥልጣን በተመለከተ በሕገ ክርስቲያን አንቀጽ 30 ቁጥር 1 እስከ 21 እንደሰፈረው፡-
1.
የቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደር በየጊዜው የሚወስናቸውን ጉዳዮች ከየቤተ ክርስቲያናቱና ከልዩ ልዩ /ቤቶች የሚቀርቡትን ጥያቄዎች በሕጉ መሠረት መፈፀምና ማስፈፀም፣

2. ዋናውን /ቤት፣ የኮሚሽኑን፣ የቦርዶችን፣ የድርጅቶችንና የመምሪያዎችን በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የሚገኙትን የሥራ ዘርፎችን ሁሉ ማስተዳደርና መምራት፣

3.
ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ በትክክል ገቢ መሆኑንና በሕጋዊ መንገድ ወጪ እየሆነ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት መዋሉን መቆጣጠር፣

4.
የመምሪያና የልዩ ልዩ ድርጅቶች ሓላፊዎችን እያጠና እና ፓትርያርኩን እያስፈቀደ መሾም፣ የሥራ ሓላፊዎችን የሥራ ዝውውርና ዕድገት በአስተዳደር ጉባኤ እየተጠና እየተወሰነ እንዲፈፀም ማድረግ፣

5.
በየደረጃው ያለውን የሠራተኛ መብትና ግዴታ ማለትም የጡረታ፣ የጤና አጠባበቅ፣ የደረጃ ዕድገት፣ የፈቃድ አሰጣጥ፣ የዲስፕሊን ውሳኔ አፈጻጸም እና የመሳሰሉትን ሁሉ በሕጉ መሠረት መፈጸማቸውን መቆጣጠርና አመራር መስጠት፣

6. በበጀት የተመደበውን ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት በፊርማው ማንቀሳቀስ፣

7. ማናቸውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ ገቢና ወጪ በሕጋዊ የሂሳብ አያያዝና ደንብ መሠረት መሠራቱን መታተልና መቆጣጠር. . . ወዘተ እንደሚያካትት ተደርግጓል፡፡

ነገር ግን ይህን ድንጋጌ በመጣስና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ስልጣን በመጋፋት ቅዱስ ፓትርያርኩ በማን አለብኝነት አመመራቸው የወደዱትን ለመጥቀም ሲሉ አላግባብ ሹመዋል፣ የደረጃ እድገት ሰጥተዋል፣ ቀጥረዋል፣ አዛውረዋል፡፡ በግል የጠሉትንም ከቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ውጪ ሽረዋል፤ ከደረጃ ዝቅ አድርገዋል፣ ደመወዝ አግደዋል፣ ከሥራ አባርረዋል፡፡ በዚህም የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለከፍተኛ ብክነት ዳርገዋል፡፡

3.
የሲኖዶሱን ሥልጣን በተመለከተ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 7 በቁጥር 11 እና 12 ላይ ማለትም፡-
በውጭ አገር ለአገልግሎት የሚመደቡ እንዲሁም በአገር ውስጥ ትምህርት ተምረው የውጭውን ትምህርት መማር የሚችሉ ካህናትን እየመረጠ እንዲላኩ የማድረግ፣

ማንኛውም ሰው ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክሎ ለሥራም ሆነ ለጉብኝት ወደ ውጭ አገር በሚላክበት ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ እየፈቀደ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

እንዲሁም የፓትርያርኩን ሥልጣንና ተግባር በሚገልጸው አንቀፅ 15 ቁጥር 12 ላይ ፓትርያርኩ በውጭ ስብሰባ ለመገኘትም ሆነ ጉብኝት ለማድረግ በሚፈልጉበት ጊዜ ስለ ተልእኮው ጉዳይ አስቀድሞ በቅዱስ ሲኖዶስና ቋሚ ሲኖዶስ ማስወሰን እንደሚገባቸው ተደንግጓል፡፡

ነገር ግን ፓትርያርኩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ባላቸው ንቀት ምልዓተ ጉባኤውን ሳያስፈቅዱ ክብረ ቤተ ክርስቲያንን በሚያስነቅፍ መልኩ ፕሮቶኮል ያልጠበቁ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል፡፡ ያለምንም ብቁ ምክንያትና ተልዕኮ በየጊዜው በቤተ ክርስቲያኒቱ ብር በተራ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በተለያዩ ዓለማት አጀብ በማስከተል በመውጣት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለስብከተ ወንጌል ከማዋል ይልቅ መንሸራሸሪያ አድርገውታል፡፡ በዚህም የድሀይቱን ቤተ ክርስቲያን ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ እንዲባክን አድርገዋል፡፡

4.
የታላላቅ ገዳማት አበምኔቶችና የታላላቅ አድባራት አስተዳዳሪዎች በየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት እየተመረጡ ሲቀርቡላቸው መዓርግ ስም እየሰጡ መሾም ሲገባቸው ከተሰጣቸው ሥልጣን ገደብ አልፈው ማንንም ሳይጠይቁ በመሾምና በመሻር ፓትርያርኩ ሕግን ተላልፈዋል፡፡ በተጨማሪም የተመደበ በጀት ይኑር አይኑር ሳይጠናና ሳይረጋገጥዓላማዬን ያሳኩልኛልያሏቸውን ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት /ቤትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመላክ፣ በግዴታም እንዲቀበሉ በማስገደድ ከሕግ የወጣ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሀገረ ስብከቱንና አድባራቱን የእዳ ተሸካሚ አድርገዋቸዋል፡፡

5.
የቤተ ክርስቲያኒቱ የሀገረ ስብከት አወቃቀር መሠረት የሚያደርገው የዞን አስተዳደርን ስለሆነ እንደመንግሥት አወቃቀር ከክልል መስተዳድሮች ጋር በቀላሉ ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችል አሠራር የለም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የመዋቅር ማስተካከያ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች ቤተ ክርስቲያኒቱን በክልል ደረጃ ሊወክል የሚችል አሠራር ተዘርግቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከየክልሎቹ መንግሥታት አሠራር ጋር በቀላሉ ተቀራርባ መሥራት የሚያስችላትን አወቃቀር መፍጠር ነበረባት፡፡ ሆኖም ፓትርያርኩ ስልጣኔን ይሸራርፍብኛል ከሚል አቋም ይህን ለመተግበር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ችግሩ እስከ አሁን ዘልቋል፡፡

6.
ጋጠ ወጥ በሆኑ ዘፈኖቿ በዓለም ዘንድ የምትታወቀውንና እነዚህ ዘፈኖቿን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመዝፈን የመጣችውን (ቢዮንሴ የምትባል) ዘፋኝ በቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት የቤተ ክርስቲያንን፣ የአባቶችንና የምዕመናን ክብር በሚነካ መልኩ የፈጸሙት አሳዛኝ ታሪካዊ ስህተት የእርሳቸውን መንፈሳዊ መሪነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ በእርግጥ ግለሰቧ ቤተ ክርስቲያንን መጎብኘት ከፈለገች እንደማንኛውም ጎብኚ ልትጎበኝ ትችላለች፡፡ ነገር ግን ሁሉ የዐውደ ምሕረት አጀብ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ እርሳቸውም ቢሆኑ መነጋገር ካስፈለጋቸው በእንግዳነቷ በቢሮአቸው ጋብዘዋት ማነጋገር ሲችሉ ብጹዓን አባቶችን ሰብስበው ለስምንት ሰዓታት ሙሉ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሲጠብቁ መዋላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር የሚያጎድፍና የምእመናንን አንገት ያስደፋ ተግባር ነው፡፡

7.
የቅዱስ ሲኖዶስን ፈቃድና እውቅና ሳያገኙና የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና ሳይጠብቁ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን እንደ ቀበሌ /ቤት በመቁጠር የራሳቸውን ምስል ማስለጠፋቸውና ለዚህም የስዕል ሰሌዳ ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለግለሰቦች መበልጸጊያና ለብክነት መዳረጋቸው ቤተ ክርስቲያኒቱንና ምእመናንን ያሳዘነና በማሳፈር ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡

8.
ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሚያዝዘው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ሳይፈቅድና አመራር ሳይሰጥ በራሳቸው የግል ፈቃድ ዝክረ ቤተ ክርስቲያን በማለት በሽልማት ስም ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ ሰዎችን በማሰባሰብ ግልጽ ባልሆነ መንገድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በርካታ ገንዘብ የገቢና ወጪ ሕጋዊ አሠራር በሌለው መንገድ ከቤተ ክርስቲያኒቱም ጭምር እንዲሰበሰብ አድርገዋል፡፡ በዚህም ምዕመናን ቤተ ክርስቲያኒቱን በጥርጣሬ እንዲመለከቷት በር ከፍተዋል፡፡ ከራስ ወዳድነታቸው የተነሳ ለራሳቸው ስጋዊ ዝና ሲሉም የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ በትውልድ ፊት አጉድፈዋል፡፡

9.
በመከራ ውስጥ አልፎ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ለተማረው ተገቢ ሥራ መደብ ከመስጠት ይልቅ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደግል ድርጅት በመቁጠር በዘመድ አዝማድ ወይዘሮዎችና አቶዎች ወሳኝ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቦታዎች እንዲይዙ በማድረጋቸው ቤተ ክርስቱያኒቱን ለከፍተኛ ምዝበራና ውርደት አጋልጠዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥነ ምግባር የሌላቸው ወይዘሮዎችን በማረም ፈንታ ሽፋንና ደጋፊ በመሆን ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸሙ ነው፡፡

10.
በቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብና ንብረት ላይ በማን አለብኝነት በማዘዝ ዛሬ ቤተ ክርስቲያኒቱ በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ላይ እንድትገኝ አድርገዋል፡፡

11.
በአምባገነናዊ አስተዳደር ሂደታቸው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ፈረሰ፣ ንብረት ተዘረፈ፣ ገንዘብ ተመዘበረ፣ ቀኖና ተፋለሰ፣ አድልዎ ነገሰ፣ የሰው መብት ተጣሰ፣ ወዘተ በማለት ማስተካከያና እርምት እንዲደረግ የሚጠይቁ ብፁዓን አባቶችን ለማስደንገጥ ከሀገረ ስብከታቸው ያነሳሉ፣ በጠላትነትም ይፈርጃሉ፡፡ በመንግሥት ባለስልጣናት ስምም ያስፈራራሉ፡፡


12. ከሀገር ውጭ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግሉ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ከመላክ ይልቅ በገንዘብና በዘመድ አዝማድ የሚላከው ይበልጣል፡፡ በዚህ መልኩ የተላኩት ብዙ ሰዎች ለቤተ ክርስቱያኒቱም ዕድገት ሳይሆን ከሃገር መውጣታቸውን ለግል ጥቅማቸው ማስፈጸሚያ በማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በማዋረድ ምዕመናንን እያሳቀቁ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመ ነው፡፡

13.
ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በመጡ የተለያዩ የውጭ የትምህርት ዕድሎች ዘመዶቻቸውን በቤተ ክርስቱያኒቱ ስምና ገንዘብ ልከዋል፡፡ የሔዱትም ሰዎች አብዛኞቹ በዚያው ስለሚቀሩ የተያዩ ኤምባሲዎችና ቆንስላ /ቤች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያላቸው እምነት በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እያለ መጥቷል፡፡ ይህም ለቤተ ዘመድ የሚሠሩት ተራ ጥቅማ ጥቅም ቤተ ክርስቲያኒቱን ብዙ የውጭ ሀገር ሰዎች በዝቅተኛ አይን እንዲመለከቷት አድርጓል፡፡

14.
በዘመነ ፕትርክናቸው ከምንጊዜውም በላይ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መዳከሙ ብቻ ሳይሆን መጥፋቱ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያላት የምዕመናን ቁጥር መቶኛ ድርሻ በተዓምራዊ ፍጥነት እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ በአንጻሩም የሌሎች እምነት ተከታዮች በከፍተኛ ጥፍነት እያደገ መሆኑን 1999 እና 2000 . ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት በግልጽ እያሳየን ነው፡፡

15. በሙስናና በተለያዩ ከፍተኛ ችግሮች በደል ተገኝቶባቸው ከመንግሥት በግምገማ የሚባረሩ አካላትን ከጥፋታቸው ሳይታረሙ ከነችግራቸው በማቅረብ ቤተ ክርስቱያኒቱን የዘራፊዎች ዋሻ አድርገዋልታል፡፡

16.
ያለምንም ይሉኝታ በቤተሰብና በቤተዘመድ በእውቅና እንዲፈጸም በሚያደርጉት የቅጥር ሂደት ባለሙያዎችና ምሁራን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ምንም ድርሻ አግኝተው ሙያቸውን ለቤተ ክርስቲያን ማበርከት እንዳይችሉ አድርገዋል፡፡

17.
በየአህጉረ ስብከቶች የሚገኙ ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቱያናት እየተዘጉ ካህናትና አገልጋዮቿ በረሀብና በመተዳደሪያ እጦት እየተሰደዱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ፓትርያርኩ ግን ለዚህ አንዳች መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ስለራሳቸው ዝናና ክብር የህዝብ ግንኙነት ሥራ እንዲሠራላቸው አሜሪካን ሃገር ለሚገኘው የሃገር ፍቅር ሬዲዮ አዘጋጅ 100‚000.00 (መቶ ሺህ ብር) እንዲሰጥ ማድረጋቸው ዕለት ዕለት የሚያስጨንቃቸው የራሳቸው ስምና ዝና መታወቅ እንጅ የቤተ ክርስቲያን ችግር መፍትሔ ማግኘቱ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

18.
ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጋር ተያይዞ በሀገር ውስጥ በየክልሉ እንዲሁም ከሀገር ውጭ በሚፈጠሩ ችግሮች በስተጀርባ እርሳቸው የተለያየ የጥቅም ግንኙነት ስለሚያደርጉ ለችግሮቹ መፍትሔ ለመስጠት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ለችግሮቹ መፍትሔ ከስጠትም ይልቅ ችግሮቹ በተከሰቱበት ሀገረ ስብከት አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ በመግባት ግጭቶች እንዲባባሱ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

19.
በተለያዩ ጊዜያት የቤተ ክርስቲያኒቱን የኢኮኖሚያዊ ልማት ተሳትፎ ያሳድጋሉ፣ ገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ከመዘጋት ያድናሉ ተብለው የታመባቸው የተለያዩ የልማት ፕሮጀክት ጥናቶች ለምሳሌ የቱሪዝም፣ የግብርናና ወዘተ ተግባራዊ እንዲሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ከተወሰነ በኋላ ሥራ ላይ እንዳይውሉ ሆን ብለው አምባገነናዊ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ተዳፍነው እንዲቀሩ አድርገዋል፡፡

20.
ፓትርያርኩ በሚሰጧቸው የልብ ልብ ስለ ፓትርያርኩ እንጂ ስለ ቤተክርስቲያን የማያውቁና የማይጨነቁ ቤተ ዘመዶቻቸው ሊቃነ ጳጳሳትን ሳይቀርና እውነተኞች የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልጋዮች እየገላመጡ እና እያሳቀቁ ነጻነት እንዳይሰማቸው ያደርጋሉ፡፡

21.
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንና የኪራይ ቤቶች አስተዳደር የገንዘብ ስርጭት እና አጠቃቀም ላይ የእርሳቸውን የግል ጥቅም በሚያስከብር ስውር መንገድ የሚሠራበት ሁኔታ በመኖሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለከፍተኛ ሙስና እየዳረግዋት ነው፡፡ ለምሳሌ ቢያንስ በወር ውስጥ ለግል ጥቅማቸው ህጋዊ ባልሆነ አሠራር ከቤቶች ኪራይ እስከ 10‚000.00 (አሥር ሺህ) ብር ይወስዳሉ፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት ላይ በማን አለብኝነት እንደፈለጋቸው እያዘዙ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡

22.
የቤተ ክርስቲያኒቱን ሚዲያዎች በተገቢው መንገድ አደራጅቶ ለምዕመናን የማስተማሪያ እና ቤተ ክርስቲያኒቱን ማስተዋወቂያ መንገድ ከማድረግ ይልቅ ያለምንም ኤዲቶሪያል ፖሊሲና ግልጽ አሠራር ለራሳቸው መጠቀሚያ እንዲሁም ማሳደሚያ አድርገዋቸዋል፡፡ ይህም ሰዎችን ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ የተሳሳተ ስዕል እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡
23.
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ራዕይ አልባ እንድትሆን ማድረጋቸው አስቸኳይና አፋጣኝ መፍትሔ የሚፈለግለት ጉዳይ ሆኗል፡፡ በመሆኑም አስፈላጊ የሆነውን የመፍትሄ ሃሳብ ከልብ አጢኖ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ፦የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ዋና አንገብጋቢ ችግሮች እና መፍትሔዎች፦ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ” (ግንቦት 2001 .) ከገጽ 3-9

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)