June 2, 2011

Voice Messages to Deje Selamማኅበረ ቅዱሳን ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

  • ‹ከተቋቋመ ጀምሮ ኦዲት ተደርጐ አያውቅም›› የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
  • ‹‹ይህ ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል ነው›› ማኅበረ ቅዱሳን

(Reporter Newspaper):- ከተቋቋመ 19 ዓመታትን ያስቆጠረው ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፀድቆ ከተሰጠው ሕግና ደንብ ውጭ መንቀሳቀሱን ካላቆመ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓርትያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በትናንትናው ዕለት አስጠነቀቀ፡፡ ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓተ ቀኖና ተከትሎ የሚሠራ በመሆኑ ምንም ዓይነት ሕግና ሥርዓት እንዳልጣሰ በመግለጽ ለማስጠንቀቂያው ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እንደገለጹት፣ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፀድቆ የተሰጠውን ሕግና ደንብ ወደ ጐን በመተው፣ ያለሥልጣኑና ቦታው ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያንና የኅብረተሰቡን ሰላም በሚነካ መልኩ ይንቀሳቀሳል፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አመራሮችና የራሱ አመራሮች አስተላልፈውት የነበረውን ባለስድስት ነጥብ (በ2002 ዓ.ም.) ውሳኔም አላከበረም፡፡ ግንቦት 10 ቀን 2003 ዓ.ም. ተጀምሮ ግንቦት 16 ቀን 2003 ዓ.ም. የተጠናቀቀውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ሰላም ለማወክ ተንቀሳቅሷል፡፡

ማኅበሩ ሥራውን በመምሪያው ሥር በማለፍ እንዲሠራ፣ የሕትመት ውጤቶችንና የሚዲያ ሥርጭቶችን በሙሉ በተመደቡ ሊቃውንት እንዲያሠራጭ መታዘዙንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመ ጀምሮ ኦዲት ተደርጐ እንደማያውቅ የገለጹት አባ ሠረቀ ብርሃን፣ ለ19 ዓመታት ግብርና ቀረጥ ሳይከፍልባቸው በቤተ ክርስቲያኗ ስም የተከፈቱ ልዩ ልዩ የንግድ ተቋማትንና የገቢ ማስገኛ ማዕከላትን እንዲያስመዘግብና ቢሮውን ለኦዲት አድራጊዎች ክፍት አድርጐ እንዲያስመረምር ትዕዛዝ መተላለፉንም አስታውቀዋል፡፡

ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በሆነ መንገድ በራሱ ፈቃድ እየፈጸመ ያለውን የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲያቆምና ‹‹አለኝ›› የሚለውን መረጃ ለቤተ ክርስቲያኗ አካላት ማቅረብ እንዳለበት የገለጹት ኃላፊው፤ ‹‹ካላቀረበ ግን በስም ማጥፋት ውንጀላ ተጠያቂ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ማኅበሩ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ውጭ ይንቀሳቀሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ተጠይቀው፤ ‹‹ብዙ ሰው ያልገባው እዚህ ላይ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሃይማኖት ህፀፅ የለበትም፤ ያለበት የአስተዳደር ችግር ነው ይላሉ፡፡ በእኛ እምነት ግን ስንዴ ባለበት ቦታ ሁሉ እንክርዳድ አይጠፋም፤ አለ እንላለን፡፡ እምነት ባለበትም የተለያዩ ህፀፆች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

የሃይማኖት ህፀፅ ያለበት ሰው በአግባቡ ተመርምሮ ለሊቃውንት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚያገኝ የተናገሩት ኃላፊው፣ ማኅበሩ ግን ያለምንም ማስረጃ ስም እንደሚያጠፋ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ ያለስማቸው ስም ሰጥቷቸው የነበሩ አባቶች በቅዱስ ሲኖዶሱ ተመርምረው ነፃ መውጣታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በማኅበሩ ውስጥ ግን ብዙ መናፍቃኖች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኗን ሕግጋት በደንብ ተምሮና አውቆ መተግበር ለሚችል በየደረጃው የተቀመጡትን ማዕረጐች የሚሰጠው ቢሆንም፣ ማኅበረ ቅዱሳን ሕግና ሥርዓትን በመጣስ እንደ ክብር ዶክትሬት፣ ድቁናንና ቅስናን እንደሚሰጥ አባ ሠረቀ ብርሃን አመልክተዋል፡፡

በመንበረ ፓርትያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃና መምሪያ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያና ማኅበሩ ፈጽሟል ስለተባለው ግድፈቶች በሚመለከት ያነጋገርናቸው የማኅበረ ቅዱሳን ማኅበር ዋና ፀሐፊ መምህር ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም ምላሽ መስጠት የጀመሩት ‹‹ይኼ የማኅበረ ቅዱሳንን ስም ማጥፋት ነው፤›› በሚል ነው፡፡ ‹‹የቤተክርስቲያኗም ሊቃውንት ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በመምሪያውና በእኛ መካከል ችግር እንዳለ ተነጋግረናል፤›› የሚሉት ዋና ፀሐፊው፣ በተነጋገሩት መሠረት ችግሩን የሚያጣራ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳትና አራት ሊቃውንት ያሉበት ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶሱ ተቋቁሞ ጉዳዩን እያጣሩት እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ችግር ፈጣሪ አለመሆኑን፣ ችግር ለመፍጠር የሚያስችል ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለበትና ስሙን በከንቱ የሚያነሱትም ያለምንም ምክንያት በውስጣቸው ካደረባቸው ፍርኃት የተነሳ መሆኑን መምህር ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ እየታገለ ያለው ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀኖናና ዶግማ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን መሆኑን የገለጹት ዋና ፀሐፊው፣ ትውፊቱንና ሥርዓቱን ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ ሊያስወቅስ እንደማይገባም አስታውቀዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በሕግ የተቋቋመ ማኅበር እንደመሆኑ መጠን፣ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የውስጥ ኦዲተና ኢንስፔክሽን እንዳለው የገለጹት ዋና ፀሐፊው፣ አንድም ዓመት ቢሆን ኦዲት ሳይደረግ እንዳልቀረ፣ ለሚመለከታቸው የቤተክህነት ኃላፊዎች ሪፖርት እንደሚያደርግና የ2001 ዓ.ም. ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው ግርማ ዋቅጅራና ጓዶቹ የኦዲትና ምርመራ ድርጅት ኦዲት ማስደረጋቸውንና ሪፖርት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ይኸ ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል ነው፡፡ በሕግም እንጠይቃለን፤›› ያሉት መምህር ሙሉጌታ፣ መምሪያው ለምን እንደዚህ እንዳለ ግን መገረማቸውን ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ ከ15 ሺሕ በላይ ቋሚ አባላትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች እንዳሉት የገለጹት ዋና ፀሐፊው፣ 120 ሺሕ ተማሪዎችን መንፈሳዊ ትምህርት በማስተማር ማስመረቃቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ሥርዓት ውጭ ዲያቆናትና ቄሶችን ይሾማሉ፣ ማዕረግ ይሰጣሉ ስለሚባሉት ሲናገሩ፣ መምሪያው ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ መያዙንና በሕግም እንደሚያስጠይቀው የገለጹት መምህር ሙሉጌታ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ መነኮሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዳሉ ተናግረው ሁሉም ምሁር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ተሃድሶን በሚመለከት መምህር ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ ማኅበሩ አጠቃላይ ጥናት አድርጓል፡፡ ተሃድሶ የለም የሚል ካለ ራሱ ነው ማለት ነው፡፡ በስውር በከፍተኛ ፈንድ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከ17 በላይ ድርጅቶች ይረዱታል፡፡ እነማን እንደሆኑ ግን አልጠቀሱም፡፡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ አቅርበው ተወያይተዋል፡፡ ከ30 በላይ ለሚሆኑ አባቶች በጽሑፍ አስታውቀዋል፡፡

2 comments:

Anonymous said...

እነሆም እኔ እስከአለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋርነኝ ማቴ 28 20 ብሎእንዳለው ጌታችን መድሀኒታችን ልትፈሩና ልትሰጉ አይገባችሁም በማስጠንቀዊያላይ ማስጠንቀቂያ ቢደራርቡም እውነትን ስለያዛችሁ እግዚአብሄር ከናንተጋር ነው በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ ዮሐ 16 33 ስለዚህ ሳያውቁትየደጋፊዮቻችሁን ቁጥር እያበዙት ነውና በሚከስዋችሁ ክስ አትዘኑ!

ርብቃ ከጀርመን said...

እነሆ እኔ እስከ ዓለምፍጻሜድረስ ሁልግዜ ከእናንተ ጋር ነኝ ማቴ 28 20 እንዳለው ጌታችን በቃሉ እውነትን እስከያዛችሁ ድረስ ምንምየሚያሰጋችሁ ነገር የለም በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገርግንአይዞአችሁ እኔዓለምን አሸንፌዋለሁ ዮሐ 16 33 ስለዚህ ስለናንተ በሚናገሩት ውሸትና ቅጥፈት ሳያስቡት የደጋፊ አባሎቻችሁን ቁጥር ነውእያበዙት ያሉት አይዞአችሁ የቤተክርስትያን አምላክ ይፈርዳል መጭውም የጾም ሰአት ስለሆነ ባንድልብ ሆነን ሁሉን ቻይለሆነው አምላክ ማመልከት ነው ክርስቲያን በቀሉን(ፍርዱን) ከላይ ነው የሚጠብቀው!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)