June 5, 2011

ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን በደብረ አሚን ተ/ሃይማኖት የከረረ ተቃውሞ ገጠማቸው፤ የተጎሸሙም አሉ

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።
  • የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምክሐ ደናግል ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በአሸናፊ ገብረ ማርያም፣ ዳግማዊ ደርቤ፣ እስጢፋኖስ ሣህሌ፣ ምርትነሽ ጥላሁን እና ሌሎች መሰሎቻቸው ላይ የአካላዊ ቅጣት ርምጃ በመውሰድ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን አባረሩ፤ ከተባረሩት ውስጥ የሕገ ወጦቹን ሥራ በማተም እና በማከፋፈል ተባባሪ የሆኑ ‹‹መዝሙር ቤት›› ባለቤቶች ይገኙባቸዋል፤ ወላዋይ አገልጋዮችም አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል
  • ወጣቶቹ ሕገ ወጦቹን የቀጡበት አኳኋን ጉዳዩ የሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ አስተዳደር ሕገ ወጦቹን በተጨባጭ ለመቆጣጠር ባለመቻሉ የምእመኑ ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን እንደሚያመለክት ተገልጧል
  • ‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዝም በማለታቸው ይህን ርምጃ ለመውሰድ ተገደናል፤ የተክለ ሃይማኖት ድል በዮሴፍም ይደገማል፤ ሕገ ወጦቹን ከአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በማጽዳት የሐዋሳን ምእመናን እምባ እናብሳለን፤ ሃይማኖታችንን መጠበቅ ብቻ ማእከል ያደረገው ርምጃችን ሕገ ወጦቹ ስሕተታቸውን አርመው የበደሉትን ምእመን ይፋዊ ይቅርታ እስኪጠይቁ አልያም ለይቶላቸው ወደ መናፍቃኑ ጎራ እስኪገቡ ድረስ ይቀጥላል!!››  (የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ወጣቶች)
  • ‹‹ሊቀ ካህናት›› ጌታቸው ዶኒ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ሐላፊ ሆነው መሾማቸው እየተነገረ ነው፤ የጅጅጋን እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብት ሥራ አስኪያጆችን ለማስነሣት የአድማ ፊርማና ምክክር እየተካሄደ  ነው
(ደጀ ሰላም፤ ጁን 5/2011)፦ እሑድ ግንቦት 29 ቀን 2003 ዓ.ም፤ ከረፋዱ 5፡00 ሆኗል፡፡ ጠዋት በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በሥርዐተ ተክሊል ጋብቻውን የፈጸመው ዘማሪ ፈቃዱ አማረ ወደ ሠርጉ የጠራቸው ታዳሚዎች ወደሚጠባበቁበት የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ እያመ ነው፡፡ በደብሩ አዳራሽ ቀደም ብለው የተገኙት ዘማሪዎች (ዳግማዊ ደርቤ፣ አሸናፊ አበበ፣ ታምራት እና የትምወርቅ) ማቀንቀናቸውን  ቀጥለዋል፡፡

ሞያ በልብ ያሉት የደብሩ ዲያቆናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት እና በቀናዒነታቸው የታወቁት የአጥቢያው ወጣቶች ደግሞ ስለ መርሐ ግብሩ ዝርዝር እና በመርሐ ግብሩ ላይ ስለሚያገለግሉ ሰባክያን እና ዘማርያን ማንነት አስቀድመው ከሙሽራው ጋራ በተነጋገሩት መሠረት ቦታ ቦታቸውን ይዘው ገቢውንና ወጪውን እየቃኙ አካባቢውን በንቃት እየተቆጣጠሩ ነው፡፡ አስቀድሞ ከሙሽራው ጋራ በተደረገው ንግግር ወጣቶቹ፣ ‹‹በቅዱሳን ላይ አፋቸውን አላቅቀዋል፤ በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የስድብ ቃል ተናግረዋል፤ በሃይማኖታቸው ሕጸጽ አለባቸው፤ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ መልእክተኞች ናቸው›› ያሏቸውን ሰባክያን እና ዘማርያን ስም በመዘርዘር እግራቸው ሰበካውን እንዳይረግጥ እንዲያስጠነቅቃቸው፣ ይህ ካልሆነ ግን የከፋ ርምጃ እንደሚወስዱባቸው አስታውቀዋል፤ በዚህም መሠረት መልእክቱ በተለያየ መንገድ እንደደረሳቸው ተረጋግጧል፡፡ ወጣቶቹ ይህንኑ ስጋታቸውንና ማስጠንቀቂያቸውን ለደብሩ አስተዳደርና ለአቅራቢው የፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ በጻፉት ደብዳቤ በማሳወቃቸውም ከ40 ያላነሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኀይሎች በደብሩ ዙሪያ ተገኝተዋል፡፡

ከየአብያተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት ቢወገዱም እንደ ድንኳን ሰባሪ ሳይጠሩ በየሠርጉ አዳራሽ እየገቡ በማወክ የኦርቶዶክሳውያንን ልብ ማቁሰልን ሥራዬ ብለው የተያያዙት ዘማሪ እና ሰባኪዎቹ ግን የወጣቶቹ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይገታቸው ከመናፍቃኑ ጋራ አብረው ተባብረው ጽርፈት ወደሚናገሩባቸው ጻድቅ አጥቢያ ያለኀፍረት ለመምጣት ደፈሩ፡፡

‹‹ደጅሽ ላይ ቆሜ እጠራሻለሁ›› በተሰኘውና በሌሎች አምስት የአልበም ሥራዎቹ የሚታወቀውን ሙሽራውን ዘማሪ ፈቃዱ አማረን የያዘው መኪና ከደብሩ ቅጽር ሲደርስ እግራቸው ሰበካውን እንዳይረግጥ ማስጠንቀቂያ ከተላለፈባቸው ሕገ ወጦች አንዱ የሆነው እስጢፋኖስ ሣህሌ (በቅጽል ስሙ ቄሴ) በመኪናው ውስጥ እንዳለ በወጣቶቹ እልምት ውስጥ ገባ፡፡ ለሙሽራው ሁለተኛ ሚዜ እንደ ነበር ተነግሯል፡፡

ከመኪናው እንዲወርድ በወጣቶች የታዘዘው እስጢፋኖስ ሣህሌ ከመኪናው እንደወረደ የተቀበለው ሰማይ ምድሩን የሚያዞር ጥፊ ነበር፡፡ ለሙሽራው ሁለተኛ ሚዜ በመሆኑ አስተያየት እንዲደረግለት የጠየቁ ምእመናን ቢኖሩም ‹‹የእርሱ ሚዜነት ከተክልዬ ክብር አይበልጥም፤ ሲሳሳት አታርሙትም!!›› ነበር የወጣቶቹ መልስ፡፡ እስጢፋኖስ እየተገፈተረ ከቅጽሩ እንዲወጣ ተደረገ፡፡

ይህ ርምጃ በሚወሰድበት ቅጽበት የሕገ ወጥ ቡድኑ ‹‹ሶፍትዌር›› እንደሆኑ  ከሚነገርላቸው ግለሰቦች አንዱ የሆነው አሸናፊ ገብረ ማርያም ወደ ቅጽሩ ገብቶ በመሳለም ላይ ነበር፤ የሚከታተሉት ወጣቶችም በመጠጋት ‹‹አሸናፊ፣ የሰደብሃቸውን ተክልዬን ከተሳለምህ ይበቃሃል፤ ከዚህ በኋላ ቀጥ ብለህ ውጣ›› ይሉታል፤ አሸናፊ ግን በእምቢታ ያንገራግራል፤ ከወሬ ይልቅ ተግባራዊነትን መርሃቸው ካደረጉት ወጣቶቹ አንዱ ቀሲስ አሸናፊ በሱሪ ኪሱ የያዘውን/በአባ ሰረቀ አነጋገር የወተፈውን/ መስቀል፣ ‹‹ማነው ይህን መስቀል ለአንተ የሰጠህ?›› በሚል ላጥ አድርገው ይነጥቁታል፡፡ ወዲያው ሌላው ወጣት ቡጢ ይመታዋል፤ የወጣቶቹን ማምረር ለመረዳት እልኩ ያልረዳው አሸናፊም ‹‹እናትህ. . . ›› በማለት የመታውን ወጣት ይሳደባል፤ የዐይን እማኞች እንደተናገሩት እንኳንስ ከ‹‹ቀሲስ›› ከሌላው በማይጠበቀው በዚህ ስድቡ የወጣቶቹን ቁጣ ያባባሰው አሸናፊ ፋታ በማይሰጠው የወጣቶቹ ጥቃት እየተመታ በገላጋዮች ብርታት ክፉኛ ከመጎዳት ተርፎ ከስፍራው ተሸኝቷል፡፡ እርሱ እየተሸኘ ወደ ቅጽሩ በመግባት ላይ የነበራችው ምርትነሽ አንድ ጥፊ አርፎባት በመጣችበት አኳኋን ስትመለስ እያለቀሰች ነበር፡፡

ወጣቶቹ በመቀጠል ወደ አዳራሹ አመሩ፤ ቀደም ብሎ ወደ አዳራሹ ዘልቀው ለአፍታም ቢሆን ድምፅ ማጉያ ለመጨበጥ ዕድል ካገኙት ውስጥ የትምወርቅ እና ቅድስት ምትኩ ከአዳራሽ ታንቀው ከወጡ በኋላ የወጣቶቹን ጉሽሚያና ርግጫ እየቀመሱና እያለቃቀሱ በአስቸኳይ ከአካባቢው እንዲርቁ ተደረጉ፡፡

ዳግማዊ ደርቤ ‹‹የቦኤዝን እርሻ አልቃርምም እኔ. . .›› እያለ በአዳራሹ በማዜም ላይ ነበር፡፡ የወጣቶቹን ሁኔታ አስቀድመው የተመለከቱ ጓደኞቹ ማዜሙን እንዲያቆም መክረውት ነበር፤ አንድ ወጣት ትከሻውን መታ አድርጎ ካስቆመው በኋላ እየገፋ ወደ ውጭ እንዳስወጣው የበሩን ግራና ቀኝ ይዘው የቆሙ በረኞች የቡጢ ናዳ ይቀበለዋል፡፡ አንድ የዐይን እማኝ እንደ ተናገሩት፣ ዳግማዊ ከቅጽሩ የወጣው ወጣቶች ትክሻ ነበር፡፡

ወጣቶቹ በግልጽ የሚያውቋቸውን ሕገ ወጦች ካባረሩ በኋላ ማንነታቸውን የማይለዩዋቸው ሌሎች መኖራቸውን ለመለየት በጠቋሚ አሰሳ አደረጉ፤ እንደ ዐይን ምስክሮቹ ማብራሪያ በነደደ ቁጣ የታጀበችው ይህች የወጣቶቹ አሰሳ ቀና የሚባሉትንና በሠርጉ ላይ ለታደሙት ሌሎች አገልጋዮች ሳይቀር አርዕድ አንቀጥቅጥ የሆነች ቅጽበት ነበረች፤ ራሳቸውን በየሰዉ ጀርባ ሲሸሽጉ የተስተዋሉም ነበሩ፡፡ በአሰሳው የሕገ ወጦቹን ዘማርያን እና ሰባክያን ሥራ በማሳተምና በማከፋፈል ተሳትፎ አላቸው የተባሉት የአብ፣ የቢታንያ፣ የቬሮኒካ እና የአንጾኪያ መዝሙር ቤት ባለቤቶች ተለይተው እንዲወጡ ተደርገዋል ተብሏል፡፡ ከሕገ ወጦቹ ጋራ በመሞዳሞድ ወላዋይ አቋም የሚታይባቸው አገልጋዮችም በወጣቶቹ ማሳሰቢያ /ቢጫ ካርድ/ ተሰጥቷቸዋል - ምንጮቹ ማሳሰቢያ የተሰጣቸውን አገልጋዮች ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ በአዳራሹ የአሸናፊን ድርሰት ስታዜም የነበረች አንዲት ዘማሪም ምርጫዋን አስተካክላ ተገቢውን መዝሙር እንድትዘምር አድርገዋታል፡፡

ለሙሽራው ቅርብ የሆኑ የዜናው ምንጮች ዘማሪ አማረ ፈቃዱ ሕገ ወጦቹን ዘማርያን እና ሰባክያንን አለመጥራቱን፣ ቢመጡም መድረክ እንዳይሰጣቸው አስተባባሪዎቹን አዝዞ እንደ ነበር አስረድተዋል፡፡ በአንጻሩ ወጣቶቹ የቀና ሃይማኖታዊ አቅዋም እንዳላቸው ያመኑባቸውን አገልጋዮች በታላቅ አክብሮት እየተቀበሉ ሲያስተናግዱ ታይተዋል፤ ከሕገ ወጦቹ አገልጋይ ነን ባዮች ይልቅ ነጻ አገልግሎት ለመስጠት ለብሰው ከተዘጋጁት የሰንበት ት/ቤቱ ወጣት ክፍል አባላት በኵረ ትጉሃን ፈንታ ገላው መርሐ ግብሩን በመምራት፣ መ/ር ዘመድኩን በቀለ እና ዲያቆን ታዴዎስ ግርማ መርሐ ግብሩን በማስተባበር፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የዕለቱን ትምህርት በመስጠት፣ ዘማርያኑ ዲያቆን ልዑል ሰገድ፣ ዲያቆን እንግዳ ወርቅ፣ አረጋዊ፣ ለሰባክያን ጥምረቱ ቀጣይ የገንዘብ ርዳታ በማስተባበር እየረዳች የምትገኘው ዘማሪት ፋንቱ ወልዴ እንዲሁም አዲስ ለማ በመዘመር ሲያገለግሉ ውለዋል፡፡ መምህር ዳንኤል ክብረት ‹‹ወሳኙ ሃይማኖት ነው›› በሚል ርእስ በሰጡት በዚሁ ትምህርት ‹‹ሃይማኖት የሌለው ሰው በሰማይም በምድርም መቅሠፍት አያጣውም›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

በዙሪያው እና በቅጽሩ ክዋኔውን በአንክሮ እና በድንጋጤ ሲታዘቡ የነበሩ ምእመናን፣ ‹‹ደግ አደረጉ! እነርሱስ ቢሆን ማን ኑ አላቸው? ደብሩኮ ተክለ ሃይማኖት ነው፤ ከጥንት ጀምሮ ይታወቃል፤ እየተነገራቸው/እያወቁ መምጣታቸው ድፍረት ነው፤ ቃለ እግዚአብሔሩን እንደሆን አይመሩበትም፤ አሁን እንኳ ዱላ ነው የሚገባቸው!! ድሮም የበላዮቹ ሳይሆኑ የምእመኑ ብርታት ነው ቤተ ክርስቲያንን የጠበቃት…›› ሲሉ መደመጣቸው ተዘግቧል፡፡ ሌሎች የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ደግሞ ቦታው የለመደ ስለ መሆኑ ተመሳሳይ ትውስታቸውን አካፍለዋል።

በ1986 ዓ.ም ክረምት ወራት አሁን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ባለሥልጣን ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ በወቅቱ በመላው የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ሲሰጥ የነበረውን የፀረ-ተሐድሶ ኑፋቄ ኮርስ ለማስቆም ይነሣሣሉ፤ በዚህ ጊዜ የአካባቢው ወጣቶች እኚህ ባለሥልጣን አይደለም በጻድቁ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መገኘት ከፒያሳ በታች የመውረዳቸው ዜና ቢሰማ ልክ እንደሚያገቧቸው ስላስጠነቀቋቸው ጥቂት ለማይባል ጊዜ ተሸማቅቀው ይኖሩ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ በዚሁ ዓመት ጾመ ሁዳዴ ከመግባቱ በፊት ሠርጋቸውን በአጥቢያው አዳራሽ ያደረጉ ሌላ ስም ያወጡ አገልጋይም የጋበዙት መምህር የማይሆን ስለነበር በወጣቶች ማስጠንቀቂያ በሌላ ተተክተዋል፡፡

‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዝም በማለታቸው የዛሬውን ርምጃ ለመውሰድ ተገደናል፤›› ያሉት የአጥቢያው ወጣቶች ‹‹የተክለ ሃይማኖት ድል በዮሴፍም ይደገማል፤›› በማለት እነበጋሻው በየሳምንቱ የሚፈነጩበትን የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ከሕገ ወጦች በማጽዳት ርምጃቸውን እንደሚቀጥሉ ዝተዋል፡፡ በሌላ በኩል መንፈሳዊ ቅንዐት የተመላበት የወጣቶቹ የማጽዳት ርምጃ የራሱ ምልከታዎች እንዳሉት ስለ ድርጊቱ የወጡ አስተያየቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከእኒህም መካከል፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶች በተቆርቋሪ ወገኖች የሚሰጣቸውን መረጃ መዝነው ተገቢውን አፋጣኝ ርምጃ ያለመውሰዳቸው ‹እግርን መጎተት› አልፎ አልፎም ዳተኝነት የወለደው ነው››፤ ‹‹ስለ ወቅታዊው የቤተ ክርስቲያን ችግር የሚተላለፈው መልእክት የጥቂቶች መሆኑ አብቅቶ ምእመኑን የተዋሐደው መሆኑንና ምእመኑ የተግባር መመሪያው ማድረጉን የሚያረጋግጥ ነው››፤ ‹‹አገልጋዮች ስለሚዘምሩበት እና ስለሚያስተምሩበት ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰበ ነው፤›› የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› አመራሮች ላይ የእስር ቅጣት ወሰነባቸው
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 4/2011)፦ የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚያዝያ ወር ውስጥ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ባስነሡት ብጥብጥ በንጹሐን ምእመናን ላይ ከፍተኛ የድብደባ ወንጀል ፈጽመዋል ባላቸው አራት የ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› ማኅበር አመራር በሆኑ ተከሳሾች ላይ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሐሙስ፣ ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት ገዛኸኝ አበራ እና አየነው የተባሉት ግለሰቦች በ8 ዓመት፣ ተስፋዬ በ5 ዓመትና ጌታሁን የተባሉት ደግሞ በ3 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

ውሳኔው በተላለፈበት ዕለት ምሽት የእኒሁ ወንጀለኞች ጥቂት ደጋፊዎች በገዳሙ ዐውደ ምሕረት ላይ በመውጣት በድምጽ ማጉያ ‹‹ወንድሞቻችን ተፈረደባቸው፤ ታሰሩ፤›› እያሉ የከተማውን ደጋግ ምእመናንን እና የማኅበረ ቅዱሳንን ስም እየጠሩ ሲወነጅሉ እንደነበር ተገልጧል፡፡ እኒሁ ግለሰቦች በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ተመርጠውና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተመድበው የሄዱትን አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ወደ ቢሯቸው እንዳይገቡ ለመከላከል ሞክረው እንደነበር ታውቋል፡፡ ይሁንና በፖሊስ ኀይል ከአካባቢው እንዲርቁ ከተደረገ በኋላ ሥራ አስኪያጁ ሥራ ለመጀመር መቻላቸው ተመልክቷል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ አላግባብ ከተሰጣቸው ሥልጣን እንዲወገዱ የተደረጉት ‹‹ሊቀ ካህናት›› ጌታቸው ዶኒ በተሰራጨው ቪ.ሲ.ዲ ስሜ ጠፍቷል ያሉበትን ክስ በዚያው በሐዋሳ ከተማ ሆነው እየተከታተሉ ሲሆን ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ምክትል ሐላፊ ሆነው መሾማቸው ተነግሯል፡፡Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)