June 28, 2011

“የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሚና በአየር ንብረት ለውጥ” የተሰኘ ጥናታዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ


  • TO READ IN PDF CLICK HERE.
  • “ቤተ ክርስቲያን ከአየር ንብረት ለውጥ ፈንዶች (ካርቦን ንግድ) ተጠቃሚ ልትሆን ይገባል”፤
  • በዓመት እስከ ከ150,000 - 200,000 ሄ/ር ደን ይራቆታል፤ በመልሶ ማልማት የሚተካው ከ2000 ሄክታር አይበልጥም፤ ለብሔራዊ ፓርኮች መጀመርና ለመንግሥት ደኖች መከለል መሠረት ለሆኑት የቤተ ክርስቲያን ተፈጥሯዊ የደን ይዞታዎች መንግሥት የሕግ ከለላ እንዲሰጥ ተጠይቋል፤
  • በሐዲስ  ኪዳን  ውስጥ ብቻ ለ1733 የበሽታ ዐይነቶች ፈውስ ሊሰጡ የሚችሉ 4200 የሚደርሱ የዕፀዋት ዓይነቶች መጠቀሳቸውን ተወስቷል፡፡
  • ለቅብዐ ሜሮን የሚሆኑት ዕፀዋት ውጤቶች በአብዛኛው ከግብፅ እና ከሱዳን የሚመጡ ናቸው፤ በሀገር ውስጥ የማልማቱ ጅምር እንዳለ ተጠቁሟል
(ደጀ ሰላም፤ ጁን 28/2011)፦ የአየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተጽዕኖዎች በመቀነስ እና ለውጡን በመግራት ተስማሚ የአኗኗር ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ሀገር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ አጋር ልትሆን እንደምትችል ተመለከተ፡፡
ለአካባቢ ጥበቃ እና ክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ እንዲሁም የተፈጥሮ አካባቢን በመጠበቅ ረገድ ቤተ ክርስቲያኒቱ በተጨባጭ የምታበረክተው ድርሻ ተገቢው እውቅና እንዲሰጠው፣ የአየር ንብረት ለውጥን ምንነት ለማስጨበጥ የሚቀርቡ አስረጅዎች ኅብረተሰቡ በችግሩ መንሥኤዎች እና መፍትሔዎች ላይ የሚኖረውን አመለካከት የሚወስኑ በመሆናቸው ከአግባብነት አኳያ ጥንቃቄ እንዲደረግባቸውም ተጠይቋል፡፡


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የጥናት እና ምርምር ማዕከል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሚና በአየር ንብረት ለውጥ” በሚል ርእስ ትናንት በብሔራዊ ሙዝየም አዳራሽ ባካሄደው የሙሉ ቀን ጥናታዊ የውይይት መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፣ ቤተ ክርስቲያን የደን ሽፋን መራቆት ተባብሶ በሚታይባቸው በሰሜናዊ እና መካከለኛ የኢትዮጵያ ክፍሎች አገር በቀል ዛፎችን በመጠበቅ እና በመከባከብ እንዲሁም ለአገር በቀል ዕፅዋት የዘር ምንጭ በመሆን “የደን ደሴት” ፈጥራ መቆየቷ እምነት እና የአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን ቁርኝት እንደሚያሳይ ተገልጧል፡፡

“የአየር ንብረት ለውጥ እና ሃይማኖታዊ እሳቤ” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት በአካባቢ ሳይንስ የግል አማካሪ የሆኑት አቶ ወንድወሰን ሚቻጎ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቆጣጠር “የጉዳት መጠኑን መቀነስ” /Mitigation/ ወይም “ተጽዕኖውን በመግራት ተስማሚ ተፈጥሯዊ አካባቢን መፍጠር” /Adaptation/ የተሰኙ ሁለት ዋነኛ አማራጮች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመግራት ተስማሚ ተፈጥሯዊ አካባቢን መፍጠር የተሻለ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን የተናገሩት አማካሪው፣ ኅብረተሰቡ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ተጨባጭ እና ታሳቢ ተጽዕኖዎች ትክክለኛ አመለካከት እና አረዳድ ይዞ ተፈጥሯዊ አካባቢውን እንዲጠበቅ እና እንዲከባከብ በማስቻል /shaping public understanding and perception of climate change adaptation/  ረገድ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሚና እንዳላት አብራርተዋል፡፡ ለዚህም “ቤተ ክርስቲያን በአስተምህሮዋ የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት ነው የምታየው?” የሚለው ወሳኝ መሆኑን አማካሪው ጠቁመዋል፡፡ በአሜሪካው ያሌ ፕሮጀክት በአየር ንብረት ለውጥ ግንዛቤ ዙሪያ በሠራው ጥናት እስከ 63 በመቶ አሜሪካውን የዓለም ሙቀት መኖሩን ቢያውቁም የሙቀት መጨመሩን ትክክለኛ መንሥኤ እንደማያውቁት፣ ይህም ጥቂቶች የሙቀት መጠኑ ስለ መጨመሩ የሚቀርበውን መረጃ እስከ መጠራጠር ሲያደርሳቸው ሌሎችም ስለ ችግሩ መነሻ ያልተሟላ ግንዛቤ እንዲይዙ እንዳደረጋቸው በቀረበው ጽሑፍ ላይ ተመልክቷል፡፡

ቀደም ሲል ስለ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምንነት የተላለፈበት መንገድ ቆይቶ ከቫይረሱ ጋራ በሚኖሩት ወገኖች ላይ አድልዎ እና መገለል እንዲደርስ በማድረግ በውስን አቅማችን በመከላከሉ ላይ አተኩረን እንዳንሠራ ውድ ዋጋ እንዳስከፈለን ያስታወሱት ጥናት አቅራቢው፣ ዛሬም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚታየውን የድርቅ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ ከፈጣሪ ቁጣ ወይም አንድ ጊዜ ከተወሰነ ተፈጥሯዊ ሂደት ጋራ ብቻ ተወስኖ እንዲታይ የሚያደርጉ አቀራረቦች የሰው ልጅ በቀውሱ ዙሪያ ያለበትን ሓላፊነት እንዳይወጣ የሚያዘናጉና ተነሣሽነቱን የሚያመክኑ በመሆናቸው ጥንቃቄ እንደሚያሻቸው መክረዋል፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤያት መሳተፍ ከጀመሩበት እ.አ.አ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄዱት ስብሰባዎች የአየር ንብረት ለውጥንና የብዝሐ ሕይወት ጥበቃን ቴዎሎጂያዊ እና ኤቲካል መሠረተ ሐሳቦች ከማብራራት በቀር አማኞች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ስላላቸው አመለካከት እና አረዳድ ትኩረት እንዳልተሰጠው አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡ 

ከዚህ አንጻር በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ምእመናንና በርካታ የዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ያሏት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአካባቢ ጥበቃ የሚያስፈልጉ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሀብቶች ያሏት በመሆኑ በምእመናን አመለካከት እና አረዳድ ላይ መሥራት የሚቻልና የሚገባ ስለ መሆኑ በአቶ ወንድወሰን ጥናት ላይ ተመልክቷል፡፡ ብዙዎቹ ምእመናኗ በአካባቢ መራቆት እና በአየር ንብረት ለውጥ በተጠቁት አካባቢዎች እንደ መገኘታቸውም መጠን፣ እኒህ ሀብቶቿ ወቅታዊ ይዞታቸው ታውቆና የተቀናጀ የአጠቃቀም ዕቅድ ተዘጋጅቶላቸው ስለ ችግሩ ምንነት፣ መንሥኤ እና መፍትሔ ትክክለኛ ግንዛቤ/The Right framing of  perceptions on Climate Change for effective and efficient Adaptation and Implementation/ ለመፍጠር በሚያስችል አኳኋን መደራጀት እንደሚገባቸው አማካሪው አሳስበዋል፡፡

የአማካሪውን ጥናት መነሻ ያደረገውን ውይይት የመሩት ዶ/ር መኩሪያ አራጋው በበኩላቸው፣ “መሬት በተፈጥሯዊ ዑደቷ ወደ በረዷማነት እየቀዘቀዘች እንደምትሄድ ይገምት የነበረ ቢሆንም በሰው ልጅ በተለይም ያደጉት አገሮች ኢንዱስትሪያዊ ስምሪት ወደ አካባቢ አየር በሚለቋቸው ጋዞች ምክንያት ሙቀቷ እየጨመረ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ350 ዓ.ዓ ጀምሮ ድርቅ ስለመኖሩ በታሪክ የተመዘገበ ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጡ ግን በዋናነት የካርቦን ልቀትን መንሥኤ ካደረገው የዓለም ሙቀት መጨመር ጋራ የሚያያዝ ነው፡፡ ይህም ቢያንስ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ በተወሰዱት ሜትሮሎጂያዊ መረጃዎች ተረጋግጧል፤” ብለዋል፡፡ 

አንድ የውይይቱ ተሳታፊ በሰጡት አስተያየት፣ “ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ስጦታ ናት፤ ስጦታ ደግሞ ጥበቃና ክብክቤን ይሻል፤ ተፈጥሮን መከባከብ አዳማዊ ሐላፊነትና ተግባር ነው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ‹እንደምን ማሸነፍ ትችላለህ?› እየተባሉ ከሚተረጎሙት መጻሕፍት ጀምሮ የማያቸው ነገሮች ሁሉ ለተፈጥሮ አካባቢ መጠበቅ አስተዋፅኦ ካለው ማኅበራዊ መተሳሰብ ይልቅ ግለሰባዊ አሸናፊነትን/የበላይነትን/ የሚያበረታቱ ካፒታሊስታዊ አካሄዶችን ነው፡፡ ይህም ለ'Tragedy of the Common' አደጋ ይዳርገናል፤” ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እኚሁ የውይይት ተሳታፊ በአስተያየታቸው ማጠቃለያ ላይ አንድ ጥያቄ አዘል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል - “ቅዱስ ጴጥሮስ በካልኣይ መልእክቱ ምዕ.3 ቁጥር 8 ላይ የሰማይ ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል፤ ምድርም በእርሷም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል፤ የሚል ቃል መስፈሩን በማስታወስ እየሞቀች ሄዳ በታላቅ ትኵሳት ወደምትፈታዋ ዓለም መሄዳችን ቀድሞ የተጻፈና አይቀሬ ነው፤ ስለዚህ እንሁን የምትሉት?”

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ሳይንስ ባለሞያ የሆኑት አቶ ቱሉ ቶላ ቶራ፣ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተዋፅኦ የካርቦን ልቀትን ለመቆጣጠር” በሚል ርእስ ባቀረቡት ሌላ ጥናት፣ ከ35,000 በማያንሱት የቤተ ክርስቲያኒቷ አድባራት እና ገዳማት ይዞታዎች ውስጥ ተጠብቀው የሚገኙት የአገር በቀል ዛፎች በሌላው የሀገሪቱ ክፍል ከሚገኙት የደን ሽፋኖች በላቀ መልኩ ለዓለም ሙቀት መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለውን የካርቦን ጋዝ አቅበው የማስቀመጥ/Carbon Sequestration/ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው፣ ይህም ለካርቦን ንግድ/Carbon trade/ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን የጋራ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡ ባለሞያው በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አቅጣጫዎች የሚገኙ የሰባት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን/ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ፣ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ ርእሰ አድባራት እንጦጦ ቅድስት ማርያም፣ ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም፣ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና የካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል/ የተፈጥሮ ደን ይዞታዎች በዝርያ፣ ከመሬት በላይና ከመሬት በታች ባላቸው ዕድገት፣ ስፋትና የሽፋን መጠን በመለየት የካርቦን መጠንን አቅበው ለመያዝ ስላላቸው ጠባይ የመስክ እና የቤተ ሙከራ ምርምሮችን አካሂደዋል፡፡

በሌሎች የሀገሪቱ ስፍራዎችና በዓለም ደረቅና ርጥብ የትሮፒካል አካባቢ ከሚገኙ ተመሳሳይ ቁመና ካላቸው የደን ሽፋኖች ጋራ አነጻጽረዋል፡፡ በውጤቱም በሀገሪቱ ሌሎች ስፍራዎች ከሚገኙ ደኖችና ከውጭ ከመጡት ዝርያዎች ይልቅ ምርምሩ በተደረገባቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያሉት የአገር በቀል ዛፎች ዝግ ያለና ጥንክርና ያለው የዕድገት ጠባይ ብዙ ካርበን/ከ515.30 - 2496.79 ቶን ካርቦንዳይኦክሳይድ ጋዝ በሄክታር/ አቅበው ለመያዝ ያስችላቸዋል፡፡ ይህም በከተማው የካርቦንን ልቀት በመቀነስ የአየር ንብረት ተጽዕኖውን ለመግራት፣ የከተማውን አረንጓዴ ልማት በማገዝ ለብዝሐ ሕይወት ጥበቃ ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ባለሞያው አስረድተዋል፡፡ ስለዚህም እንደ ወይራ፣ ዋርካ፣ የሐበሻ ጥድ፣ ኮርች፣ አርዘ ሊባኖስ፣ ግራር፣ ጠመንጃ ዛፍ፣ ዘንባባ፣ የሐበሻ ባሕር ዛፍና የመሳሰሉት ዛፎች በቆየው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ መሠረት በራሳቸው ስላላቸው ዋጋ ሲባል መጠበቅ እንደሚገባቸው ባለሞያው አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን ተፈጥሯዊ ደኖች “የዘራፊ መሸሸጊያ ሆነዋል” በሚል መመንጠራቸውን፣ በምትኩ የገበያ አዋጭነት በሚል በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መተካታቸውን፣ ከሰል ለማክሰል በሚል መቃጠላቸውን በመከላከል ቤተ ክርስቲያን ለአካባቢ ጥበቃ ባላት አስተዋፅኦ ፋይናንሳዊ ጥቅም/Payment for environmental services/ የሚያስገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደያስፈልግ ባለሞያው አሳስበዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ተፈጥሯዊ ደኖች አገር በቀል ዛፎች ለዘር ተርፈው የሚገኙባቸው “የደን ደሴት” መፍጠራቸውን ያስረዱት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሞያው አቶ ተስፋዬ አራጌ፣ ቤተ ክርስቲያንዋ ያለውን አገር በቀል ዛፍ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን አዲስ ችግኞችን በመትከልና በመከባከብ  የተፈጥሮ አካባቢን በመጠበቅ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ቤተ ክርስቲያንዋ የራስዋን ቅጥር በደን ከመሸፈን አልፋ ዛሬ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ለሚገኙ ብሔራዊ  ፓርኮች መመሥረት ምክንያት እንደ ሆነች መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ለመመሥረቱ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ የቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን በቦታው መኖሩ ነው፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን የደንቆሮ ደን ብሔራዊ ፓርክ መነሻው የምስካበ ቅዱሳን ማርያም ገዳም መሆንዋ እንዲሁም በጣና ደሴት ለሚገኘው የተፈጥሮ ደን ጥበቃ ዋነኛው የገዳማቱ መኖር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥናት በተደረገባቸው የደቡብ ጎንደር ሦስት ወረዳዎች  እንደታየው፣ እንደ ሊቦ ከምከም ጣራ ገዳም እና በፋርጣ ወረዳ የሚገኘው የዓለም ሳጋ የመንግሥት ደኖችና በዳራ ወረዳ የመካነ ሰማዕት ገላውዴዎስም ከገዳማት ይዞታዎች የተወሰዱና ዛሬም ከገዳማቱ ጋራ የተቆራኙ ናቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ደኖችን መቁረጥ በቃለ ዐዋዲ የተከለከለና የተወገዘ ነው፡፡ ምእመኑ የቤተ ክርስቲያን ዐጸድን መቁረጥ የሚያስቀስፍ እንደሆነ ስለሚያምን አይደፍርም፤ እንሰሳትንም አያስገባም፡፡ “ዐጸድ የሌለው ደብር ጽሕም  የሌለው መምህር፣ ለሰው  ጨርቅ ነው ልብሱ፤ ለቤተ ክርስቲያን ደን ነው ሞገሱ፣ ጥምጣም የሌለው ካህን፤ ጥምጣም የሌለው ካህን፣ አጸደ የሌለው ቤተ ክርስቲያን፤” የሚሉት የማኅበረሰቡ ብሂሎች የቅዱሳን መጠለያና መጠጊያ ሆኖ ለኖረው የቤተ ክርስቲያን የተፈጥሮ ደን ምእመናን ያላቸውን አመለካከትና አክብሮት የሚያጠይቁ ናቸው - እንደ አቶ ተስፋዬ ማብራሪያ፡፡

በአንጻሩ በአንዳንድ አካባቢዎች የጥቅም መጋጨት እና ከመንፈሳዊ  ክብር ይልቅ ለቁሳዊ ጥቅም ዋጋ እየተሰጠው መምጣቱ፤ ምእመኑ እና የሃይማኖት መሪዎች በደንና አካባቢ ጥበቃ  ላይ  እያበረከቱ ያለውን ተግባር ያለመገንዘብ፣ በመንፈሳዊ መሪዎችና በግብርና ጣቢያ ሠራተኞች መካከል ደንን በመጠበቅ የጋራ ግንዛቤ ያለመፍጠር፤ መንፈሳዊ ቅርሱ/እምነቱ/ የተፈጥሮ አካባቢን ለመጠበቅ የሚያበረክተውን ድርሻ ያለመረዳት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተፈጥሮ አካባቢን በመጠበቅ የምታበረክተውን አስተዋፅኦ ያለመገንዝብና እውቅና ያለመስጠት በድክመት የሚጠቀሱ መሆናቸው በጽሑፍ አቅራቢው ተመልክተዋል፡፡ መንፈሳዊ መሪዎችና ቤተ ክርስቲያንዋ የተፈጥሮ አካባቢን በመጠበቅ ስለሚያበረክቱት ድርሻ ዕውቅና መስጠት፣ መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት በጋራና በመመካከር መሥራት፣ ለቤተ ክርስቲያን የደን ክልል በመንግሥት በኩል የሕግ ሽፋን መስጠት፣ እምነት እና የአካባቢ ጥበቃ ያለውን ቁርኝት መገንዘብ በጥናቱ የተጠቆሙ የመፍትሔ ሐሳቦች ናቸው፡፡

ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚሁ ጥናታዊ የውይይት መድረክ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ሳይንስ መምህራንና ተማሪዎች፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋራ ተያያዘ የሚሠሩ ልዩ ልዩ መንግሥታዊ የሆኑና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል፤ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችም በባለሞያዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡3 comments:

Anonymous said...

It is great Job MK. U have to show everyone all the benefits of our church. Ethiopian orthodox tewhado church is not only religious organization but also she gives many social and natural values to the country. So we should always work on these kind of research and show everyone what the church contributes to the country and its people. ስንዱ እመቤት አይደለች !!!!

Anonymous said...

It is interesting article. we should start intervention by implementing all
the useful studies like this on various
issues.Last time I remember Mahbere Kidusan has taken the responsibility and we had planted treesin Entoto area. let us do it all over the country now. At least we can plant in our areas.

It WILL BE 80 MILLION trees per day if we all patricipate today-including aregawiyan,kids and all.

Let us do it.

Anonymous said...

ቤተክርስትያን ለሃገራችን ያበረከተችው ይሄ ብቻ አይደለም። ሁሉም በየአቅሙ እና በየችሎታው እንደዚህ በጥናት የተደገፈ መረጃ ስለቤተክርስቲያናችን ቢያቀርብ ቢያንስ ባለማወቅ ከሚሰነዘሩባት ትችቶች መጠበቅ እንችላለን። አውቆ የሚያጠፋንም አፉን ያስይዛል። ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ የሚመካበትን ባህሉን እና ቅርሱን ጠብቃ ያቆየች እንዲሁም የኔ የሚለው ነገር እንዲኖረው ያደረገች ናት። በእውነት ማህበረ ቅዱሳን በጣም ትልቅ እና የሚያስደስት ስራ ነው የሰራችሁት። እግዚአብሄር የአገልግሎት ዘመናችሁን ያርዝምላችሁ፤ ይባርክላችሁ። በርቱ!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)