June 16, 2011

"ቅዱስ ሲኖዶስ ሲባንን" (የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ)

To Read in PDF Click HERE.
(መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ 56 ዓመት ቁጥር 120፣ ግንቦት 2003 ዓ.ም)፦ የዘንድሮው ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ሲኖዶስ ጉባኤ በየፈርጁ ያሳለፋቸው ወቅታዊ ውሳኔዎች ለቤተ ክርስቲያናችን ህልውና መጠበቅና መጠናከር የሚበጁ፤ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በተገቢው መንገድ ለመወጣት የሚያስችሉ ከላይ እስከ ታች ሰላምንና መረጋጋትን የሚያሰፍኑ ተገቢ ውሳኔዎች ናቸው፡፡


በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ርእሰ መንበርነት የተመራው ይኸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ካሳለፋቸው ወቅታዊ ውሳኔዎችም ዋና ዋናዎቹን ብንጠቅስ ከመንበረ ፓትርያሪኩ ጀምሮ እስከ አህጉረ ስብከት ያለው የሥራ ብልሽት የሚፈጠረው ማእከላዊነትን ባልጠበቀ አሠራር በመሠራቱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከላይ ወደ ታች የመጣውንም ሥራ ከታች ወደ ላይ ለማስተካከል እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና ጊዜ የሚፈጅ ይሆናል፡፡
ይህም በመሆኑ ከመንበረ ፓትርያሪኩ ጀምሮ እስከ አህጉረ ስብከት ያለው ማእከላዊነትን ያልጠበቀ አሠራር ከእንግዲህ ወዲህ መቀጠል እንደሌለበት (እንዲያከትም) የተላለፈው ውሳኔ በተግባር ከተተረጎመ ችግር አስወጋጅና መፍትሔ ሰጭ ውሳኔ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ዋና የደም ሥር የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ነው፤ ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ት/ቤቶችም የተፈጠሩትና ዛሬ እግር ተክለው ራሳቸውን ችለው መጓዝ የጀመሩት በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሞግዚትነት መሆኑን ሁሉም የሚያውቀውና ሊያስተባብለው የማይችል ሐቅ ነው፡፡ ስለሆነም የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሳይሸራረፍ በማንኛውም ግብረ ኃይል እንዲጠናከርና በቂ ትምህርት ሳይኖራቸው፣ በእምነታቸውም አጠራጣሪዎች ሲሆኑ በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ተቆጣጣሪ የሌለውና የቦዘነ ዐውደ ምሕረት ስላገኙ ቤተ ክርስቲያኒቱን የገቢ ምንጭ፣ ተከታዮቿ ምእመናንንም ያልተጣራ ሸቀጣ ሸቀጣቸው ማራገፊያ (ማጣሪያ) ባደረጉ ሰርጎ ገብ ሰባክያን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግና ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድባቸው የተላለፈውም ውሳኔ እጅግ አንገብጋቢ ውሳኔ ነው፡፡ በመሆኑም ለተግባራዊነቱ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ ነኝ የሚል ሁሉ ሊረባረብበት የሚገባ የወቅቱ ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡


ኧረ ለመሆኑ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሰርጎ ገብ ሰባክያንን እንዲቆጣጠር ተላልፎ የነበረውን ትእዛዝ መልሶ የሻረው ማን ነው? በአዲስ አበባም ሆነ በአህጉረ ስብከት ርእሰ ከተማ ዐውደ ምሕረቱን ሁሉ ሰርጎ ገብ ሰባክያን የገበያ ማእከል ሲያደርጉት የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና ወርሐዊ ደመወዝ የሚከፈላቸው መደበኞቹ ሰባክያነ ወንጌልስ የማንን ጎፈሬ ነው የሚያበጥሩት? ምናልባት እንደ ኤሳው ብኵርናቸውን በምስር ንፍሮ ሽጠውት ይሆን?

ሌላው በጋዜጣችን ተደጋግሞ እንደተጻፈው የቱሪስቶች መስሕብ የሆኑት እንደ ርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ የጣና ሐይቅንና የጻድቃኔ ማርያምን የመሳሰሉት ታሪካውያን ሥፍራዎች ከጎብኝዎች በሚያገኙት ገቢና በሌላውም የልማት ውጤታቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ በጀት አጋዥ ኃይል ሊሆኑ ሲገባቸውና በመሬት ላራሹ ዐዋጅ የተጎዱትን ገዳማትና በገቢ እጥረት የተቸገሩትን የገጠር አብያተ ክርስቲያናት መደጎም ሲችሉ ለእውነተኞቹ መናንያን ሳይሆን ለቀበሮ መናንያን መጠቀሚያና ለመንገደኛ አስተርጓሚዎች ሲሳይ በመሆን ዘመናትን ማሳለፋቸው ከማንም የተሰወረ ምስጢር አይደለም፡፡

ስለዚህ ከወጭአቸው በላይ ገቢ የሚያስገኙትን ታሪካውያን ሥፍራዎችን (ቅዱሳት መካናትን) ለማስጎብኘትና ብርቅና ድንቅ የሆኑ ቅርሶቿን ጠብቆ ለትውልደ ትውልድ ለማስተላለፍ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ጥረት በዘመናዊ መልክ ለተቋቋመው የቅርሳ ቅርስ ጥበቃ መምሪያ የሥራ ማከናወኛ ዓመታዊ በጀት በመፍቀድ የተላለፈው ውሳኔ ሊደገፍ የሚገባው ነው፡፡ ለርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ታሪካዊ ሙዝየም ግንባታ በቋሚ ሲኖዶስ የተፈቀደውም የሥራ ማስጀመሪያ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በከሣቴ ብርሃን ሰላማ ስለሚሰጠው የነገረ መለኮት ትምህርት ጥራት መጠበቅ የተላለፈውም ውሳኔ የሚጠበቅ ውሳኔ ነው፡፡

እንደ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ እንደ ትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ፣ እንደ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የመሳሰሉት አስፈላጊ መምሪያዎችም ከአዲሱ የቅርሳ ቅርስ መምሪያ ትምህርት ወስደው በባለሞያ በማስጠናት ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ በጀታቸውን በቅዱስ ሲኖዶስ ካላስፈቀዱ በስም ብቻ ወይም ከሀገረ ስብከት ወደ ሀገረ ስብከት እየተዘዋወሩ ሊሠራ የሚገባው በዚህ መልክ ነበር ብሎ በመለፈፍ ብቻ ተልእኳቸውን ሊፈጽሙ አይችሉም፤ ወይም በጥቅማ ጥቅም በመታለል ሌሎች ማኅበራት በአዘጋጁት ትምህርታዊ ጉባኤ ላይ እየተገኙ በማስተማር ብቻ ሓላፊነታቸውን በትክክል ሊወጡት አይችሉም፡፡ ሳይደራጁ ሌሎች መብታችንን ወሰዱብን ወይም በመብታችን ተጠቀሙበት ብሎ መንፈራገጥም ትርፉ መላላጥ ብቻ ይሆናል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያሳለፈው ጠቃሚ ውሳኔ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ በባንኮ ዲሮማ አካባቢ የሚገኘው የቤተ ክርስቲያናችን ክፍት ቦታ ዘመናዊ ሕንጻ ተገንብቶበት ገቢ እንዲያስገኝና ወርሐዊ ኪራይ ሳይከፍሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንጻዎች በነጻ የሚጠቀሙት አቅም ያላቸው ድርጅቶች ሁሉ ቢሮ ሠርተው በራሳቸው ቢሮ እንዲጠቀሙ፣ በብላሽ የያዙትም ሕንጻ ተከራይቶ ለቤተ ክርስቲያናችን የገቢ ምንጭ እንዲሆን የተላለፈውም ውሳኔ ይበል የሚባል ውሳኔ ነው፡፡

ወደፊትም መንግሥት የሠራተኛውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከሚያደርገው ጥረት ጎን በመቆም በመንበረ ፓትርያሪኩ ዙሪያ ባለው ክፍት ቦታ ቤተ ክርስቲያን የመኖሪያ ሕንጻ አሠርታ ተገቢውን ክፍያ እየከፈሉ በኅብረት እንዲኖሩ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ያቀረቡት አቤቱታ ወቅታዊ ስለሆነ ተቀባይነትን አግኝቶ ተግባራዊ እንዲሆንና እንደ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የመሳሰሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ የማምረቻ ተቋማትም የግንባታ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶላቸው በዘመናዊ መልክ ተደራጅተው ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያኒቱን ይበልጥ እንዲጠቅሙ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ይጠበቃል፡፡

ያም ሆነ ይህ የዘንድሮው ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ያሳለፋቸው ወቅታዊ ውሳኔዎች አብዛኞቹ ለቤተ ክርስቲያናችን ጠቀሜታ ያላቸውና ማእከላዊነትን ያልጠበቀ ብልሹ አሠራርን ሊያስወግዱ የሚችሉ በመሆናቸውና አምናም ሆነ ታችአምና፣ ከዚያ በፊትም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወሰኑት ጠቃሚ ውሳኔዎች ሁሉ ውኃ በልቷቸው የሚቀሩት አስፈጻሚ አካል በመታጣቱ ስለሆነ በየደረጃው የምንገኝ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ሁላችን ማለት ከመንበረ ፓትርያሪኩ ጀምሮ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ባለሥልጣናት ሠራተኞች፣ የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሠራተኞች፣ የየድርጅቱ የሥራ ሓላፊዎች እና ሠራተኞች፣ የወጣት መንፈሳውያት ማኅበራትና የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ምእመናንም ጭምር ለውሳኔው ተግባራዊነትና ከውሳኔው ውጭ ለሚፈጸሙ ተግባራት ተቃውሞ በነፍስ ወከፍ ልንረባረብና ቅዱስ ሲኖዶስ ሲባንን እኛም አብረን ልንባንን ይገባናል፤ መንግሥት የሕገ መንግሥት ተገዥ እንደሆነ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም የሕገ ቤተ ክርስቲያን ተገዥ መሆን ይገባታልና፡፡
/ዜና ቤተ ክርስቲያን፣ 56 ዓመት ቁጥር 120፣ ግንቦት 2003 ዓ.ም/

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)