June 8, 2011

በስምዐ ጽድቅ ኅትመት ላይ የተጣለው እገዳ ተነሣ

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።
  • “እገዳው በአጣሪ ኮሚቴው ሥራ ላይ እንቅፋት ሊፈጥር ይችል ይሆናል፡፡” (የመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት)
  • እነ አባ ሰረቀ ደብዳቤው ከመዝገብ ቤት እንዳይወጣ ለማሳገድ ሞክረዋል::
  • የዋና ሓላፊው ሕገ ወጥ እግድ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አስቆጥቷል፤ የጠቅ/ቤ/ክ ሓላፊዎችን አሳዝኗል
  • የአባ ሰረቀ እግድ በዋ/ሥ/አስኪያጁ መሻሩ ዋና ሓላፊው በሕገ ወጥ መግለጫቸው በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እወስዳቸዋለሁ ያሏቸው አስተዳደራዊ ርምጃዎች ከድብቅ ዓላማቸው የሚመነጩ ከመሆናቸው ውጪ መሠረተ እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው::
(ደጀ ሰላም፤ ጁን 8/2011)፦  በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በየ15 ቀኑ እና በየወሩ በሚያሳትማቸው የስምዐ ጽድቅ እና የሐመር መጽሔት ኅትመት ላይ በመምሪያው ዋና ሓላፊ በሕገ ወጥ መንገድ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሣቱን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡


የማኅበረ ቅዱሳንን የኅትመት ውጤቶች ለረጅም ዓመታት ሲያትም መቆየቱ ለተገለጸው ለሜጋ ማተሚያ ድርጅትና ለሌሎች አምስት ማተሚያ ቤቶች እንዲሁም ለብሮድካስት ባለሥልጣን ዛሬ የተላከው የእግድ መሻሪያ ደብዳቤ በዋና ሥራ አስኪያጁ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ፊርማ የወጣ ነው፡፡ በደብዳቤው ላይ እንደተመለከተው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ “በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሥር ስላለው ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የሥራ እንቅስቃሴ አጣርቶ የሚያቀርብ ብፁዓን አባቶች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት ንትርክ እና ጭቅጭቅ መፈጠሩ በማጣራቱ ሥራ ሂደት ላይ ዕንቅፋት ሊፈጠር ይችል ይሆናል፡፡”

የማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ የእገዳው መጣል ትክክል እንዳልሆነ የገለጹትን መሠረት ያደረገው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ደብዳቤ፣ አባ ሰረቀ “በመምሪያው በኩል በሊቃውንት እያስመረመረ እንዲያሰራጭ የታዘዘውን ሥራ ላይ አላዋለም” በሚል ከግንቦት 1 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ የማኅበሩ መጽሔት እና ጋዜጣ እንዳይታተም ለማተሚያ ድርጅቶች የጻፉት እገዳ መነሣቱን አስታውቋል፡፡

እግዱን የሚሽረው ደብዳቤ ዛሬ ሊወጣ የቻለው የማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የአባ ሰረቀ አካሄድ ከእርሳቸው አቅም በላይ መሆኑን በመግለጽ ግንቦት 29 ቀን 2003 ዓ.ም የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ/ጽ/ቤት ጉዳዩን በትኩረት ተመልክቶ መፍትሔ እንዲሰጥበት የጻፉት ደብዳቤ በማኔጅመንት ኮሚቴው ከታየ በኋላ ነው፡፡ በውሳኔው የተበሳጩት የማደራጃ መምሪያው ሓላፊ አባ ሰረቀ እና ምክትል ሓላፊው መምህር ዕንቁ ባሕርይ ተከሥተ ደብዳቤው የመዝገብ ቤቱን ሥርዐት አሟልቶ ወጪ እንዳይደረግ ከመዝገብ ቤቱ ሠራተኞች ጋራ ሲነታረኩ ታይተዋል፡፡

ሠራተኞቹ ደብዳቤውን እንዲያቆዩት ሲያከላክሉ የነበሩት የመምሪያው ሓላፊዎች አፈጻጸሙን ለመከታተል በሥፍራው ከነበሩት የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ሓላፊዎች ጋር ኃይለ ቃል መለዋወጣቸው ተሰምቷል፡፡ ንግግራቸውን የተከታተሉት በአካባቢው የነበሩ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ሠራተኞች እና መምሪያ ሓላፊዎች በአባ ሰረቀ ድርጊት ማዘናቸው ተመልክቷል፡፡ እነ አባ ሰረቀ በቃል የመዝገብ ቤቱ ሠራተኞች ደብዳቤውን ወጪ ከማድረግ ተቆጥበው እንዲያቆዩት እየተጨቃጨቁ በተመሳሳይ ጊዜ ጉዳዩ ወደ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዘንድ እንዲደርስ ሲጥሩ እንደነበር ተገልጧል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሰሞኑን ከአዲስ አበባ አድባራትና እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሒሳብ ሹሞች እና ገንዘብ ያዦች የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ ከሓላፊነታቸው ለማስነሣት ሲሰበሰብ በነበረ የአድማ ፊርማ ጉዳይ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ እንደመከረ በተገለጸው የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የነበሩ በመሆናቸው ለጊዜው የእነ አባ ሰረቀ ጥረት ላይሠምር እንደ ቻለ ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡ ጥረታቸው ያልሰመረላቸው እነ አባ ሰረቀ ብቻ ሳይሆኑ ቋሚ ሲኖዶሱ በስብሰባ ላይ በነበረበት ሁኔታ እዚያው ቆመው ተራ በመጠበቃቸው መከፋታቸውን በስልክ ሲናገሩ የተሰሙት ወ/ሮ እጅጋየሁ ጭምር ናቸው፡፡ ተደጋጋሚ ጥሪ በሞባይል ስልካቸው እያስተናገዱ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የታዩት ወይዘሮዋ ዛሬ በሁለት ምክንያት እዚያ እንደተገኙ ምንጮቹ ጠቁመዋል፤ አንድም - በሰዓቱ እነ አባ ሰረቀ ለነበረባቸው ጭንቀት ‹ፍጡነ ረድኤት› ለመሆን፤ ዳግመኛም ቅዳሜ ዕለት በደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ላይ አጠፌታ ለማሰጠት በቀጠለው ጥረት ተጎድተናል ለሚሉት ወገኖች አቤቱታ ለማቅረብ፡፡

የአባ ሰረቀ እገዳ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትንም ማስቆጣቱ የተጠቆመ ሲሆን ዛሬ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ደብዳቤ መሻሩ ደግሞ፣ “ዋና ሓላፊው በሕገ ወጥ መግለጫቸው በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እወስዳቸዋለሁ ያሏቸው አስተዳደራዊ ርምጃዎች ከድብቅ ዓላማቸው የሚመነጩ ከመሆናቸው ውጪ መሠረት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው፤” ብለዋል - ታዛቢዎች፡፡ እግዱ በማጣራቱ ሂደት ለማለፍ መያዣ መጨበጫ ያጡት ዋና ሓላፊው የአጣሪ ኮሚቴን ተግባር አስቀድመው በሚፈጥሩት ውዝግብ በመጥመድ ለማሰናከልና የመደራደሪያ አቅም ለመፍጠር የዘየዱት ሊሆን እንደሚችል የሚጠራጠሩ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው የዛሬው ውሳኔ አባ ሰረቀ፣ “በቅድመ ማጣራቱ ሂደት የተከናነቡት የመጀመሪያው የሕዝብ ግንኙነት ክስረት” ሊባል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና ማኅበረ ቅዱሳን የገጠመውን መሰናክል እንደምን እያስወገደ ራሱን ለቀጣይ አገልግሎት በሁለንተናዊ ስልት ማዘጋጀት እንደሚገባው ተጨማሪ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ እንደሆነም መክረዋል፡፡ 

ከተጀመረ 18 ዓመታትን ያስቆጠረው እና እገዳ የተጣለበት የ18 ዓመት ቁጥር 18 እትሙ በሌላ ማተሚያ ቤት ከታተመ በኋላ ከትናንት ጀምሮ በስርጭት ላይ እንደሚገኝ መግለጻችን ይታወሳል፡፡ 

/ቋሚ ሲኖዶስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ጉዳይ የደረሰበትን ውሳኔ እንደደረሰን እናቀርባለን/Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)