June 6, 2011

ሰበር ዜና - የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ኅትመት ታገደ

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።
  •  እግዱ አባ ሰረቀ ለሜጋ ማተሚያ ኢንተርፕራይዝ የጻፉትን ደብዳቤ እና የብሮድካስት ባለሥልጣን ለኢንተርፕራይዙ ሰጥቶታል የተባለውን የቃል ትእዛዝ መነሻ ማድረጉ ተነግሯል
(ደጀ ሰላም፤ ጁን 6/2011)፦ ከ1985 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በሕትመት ላይ የነበረው እና በማ/ቅዱሳን የሚታተመው ስምጸ ጽድቅ ጋዜጣ እንዳይታተም እገዳ እንደተጣለበት ምንጮቻችን አስታወቁ። የጋዜጣው አሳታሚ የሆነው የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት እና የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ጽ/ቤት አባላት ከመምሪያው ሊቀ ጳጳስ እና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ ተወያይተዋል፡፡


ውይይቱን የተከታተሉት የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች አባ ሰረቀ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ጉባኤ ላይ እርሳቸው የመምሪያው ዋና ሓላፊ ቢሆኑም ማኅበሩ ከእርሳቸው ጋራ መወያየት እንደማይሻ፣ መምሪያውን እንደማያከብር ይልቁንም እርሳቸውን እያለፈ ቤተ ክህነቱን ለሚጠይቅበት ጉዳይ ሁሉ የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት ተባባሪ መሆኑ “በዋና ሓላፊነታቸው ጣልቃ መግባት” መሆኑን አዘውትረው በመጥቀስ ማኅበሩን እንደሚከሱ እና ዋና ሥራ አስኪያጁን እንደሚወቅሱ፣ ይሁንና ማኅበሩ ከእርሳቸው ጋራ ለመወያት ፈቃደኛ ቢሆን “ሁሉም ነገር ቀርቶ ችግሩ እንደሚስተካከል” እንደሚናገሩ ተገልጧል፡፡

“የጋዜጣው ኅትመት አላግባብ ማገድ ቤተ ክርስቲያን በሕግ ያቋቋመችውን ማኅበር ያለሕግ ከመዝጋት አይተናነስም” ያሉት የማኅበሩ አመራሮች በበኩላቸው የመምሪያው ዋና ሓላፊ ሥራ ከጀመሩበት ወቅት አንሥቶ እስከ ስድስት ጊዜ ለፊት ለፊት ውይይት በደብዳቤ መጠየቃቸውን፣ ይሁንና ዋና ሐላፊው ፈቃደኛ ካለመሆናቸውም በላይ “ማኅበሩን ዐውቀዋለሁ፤ ገለጻ አያስፈልገኝም፤” በማለት የማኅበሩን የተለያዩ ጥሪዎች ከመናቅ ጀምሮ ከማኅበሩ ጋራ ለመሥራት እንደማይሹ የገለጹበትን ሁኔታ አስታወሰዋል፡፡ በቅርቡ ዋና ሐላፊው በብዙኀን መገናኛ ቀርበው በሰጡት መግለጫ ማኅበሩን መወንጀላቸውንና ይህም በአጣሪው ኮሚቴ ተግባር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ያስረዱት አመራሮቹ፣ አባ ሰረቀ የማኅበሩን የሚዲያ ውጤቶች ለመገምገም ያወረዱት መምሪያ ማኅበሩ የራሱን ኤዲቶሪያል ቦርድ አቋቁሞ እንዲሠራ በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተደነገገውን የሚተላለፍ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ይሁንና ጉዳዩን በመርሕ ሳይሆን በአፈጻጸም ደረጃ ተቀብሎና ተግባብቶ ለመሥራት በሚል ከሊቃውንት ጉባኤ ለተመረጡት ሦስት የኤዲቶሪያል ልኡካን በየወሩ ለእያንዳንዳቸው ብር 1000 አበል እየከፈለ ለመሥራት በሚችልባቸው አግባቦች ላይ ምክረ ሓሳብ አርቅቆ የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ባሉበት ከማደራጃ መምሪያው ተወካዮች ጋራ ስምምነት የተደረሰበት ውይይት አካሂደው እንደነበር፣ በሂደት ግን መምሪያው ጉዳዩን ባለመከታተሉ መስተጓጎሉን አብራርተዋል፡፡ 
በቅርቡ የማዳራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ለሃገር ውስጥ እና ለውጭ ብዙኀን መገናኛ የሰጡት መግለጫ ሕገ ወጥ መሆኑን ያስታወቁት የማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የአባ ሰረቀ አካሄድ ከእርሳቸው አቅም በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመምሪያው እና በማኅበሩ መካከል ያለውን ችግር እንዲያጣራ ያቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን በጀመረበት ወቅት የተላለፈው የአባ ሰረቀ እግድ ዋና ሓላፊው ባልተሰጣቸው ሥልጣን የፈጸሙት እና አሠራሩን ያልተከተለ ተግባር ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው ለእግዱ መሻሪያ ተጽፎ የጋዜጣው ኅትመት እንዲቀጥል የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን ጠይቀዋል፡፡ “ከግራ ከቀኝ እሳት እየነደደብኝ ነው” በማለት በሁኔታው በእጅጉ መታወካቸውን የተናገሩት ብፁዕነታቸው በመምሪያው ሊቀ ጳጳስ የተገለጸውን በመጥቀስ ለሜጋ ማተሚያ ኢንተርፕራይዝ እንደሚጽፉ ይጠበቃል፡፡

“ውይይት በሆነ ጉዳይ ላይ ለመግባባት ወይም መረጃ ለመለዋወጥ ነው፤ አሁን አባ ሰረቀ ይሁነኝ ብለው በዓላማ የማኅበሩን አገልግሎት ለማደናቀፍ በግላጭ እየሠሩ ባሉበት ሁኔታ ግን ከእርሳቸው ጋራ የቀጥታ ውይይት ማካሄድ የማይሞከር ነው፤” ያሉት አመራሮቹ ከዚህ በኋላ በጉዳዩ ላይ ለውይይት መቀመጥ የሚቻለው ከአጣሪው ኮሚቴ ጋራ እና ኮሚቴው በሚያስቀምጣቸው አግባቦች ብቻ ነው ማለታቸው ተመልክቷል፡፡ የጋዜጣውን እግድ በተመለከተም ከጥንቱም በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት እንጂ አባ ሰረቀ ለማተሚያ ቤቱ ስለ ፈቀዱ የሚያሳትሙት ስላገዱ ደግሞ የሚያቆሙት ከቶም ሊሆን እንደማይችል ከሜጋ ሐላፊዎች ጋራ ባደረጉት ውይይት አስረግጠዋል - “ቀድሞም አትሙላቸው ብለው እንዳልጻፉ ሁሉ አሁንም መከልከል አይችሉም፡፡”

አባ ሰረቀ ለማተሚያ ቤቱ የጻፉት እግድ ከተቋሙ የውጭ ግንኙነት አሠራር አኳያ ሲታይ ቢያንስ ከበላያቸው ያሉትን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሁለት የመዋቅር እርከኖች(የዋና ሥራ አስኪያጁን እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትን/የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን) አልፎ የሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዜናው ምንጮች እንደጠቆሙት ማኅበረ ቅዱሳን በየጊዜው የሚያድሰውን የሚዲያ ውጤቶቹን ፈቃድ ያገኘበት ኦሪጅናል ፈቃዱ የሚገኘው በአባ ሰረቀ እጅ ነው፡፡ አሁን ባለው የብሮድካስት ባለሥልጣን አሠራር ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው አብያተ እምነት እና የፖሊቲካ ፓርቲዎች የመሳሰሉት ተቋማት ዓላማቸውን ለሚያስፈጽሙባቸው የኅትመት ውጤቶች ፈቃድ ዓመታዊ እድሳት እንደማያስፈልጋቸው በ2000 ዓ.ም የወጣው የመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነጻነት ዐዋጅ አንቀጽ 9 ንኡስ አንቀጽ 3 ላይ እንደሚደነግግ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ አኳያ ኅትመቱ የታገደው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዚህ ዐዋጅ መሠረት በቀድሞው አሠራሩ ይቀጥል እንደሆን አልያም እንደሌሎቹ የግል ጋዜጦች በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተመዝግቦ ግብር እየከፈለና ዓመታዊ እድሳት እየፈጸመ ይሠራ እንደሆን ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

አንዳንድ የጉዳዩ ተከታታዮች አባ ሰረቀ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በብዙኀን መገናኛ ቀርበው የሰጡትና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የበላይ ሓላፊዎች “ሕገ ወጥ ነው” የተባለው መግለጫ እንደ ሬዲዮ ፋና እና እንደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ  ባሉት የመንግሥት ብዙኀን መገናኛዎች ተከታታይ ሽፋን ያገኘበት አኳኋን፣ “በጉዳዩ የፓትርያርኩ ጽ/ቤት እና አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግፊት/ይሁንታ እንዳለበት ያሳያል” ብለዋል፡፡ የጉዳዩ ተከታታዮች፣ መግለጫው በተጠቀሱት ሚዲያዎች እንዲሰራጭ አባ ሰረቀ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት ድረስ በመሄድና ግለሰቦችን በስም ጠርተው በመወንጀል የተጉበትን፣ ይህን ተከትሎ ከኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በኩል በተሰጠ ትእዛዝ የኤዲቶሪያል ውሳኔ ተደርጎ በፋና ሬዲዮ የተላለፈው ዜና በኢ.ቴቬ የተደገመበትን ሁኔታ እንደሚያውቁ ይናገራሉ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ አባ ሰረቀ በሕገ ወጥ መግለጫቸው “ማኅበሩ በ19 ዓመት ውስጥ አንድም ጊዜ ኦዲት ተደርጎ እንደማያውቅ” በድፍረት በተናገሩበትና በሌሎችም ስም አጥፊ ጉዳዮች ላይ ክስ ለመመሥረት መወሰኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይሁንና አስተያየት ሰጪዎች ማኅበሩ በአገልግሎቱ አሁን በግልጽ እየገጠመው ካለው መሰናክል እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ካንዣበበው አደጋ አኳያ ተመጣጣኝ፣ ሰላማዊ እና በጭብጥ የተመዘነ የአገልግሎት ስልት ለውጥ ለማድረግ በጠቅላላ ጉባኤው የወሰነውን ቀልጥፎ ወደሚተገብርበት አመራር እንዲገባ ይጠብቃሉ፡፡

ስምዐ ጽድቅ በትርጉሙ የእውነት ምስክር ማለት ሲሆን ጋዜጣ በጥር ወር 1985 ዓ.ም የተቋቋመ፣ በመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ጋዜጣ ነው፡፡ ለዓመታት ሳያቋርጥ የቆየው ኅትመቱ በአባ ሰረቀ እንዲታገድ የተደረገው የ18ዓመት ቁጥር 18 እትም ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ለኅትመት ከገባ በኋላ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የአሁኑ የጋዜጣው እትም አባ ሰረቀ በሕገ ወጥ መግለጫቸው በሰነዘሯቸው ውንጀላዎች ላይ የመምሪያውን ሊቀ ጳጳስ አስተያየት እና ሌሎች ብፁዓን አባቶች ስለ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔ የሰጧቸውን ቃለ ምልልሶች የያዘ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ለመጻፍ እንደሚቸገሩ የገለጹትን የእግድ መሻሪያ የሚገልጽ ደብዳቤ ቢጽፉም አባ ሰረቀ ጉዳዩን እንደተለመደው ወደ ፓትርያሪኩ በቀጥታ በመወሰድ ዋጋ ለማሳጣት እንደሚሞክሩ ተገምቷል፡፡ አሁን በአባ ሰረቀ የተጀመረው የጋዜጣው ኅትመት እግድ ማኅበሩ በሚያሳትማቸው የሐመር መጽሔትና ሌሎች ሥራዎች ላይ ተፈጻሚ ከመሆን አልፎ የማኅበሩ ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ እስከማገድ ደርሶ ማኅበሩ የአባላቱን ሞያ እና ገንዘብ ከበጎ አድራጊዎች እገዛ ጋራ በማቀናጀት የገባበትን የሁለት ዐሥርት ዓመታት አገልግሎት እንዳያስተጓጉለው ተሰግቷል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)