June 2, 2011

ስለ እግዚአብሔር የሚገዳቸው ብፁዕ አባት

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።


(ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ፤ ተባባሪ ፕሮፌሰር):- ለተመረጡት ሞት እረፍት መሆኑን ባምንምና ብፁዕ አባታቻን አቡነ በርናባስም የእድሜ ባለጸጋ መሆናቸውን ባውቅም እረፍታቸውን ስሰማ ማዘኔ አልቀረም። በተለይ በዚህ ወቅት እንደዚህ አይነት ብፁዕ አባት አስፈላጊነቱ ግልጽ ስለሆነ። ብፁዕነታቸውን በአጭሩ ለማሰብ ነው አነሳሴ። 

ብፁዕ አባታችንን በአካል የማውቃቸው ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት ከሁለት ዓመት በላይ በቆየሁባት የባህር ዳር ከተማ ነው።  በወቅቱ በከተማው በሚገኘው ሽምብጥ ሚካኤል ከነበረው የሰራተኞች ጉባኤ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ለባህር ዳር ፓሊ ቴክኒክና ለባህር ዳር ፔዳ ተማሪዎች መሐል ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ወርኃዊ ጉባኤ ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት ጋር በተያያዘ አገኛቸው ነበር። በወቅቱ የማኅበረ ቅዱሳን አባል መሆኔን መግለጽ ሳያስፈልገኝ ብፁዕነታቸው ስለ ማኅበሩ እንቅስቃሴ የነበራቸውን በጎ አመለካከት ግልጽ ነበር። ይህ የብፁዕነታቸው  አባታዊና መንፈሳዊ እይታ በወቅቱ የነበረውን ማኅበሩን በፓለቲካ የመጠርጠር  የአካባቢው የመንግሥት አካል ስጋት በሚያውቁት መጠን ለማስረዳት አስችሏቸው እንደነበር አውቃለሁ።
መንግሥት የራሱን የቤት ሥራ ሰርቶ ማኅበሩ በዓላማም በተግባርም ከፓላቲካ ነጻ መሆኑን አሳምሮ ካወቀ ከአስራ አምስት ዓመታት በኃላ እነሆ በአሁኑ ወቅት የማኅበሩ ይከሰስ ይወቀስና ይፍረስ ጥሪና ጥረት ከቤተ ክህነት እምብርት መሆኑን ለሚያይ ሰው የብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ አይነት መንፈስ እየጠፋ መሄዱ አያስጨንቀውም አይባልም።

የዛሬ ሦስት አመት በወቅቱ እኖርበት ከነበረው ስዊድን ለእረፍት ወደ አገር ቤት በሄድኩበት ወቅት የሆነ ቀን እኔ ወደ መቀሌ ለመብረር ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስም ወደ ባህር ዳር ለመብረር ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አገኝህዋቸው። በአጋጣሚው እየቦረቅኩ ለማናገር ብመኝም የበረራ መስመራችን የተለያያ ሰለሆነ በስስት አይቼና ተሳልሜ ተለየህዋቸው። ለካስ የመቀሌና የባህርዳር መንገደኞች መቆያ ክፍል አንድ ኖራል ከደቂቃዎች በኃላ ብፁዕነታቸውን መልሼ አገኘህዋቸው።  እንደገና በማየቴ ተደስቼ የበረራ ሰዓቴ እስኪደርስ ወደተቀመጡበት ሄጄ ባህር ዳር በነበርኩበት ጊዜ የነበረንን ትውውቅ አስታውሼ መጫወት ጀመርን። ከጨዋታችን አንዲት ዘለላ ……
ብፁዕ አባታችን፡ “ስዊድኖች ሰላም ናቸው ይባላል። እስርቤትም፤ፓሊስም የለም ይባላል።”
እኔ፡ “እስርቤትም ፓሊስም ያለ ቢሆንም…  ልክ ነው አገሩ ሰላማዊ አገር ነው። ሰዎቹም ሰላም ናቸው”
ትንሽ ቆየት ብለው
“ለመሆኑ እምነታቸው እንዴት ነው?” ብለው ጠየቁኝ።
“ከመቶው አርባ የሚሆነው ስዊዲናዊ እግዚአብሔር የለም ብለው ነው የሚያምነው” ስላቸው
ደነገጡ ….
“ሥሉስ ቅዱስ… አዪ ..ታዲያ ምኑን ሰላም ሆኑት… እግዚአብሔር የለም እያሉ የሚገኝ ሰላም ሰላም አይደለም ልጄ”…. አባባላቸው ዛሬ ድረስ ጆሮዬ ላይ ያቃጭላል። የዛን ቀን ስለእግዚአብሔር የሚገዳቸው ብፁዕ አባት አቡነ በርናባስን በማግኘቴ ደስ እያለኝ ወደ አውሮፕላኔ ገባሁ። ከብፁዕ አባታችን አባባል የተረዳሁት ስለእግዚአብሔር፤ ስለህዝቡና ስለቤቱ ሊገደን ይገባል የሚለውን ነው። አዎ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያለው ኑፋቄ-ጠገብ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ሊገደን ይገባል። ዛሬ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የመስጠትና የማስፈጸም አቅሙ ፈተና ላይ መውደቅ ሊገደን ይገባል። ዛሬ እጅጋየሁ-አዊ የቤተ ክህነት ዙሪያ ማን አለብኝነት ሊገደን ይገባል። ዛሬ የሐዋሳ ምእመናን መከራ ሊገደን ይገባል።
የብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን ።


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)