June 1, 2011

ትዕቢት እና ዕብሪት (arrogance) የመላባቸው የአባ ሰረቀ መግለጫዎች

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።

(ደጀ ሰላም፤ ጁን 1/2011)፦
 • አባ ሰረቀ ትናንት የሰጡትን መግለጫ የማ/መምሪያው ሊቀ ጳጳስ ያውቁት እንደ ሆነ ሲጠየቁ ‹‹አይመለከታቸውም፤ ውሳኔዎችን የማስፈጸም አስተዳደራዊ ሥራ የእኛ ነው፤ እርሳቸው ለክብር ብቻ የተቀመጡ ናቸው›› ብለዋል፤ እርሳቸው ‹‹ወልደ ሳሙኤል›› የተባሉበትን የደብረ ዐባይ ቅዳሴ ሞያ የት እንዳሳዩት ባይታወቅም የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የተዘጋ ቤተ ክርስቲያን ከማስከፈት ጀምሮ ሊቀ ማእምራን የተሰኙበት መዓርገ ዲቁና እና መዓርገ ቅስና ለእርሳቸው ‹‹ሥርዐቱን ያልጠበቀ›› ከመሆኑም በላይ ‹‹አሐዱ አብ ብለው የማይቀድሱበት፣ ነአኵቶ ብለው የማያመሰግኑበት ያለትምህርት ከሚገኘው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ›› ተለይቶ እንደማይታይ ተናግረዋል፡፡
 • ያለታክስ መለያ ቁጥር ንግዳዊ ተቋም ከፍቶ ግዥና ሽያጭ ማካሄድ በማይቻልበት ሥርዐት፣ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የውስጥ እና የውጭ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን እየተሠራ ለማደራጃ መምሪያው ሪፖርት በሚቀርብበት ሁኔታ የማኅበሩ የገቢ ማስገኛ ማእከላት ለ19 ዓመታት ግብር እና ቀረጥ ሳይከፍሉ፣ በኦዲተር ፈጽሞ ሳይመረመሩ ቆይቷል ብለዋል፡፡
 • በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ማኅበሩ ነጻ አገልግሎት በሚሰጡ አባላቱ በሚያቋቋመው ኤዲቶሪያል ቦርድ የኅትመት ውጤቶቹን እንደሚያስገመግምና ከእርሱ በላይ የሚሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ እንደሚመራ ተመልክቷል፡፡ አባ ሰረቀ ግን ከግንቦት 1 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ‹‹ከመመሪያው እና ከሊቃውንት ጉባኤ መርጫቸዋለሁ›› ለሚሏቸው ሦስት፣ ሦስት ሰዎች ማኅበሩ በየወሩ ብር 1000 አበል እየከፈለ ‹‹የኅትመት ውጤቶቹን እና የሚዲያ ስርጭቱን›› እንዲያስገመግም  የሚያስገድድ ደብዳቤ ጽፈዋል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ካጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ አልቀው መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም ፓትርያሪኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳት እና የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮች በተገኙበት ጉባኤ ተላልፈዋል ከተባሉትና እርሳቸው ‹‹ስድስቱ ቃላተ ወንጌል›› በሚል ቁልምጫ ከሚጠሯቸው ስድስቱ ውሳኔዎች አንዱ የሆነውንና ከዚሁ ጋራ የተያያዘውን በትላንቱም መግለጫቸው አካትተዋል - ‹‹የሕትመት ውጤቶቻቸውና የሚዲያ ስርጭቶች በሙሉ በታዘዘው መሠረት በተመደቡት ሊቃውንት እንዲሰራጭ እንዲያደርጉ››
 • መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም የተካሄደው ስብሰባ አጠራር ድንገቴና አጀንዳውም የማደራጃ መምሪያውን ድክመት እንደሚያሳይ ከመገለጹም ባሻገር ውሳኔዎቹም ቅዱስ ሲኖዶስ ለማኅበሩ ያጸደቀውን መተዳደሪያ ደንብ የሚፃረር በመሆኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ማኅበሩ ተቃውመውታል ተብሏል፡፡ አባ ሰረቀ ግን ውሳኔውን መርሕ በማድረግ ማተሚያ ቤቶች የማኅበሩን የኅትመት ሥራዎች እንዳያትሙ የሚያሳስብ ደብዳቤ ሰሞኑን ማሰራጨታቸው ተሰምቷል፡፡
 • የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በማደራጃ መምሪያው እና በማኅበሩ መካከል ያለውን ችግር የሚያጣራ ሰባት አባላት(ከሊቃነ ጳጳሳት - ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፤ ከሊቃውንት ጉባኤ - መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣ ሊቀ ሥዩማን ራደ አስረስ፣ መልአከ ሰላም ዓምደ ብርሃን፤ ከሕግ አገልግሎት - አቶ ይሥሐቅ፤ ከውጭ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል) ያሉበት አጣሪ ኮሚቴ ባቋቋመበት ሁኔታ የትላንቱን መግለጫ የመስጠቱን አስፈላጊነትንም ተጠይቀዋል - አባ ሰረቀ፡፡ ‹‹አሁን የምንናገረውን ለአጣሪ ኮሚቴውም እንገልጻለን፤ የዛሬውን መግለጫ የምንሰጠው ግን ማኅበረ ቅዱሳን ከሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዲቆጠብ ነው፤›› በማለት መመለሳቸው ተዘግቧል፡፡
 • አባ ሰረቀ ማኅበሩ አለሥልጣኑና አለቦታው ገብቶ ‹‹ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ›› ይፈጽማቸዋል ከሚሏቸው ተግባራት መካከል የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን የመከላከል እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡ ለአባ ሰረቀ ይህ ሕጋዊና ተገቢነት ያለው የራስን ሃይማኖታዊ ማንነት የመከላከል እንቅስቃሴ፣ ‹‹በአገልጋይና በተገልጋይ መካከል ለዘመናት የቆየውን ጤናማ ግንኙነት የሚያሻክር የስም ማጥፋት ዘመቻ›› ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ይሁን ይህን ግልጽ እና ወቅታዊ አደጋ መከላከል ማእከል በማድረግ ጥምረት የፈጠሩ ወገኖች በቆሙባቸው መድረኮች የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን የትመጣ እና መገለጫ ባሕርይ ከማስረዳት በቀር በስም ለይተው የሚያወግዙት አካል ስለ መኖሩ አባ ሰረቀ ያቀረቡት ማረጋገጫ የለም፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ከተጣሉበት ግዴታዎች አንዱ የሆነውን ይህን ተግባር መፈጸሙ በራሱ ‹‹በስም ማጥፋት ወንጀል ስለሚያስጠይቅ›› በትላንቱ መግለጫቸው ‹‹ዘመቻው እንዲቆም›› አዝዘዋል፡፡
 • የተሐድሶ ኑፋቄ በመኖሩ ላይ ያላቸውን እምነት የተጠየቁት አባ ሰረቀ ‹‹ጥንቱንም ቢፀ ሐሳውያን፣ ሐራ ጥቃ. . . የምንላቸው ነበሩ፤ አሁንም አሉ›› በማለት ካስረዱ በኋላ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ተሐድሶ አለ በማለቱ ስሕተት ነው ማለቴ አይደለም፤ ለእኛ ይሄ ነው ብሎ ያመጣው መረጃ የለም፤ ስለምን አጥር ዘሎ እየሄደ በየአዳራሹ ሰዎችን እየሰበሰበ በአደባባይ ይገልጻል?››
 • ከአርባ ሺሕ በላይ ማኅበራት እንዳሉ እየተነገረ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የተለየ ትኩረት ስለተደረገበት ሁኔታ የተጠየቁት አባ ሰረቀ የማይታወቁ ሌሎች በርካታ ማኅበራት መኖራቸውን፣ ጉዳዩ ሌሎቹንም ማኅበራት እንደሚመለከትና በተለይም በመዝሙራት በኩል በቤተ ክርስቲያን ‹ሳንሱር› ሳይደረጉ መውጣት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ ዋና ሐላፊው ይህን ይበሉ እንጂ ለያሬዳዊ ዜማ መጠበቅ ሰንበት ት/ቤቶችን እና ማኅበራትን በማገዝ እና በመከታተል ረገድ በተጨባጭ ያደረጉት የሚጠቀስ እንቅስቃሴ የለም፡፡ እንዲያውም በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ40,000 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች በራሳቸው አቅም የተደራጁባቸውን ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች የታቀፉባቸው ጥቂት ሺሕዎች በመሆናቸው በ29ው የመንበረ ፓትርያሪኩ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና በቅርቡም ማኅበረ ቅዱሳንን ለመወንጀል በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በሁለቱ ኮሌጆች በጠሯቸው ስብሰባዎች ላይ ተግተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯቸዋል፡፡

አባ ሰረቀ ስለ ደጀ ሰላም
 • አባ ሰረቀ ስለ ደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ ማንነት እና የጡመራዎቹ ይዘትም ተጠይቀዋል፤ ጠያቂውም በምን ባርኔጣ በቦታው ላይ እንደተገኘ የሚያጠያይቀው ዲያቆን ትዝታው ሳሙኤል ነው፤ መቼም በጋዜጠኛነት እንዳልሆነ ለብዙዎች ግልጽ ነው፡፡ በትላንቱ ዘገባችን እንዳመለከትነው ሰሞኑን አባ ሰረቀ በቅድመ ቃለ ምልልስ(preinterview) ዝግጅታቸው በቢሯቸው አብረዋቸው ከመከሯቸው ግለሰቦች ትዝታው አንዱ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ምናልባትም የትላንቱ የአባ ሰረቀ ሕገ ወጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ዋነኛ መዳረሻ ትዝታው ሳሙኤል፣ በጋሻው ደሳለኝ፣ ያሬድ አደመ እና በሪሁን ከቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሳያገኙ በቤተ ክርስቲያን ስም የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት የማይወክል ፕሮግራም ስለሚያስተላልፉበት ‹‹ታኦሎጎስ›› የተሰኘ የቴሌቪዥን ዝግጅታቸው ግብአት እንዲሆን የታቀደ ሳይሆን እንደማይቀር እየተነገረ ነው፡፡
 • ከትዝታው ሁለት ፍረ አልባ ጥያቄዎች መካከል አስመልክቶ የደጀ ሰላምን ማንነት አስመልክቶ ላነሣው ‹ጥያቄ› ይሁን ክስ አባ ሰረቀ ሲመልሱ፡- ‹‹የደጀ ሰላም ድረ ገጽ ዋና ዓላማ ቤተ ክርስቲያንንና አገርን መበታተን ነው፤ ስላልቻሉ እንጂ አገሪቱን እንደ ሊቢያ ሊያደርጓት ያስባሉ፤. . .ማዘጋጀት ይቻላል ግን የሚስተካከል ከሆነ በሚል በትዕግሥት እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

አባ ሰረቀ ስለ ስማቸው - ሰረቀ ወይስ ሠረቀ?
 • ከሁለት ሰዓት ተኩል በላይ ከዘለቀው ሕገ ወጡ ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ ከጋዜጠኞችና ከመምሪያው ባልደረቦች ጋራ ለጸሎት የቆሙት አባ ሰረቀ ‹‹ስሜ የግእዝ ስም ነው፤ ስሜን በትክክል ጽፋችሁ አሳዩኝ?›› ሲሉ ለጋዜጠኞቹ ድንገቴ የሆነ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ በጥያቄአቸው ግር የተሰኙት ጋዜጠኞችም እርስ በርሳቸው ይተያያሉ፡፡ አንዱ የሌላውን በማየት በእሳቱ/ሰዉ ‹ሰ› በጉልሕ የጻፉትን (‹ሰረቀ›) ያሳዩዋቸዋል - ዋና ሐላፊውም ‹‹ኤክስ›› ሲሉ ጋዜጠኞቹ በድንገቴ ፈተናው መውደቃቸውን ይነግሯቸዋል፤ ወዲያው ከመምሪያው ባልደረቦች መካከል ‹ሰረቀ› ሳይሆን ‹ሠረቀ› ተብሎ በንጉሡ ‹ሠ› እንደሚጻፍ ያስረዳል፡፡
 • ‹ሠረቀ› ማለፊያ ነው፤ ‹ሰረቀ›ስ ምንድን ነው? ሲጠብቅ እና ሲላላ? የሆሄያቱ አገባብ ልዩነት ያልተረዳት አንዲቷ ጋዜጠኛ ለጓደኛዋ የጠየቀችው ነበር፡፡

 • ትላንት ከቀትር በፊት የአባ ሰረቀን ጋዜጣዊ መግለጫ ያስተናገደው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ሕንፃ በሌላው የስብከተ ወንጌል አዳራሹ ደግሞ ጌታቸው ዶኒ አላግባብ ከተሰጠው የሥራ አስኪያጅነት ሥልጣን በቅዱስ ሲኖዶስ መወገዱን ለመቃወም ነው በሚል የመጡት ቡድኖች ከአቡነ ጳውሎስ እና ከአራት ሊቃነ ጳጳሳት(ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ) ጋራ ያካሄዱትን ዛቻ እና ኀይለ ቃል የተመላበት ስብሰባ እያስተናገደ ነበር፡፡
 • በሐዋሳው ውዝግብ በድብደባ ወንጀል በተመሠረተባቸው ክስ ፍርዳቸውን የሚጠባበቁትና የ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› ማኅበር አመራር አባላት በሆኑ ግለሰቦች ተቀስቅሰው የመጡት እኒህ ቡድኖች ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ሊያነጋግሯቸው የመጡትን ብፁዓን አባቶች፡- ‹‹እናንተ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊና ጉዳይ አስፈጻሚ ጳጳሳት ናችሁ፤ ተሐድሶም ጴንጤም የሚባል የለም፤ ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው ነው፤ አቡነ ናትናኤል የማኅበረ ቅዱሳን-ደጀ ሰላም ሪፖርተር ናቸው፤ የሚገባ መሥዋዕትነት ባይሆንም አቡነ ገብርኤል ወደ ሐዋሳ የሚመጣ ከሆነ እንገድለዋለን፤›› የሚሉ በገዛ ጭብጨባቸው የታጀቡ የዛቻ እና የዘለፋ ንግግሮች ሲያሰሙ መዋላቸው ተገልጧል፡፡
 • በሁኔታው ያዘኑት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ‹‹ቅዱስ አባታችን፣ እዚህ የመጣሁት ልሰደብ አይደለም›› በሚል ወጥተው ሲሄዱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልም ተከትለዋቸዋል፤ ይሁንና ሁለቱም አባቶች በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ልመና ከበር ተመልሰው እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ ወዲያውም ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ‹‹የት ነው የተማራችሁት? ማን ነው ስድብ ያስተማራችሁ? እናንተንኮ አናውቃችሁም›› በሚል ገሥጸዋቸዋል፡፡
 • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ከጎናቸው አስቀምጠው ሲያሰድቡ የዋሉት ፓትርያሪኩም ‹‹እንደዚህ ነው የመከርኳችሁ? እንዴት እንዲህ ባለ ኀይለ ቃል ትናገራላችሁ?›› ማለታቸው ነገሩ አስቀድሞ በእርሳቸውና በጌታቸው ዶኒ መቀናጆ የተፈጠረ እንዳስመሰለው ውይይቱን የተከታተሉ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡ ተቃዋሚ ተብዬዎቹ ‹‹አባቶቼ ከወሰኑት የተለየ ውሳኔ አትጠብቁ፤ የሚኖር ከሆነ ወደፊት እንግራችኋለን›› በሚለውና በእጅጉ እንደተበሳጩበት በተገለጸው የአቡነ ጳውሎስ ንግግር ቢሰናበቱም ፓትርያሪኩ ‹‹መምጣት አልነበረባችሁም›› ማለታቸውን ግን ታዛቢዎቹ ‹‹የማይጥም ቀልድ››   ብለውታል፡፡
 • የተቃውሞ መቀናጆው የሐዋሳ ምእመናን ግንቦት 9 ቀን በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተገኝተው ብዙዎችን ያሳመነውን የቪሲዲ ማስረጃቸውንና መግለጫቸውን በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፊት በማቅረብ ለአቡነ ጳውሎስ የመጨረሻ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት ፓትርያሪኩ የተሰማቸውን ብስጭትና እርሱን ተከትሎ በጌታቸው ዶኒ መወገድ ጠንካራ አቋም የያዙትን አባቶች በመዝለፍ ለመበቀል ያለመ እንደሆነ ተገምቷል፡፡
 • በምእመናኑ አስተባባሪዎች ላይ ክስ የመሠረተው ጌታቸው ዶኒ ‹‹መነሣቴ ካልቀረ›› በሚል በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ላይ የስም ማጥፋት የሚሰነዝር ጽሑፍ በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ላይ ለማውጣት ተዘጋጅቶ እንደነበር ለደጀ ሰላም የደረሰውና ከወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋራ የተነጋገረበት የድምፅ ማስረጃ ይጠቁማል፡፡
 • ብፁዕ አቡነ ገብርኤል መልአከ ብርሃን ይትባረክ ታጠቅን የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ መምረጣቸው የተመለከተ ሲሆን እኚህ አባት ከዚህ ቀደም በአርሲ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በሰላሌ-ፍቼ፣ በደቡብ ኦሞ-ጂንካ እና በደቡብ ወሎ-ደሴ አህጉረ ስብከት በሥራ አስኪያጅነት የሠሩ ሲሆን በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ምክትል ሐላፊ ሆነው መቆየታቸው ታውቋል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)