May 22, 2011

(ሰበር ዜና) - ጌታቸው ዶኒ ከሥራ አስኪያጅነቱ እንዲባረር ብዙኀኑ የሲኖዱሱ አባላት የደረሱበት ስምምነት በፓትርያሪኩ ተቃውሞ ገጠመው፤ የቅ/ሲኖዶስ 5ኛ ቀን ውሎ

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ
  • የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪም ከሐላፊነታቸው ይነሣሉ
  • ፓትርያሪኩ እና አቡነ ጎርጎርዮስ በውሳኔው ባለመስማማት ጌታቸው ዶኒ ‹‹መናፍቅ›› መባሉን ተቃውመዋል
  • ‹‹የሲኖዶሱ አካሄድ ውጤት የሌለው ውኃ ወቀጣ ሆኗል፤ ከግለሰብ ይልቅ ለእግዚአብሔር እና ለቤተ ክርስቲያኑ መወገን አይሻልም ወይ;››(ብፁዕ አቡነ በርናባስ)
  • ‹‹እንዴት በተሐድሶ/ኑፋቄ መኖርን በተመለከተ ድርድር ውስጥ ይገባል;››(ብፁዕ አቡነ ኤልያስ)
  • የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በመላ ወይም በከፊል ወደ ሐዋሳ ወርደው፣ ጉባኤ ሠርተው ያዘነውን ምእመን ያጽናናሉ

(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 22/2011)፦ ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬ ግንቦት 14፣ 2003 ዓ.ም አምስተኛ ቀን የዕለተ ሰንበት ውሎው በሲዳሞ ሀገረ ስብከትን የተከሠተውን ችግር አስመልክቶ በተያዘው አጀንዳ ዙሪያ የጋለ ክርክር የተሞላበትን ውይይት በማካሄድ ‹‹ሊቀ ካህናት›› ጌታቸው ዶኒ ያለአግባብ ከተሰጠው የሥራ አስኪያጅነት ሥልጣኑ እንዲባረር ወስኗል፡፡ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ‹‹በውሳኔው አላምንበትም›› ብለዋል፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ አቋም በልዩነት ተይዞ ጌታቸው ዶኒ ከሐላፊነቱ እንዲነሣ ምልአተ ጉባኤው ከቀትር በፊት የደረሰበትን ስምምነት አቡነ ጳውሎስ ከቀትር በኋላ በማፍረስ በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ተዘጋጅቶ በቀረበው ቃለ ጉባኤ ላይ ‹‹ስለማላምንበት አልፈርምም፤›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ በዚህ ሳቢያ ጉባኤው ወደ ቀጣዩ የሰንበት ት/ቤቶች እና የማኅበረ ቅዱሳን ግንኙነት አጀንዳ ከመሻገር ተገትቶ ከፓትርያሪኩ እና ሰልፋቸውን ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ካደረጉት አቡነ ጎርጎርዮስ ጋራ የጋለ ክርክር ሲያካሂድ አምሽቶ ማምሻውን ያለውጤት ተነሥቷል፡፡

የጉባኤው ምንጮች እንደተናገሩት የሐዋሳ ችግር አጣሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በጌታቸው ዶኒ ከሐላፊነት መባረር በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ተስማምተው ነበር፡፡ ከቀትር በኋላ ግን ጌታቸው ዶኒን በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ‹‹ሊቀ ካህናት›› በሚል ማዕርገ ቅስና የሰጧቸው ብፁዕ አቡነ ገብርኤል መሆናቸውን በማስታወስ ‹‹ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ መናፍቅ እንደሆነ በቀረበው ማስረጃ አላምንበትም›› በሚል ልዩነታቸውን አጠናክረው የቀረቡትን አቡነ ጳውሎስን በመደገፍ የአቋም ሽግሽግ አድርገዋል ተብሏል፡፡ በመንፈሳዊ ትምህርት እና ሹመት ካፈራናቸው መካከል ጥቂቶች ያልተለወጡ እንደሌሉ ሁሉ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒም በወቅቱ ደኅና እንደነበሩና ዛሬ የተለወጡ መሆኑን ያስረዱት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ በበኩላቸው በጌታቸው ዶኒ የሃይማኖት ሕጸጽ እና ለሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት የማይበቁ በመሆናቸው በመነሣታቸው እንደሚያምኑበት አስረድተዋል፡፡ የውይይቱን ሂደት ‹‹ውኃ ወቀጣ ሆኗል›› በሚል የጠዋቱ የምልአተ ጉባኤ በመከለሱ ማዘናቸውን የተናገሩት የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ ‹‹ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር፣ ከግለሰብ ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን መቆምና መወገን አይበልጥም ወይ;›› ብለዋል፡፡ እርሳቸውን በመከተልም ‹‹እንዴት በዚህ ጉዳይ ድርድር ውስጥ ይገባል; እንዴት መናፍቅ አይደለም ይባላል;›› በሚል አቋማቸውን በጠነከረ ስሜት የገለጹት የጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ኤልያስ ናቸው፡፡ በቀደሙት አጀንዳዎች አቡነ ጳውሎስን ሲደግፉ የቆዩት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በውይይቱ ላይ ዝምታን መምረጣቸው ተገልጧል፡፡ አቡነ ገብርኤል ከሾሙት በሚል ዕርቅም የጠየቁ ነበሩ፤ ‹‹ጉዳዩ የሃይማኖት ልዩነት ነው፤ በዕርቅ የሚፈታ አይደለም›› በሚል ተመልሶላቸዋል፡፡ 
የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከቀትር በኋላ በታየው የፓትርያሪኩ
 ግትርነት በማዘን ጉባኤውን ትተው መውጣቸው ተሰምቷል፡፡ ሁኔታው ‹‹ምልአተ ጉባኤውን በማሰላቸት በቀጣዩ አጀንዳ አቋሙ እንዲላላ አልያም ተስፋ እንዳይኖረው የማድረጉ ስልት ቀጣይ ገጽታ›› እንደ ሆነ ያመለከቱት ታዛቢዎች ሲኖዶሱ ወስኖበት ባለፈው አጀንዳ ላይ ከመቸከል ይልቅ የፓትርያሪኩ አቋም በልዩነት ብቻ ተይዞ ወደ ቀጣዩ አጀንዳ ቢሻገር መልካም እንደሚሆን መክረዋል፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ጌታቸው ዶኒ ‹‹መናፍቅ ነው›› ከሚለው ጋራ ፓትርያሪኩ በትክክለኛው መንገድ ሥራ አስኪያጅ አድርገው እንዳልሾሙት በማጋለጥ ነገሩን በቀላሉ መሻገር ይቻል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ጋራ በተያያዘ ቀጣዩን ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅነት የሚመጥነውን ሰው ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል መርጠው እንዲያሳውቁ፣ የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ መልአከ ኀይል ኀይለ ጊዮርጊስም ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ ከፓትርያሪኩ በቀር ምልአተ ጉባኤው ተስማምቶበት ነበር፤ የገዳሙን አለቃ የሚሾሙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ናቸው፡፡ ከተቻለ መላው የምልአተ ጉባኤው አባላት አልያም ከፊሎቹ ወደ ሐዋሳ በማምራት ጉባኤ ሠርተው ለረጅም ጊዜያት ያዘነውን ምእመን እንዲያጽናኑም ከቀትር በፊት ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን እና በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ ላይ በቀጣይ እንደሚወያይ የተጠበቀው ጉባኤው የሐዋሳውን ጉዳይ ሳይቋጭ ለነገ ተላልፏል፡፡ በአንዳንዶች አስተያየት የፓትርያሪኩ አቋም በትላንቱ የጉባኤ ውሎ ‹‹በወዘተርፈ›› የታለፈውን የሐውልቱን መነሣት እና ሌሎች ያልተፈጸሙ ውሳኔዎችን እንዲያነሡ ሳይገፋፋቸው እንደማይቀር ተገምቷል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)