May 17, 2011

ቤተ ክርስቲያን እንደ ሥርዓቷና ሕጓ በቅዱስ ሲኖዶስ የበላይነት ትመራ!


  • ማንአለብኝነት ይቁም! መንግስት ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች አተገባበር ድጋፍ ይስጥ!
በቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ ወሳኝ አካል እንደመሆኑ በማንኛውም ጉዳይ በሕገ ቤተክርሰቲያን እንደተጠቀሰው ሀሳቦች ላይ በአንድነት ተወያይቶ ይወስናል፡፡
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባዎች ውጥረት የበዛባቸው ስብስቡንም አደጋ ላይ የሚጥሉ እየሆኑ ይገኛል፡፡ ይህም አጀንዳ ከማስያዝ እስከ ተወሰኑ ጉዳዮች ማስፈጸም ድረስ ያሉት ጉዳዮች በህግና በሥርዓት መከናወን ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይህም

1ኛ. ተገቢ አጀንዳዎች እንዳይያዙ ማድረግ፣ ያልተገቡ አጀንዳዎች በስርዋፅ ማስገባት
ለቅዱስ ሲኖዳስ ስብሰባ አጀንዳ እንዲያደራጅ የሚዋቀር ኮሚቴ በተለያዩ አካላት ቁምስቅሉ ማየቱ አይቀርም፡፡ በሌሎች ጥቅመኞች በቅዱስ ፓትሪያሪኩ በኩል ሾልከው የሚደርሱ በርካታ ርካሽ ጉዳዮች ማጥራትና ወቅታዊ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮችን እንዲያዙ ለማድረግ ያለደም ሰማዕትነት ያስከፍላል፡፡


2ኛ. በብዙ ትግል ተቀርጸው የቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በቂ፣ ነጻና እኩል ውይይት አለማድረግ
ይህም በቂ የተሳትፎ እድል ለሁሉም አለመስጠት፣ የውይይት ጊዜው ሆን ብሎ ማባከን፣ የጥቅመኞች ፍላጎት እስካልተወሰነ ወደ ቀጣዩ አጀንዳ አለመሄድ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ ባስ ሲልም ስድብ ማዥጐድጐድ የተለመዱ ማታለያና ማሸማቀቂያ ስልቶች ሆነዋል፡፡ ሆኖም ከፓትሪያርኩ ጀምሮ እያንዳንዱ አባል ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ውሳኔ ሲያሳልፍ አስተዳደርን የሚመለከት አጀንዳ ከሆነ ከግማሽ በላይ በሆነ ድምፅ የተደገፈ ሐሳብ የሚቀበል ሲሆን ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተክርስቲያንን የሚመለከት አጀንዳ ከሆነ ደግሞ በሙሉ ድምፅ ያልፋል፡፡

3ኛ. በተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ሰበብ እየፈጠሩ አለመፈረምና ውይይት ያልተደረገባቸው ውሳኔዎችን ቀላቅሎ ማቅረብ
ብፁዓን አባቶች ለረጅም ሰዓታት አድካሚና አሰልቺ ውይይቶች አድርገው ስምምነት ላይ በደረሱባቸው ቃለ ጉባዔያት አልፈርምም ማለት ሌላው የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ድርጊት ነው፡፡ በሌላ በኩል በውይይቱ በጭራሽ ያልተነሱ የጥቅመኞች ፍላጐት በግልጽ የሚያንፀባርቁ ውሳኔዎች በቃለ ጉባዔያት አካቶ በማቅረብ በሌላ ንትርክ ዋናውን ጉዳይ የማስረሳት ሂደቶች ይከናወናሉ፡፡ እንዲሁም የተሳትፎ መከታተያ ወረቀት ላይ ያሉ ፊርማዎችን በመጠቀም ውይይት ያልተደረገበትና ያልተፈረመበት የጥቅመኞች ፍላጐት  አባሪ ተደርጎና እንደጸደቀ ሆኖ በቅዱስ ሲኖዶስ ስም ይበተናል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ የኃላፊነት ወሰን በመቶዎችና በሺህዎች የሚቆም አይደለም፡፡ ለሀገሪቱ አብላጫ ህዝብ ለሚሊዮኖች እንጂ፡፡ በስሙ የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶች ኋላ ማጣፊያ እንዳያሳጡ ያሰጋል፡፡

4ኛ. በፊርማ በአግባቡ የተረጋገጡ ግልጽ ውሳኔዎችን በማን አለብኝነት አለመተግበር
ቅዱስ ሲኖዳስ በተለያዩ ጊዜያት ወቅታዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አስልፏል፡፡ ፓትሪያርኩም በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡትን ውሳኔዎች፣ የተላላፉ መመሪያችንና ውሳኔዎችን ለትግበራ በፊርማ ማስተላለፍና አተገባበራቸውም መከታታል እንደሚኖርባችው ሕገ ቤተክርስቲያን በግልጽ ያስረዳል፡፡ ሆኖም ውሳኔዎች እየተተገበሩ አይደሉም፡፡ ይህም ውሳኔዎቹ ለትግበራ ለሚመለከታቸው አካላት ስለማይመሩና ከተመሩም በኋላ በጥቅመኞች በሚደረገው ሽኩቻና ጠለፋ ነው፡፡ እንዲሁም በማንአለብኝነት፡፡ ጉዳዩ በአንክሮ ለሚከታተለው ሰዎቹ ለመንፈሳዊው ዓለም ሕልውና የነፈጉትም ያስመስላቸዋል፡፡ በዚህም ምዕመናንን ግራ ከመጋባት አልፈው ተስፋ ወደ መቁረጥ እየሄዱ ይገኛሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ባሳለፈችው ታሪኳ አስገራሚና አስደናቂ ሆና እስከአሁን የዘለቀችው በአባቶች መንፈሳዊ አመራርና ለአስተዳደራዊ ህጓ መንግስት ጥብቅና እየቆመላት ነው፡፡  እንኳን ለአንዲት ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ብሔራዊት ቤተ ክርሰቲያን ይቅርና ለግለሰብ እንኳን መንግስት ጥብቅና ይቆማል፡፡ ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው ማለት መንግስት በቤተ ክርስቲያ ውስጥ ህግና ሥርዓት አያስጠብቅም ማለት አይደለም፡፡

ስለሆነም መንግስት፡-
1ኛ. ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የHeግ ጥብቅና ከለላ ያድርግ
በአባቶች ላይ የሚደረግው ማስፈራሪያና ዛቻ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ማስፈራሪያ ዛቻውም ከአካላዊ ጥቃት እስከ በውሸት እስከተቀነባበሩ የአባቶች ግብር የሚኮስሱ የኦዲዮ ቪዥዋል ውጤቶች ይደርሳል፡፡ በዚህም አባቶችን በማሸማቀቅ ሀሳባቸውን በነፃነት አንሸራሽረው ተገቢውን ውሳኔ እንዳይወስኑ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ በመሆኑም መንግስት ካለፈው ተሞክሮና ከመደበኛ ኃላፊነታቸው ስፋት አንፃር ለአባቶች ተገቢውን የህግ ጥበቃና ከለላ መፍጠር ግድ ይለዋል፡፡

2ኛ. ተመልካቾችን በስብሰባዎች ላይ ይወክል
የቅዱስ ሲኖዳስ አባላት ሁሉም እኩል ድምጽ ያላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም አባቶች የተመጣጠነና እኩል ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ውሳኔዎች በተገቢው ሁኔታ መወሰን ይኖርባቸዋል፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የንግግር ዕድል በመንፈግና እያሰላቹ የውሳኔ ሀሳብ በማስቀየር የአባቶችን ነፃነትና እኩልነት እየተሸረሸረ ነው፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ከሚኖራት ተፅዕኖ አንፃር መንግስት ቤተ ክርስቲያኒቷ ራሷ የሰጠችው የአባቶችን ነፃነትና እኩልነት በየስብሰባው አለመረጋገጡን ለማረጋገጥ ተመልካቾት መላክ ይኖርበታል፡፡ ስብባዎችም ከአምባገነኖች ፈቃድ ወይም በቤተክርስቲያኒቷ ሥርዓትና ሕግ መሠረት መከናወኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

3ኛ. የተወሰኑ ውሳኔዎች አተገባበር ላይ ድጋፍ ይስጥ
ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የተረጋጋ ማኅበራዊ ሥርዓትና የኑሮ ባህል ቤተ ክርስቲያን ዋነኛውን ድርሻ ትወስዳለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን የተረጋጋውን ማኅበራዊ ሥርዓትና የኑሮ ባህል ከመንፈሳዊና ሠላማዊ ሥርዓቷና ህጓ ቀድታ ለሁሉም ያከፈላቸው ነው፡፡ በየጊዜው በሚደረጉ ሀገራዊ ጥሪዎች ድንገት ብቅ የሚለው ያለተገመተ ምላሽና ወኔ እርሷ የዘራችው ነው፡፡ የእርሷ መረጋጋት የሀገሪቱ መረጋጋት ነው፡፡ መነሳሳቷም ለሀገሪቱ ይተርፋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ነባራዊ ሁኔታዎችን ዳስሶ እያጸናና እያሻሸለ ወስኖ የሚሄድባቸው ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያኒቷን ከወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አጣጥሞና አረጋግቶ ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የሚወሰኑ ጉዳዮችን አተገባበር ላይ መንግስት ለቤተ ክርስቲያኒቱን ተገቢውን የህግ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ጉዳዮች እየተወሰኑ በጥቅመኞች መልሰው እየታፈኑ ቤተ ክርስቲያን ወስጧ እየተናጠ፤ በዝምድና በሙስና እየተበጠበጠ የተረጋጋ ሀገር ማሰብ እጅግ ከባድ ነው፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመን ሰምቶ ያመነና ብፁዕ የተባለ ነው፡፡ ለሃይማኖቱም እጅግ ቀናዒ ነው፡፡ እንኳን ቤተ ክርስቲያንን የሚንጡ ሙሰኞች ለማረም ይቅርና ወቅቱን ጠብቆ በቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚደረጉ ቀኖናዊ ለውጦች እንኳን ጠንካራ አቋም አለው፡፡ ሃይማኖቱ ማንነቱና የነገ ተስፋው ነው፡፡ ምድራዊ ያለሆነ ሰማያዊ፡፡ ምድራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው አቋም ሰማያዊው ላይ እንዳለው ሊሆን አይችልም፡፡ ዝምታውና እርጋታው ቆፈን የያዘው የሚያስመስለው ተስፋው እስኪሟጠጥ ለጊዜው ነው፡፡ ማንነቱና ተስፋው የታፈነና የተነጠቀ ደግሞ የመሰለውን ለማድረግ ወደኋላ አይልም፡፡ በቅርቡም በአንድ መጽሔት ላይ "እግር አልባ ባለክንፍ ብሎ" ያለ ክንፍ በሀሳብ ሲከንፍ የማይነካውን አጓጉል የነካ ጸሐፊ ላይ የደረሰውን ልብ ይለዋል፡፡ ሥርዓትና ሕግ ጨዋነትና ታጋሽነት ከማንነትና ከተስፋ አይበልጡም፡፡ ወንጌሉም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል ነው የሚለው፡፡ የሐዋርያት ሥራ 2፥ 26፡፡ ስለዚህም ሳይቃጠል በቅጠል እንላለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያናችንን ይባርክ!                          
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)