June 3, 2011

የወ/ሮ እጅጋየሁ ቃለ ምልልስ ከቁምነገር መጽሔት ጋር

Photo: Courtesy of Addis Journal.
To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።
በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት አካባቢ እንደ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ አወዛጋቢ ሴት የለም፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ የዝነኛው ድምፃዊ የማህሙድ አህመድ የቀድሞ ባለቤት ናቸው፡፡ ከድምፃዊው ጋር የፍርድ ቤት የፍቺ ጣጣቸው ገና አልተቋጨም፡፡ ዝነኛውን ማህሙድ ሙዚቃ ቤትን ሽጠው ብሩን ተካፍለውታል፡፡ “ እሱ ነው ይሸጥ ያለው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ወ/ ሮ እጅጋየሁ ከፓትሪያርኩ ጋር ስማቸው አብሮ ይነሳል፤ “ፈላጭ ቆራጭ እርሳቸው ናቸው” በሚል፡፡ ቁም ነገር መጽሔት ያተመው የሴትየዋ አስገራሚ ቃለምልልስ በከፊል ይህን ይመስላል፡፡

ጥያቄ፡- በነገራችን ላይ ወ/ሮ እጅጋየሁ እድሜሽ ስንት ነው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- እግዜአብሄር ይመስገን 66ኛ ዓመቴን ጨርሻለሁ


ጥያቄ፡- ወደ ቅዱስ ፓትሪያርኩ ጋር እንዳትገቢ አልተባልሽም?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- በፍጹም፡፡ ማንም አላለኝም፡፡ አሁን ያልከው ጉዳይ በወቅቱ አንድ ጋዜጣ ላይ ተጽፎ አንብቤያለሁ፡፡ ከዚያ በፊት እውነተኛ ነገር ነው የሚዘግበው ብዬ የማስበው ጋዜጣ ነበር፡፡ ነገር ግን የሌለና ያልተደረገ ነገር መጻፉን ስመለከት ወደ ክስ ከመሄድ ይልቅ አዝኜበት ነው የተውኩት፡፡
በመጀመርያ ደረጃ ቤት ክህነት የምገባው እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ ብዙ ሴቶች ይገባሉ፡፡ እኔ ግን የትና ማን ጋር እንደምገባ ይታወቃል፡፡ የማንም ደላላና ወሬ አቀባይ አይደለሁም፡፡ ይህንን ላረጋግጥልህ እችላለሁ፡፡ ይህንን ለማድረግ እድሜዬ፣አስተዳደጌ፣ ሃይማኖቴ አይፈቅድም፡፡ በሁለት ቢላ የምበላ ሴት አይደለሁም፡፡ እኔ የምገባበት ቦታ የታወቀ ነው፡፡ ሽፍንፍን የለውም፡፡ እግዜአብሔር የመረጣቸው ከእስር ቤት አውጥቶ ከስደት መልሶ መርጦ “ልጄ አንተ ነህ፤ ወንበሬም ያንተ ነው” ብሎ ያስቀመጣቸው ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋር ነው የምገባው፡፡ የምገባው ከእርሳቸው ቡራኬና በረክት ለማግኘት ነው፡፡ እንደማንም ወሬ ላመላልስ አይደለም የምገባው፡፡ ይሄ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ስለ እኔ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የተነሳ ነገር የለም፡፡

ጥያቄ፡- የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች በአባቶች መሀል አለመግባባት እንዲፈጠር የምታደርገው እሷ ነች ይላሉ፡፡

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- የምትለውን ማኅበር እኔ አላውቀውም፡፡ የጽዋ ማኅበር ይሁን ወይም ሌላ እኔ አላውቀውም፡፡ የማኅበረ ማርያም፣ ማኅበረ ግሸን የሚባል አውቃለሁ፡፡ ራሱን ቅዱስ ብሎ የሚጠራ ማኅበርን ግን አላውቅም፡፡ አሉባልታን የሚያናፍሰው የአጋንንት ማኅበር ካልሆነ ማን ሊሆን ይችላል? ሃይማኖት ያለው ሰው አሉባልታ ላይ ጊዜ አያጠፋም፡፡  እኔን እዚህ እንዳልገባ ሊከለክሉ የሚችሉት ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ብቻ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- በነገራችን ላይ ከብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ጋር ዝምድና አላችሁ እንዴ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- የለንም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ዝምድና የሚባል ነገር ከእርሳቸው ጋር የለኝም፡፡ ዝምድናው ባይኖረኝም ግን የመንፈስ ቅዱስ አባቴ ናቸው፡፡ እንደማንኛውም ሰው ቀርቤ አይቻቸዋለሁ፡፡ የዋህ፣ ቅን፣ ሩህሩህ፣ ደግ፣ ይቅር ባይ፣ ሐሰት በአንደበታቸው የማይዞር አባት መሆናቸውን ነው የተረዳሁት፡፡ ካለቀሰው ጋር ሁሉ የሚያለቅሱ፣ ሩህሩህ አባት መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእኚህ አይነት አባት ማግኘቷ ራሱ ትልቅ በረከት ነው፡፡

ጥያቄ፡- የእቅዴን ያህል ሰርቻለሁ ትያለሽ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- እግዜአብሔር ይመስገን፡፡ እግዜአብሔር በረዳኝ መጠን የተቻለኝን ያህል ድጋፍ አደርጋለሁ፡፡ ሰዎችን እረዳለሁ፡፤ ከዚህ በፊት 64 ኪሎ ግራም እጢ ለ22 ዓመት ማህፀኗ ውስጥ ይዛ የኖረችን ሴት ከሰውነቷ ውስጥ እንዲወጣ አድርገናል፡፡ ያለ ፊንጢጣ የተወለደች ልጅንም ረድቻለሁ፡፡ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን በተቻለኝ አቅም ለመስራት እሞክራለሁ፡፡ በምድረ ከብድ አቡዬ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም ብትሄድ በግል ገንዘቤ ለጳጳሳት ማረፊያ 12 ክፍል ቤት ሰርቻለሁ፡፡ ትልቅ አዳራሽም አለው፡፡ ብፁዕ አባታችን ናቸው ባርከውና ቀድሰው ስራ ያስጀመሩት፡፡ ሰከላ አቡዬ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳምም እንደዚሁ ቆርቆሮ አልብሻለሁ፡፡ ባህር ዳርም ቤዛዊት ማርያም የአቅሜን ሰርቻለሁ፡፡ ሰዎችን በማስታረቅም የማምን ሰው በመሆኔ የተቀያየሙትን ሁሉ ሰብስቤ አስታርቃለሁ፡፡ በብፁእ አባታችን ላይ መጥፎ ነገር ሲናገሩ የነበሩ ሰዎችን ሳይቀር አስታርቃለሁ፡፡ ተቧድነው የሚናከሱትን ሁሉ ይቅር እንዲባባሉ አድርጌያለሁ፡፡ እሳቸውም ይቅር እንዲሏቸው አድርጊያለሁ፡፡

ጥያቄ፡- ቢሮሽ የቤተ ክህነት ነው፡፡ ማን ነው የሰጠሸ? ፓትሪያርኩ ናቸው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ብፁእ አባታችን አስከዛሬ ድረስ ይሄ ይደረግልኝ ብያቸው አላውቅም፡፡ እሳቸውም ሰጥተውኝ አያውቁም፡፡ ወሬው ግን ቀድሞ ይወራል፡፡ አሁን ያለሁበት ቢሮ የቤተ ክህነት ቤት ነው፡፡ ጨረታ ሲወጣ ተጫርቼ ነው፡፡

ጥያቄ፡- መኖርያ ቤቱስ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ሥላሴ ጋር ያለው ቤት የእኔ አይደለም፤ የልጄ ቤት ነው፡፡ እሱንም የዛሬ ስንት ዓመት የወደቀ የፈራረሰ ቤት ስለነበረ 284 ሺህ ብር ወጪ አድርጌ ሰርቪስ ሰርቼ፣ አሳድሼ አጥር ሰርቼ ነው ልጄ እየኖረችበት ያለቸው፡፡

ጥያቄ፡- ማን ሰጠሸ፤ ፓትሪያርኩ አይደሉም?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- የዚያን ጊዜ እንዲያውም ከፓትሪያርኩ ጋር አንተዋወቅም፡፡ የሰጡኝ ብፁእ አቡነ ቄርሎስ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ የተሰጠኝ ቤት የለም፡፡

ጥያቄ፡- በቤተክህነት ግቢ ውስጥ እጅሽ ረጅም እንደሆነ ይገለጻል፡፡ በእርግጥ የእጅሽ ርዝመት ምን ያህል ነው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- በጣም ጥሩ፡፡ ይገርማል ይህ አባባል እኔን እራሴን አንዳንዴ ብቻዬን ቁጭ ብዬ ያስቀኛል፡፡

ጥያቄ፡- በቤተ ክህነት ሥልጣንሽ ምንድነው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ምንም ሥልጣን የለኝም፡፡

ጥያቄ፡- የቤተክህነቱ ሠራተኛ ነሽ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- አይደለሁም፤ እኔ ቤተክህነት ምንም ነገር የለኝም፡፡ አባቴ ግን ትልቅ አባት መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ አባቴ የክርስቶስ እንደራሴ ናቸው፡፡ መከበር አለባቸው፡፡ አትንኩዋቸው ነው የምል፡፡

ጥያቄ፡- ለመጀመርያ ጊዜ ቅዱስ አባታችንን ያወቅሻቸው መቼ ነበር?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ቅዱስ አባታችንን ለመጀመርያ ጊዜ ያየኋቸው ፓትሪያርክ ሳይሆኑ በፊት ነው

ጥያቄ፡- የት?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- አሜሪካ ሎሳንጀለስ

ጥያቄ፡- እዚያ እያሉ ውዝግብ ገጥሟቸው ያውቃል?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ያኔማ አባታችን አባታችን ነው የሚባሉት፡፡ የተከበሩ ልዩ አባት ናቸው፡፡ የሎስአንጀለሷን ማርያም ያቋቋሙት እሳቸው ናቸው፡፡ አሜሪካ ሰባት ቤተክርስቲያናት አቋቁመዋል፡፡

ጥያቄ፡- እዚህ ከ200 በላይ ቤተ ክርስቲያን ማሰራታቸው ይነገራል

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- የዚህማ ምኑ ተነግሮ፡፡ ምን ያልሰሩት አለ…ልማቱስ…ግንባታውስ…ት/ቤቱስ…ድሮ ቄስ የረባ ደሞዝ አልነበረውም፡፡ ዛሬ የምታየው ከሺህ ብር በላይ ደሞዝ የሚከፈለው ቄስ ሁሉ ድሮ ወይ በጤፍ ወይ በሰላሳ ብር ብቻ ነበር የሚያገለግለው፡፡

ጥያቄ፡- ብዙ የሠሩትን ያህል ብዙ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ጻድቅ ሰው ይዋረዳል፡፡ ይሰደባል፣ ጌታ እየሱስ ክርስቶስም ያን ሁሉ መከራ የተቀበለው እያገለገለ ጥሩ ስራ እየሰራ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ለአባታችን ሀውልት የማቆሙን ነገር ከጠነሰሱት ውስጥ አንዷ አንቺ…

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ዛሬ ይህን ጥያቄ በመጠየቄ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ይህን ጥያቄ ነበር እኔ ያጣሁት፡፡ እውነቱ እንዲወጣ እፈልጋለሁ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ቅዱስ አባታችን ሀውልት ይሰራላቸው ብዬ ያመነጨሁት ሐሳብ የለኝም፡፡

ጥያቄ፡- የማን ሐሳብ ነው ታድያ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ቃሊቲ ያለችው ቁስቋም ማርያም ፅላቷ ለጥምቀት ከወጣ በኋላ አልገባም ብሎ አልመለስም አለ፡፡ ለብዙ ጊዜ ተቀምጦ ሕዝቡ በምህላ በለቅሶ በጭንቀት ላይ ነበር፡፡ በኋላ ቤ/ክ አሰራለሁ ብለው መሰለኝ አንድ ሰው ሰሩ፡፡ እሱ ከተሰራ በኋላ አሁንም ማስገባት አልተቻለም፡፡ ከብዙ ምህላ በኋላ ቅዱስ አባታችን ቦታው ድረስ ሄዱ፡፡ ያን ጊዜ “እስካሁን ያልተቻለውን አሁን እኚህ ሊያስገቡ ነው?” እያሉ የተቹ ነበሩ፡፡ በአንድ ቡራኬ ነው፡፡ ድፍት ብለው ወድቀው ጸሎታቸውን ካደረሱ በኋላ ብድግ አድርገው |ፅላቱን ያስገቡት፡፡

በዚህ ምክንያት እዚያ ያለው ሕዝብ በሙሉ “ሐውልት ሊሰራላቸው ይገባል፤ በሕይወት እያሉ ተቀርፆ ማየት አለባቸው” ብሎ ተነሳ እንጂ እኔ ያመጣሁት ሐሳብ አይደለም፡፡ እኔ ያመጣሁት ሳንቲም የለም፡፡

ጥያቄ፡- በማን ገንዘብ ተሠራ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ያው ሕዝብ ያዋጣላቸው ነው

ጥያቄ፡- ሕዝቡ ምን ያህል አዋጣ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ከአራት መቶ ሺ ብር በላይ

ጥያቄ፡- ስለዚህ ለሀውልቱ ግንባታ ውስጥ የለሽበትም ማለት ነው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ያን ነገር ስሰማው የሳቸውን ክብር ማየት ከማንም በላይ ምኞቴ ስለነበረ ተደስቼ በዓሉ በሚደምቅበት መንገድ ማገዝ ጀመርኩ፡፡

ጥያቄ፡- ለምሳሌ ምን በማድረግ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ቅዱስ አባታችን እንዳይሰሙ ሰርፕራይዝ አድርጓቸው ብዬ በአሉ ድምቀት እንዲኖረው ያማረ እንዲሆን አድርጌያለሁ

ጥያቄ፡- ቦሌ መድኃኔዓለምን ለምን ተመረጠ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- በሳምንት ሦስቴ እየመጡ እዚያች ጭቃ ላይ ቁጭ እያሉ ከኪሳቸው ገንዘብ እያወጡ በሬ እያረዱ ያሰሩት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የመረጥነው።

ጥያቄ፡- ሀውልቱ ከምንድነው የተሰራው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- አምስት መቶ ዓመት መቆየት በሚችል ፋይበር በሚባል ነገር ነው የተሰራው

ጥያቄ፡- ስለሀውልቱ መቆም አባታችን ምንም አያውቁም ያልሽ ኝ መሰለኝ

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- መድኃኔዓለም ምስክሬ ነው፡፡ እመቤቴን እልሀለሁ፡፡ ምንም ነገር አያውቁም

ጥያቄ፡- የመረቁት ግን እሳቸው ናቸው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ጉዳዩን ሳያውቁት ነዋ የተጠሩት

ጥያቄ፡- እንዴት?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ሲጠሩ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀናቸው ተማሪዎች ስላሉ ይምጡና ይመርቁልን ብለዎታል ተብለው ነው የተጠሩት፡፡

ጥያቄ፡- አላወቁማ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ምንም የሚያውቁት ነገር የለም

ጥያቄ፡- ሲያዩት ምን አሉ

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- መጡ፤ የእውነት ለመናገር ከመጡ በኋላ ሪቫኑን በመቀስ ቆረጡ ከዚያ የተሸፈነውን ክፈቱት አልናቸው፡፡ ሲከፍቱት በጣም ደነገጡ፡፡ እንዲያውም ደንግጠው መስቀላቸውን እንዲህ አይናቸው ላይ አድርገው የተከዙበት ፎቶ ግራፍ አለ፡፡ ላሳይህ እችላለሁ፡፡ ለማስረጃ፡፡

ጥያቄ፡- ከዚያስ ምን አሉ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- አይገባኝም ነው ያሉት፡፡ ይሄ ነገር ለኔ አይገባም ነው ያሉት፡፡ ምን ስላደረኩ፤ ማን ነኝና፤ ብለው ራሳቸውን ዝቅ ያደረጉ አባት ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- አሁን የሀውልቱ መጨረሻ ምንድነው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ሐውልቱማ አሁንም አለ፡፡ ይኖራል፣ ይቀጥላል፡፡ የሚፈርስ ሀውልት የለም፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)