May 18, 2011

ቅዱስ ሲኖዶስ የዛሬ ጠዋት ውሎ


To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት PDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ
  • ቅዱስ ሲኖዶስ የአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት አጀንዳን ወድቅ አደረገ
  • ፓትርያርኩ የሐዋሳ ምእመናን ጥያቄ በአጀንዳ መያዙን ተቃውመዋል
  • ሲኖዶሱ በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል በተፈጠረው ችግር ላይ ይወያያል
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 18/2011)፦ ከጅምሩ ውዝግብ ያላጣው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዛሬ ረፋድ ላይ ተጀምሯል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ከቀትር በፊት ውሎው አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበትን የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እና ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሚገኙበት ይኸው የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴም 18 የተለያዩ አጀንዳዎችን አቅርቧል፡፡


እንደ ጉባኤው ምንጮች ገለጻ “ልዩ ልዩ” በሚል ከተያዙት የበጀት እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መካከል ዐበይት እና ወቅታዊ ያሏቸውን ስድስት አጀንዳዎች ጠቅሰዋል፡፡ እኒህም፡- 1) የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አፈጻጸም፣ 2) በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ስላለው የሥራ ግንኙነት ችግር፣ 3) የሲዳማ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች(ሲዳሞ) ሀገረ ስብከት ስላለው አስተዳደራዊ ችግር እና የምእመናን ጥያቄ፣ 4) ስለ ሊቃነ ጳጳሳት ዝውውር ጥያቄ እና ችግር ስላለባቸው አህጉረ ስብከት ጉዳይ፣ 5) የተተኪ ቋሚ ሲኖዶስ አባላት ምርጫ፣ 6) ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚኖራትን አጠቃላይ አስተዋፅኦ አስመልክቶ የቀረቡት ሲሆኑ ሁሉም የምልዓተ ጉባኤውን ድጋፍ ማግኘታቸው ተዘግቧል፡፡

ቀደም ሲል በፓትርያርኩ ቀርቦ በቋሚ ሲኖዶስ ተቃውሞ የገጠመው የተጨማሪ 30 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጥያቄ በብዙዎች እንደተገመተው በምልአተ ጉባኤው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በዚህ እና በትናንቱ የሐዋሳ ምእመናን ጠንካራ “የማጠቃለያ አቤቱታ” አቀራረብ በእጅጉ እንደተቆጡ የተነገረላቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የምእመናኑ ጥያቄ በአጀንዳ ተይዞ የምልአተ ጉባኤው የውይይት ነጥብ በመሆኑ ጉዳይ ላይ ተቃውሞ እና የአቋም ልዩነት በማሳየታቸው በሲኖዶሱ የስብሰባ ሥነ ሥርዐት መሠረት አጀንዳው ያለፈው በአብላጫ ድምፅ ተደግፎ መሆኑን የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ለገበያ በዋሉት አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ሳይቀር ሽፋን የተሰጠውን የሐዋሳ ምእመናን ጥያቄ የምልአተ ጉባኤው አባላት ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ “ሰውን ባናፍር እግዚአብሔርን መፍራት አይገባንም ወይ? ያ ሁሉ ሕዝብ ከመሬት ወድቆ የጠየቀውን ጥያቄ እንደምን ሳንመለከት እናልፋለን? አጀንዳውን ባይደግፉትም ችግሩ እውነታነት አለው” በሚል አጽንዖት ጭምር አጀንዳው መያዙን ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡ “አጀንዳው ከማንም በላይ ራሳቸውን የሚያስጠይቃቸው በመሆኑ ነው ፓትርያርኩ መቃወማቸው” ብለዋል ምንጮቹ፡፡

ቅዱስነታቸው ከስብሰባው ቀደም ብሎ ትናንት ማምሻውን ምእመናኑ በተዘገበው አኳኋን ይመጡ ዘንድ ፈቃድ በተሰጠበት ሁኔታ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ከመንግሥት አካል ጋራ መነጋገራቸው ተሰምቷል፡፡ በአንዳንድ ምንጮች ምልከታ በአራተኛው አጀንዳ በተመዘገበው የጳጳሳት ዝውውር ጉዳይ ፓትርያርኩ በሚወስዱት ጠንካራ አቋም ደስተኛ ባልሆኑባቸው በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ከሐላፊነት እንዲነሡ ሳይጠይቁ እንደማይቀር ተገምቷል፡፡

በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ እና ማኅበረ ቅዱሳን መካከል ያለው የሥራ ግንኙነት ችግር በምልዓተ ጉባኤው በአጀንዳነት እንዳይያዝ የመምሪያው ሐላፊ በግልጽ በሚታይ የማግባባት ዘመቻ (ሎቢ) ተጠምደው እንደነበር ተገልጧል፡፡ ቀደም ሲል መዋቅርን ሳይጠብቁ እስከ ፓትርያርኩ ድረስ እንዳልተካሰሱበትና በየመድረኩ እንዳልተሯሯጡበት አሁን ደርሶ “ጉዳዩ በመምሪያው ሊያልቅ የሚችል ነው” ማለታቸው የምልአተ ጉባኤውን አባላት አላሳመነም፡፡

በታዛቢዎች አስተያየት አጀንዳው የምልአተ ጉባኤው የውይይት ነጥብ መሆኑ የመምሪያውን ሓላፊ በሁለት ነገር ያሰጋቸዋል፤ አንድም - ላለፉት ስድስት ዓመታት በመምሪያ ሓላፊነታቸው የፈየዱት ነገር ባለመኖሩ እንዲያውም በሌላ ዓላማ ተጠምደው የቆዩ የግርግር እና ሁከት ፈጣሪ ሰው መሆናቸው ለፀሃይ ብርሃን ስለሚጋለጥ፤ በሌላም በኩል መድረኩ/አጀንዳው/ ለጊዜው ያልተሳካው ለከፍተኛ ማዕርግ የታጩበት መመረጥ ከዚህ በፊት በአንዳንድ ተሿሚዎች ዘንድ እንደታየው በፈጠራ ታሪክ ሳይሆን ማንነታቸውና የሥራ ፍሬያቸው በተጨባጭ የሚፈተሽበትን ዕድል ስለሚፈጥር፣ ይህ የሚያስከትለውን መዘዝ ለማጨናገፍ በማሰብ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

“ባለጉዳዮችን አናስተናግድም” በሚል የመግቢያ በሮች ማስታወቂያ እና በጠንካራ የመንበረ ፓትርያርኩ ዙሪያ ጥበቃ ሥር የተጀመረው ጉባኤው ከቀትር በኋላም ቀጥሎ በአጀንዳዎቹ ላይ በዝርዝር መነጋገር መጀመሩ ተዘግቧል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)