May 31, 2011

አባ ሰረቀ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ፤ ተሐድሶን መቃወምን ተቃውመዋል

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ

(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 31/2011)፦ አባ ሰረቀ የተባሉት የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሐላፊ ዛሬ ይሰጡታል ተብሎ በሚጠበቀውና ለደጀ ሰላም በደረሰው ጽሑፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ “ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና በሚጻረር መልኩ በአገልጋይና በተገልጋይ መካከል ለዘመናት የቆየውን ጤናማ ግንኙነት በሚያሻክር አኳኋን አለስልጣኑ በመግባት የሚተገብረው ዐዋጅ ነው” አሉ።


ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት በመምሪያው ስም መግለጫ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው መግለጫ ለወጣቱ “የክረምት ችግኝ ተከላን፣ ለዐባይ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዥ፣ የደሞዝ ልገሳ፣ የሞራልና የጉልበት ድጋፍ በማድረግ” ጥሪ ማር ተለውሶ የቀረበ የዋና ሐላፊው አጀንዳ መሆኑን የዜና ምንጮቻችን አስረድተዋል። መግለጫውን የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦንስ እና የጠ/ቤ/ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደማያውቁት የተደረሰበት ሲሆን ጉዳዩ በዋነኝነት የሚያጠነጥንበት ማኅበረ ቅዱሳን በበኩሉ መግለጫው “አግባብነት የሌለው ነው” ሲል ተቃውሞታል።

 “የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ባለው ውሱን የሰው ኃይልና በጀት በመንቀሳቀስ በመላ ዓለም የሚገኙ ወጣቶች ወጥ የሆነ የትምህርትና መዝሙር ሥርዐት እንዲኖራቸው ከምንጊዜውም በላይ በመንቀሳቀስ ላይ” እንደሚገኝ መግለጫው ያብራራል።

አባ ሰረቀ አላግባብ ከተሰጠው የሲዳሞ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ሥልጣን በሰሞኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተባረረው መናፍቁ ጌታቸው ዶኒ የሐዋሳ ምእመናን ባዘጋጁትና የብዙዎችን ትኩረት በመሳብ በስፋት እየተሰራጨ በሚገኘው ቪሲዲ “ስሜ ጠፍቷል” በሚል በምእመናኑ አስተባባሪዎች ላይ የመሠረተው ክስ “ተጠናክሮ እንዲቀጥል” የሚጠይቅ ደብዳቤ ለክልሉ የፍትሕ እና ጸጥታ ቢሮ ጽፈዋል፤ በዚህም ቀደም ሲል ከጌታቸው ዶኒ ጋራ በድብቅ የተስማሙበትንና በማስረጃ የተረጋገጠባቸውን የማደራጃ መምሪያውን የዋና ሐላፊነት ሥልጣን ተጠቅመው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን የማስፋፋት ያልተቀደሰ ኪዳን አድሰዋል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዚህ የፀረ ማ/ቅዱሳን እንቅስቃሴ መሪ እና የተሐድሶው ቡድን አቀንቃኝ የሆኑት ዋና ሐላፊው አባ ሰረቀ ባለፉት አምስት ዓመታት ማኅበሩን ከታገሉበት የበለጠ እንቅስቃሴ በማድረግ በቀጣይ ማኅበረ ቅዱሳንን “በሕግ ለመጠየቅ” መዛታቸው ተሰምቷል። ከዚህም ባሻገር ሁሉም ማተሚያ ቤቶች የማኅበሩን ጋዜጣ፣ መጽሔት እና መጻሕፍት እንዳያትሙ የሚከለክል ደብዳቤ አሰራጭተዋል ተብሏል።


በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የዘመኑን ትውልድ ከአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የመጠበቅ ሐላፊነት የተጣለበት ማኅበረ ቅዱሳን ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ለመከላከል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ‹‹የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና በሚጻረር መልኩ በአገልጋይና በተገልጋይ መካከል ለዘመናት የቆየውን ጤናማ ግንኙነት በሚያሻክር አኳኋን አለስልጣኑ በመግባትና የቤተ ክርስቲያን ሰንሰለታዊ መዋቅር በመጣስ›› የሚተገብረው ነው ሲል የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አስታወቀ፡፡ ‹‹የመምሪያውን ውሳኔዎች እና መመሪያዎች አይቀበልም፤ ተግባራዊ ለማድረግም ፈቃደኛ አይደለም›› ባለው በማኅበረ ቅዱሳን ላይም ከበፊቱ የበለጠ በመንቀሳቀስ ማኅበሩን በሕግ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጧል፡፡ 

ከግንቦት 10 - 16 ቀን 2003 ዓ.ም የተካሄደው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በመምሪያው እና በማኅበሩ መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ሰባት አባላት(ከሊቃነ ጳጳሳት - ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፤ ከሊቃውንት ጉባኤ - መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣ ሊቀ ሥዩማን ራደ አስረስ፣ መልአከ ሰላም ዓምደ ብርሃን፤ አቶ ይሥሐቅ - ከሕግ አገልግሎት) ያሉት አጣሪ ኮሚቴ ባቋቋመበት ሁኔታ መግለጫው መሰጠቱ አግባብነት የጎደለው መሆኑን የገለጸው ማኅበረ ቅዱሳን በበኩሉ፣ በሕግ የታወቀ የቤተ ክርስቲያን አንድ የአገልግሎት አካል እንጂ እንደ ባዕድ መግለጫ የሚወጣበት አለመሆኑን ለመመሪያው፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት እና ለመንበረ ፓትርያሪክ ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡

የዛሬው የዋና ሐላፊው መግለጫ በመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ይሁን መምሪያው ተጠሪ በሆነለት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት እንደማይታወቅ ተመልክቷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ አጣሪ ኮሚቴውን ከሠየመ በኋላ በእጅጉ ስለመጨናነቃቸው እየተነገረላቸው የሚገኙት ዋና ሐላፊው አባ ሰረቀ ሰሞኑን ከውርደት ያድኑኛል ያሏቸውን የተለያዩ አካላት ጋራ በመገናኘት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚያቀርቧቸውን ማስረጃዎች እያፈላለጉ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ የዛሬው መግለጫ ዋነኛ ይዘት አባ ሰረቀ ‹‹በጥናታዊ ጽሑፍ›› ስም እና በተለያዩ ደብዳቤዎቻቸው ሲያቀርቧቸው የቆዩዋቸውን ክሶች የያዘ ሲሆን ቀላል ግምት በማይሰጠው መልኩ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኝ የሆኑ ገላጭ አንቀጾችም አልጠፉበትም - ‹‹የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ባለው ውሱን የሰው ኃይልና በጀት በመንቀሳቀስ በመላ ዓለም የሚገኙ ወጣቶች ወጥ የሆነ የትምህርትና መዝሙር ሥርዐት እንዲኖራቸው ከምንጊዜውም በላይ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡›› ይህ ዐረፍተ ነገር በመግለጫው እንደሚታዩት ሌሎች አንቀጾች ሁሉ ተራ የአጻጻፍ እንከን ብቻ ሳይሆን ‹‹ለሰላም የቆመ ሁሉ የማኅበሩ አባል ነው›› ይል በነበረውና በዚህ ዓላማ የዓለም ክርስቲያን ወጣቶች ማኅበር አባል የነበረው ‹‹ሃይማኖተ አበው›› አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳለበት ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ሌላው የኑፋቄ አቀንቃኝ ቡድንም ‹‹ኦርቶዶክስን፣ ፕሮቴስታንትን፣ ካቶሊክን ባለመለየት ሁሉን አገልግላለሁ›› ባይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አባ ሰረቀ ሰሞኑን በቢሯቸው ባደረጉት ምክክር ከእነ በጋሻው ደሳለኝ ጋራ የታወቁ የ‹‹ሃይማኖተ አበው›› ርዝራዦች አንዶቹ እንደነበሩ ተገልጧል፡፡
ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀውን መግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ያንብቡ።


+++
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የተሰጠ መግለጫ፤              

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ራስዋን ችላ ሁለገብ አገልግሎት መስጠት ከጀመረችበት ጊዜ አንሥቶ በሁለተኛው ፓትርያሪክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጊዜ ወጣቶችን አሰባስቦና አደራጅቶ በትምህርተ ቤተ ክርስቲያናቸው አንጾ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ እንዲሆኑ ዝግጁ የማድረጉ ጉዳይ ከምንም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶት በቃለ ዐዋዲ ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶ ከረቀቀ በኋላ በሦስተኛው ፓትርያሪክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኅዳር 29 ቀን 1970 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡

ይህን ሕገ ደንብ እስከ 1986 ዓ/ም ድረስ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ሰንበት ት/ቤቶች ዘመኑንና ጊዜውን ያገናዘበ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡና እንዲያገኙ ለማስቻል ውስጠ ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ በ1986 ዓ.ም አዲስ የሰንበት ት/ቤቶች ውስጠ ደንብ ተቀርጾ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ስለታዘዘ በዚሁ መሠረት ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ አስተዳደራዊ መዋቅሩን ዘርግቶ ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ባለው ውሱን የሰው ኃይልና በጀት በመንቀሳቀስ በመላ ዓለም የሚገኙ ወጣቶች ወጥ የሆነ የትምህርትና መዝሙር ሥርዐት እንዲኖራቸው ከምንጊዜውም በላይ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ተቋማት ድረስ የሚያገለግሉ የሥርዐተ ትምህርት መጻሕፍትና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተጠንተው የተዘጋጁ መዝሙረ ማሕሌት ዝግጅታቸው ተጠናቅቆ ለሕትመት ዝግጁ ሆነው ይገኛሉ፡፡


ከዚህ በተጨማሪ ማደራጃ መምሪያው የወጣቱ ትውልድ መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ አገልግሎት የሠመረ እንዲሆን በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በዚህም ወጣቶች አብነታዊ ሥራ እንዲሠሩ አስችሏቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ብሔራዊ ዘመቻ ወጣቶች በማደራጃ መምሪያው መሪነት በተለይ ከሚሊኒየም ጀምሮ በሰፊው በመንቀሳቀስ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የሚያስመሰግን ሥራ ለመሥራት ችለዋል፡፡ ለወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ ይቀጥልበታል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚቋቋሙ ማኅበራትን የማደራጀትና የመምራት ሐላፊነት በቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ተነሥቶም ማኅበራት በሕግና በሥርዓት ሊመራበት የሚችል ሕግና ደንብ እንዲረቀቅ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሕጉና ደንቡ በተሰየሙ ሊቃውንት አርቃቂ ኮሚቴዎች ምክንያት ተጠንቶ የረቀቀ ስለሆነ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ አገልግሎት እስኪሰጥ ድረስ ሁሉም በቤተ ክርስቲያናችን ሥር የተቋቋሙ ማኅበራት ተልእኳቸውን በመለየት፣ በውስጣቸው የሚገኙ አባላትን በማጥራት፣ ከሕገ ወጥ ወይም አፍራሽ ተልእኮ በመታቀብ በትዕግስት እንዲጠብቁና ያላቸውን መረጃ በመያዝ ወደ ማደራጃ መምሪያው ጊዜያዊ የመመዝገቢያ ቅጽ አዘጋጅቶ በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡

ሕግና ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ የተሰጠው “ማኅበረ ቅዱሳንም” ቢሆን የተሰጠውን ሕገ ደንብ ወደ ጎን በመተው ሕገ ደንቡን በማይፈቅድለት መልኩ አለስልጣኑና አለቦታው በመግባት የቤተ ክርስቲያናችንና የኅብረተሰቡ ሰላም በሚነካ መልኩ በመንቀሳቀሱ ምክንያት ጉዳዩ ወደ ከፋ ሁኔታ ከማምራቱ በፊት በአጭሩ እንዲስተካከል በማለት በቅዱስ ፓትርያሪኩ መሪነት፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አመራሮች እና የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮች በተገኙበት ታላቅ ጉባኤ ተደርጎ ውሳኔዎችም አስተላልፏል፡፡ ማኅበሩ እስከ ዛሬ ድረስ ውሳኔውን አልቀበልም ብሎ ከመጻፍ ጀምሮ ማደራጃ መምሪያው ይኸው የቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ለመተግበር የሚያደርገው እንቅስቃሴም በተሳሳተ መልኩ በመተርጎም በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን መግለጹ ቀጥሎበት ይገኛል፡፡ የአሁኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም ሰላማዊ ሁኔታውን ለማወክ ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ወቅታዊ ሁኔታዎች ማደራጃ መምሪያው መግለጫ ለመስጠት ተገዷል፡፡

በመሆኑም፤

1.      የደን ጥበቃን በተመለከተ፡- ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚት ከመሆኗም በላይ አሁንም የተለያዩ መድረኮችን በመክፈት የአየር ብክለትን በመከላከል በዋናነት እየተንቀሳቀሰች ስለሆነ፤ በማደራጃ መምሪያው ሥር የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ከአሁን በፊት ችግኞችን በመትከል የቤተ ክርስቲያንና የሀገራችሁ ጥሪ አክብራችሁ በመታዘዝ ለሥራው መሳካት እንደተጋችሁ ሁሉ አሁንም በበለጠ መልኩ በዚህ ክረምት ችግኞችን በመትከል የነቃ ተሳትፎ እንድታደርጉ ማደራጃው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

2.     ቤተ ክርስቲያኒቷ የሥነ ምግባርና የመልካም ዜጋ መፍርያ ስፍራ እንደመሆኗ መጠን በሥሯ ያሉት ወጣቶች መንግሥት በነደፈው የአምስት ዓመት የልማትና የትራንፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዓባይ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዥ ከማድረግ አንሥቶ የደሞዝ ልገሳ፣ የሞራልና የጉልበት ድጋፍ በማድረግ ብሔራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ማደራጃ መምሪያው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

3.     ማደራጃ መምሪያው በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚደራጁትን ማኅበራት መቆጣጠርና ሕግ ማስያዝ ሥልጣኑ እንደመሆኑ መጠን ማኅበራትን በወጣላቸው ሕገ ደንብ መሠረት እንዲጓዙና በውስጣቸው ሃይማኖትን ተገን በማድረግ የፖለቲካ ዓላማ እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ዓላማ ያላቸውን ፀረ ሰላም ሀይሎችን በውስጣቸው ይዘው እንዳይጓዙ በውስጣቸው ካሉም አጥርቶ የማውጣት ሥራ እንዲሠሩ ማደራጃ መምሪያው ያሳስባል፡፡

4.     ማደራጃ መምሪያው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከሕግ ውጭ ለመሄድ የሚፈልጉ አካላት ደስተኞች ካለመሆናቸው የተነሳ ስጋት ስላደረባቸው በተለያዩ ዌብሳይቶች እና ሕትመቶች የማደራጃ መምሪያውን አካሄድ በተሳሳተ መንገድ በመፈረጅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ማደራጃ መምሪያው ማንኛውንም ማህበርም ሆነ ግለሰባዊ መልካም እንቅስቃሴ ለመግታት ወይም ለመገደብ ሳይሆን ሕግ ለማስያዝ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ የጣለችበትን ኃላፊነት ለመወጣት መሆኑ ታውቆ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትም ሆኑ ሌሎች አካላት ሕጋዊ በሆነ አካሄድ በማደራጃ መምሪያው ሥር ተመዝግበው ለሚጠየቁት ጥያቄ መልስ በመስጠት እንዲንቀሳቀሱ ማደራጃ መምሪያው ያሳስባል፡፡

5.     ማደራጃ መምሪያው ማኅበራትን ለመቆጣጠርና ሕግ ለማስያዝ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ከማደራጃው ጎን በመሰለፍ መረጃ በመስጠት የሞያ እገዛ በማድረግ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ሕግ መጠበቅ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማደራጃው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

6.     ማደራጃ መምሪያው የማኅበ ቅዱሳን ጤናማ ያልሆነ አካሄድ ለማስተካከል ቢያንስ ለአምስት ዓመታት እየታገለ እንደሆነና አሁንም በመታገል ላይ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ ማኅበረ ቅዱሳንን በሚመለከት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየደረጃው ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ መምሪያው ድረስ ያስተላለፈችው ውሳኔዎች እና መምርያዎች አንድም እንኳ ባለመተግበሩ ምክንያት ማደራጃ መምሪያው እጅግ እያዘነ አሁንም ማህበሩ በሕግ የማይመራ ከሆነ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከሚጠቅማት ይልቅ የሚጎዳት መሆኑን የማኅበሩ አባላት እንዲያውቁና እስከ አሁን ድረስ የሚሄድባቸው አካሄዶች ከሕግ ውጭ መሆኑን አውቀው አባላቱ በያሉበት ቦታ ሆነው ቅድሚያ ለማኅበር ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲሉ እንዲሠሩ ማደራጃ መምሪያው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

7.     ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና በሚጻረር መልኩ በአገልጋይና በተገልጋይ መካከል ለዘመናት የቆየውን ጤናማ ግንኙነት በሚያሻክር አኳኋን አለስልጣኑ በመግባትና የቤተ ክርስቲያን ሰንሰለታዊ መዋቅር በመጣስ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የተሐድሶ አዋጅ በስፋት እየተገበረ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን የእወጃ ተግባር ሥልጣንና ኃላፊነት ማዕከል ያላደረገ፣ ትውፊታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና የሚጥስ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ካለው ለሚመለከተው አካል ደረጃውን ጠብቆ ከማቅረብ ውጪ በራሱ ጊዜ ማወጅ አግባብ ባለመሆኑ ከዚህ ዓይነት ድርጊቱ እንዲቆጠብ ማደራጃ መምሪያው ያሳስባል፡፡

8.     ማህበረ ቅዱሳን በመምራት ላይ ያላችሁ የአመራር አባላት ልጆቻችን በሙሉ ምንም እንኳን እስከ አሁን የተወሰኑትን ውሳኔዎችን የተላለፉትን መምርያዎች ተቀብላችሁ ባትፈጽሙና ለመፈጸምም ፈቃደኛ አለመሆናችሁን በደብዳቤ ብትገልጹም አሁንም ማደራጃ መምሪያው አካሄዳችሁ ትክክል አለመሆኑን እየገለጸ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ቅዱስ ፓትርያሪኩ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከማደራጃ መምሪያው በየደረጃው የወሰነውን ውሳኔ እና መመሪያ ተግባራዊ እንድታደርጉ እያሳሰበ ይህ ሳይሆን ቢቀርም ማደራጃ መምሪያው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ሕግ ለማስከበር ሲባል ከበፊቱ የበለጠ እንቅስቃሴ የሚያደርግ መሆኑን እየገለጸ ማኅበሩንም በሕግ የሚጠይቅ መሆኑን በጥብቅ ያስታውቃል፡፡
                                            ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እግዚአብሔር አምላካችን ሀገራችንን በሰላም ሕዝባችንን በፍቅር አንድ አድርጎ ይጠብቅልን፡፡ አሜን

                   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
                        መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
                        የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
                            ግንቦት 23 ቀን 2003 ዓ.ም
                                 አዲስ አበባ
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)