May 29, 2011

(ሰበር ዜና) ብፁዕ አቡነ በርናባስ አረፉ

  • የብፁዕ አቡነ በርናባስ የቀብር ሥነ ሥርዐት ነገ ይፈጸማል
  •  "የትምህርት መጨረሻው መልካም ሥራ ነው፡፡" (ብፁዕ አቡነ በርናባስ)
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 29/2011)፦  ዛሬ ግንቦት 21 ቀን 2001 ዓ.ም ከሌሊቱ 10፡00 ግድም በድንገተኛ ሕመም በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ያረፉት የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ ሥርዐተ ቀብር ነገ ግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ.ም ረፋድ ላይ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት ባገለገሉበት በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ይፈጸማል፡፡ 

ግንቦት 16 ቀን ከተፈጸመው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ ግንቦት 19 ቀን በሀገረ ስብከታቸው መኪና ወደ ባሕር ዳር ያመሩት ብፁዕነታቸው ደብረ ማርቆስ ከተማ ሲደርሱ ድካም እንደሚሰማቸው በመግለጽ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና አድረው በበነጋው ጉዟቸውን ቀጥለው እንደ ነበር ተገልጧል፡፡ የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ብፁዕነታቸው በባሕር ዳር መንበረ ጵጵስናቸው ቅዳሜ ግንቦት 20፣ ከቀኑ 8፡00 ላይ ከደረሱ በኋላ ከምሽቱ 3፡00 ላይ ማረፋቸውን የስፍራው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የሰነበተ ሕማም እንደሌለባቸው፣ ግንቦት 16 ቀን የነበረውን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የመጨረሻ ቀን ውሎ ‹‹ሆዴን አሞኛል›› በማለታቸው ሳይሳተፉ መቅረታቸው ተጠቁሟል፡፡ ረቡዕ ግንቦት 17 ቀን ወደ ሕክምና የተወሰዱት ብፁዕነታቸው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈራል ተጽፎላቸው የነበረ ቢሆንም ‹‹ግዴለም፤ እዚያው ቤቴ ውሰዱኝ፤ ባሕርዳር ስደርስ እታከመዋለሁ›› በማለታቸው መንገድ መግባታቸውን እኒሁ ምንጮች  ያስረዳሉ፡፡ ብፁዕነታቸውን በመንበረ ጵጵስናቸው ተቀብለው ያሳረፏቸው የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ‹‹አልለዮትም›› ብለው ብፁዕነታቸውን ይዘው ባሕርዳር ድረስ መጓዛቸው ተመልክቷል፡፡ የብፁዕ አቡነ በርናባስ ዕረፍት እንደተሰማ የክልሉ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ከተወሰኑ የካቢኔ አባሎቻቸው ጋራ እሑድ ጠዋት በመገኘት ሐዘናቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
ለቀብሩ ሥነ ሥርዐት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከአምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ዛሬ ተሲዓት በኋላ ወደ ባሕር ዳር አምርተዋል፡፡ በባሕርዳር አየር ማረፊያ ‹‹ከ30 በላይ በሆኑ መኪኖች አቀባበል ተደርጎላቸዋል››ም ተብሏል፡፡ 

በየዓመቱ ጥቅምት ወር በሚካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አህጉረ ስብከታቸው ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በሚያደርገው ፈሰስ እና የራስ አገዝ ልማት ቀደምት በማድረግ የሚታወቁት ብፁዕነታቸው፣ ከግንቦት 10 - 16 ቀን 2003 ዓ.ም በተካሄደው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ያለልምዳቸው ባሰሙት ጠንካራ ንግግር የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆኖ በፓትርያርኩ አላግባብ በተሾመው ጌታቸው ዶኒ ላይ የተደረሰበት ውሳኔ እንዳይረጋ አቡነ ጳውሎስ የጉባኤውን አመራር ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ያደረጉበትን አካሄድ ተቃውመዋል፤ ‹‹የሲኖዶሱ አካሄድ ውኃ ወቀጣ ሆኗል፤ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር፣ ከግለሰብ ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን መወገን አይሻልም ወይ?››
በአህጉረ ስብከታቸው በቆሙበት ዐውደ ምሕረት ሁሉ፣ ‹‹የትምህርት መጨረሻው መልካም ሥራ ነው፤›› በሚለው ተደጋጋሚ ምክራቸውም ይታወሳሉ - ብፁዕ አቡነ በርናባስ፡፡

ጥቅምት 18 ቀን 1983 ዓ.ም በአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ ከተሾሙት አራት ኤጶስ ቆጶሳት(አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልስ፣ አቡነ መልከ ጼዴቅ) አንዱ የነበሩት ብፁዕነታቸው የዜማ እና የመጽሐፍ ዐዋቂ መምህር ነበሩ፡፡ በሐረር መድኃኔዓለም፣ በርእሰ አድባራት ቁሉቢ ቅዱስ ገብርኤል እና በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመሳሰሉት ታላላቅ አብያተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡  በማዕርገ ጵጵስናም በመጀመሪያ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ በመቀጠልም የምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃም እና የመተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በመጨረሻም እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው የመሩት የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል፡፡ አምላካችን ለብፁዕ አባታችን ዕረፍተ ነፍስን ሰጥቶ ከማኅበረ መላእክት፣ ከማኅበረ ጻድቃን ይደምርልን፡፡ አሜን፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)