May 24, 2011

የቅዱስ ሲኖዶስ ሰባተኛና የመጨረሻ ቀን ውሎ ርእሰ ጉዳዮች

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ
 (ደጀ ሰላም፤ ሜይ 24/2011)፦  
  •  ከግንቦት 10 - 16 ቀን 2003 ዓ.ም ለሰባት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ዛሬ ቀትር ላይ በማጠናቀቅ ከሰዓት በኋላ የዋና ጸሐፊውን ቃለ ጉባኤ በንባብ በማዳመጥ ተፈራርሟል፡፡ 
  • ፓትርያርኩ ነገ ግንቦት 17 ቀን 2003 ዓ.ም ጠዋት ሦስት ላይ ጋዜጣዊ ጉባኤ ጠርተዋል፡፡ ከጋዜጣዊ ጉባኤው ጋራ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተዋፅኦ በሚገለጽበት መድረክ ወረብ በአጫብር እና ቆሜ የያሬዳዊ ዜማ ይትበሃሎች ይቀርባል፤ ሊቃውንቱ ስለ ዐባይ እና ስለ ሕዳሴው ግድብ ቅኔ ያበረክታሉ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመመሪያ እና የድርጅት ሐላፊዎች፣ የአ/አ ሀ/ስብከት ሠራተኞች፣ የአ/አ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች እና ጸሐፊዎች የዝግጅቱ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
  • ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በ‹‹ልዩ ልዩ›› ርእስ ሥር ባስያዙት አጀንዳ የ30 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይ አቀረቡ፤ ከያዟቸው 30 ታሳቢዎች ቢያንስ  የዐሥሩ ዛሬ እንዲታይላቸው ምልአተ ጉባኤውን ጠይቀው ነበር፡፡
  •  አጀንዳው ‹‹በልዩ ልዩ ርእስ ሳይሆን ራሱን ችሎ መታየት ይኖርበታል›› ያለው ምልአተ ጉባኤው ‹‹የታሳቢ ዕጩዎቹን ማንነት ይፋ አድርጎ መረጃዎችን መሰብሰብና የካህናትን እና የምእመናንን ምስክርነት አስቀድሞ መቀበል›› አስፈላጊ መሆኑን በማስታወስ አጀንዳውን ለጥቅምት 2004 ዓ.ም የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ አስተላልፎታል፡፡
  • በትናንትናው ዕለት ከግንቦት እስከ ሐምሌ ሦስት ወራት እንዲያገለግሉ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስን፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስን እና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስን ወቅታዊው የቋሚ ሲኖዶስ አባላት አድርጎ የመረጠው ምልአተ ጉባኤው በዛሬው ዕለት ደግሞ ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ሦስት ወራት ድረስ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ይሆኑ ዘንድ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን፣ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስን እና ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን መምረጡ ታውቋል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ 1 እና አንቀጽ 12 ንኡስ 1 - 7 በየሦስት ወሩ አባላቱ የሚተኩለት እና በየዕለቱ የሚሰበሰበው ቋሚ ሲኖዶስ ሕግን የመተርጎም እና የማስፈጸም መብት፣ በምልአተ ጉባኤው የሚተላለፉ መመሪያዎችንና ልዩ ልዩ ጉዳዮች ተግባራዊ መሆናቸውን በየዕለቱ የመከታተል፣ የምልአተ ጉባኤውን መሰብሰብ የማይሹ አስተዳደር ነክ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የመወሰን፣ ከየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት የሚቀርቡትን ሪፖርቶች ተቀነባብረው ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርቡ የማድረግ፣ የቅዱስ ሲኖዶስን የመነጋገሪያ አጀንዳዎች የማዘጋጀት፣ አስቸኳይ እና ድንገተኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንዳስፈላጊነቱ እንዲካሄድ የመወሰን፣ ዓመታዊ በጀትን አጥንቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ የማስወሰን፣ ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወጭ እና ገቢ በበጀቱ መሠረት መሠራቱን የመቆጣጠር ሥልጣን እና ተግባር አለው፡፡
  • ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የቤቶች እና ሕንጻዎች አስተዳደር እና ልማት  ድርጅት እንዲሁም የዕቅድ እና ልማት መምሪያ የበላይ ሐላፊ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፤ ቀደም ሲል የነበሩበት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ለጊዜው ባሉት ዲን ቀሲስ በላይ ተገኝ እንዲመራ ተወስኗል፡፡ የደቡብ ምዕራብ አውሮፓው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በሌሉበት የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲመደቡ በቦታቸው የሶማሌ /ኦጋዴን/ ሀገረ ስብከት ብፁዕ አቡነ ሙሴ ተተክተዋል፡፡ አለመግባባታቸውን በዕርቅ የፈቱት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ወደ ቀድሞው የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀ/ስብከታቸው የተመለሱ ሲሆን ከጥቅምቱ ጉባኤ እስከ አሁን የቆዩበትን የወላይታ ሶዶ እና ዳውሮ ኮንታ አህጉረ ስብከት የደቡብ ኦሞው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ደርበው እንዲመሩ ተወስኗል፡፡
  • የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ዋና ሐላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ‹‹ሊያመልጣችሁ የማይገባ ወሳኝ እና ወቅታዊ መግለጫ›› በሚል ለበርካታ የመንግሥት እና የግል ብዙኀን መገናኛዎች ኀሙስ ግንቦት 18 ቀን 2003 ዓ.ም ጋዜጣዊ ጉባኤ መጥራታቸው ተሰምቷል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው አባ ሰረቀ ‹‹ለመመሪያው አይታዘዝም›› እያሉ በየመድረኩ በርካታ ክሦች የሚያቀርቡበትን ማኅበረ ቅዱሳንን በመወንጀል ላይ ያነጣጠረ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በበኩሉ የአባ ሰረቀ ማንነት እና አስተዳደር ለማኅበሩ ብቻ ሳይሆን ለመላዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የደቀነውን አደጋ በቀጣይነት በማጋለጥ ለመሠረተ ቢስ ውንጀላው ተመጣጣኝ ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ተገምቷል፡፡
  • አባ ሰረቀ ሳይገባቸው ሊቀዳጁት ያሰቡትን ማዕረገ ጵጵስና ያመከነው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ በአባ ሰረቀ እና በማኅበሩ መካከል የተፈጠረውን ችግር አጣርቶ ለሐምሌው ሲኖዶስ ወይም ለጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ የሚያቀርብ፣ የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በአስረጅነት እና የማኅበሩ ሁለት ተወካዮች በተጠያቂነት የሚገኙበት ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ በትናንቱ የቀትር በኋላ ውሎ ድካም እንደሚሰማቸው በመግለጽ ምልአተ ጉባኤው ወደ አጀንዳው በዝርዝር ገብቶ እንዳይነጋገር የተማፀኑት አቡነ ጳውሎስ ከብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የቀረበውን ግሩም ሐሳብ በመቀበል የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ አባላት እንዲሆኑ የተሠየሙት ከሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፤ ከሊቃውንት ጉባኤ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣ መጋቤ ሐዲስ ዓምደ ወርቅ፣ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል እና ከሕግ አገልግሎት አቶ ይሥሓቅ ናቸው፡፡
  • ‹‹ቅዱስ ሲኖዶስ አጣሪ ኮሚቴውን ከማቋቋም ጋራ መሠረታዊ የሃይማኖት እና የአቅም ችግር ያለባቸውን ዋና ሐላፊ አስወግዶ አልያም አግዶ የአጣሪ ኮሚቴው ትኩረት በዋናነት በመምሪያው እና በማኅበሩ መዋቅራዊ ግንኙነት ላይ እንዲሆን በማድረግ መሆን ነበረበት›› የሚል አስተያየት የሚሰጡ አንዳንድ ወገኖች፣ ቤተ ክህነቱ ችግሮችን በኮሚቴ የፈታባቸውን አነስተኛ አጋጣሚዎች በመጥቀስ (የሐዋሳውን በማስታወስ) ሁከት ፈጣሪው አባ ሰረቀ በሥልጣን ላይ እያሉ ችግሩ መፍትሔ የማግኘት ዕድሉ የመነመነ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም የማጣራቱን ሂደት - ማኅበረ ቅዱሳን በተቋማዊ አቅሙ ተጠናክሮ መቀጠሉ ለቤተ ክርስቲያን የሚኖረውን ስትራቴጂያዊ ፋይዳ የኮሚቴው አባላት ለሆኑት ሊቃነ ጳጳሳት እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተጨባጭ የሚያሳምንበት፤ የአባ ሰረቀን እና በአምሳላቸው የቀረጿቸውን ሎሌዎቻቸውን ትክክለኛ ማንነት በክምቹ ማስረጃዎቹ እያጋለጠ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን አደጋ በማስረገጥ ከቤተ ክህነቱ መዋቅር የሚያፈልስበት ወርቃማ አጋጣሚ አድርጎ እንዲጠቀምበት መክረዋል፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)