May 22, 2011

የቅ/ሲኖዶስ አራተኛ ቀን ውሎ (ሪፖርታዥ)

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ

  • ቅዱስ ሲኖዶስ ስብከተ ወንጌልን አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ አለመተግበሩ ተገለጸ፤ ስለ ፓትርያርኩ ሐውልት ሳይነሣ ታለፈ
  • ዋነኛው ችግር በመምሪያው አሠራር ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ነው፤
  • ሌሎች ያልተተገበሩ የሲኖዶሱ ውሳኔዎች “ወዘተርፈ እና ሌሎችም›› በሚል  ብቻ ከመወሳት በቀር በዝርዝር ቀርበው አለመገምገማቸው እያነጋገረ ነው፤
  • የሐዋሳው አጣሪ ኮሚቴ ጥናት እና የምእመናኑ አቤቱታ በሪፖርት ቀርቧል፤
  • በጨለማው ቡድን ኮሚሽን ተደርገው በስመ ‹ደኅንነት› የሚንቀሳቀሱ ጉልበተኞች የማዋከብ ተግባራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር ጠንካራ አቋም ካላቸው ብፁዓን አባቶች ጋራ ግንኙነት ያላቸውን አገልጋዮች በስልክ ያስፈራራሉ፤ በአካል በመከታተል ያዋክባሉ፡፡ መንግሥት ዜጎች ለሃይማኖታቸው መጠበቅ ለመቆም ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ መብት ሊያስከብርላቸው ይገባል፡፡
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 22/2011)፦ ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዳሜ ግንቦት 13፣ 2003 ዓ.ም አራተኛ ቀን ውሎው ስብከተ ወንጌልን አስመልክቶ በጥቅምት ምልአተ ጉባኤው ያስተላለፈው ውሳኔ በአግባቡ ተግባራዊ አለመሆኑን ገመገመ፤ ውሳኔው ተከብሮ እንዲሠራበት አሳስቧል፡፡

ያልተገባ ጥቅምን አማክለው የሚንቀሳቀሱ እና የቤተ ክርስቲያንን ዐውደ ምሕረት መነገጃ ያደረጉ ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ ያሳለፈበትን የወርኀ ጥቅምቱን ቃለ ጉባኤ እና ቀደም ሲል የወጣውን የስብከተ ወንጌል ደንብ ምልአተ ጉባኤው በንባብ አድምጧል፡፡ የሕገ ወጥ ሰባክያንን እና ዘማርያንን ስምሪት ለመከላከል የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በሚያከናውነው ተግባር ላይ በፓትርያኩ ጽ/ቤት የሚደረገው አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት የችግሩ ዋነኛ መንሥኤ መሆኑን ምልአተ ጉባኤው በደማቁ አሥምሮበታል፡፡


“ሀገረ ስብከት ቀርቶብኝ በመምሪያው የበላይ ሓላፊነቴ ተወስኜ ብሠራ እመርጣለሁ” በማለት አገልግሎቱ ከምንጊዜውም በበለጠ የሚሻውን የሙሉ ጊዜ ትኩረት ለምልአተ ጉባኤው ያስረዱት የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ “እኔ ሳግድ እርስዎ [ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ] ካልፈቀዱ ችግሩን በቀላሉ መከላከል ይቻላል” ብለዋል፡፡ ይህንና ሌሎች ተዛማጅ የስብከተ ወንጌል ችግሮችን የገመገመው ምልአተ ጉባኤው ለሁሉም አህጉረ ስብከት የተላለፈው የስብከተ ወንጌል ደንብ፣ በየካቲት ወር 2001 ዓ.ም እና በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤው በቋሚ ሲኖዶሱ የወጣው ውሳኔ ተከብሮ እንዲሠራበት፣ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሳያውቀው አንዳችም የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ  እንዳይኖር አሳስቧል፡፡ ከዚሁ አጀንዳ ጋራ በተያያዘ በቅርቡ ከነበሩበት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሥር ወጥተው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሕዝብ ግንኙነት ሥር እንዲዋቀሩ የተደረጉት የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ እና የልሳነ ተዋሕዶ ዘኦርቶዶክስ መጽሔት ኅትመቶች ዝግጅት ክፍሎች ቀድሞ ወደነበሩበት መዋቅር  እንዲመለሱ ቅዱስ ሲኖዶሱ ትእዛዝ መስጠቱ ተዘግቧል፡፡

ከስብከተ ወንጌል ባሻገር ሌሎች ያልተተገበሩ የቀደሙ የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔዎች(የአቡነ ጳውሎስን ሐውልተ ስምዕ መነሣት ጨምሮ) በምልአተ ጉባኤው አባላት ይሁን በአጀንዳ አርቃቂው ኮሚቴ፣ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው ይሁን የጥቅምቱ ጉባኤ የማስፈጸም አደራ በጣለባቸው ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዝርዝር ተወስተው አለመገምገማቸው ብዙዎች በጉባኤው ላይ የነበራቸውን ተስፋ ከወዲሁ ሊያመነምነው ጀምሯል፡፡ በአንዳንድ የስብሰባው ተከታታዮች ትዝብት፣ ፓትርያኩ የሲዳሞ ሀገረ ስብከትን እና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ያለውን የሥራ ግንኙነት ችግሮች የተመለከቱ አጀንዳዎች እንዳይያዙ አስቀድመው ተቃውሟቸውን ያከረሩት ቆይቶ እነዚያኑ የተቃወሟቸውን አጀንዳዎች በመቀበል የምልአተ ጉባኤውን አባላት ቀልብ እና የውጤታማነት አስተሳሰብ በእኒሁ ጉዳዮች ዙሪያ በማሰባሰብ /በመወሰን/ ለሌሎቹ ጉዳዮች ልብ እንዳይኖራቸው የማድረግ የሥነ ልቡና ጨዋታ ነበር፤ በትንቱ የምልአተ ጉባኤው አያያዝ ይኸው አጀንዳን አጉኖ በማሳረፍ /ወጥሮ በማርገብ/ አካሄድ የመደራደር ስልታቸው የሠራላቸው ይመስላል፡፡ ይሁንና ታዛቢዎቹ አያሌ ምልከታ የነበራቸውና ያልተተገበሩት የሲኖዶሱ ሌሎች ውሳኔዎች “ስብከተ ወንጌል እና ወዘተርፈ›› በሚል ብቻ መወዘት እንደማይገባቸው የምልአተ ጉባኤውን ተሳታፊዎች ያሳስባሉ፡፡

የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን የሥራ አፈጻጸም የገመገመው ምልአተ ጉባኤው ከቀትር በኋላ ውሎው በሐዋሳ ምእመናን በማስረጃ የቀረቡት የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ችግሮች እና ሁኔታውን ለማጣራት ለሁለት ጊዜያት የተላከው አጣሪ ኮሚቴ ያጠናቀረው ዘገባ በሪፖርት ቀርቦለት ተሰምቷል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ከተለመደው በተለየ አኳኋን ዛሬም (በእሑድ ሰንበት) ቀጥሎ በሚውለው ስብሰባው በቀረበው ሪፖርት እና በቀሪ አንገብጋቢ አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያይ ታውቋል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)