May 20, 2011

የቅዱስ ሲኖዶስ ሁለተኛ ቀን ውሎ፤ ከዕቅድ በላይ ወጪ የተደረገው 40 ሚሊዮን ብር አነጋጋሪ ሆኗል (ሪፖርታዥ )

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ

  • “በትእዛዝ ነው ይህን ያደረግነው”(የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ)፤
  • “የእግዚአብሔር ወይም የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ በሰማዩም በምድሩም  በሆነ ባልሆነው እንደባከነ” የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ ገልጧል፤
  • በዛሬ ጠዋቱ ስብሰባ ፓትርያርኩ የተቃወሟቸውን ሊቃነ ጳጳሳት በኀይለ ቃል ተናግረዋቸዋል፤ እየተካረረ በሄደው የስብሰባው መንፈስ “ነገር ያጦዛሉ” በሚል ጥርስ በተነከሰባቸው አራት ሊቃነ ጳጳሳት ላይ የሐምሌ 2001 ዓ.ም ዓይነት ጥቃት እንዳይደገም አስግቷል፤
  • “ጉባኤው በቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥርዐት መሠረት የፓትርያሪኩን ማንአለብኝነት በመግራት የቅዱስ ሲኖዶሱ የበላይነት ተከብሮ የተያዙት አጀንዳዎች ውጤታማ አመራር እንዲያገኙ ከማድረግ ሊዘናጋ አይገባም፡፡” (አስተያየት ሰጪዎች)
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 20/2011)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ረቡዕ ዕለት ባጸደቀው የ14 ዋና ዋና አጀንዳዎች ዝርዝር ቅደም ተከተል መሠረት ሐሙስ ረፋድ ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቀረበውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የስምንት ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት ላይ ተወያይቶ የማስተካከያ ሓሳቦችን በመስጠት አጽድቋል፡፡ ስለ ሪፖርቱ ዝርዝር ይዘት እና ስለተካሄደው ውይይት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በስምንት ወራት ውስጥ ብቻ በጽ/ቤቱ ከዕቅድ በላይ ወጪ ተደርጓል የተባለው ገንዘብ መጠን ለጉባኤው አባላት አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ የስብሰባው ምንጮች ለአንድ ግለሰብ ሕክምና ወጪ ከተደረገው ብር 150,000 ጀምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች የዋለው አጠቃላይ የወጪ ድምር 40 ሚሊዮን ብር  እንደሆነ ተወስቷል፡፡

ሁኔታው በተሰብሳቢዎቹ ዘንድ አነጋጋሪ እንደነበረ ተገልጧል፡፡ ይሁንና በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፡- የቤተ ክርስቲያኒቱን አጠቃላይ የምጣኔ ሀብት እና የሙዓለ ንዋይ መመሪያዎችን (ፖሊሲዎችን) የመወሰን፣ ዓመታዊውን በጀት የማጽደቅ እና ተግባራዊነቱን የመቆጣጠር ሥልጣን እና ተግባር ያለውን የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች የማስፈጸም ሓላፊነት ያለባቸው ፓትርያሪኩ፣ ዋና ጸሐፊው እና ዋና ሥራ አስኪያጁ በጉዳዩ ላይ የሰጧቸውን ማብራሪያዎች በተመለከተ በቂ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው ባያሳካም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ “በትእዛዝ ነው ይህን ያደረግነው፤ ያለምንም መነሻ እየታዘዝን ፈርሙ እንባላለን - እንፈርማለን፤” በሚል ለጉባኤው ማስረዳታቸው ተዘግቧል፡፡

በሚያዝያ ወር ለኅትመት የበቃውና በ1938 ዓ.ም እንደተጀመረ የሚነገርለት ዜና ቤተ ክርስቲያን የተሰኘው ጋዜጣ በቅርቡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች የተደረገውን ከ34 - 44 በመቶ (34-44%) የደመወዝ ማስተካከያ አስመልክቶ ባሰፈረው ርእሰ አንቀጽ፡- “ጥናቱን [የደመወዝ ማስተካከያውን/ማሻሻያውን] ያጸደቀውን አካልና አጥኚውን ክፍል ማመስገን ተገቢ ቢሆንም ወደ ሐቁ ስናመራ ግን የበለጠ ልናመሰግናቸውና ልንዘክራቸው የሚገባን የእግዚአብሔርን ወይም የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ በሰማዩም በምድሩም ሳያባክኑ በፈሪሃ እግዚአብሔር በጥንቃቄ ጠብቀው ያቁዩትንና የገቢ ምንጭ ፈጥረውልን ያለፉትን አባቶች ነው የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ልትንቀሳቀስ የቻለችበትን መላምት ፈጥረው ወይም ለትውልድ የሚተላለፍ ሥራ ሠርተው ባያልፉ ኑሮ ማሻሻያም እንበለው ማስተካከያ ዛሬ የደመወዝ ጭማሪ ከየት ይገኝ ነበር? ከጸፍጸፈ ሰማይ ወይስ ከውቅያኖስ?” ብሎ ነበር፡፡

የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ለወትሮው ከሚታወቁበት የፓትርያርኩ ዜና መዋዕል አጻጻፍ ትኩረታቸው በመቀነስ፣ ላለፈው ስሕተታቸው ‹ሕዝባዊ ንስሐ› (public confession) የገቡ በሚያስመስላቸው አኳኋን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ላይ እያጠናከሩት የመጡት የሰላ ሒስ የመሰንዘር ሂደት አካል በሆነው በዚሁ ርእሰ አንቀጽ በፓትርያርኩ ተገሥጸዋል፤ በውዳሴው ዘመን ለጋዜጣው ያልታሰበለት “ኤዲቶሪያል ፖሊሲ”ም እንዲዘጋጅለት ታዟል፡፡ ይሁንና የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ ሪፖርት የጋዜጣውን ርእሰ አንቀጽ አቋሞች በተጨባጭ አብነቶች በማረጋገጥ አሁን ያለው የአቡነ ጳውሎስ አስተዳደር የቤተ ክርስቲያኒቱን ፋይናንሳዊ አቅም ከማጎልበት፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን የምታጠናክርባቸውን እና የምታስፋፋባቸውን ተጨማሪ እሴቶች ከመፍጠር ይልቅ በሙስና እና በብኩን አሠራር ተዘፍቆ ተቋማዊ ሀብቷን እያሟጠጠ እንደሚገኝ ጉልሕ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ የሥራ ክንውን ሪፖርት ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተኩል ግድም ከመሰማቱ አስቀድሞ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ከትንት ለዛሬ ባደረው ሁለት አጀንዳዎችን ማጽደቅ አስመልክቶ በፓትርያኩ ኀይለ ቃል እና ማሸማቀቅ የተሞላበት የስብሰባ አመራር ሳቢያ በተካረረ መንፈስ ተሞልቶ እንደነበር የጉባኤው ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ከ2000 በላይ የሆኑ ምእመናን የአቤቱታ ፊርማ የተሰበሰበበትና ማክሰኞ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በመ/ፓ/ቅ/ቅ ማርያም ገዳም ቅጽር በንባብ የተሰማው የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ችግር በአጀንዳነት ተይዞ ለመወያየት እንደሚስማሙ የአቋም ለውጥ ያሳዩት ርእሰ መንበር አቡነ ጳውሎስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያን እና የማኅበረ ቅዱሳንን ግንኙነት አስመልክቶ በአርቃቂ ኮሚቴው የቀረበውን አጀንዳ ግን ከቶ ምን ሲደረግ፤ አልስማማም በማለት ተቃውመዋል፡፡

ማኅበሩ “የሐዋሳን ወጣት አሰባስቦ በአደባባይ አሰድቦኛል” ያሉት አቡነ ጳውሎስ “አጀንዳው እንዲታይ ከአባቶችም ይሁን ከሌላ የጠየቀ አካል የለም፤ ባለቤት የሌለውን አጀንዳ አናይም” በማለት ልዩነታቸውን አቅርበዋል፡፡ ይሁንና ማኅበሩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለሁሉም ብዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሰራጨው ደብዳቤ “ሓላፊነታቸውን አልተወጡም፤ የማደናቀፍ ሥራ እየሠሩ ነው” ባላቸው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊዎች ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰጥቶ በምትኩ ማኅበረ ቅዱሳንን ብቻ ሳይሆን በመላዋ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶችን ለመምራት፣ ለመቆጣጠር እና ለመከታተል የሚበቁ ሓላፊዎች እንዲመደቡ መጠየቁን ሊቃነ ጳጳሳቱ ለፓትርያኩ ያስታውሷቸዋል፡፡ የመምሪያው ሓላፊም ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስም “እንዴት አጀንዳው ባለቤት የለውም ይባላል? እኔ ቅዱስ ሲኖዶስ የመምሪያው የበላይ ሓላፊ አድርጎ ያስቀመጠኝ አለሁ አይደለም ወይ? እኔው ነኝ የምወክለው፤ ማኅበሩ ችግሩ መኖሩን በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል፤ ደብዳቤው በሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ቀርቦ ሊታይ ይችላል” በማለት ያስረዳሉ፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ እና የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ በሾማቸው ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ መካከል የ“ሓላፊ ነኝ - አይደለህም” ምልልስ በተጧጧፈበት ሁኔታ በፓትርያኩ አነጋገር እና ስብሰባ አመራር ክፉኛ ማዘናቸው የተነገረላቸው ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ፣ “የሚናገሩት ደግ አይደለም፤ ሥርዐት አይደለም፤ ከትንሽ እስከ ሀገር አቀፍ ስብሰባ ተካፍለናል፤ በስብሰባ ሥርዐት የውሳኔ አሰጣጥ እንኳንስ እኒህ ሁሉ አባቶች የደገፉትንና ከግማሽ በመቶ በላይ አንድ ጨምሮ [50+1] የሚቀርበውን ሐሳብ መቀበል አለብዎት”  በማለት ሊያርሟቸው ይሞክራሉ፡፡ ወዲያው ጉባኤው ዕረፍት ለማድረግ የተነሣ ሲሆን አቡነ ጳውሎስም ወንበር በማስወጣት በውጭ የመንበረ ፓትርያሪኩ /ፓላ/ ሜዳ ላይ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም ተነጥለው ለአንድ ሰዓት በዝምታ መቀመጣቸው ተመልክቷል፡፡

ከቆይታ በኋላ ከተቀመጡበት ተነሥተው ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ ሲገቡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም ተከትለዋቸው ከገቡ በኋላ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያን እና የማኅበረ ቅዱሳን ግንኙነት የተመለከተውን አጀንዳ መቀበላቸውን በመግለጻቸው ቀደም ሲል አጀንዳዎቹ በተያዙበት ቅደም ተከተል መታየት መጀመሩ ተነግሯል፡፡ ይኸው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና የማኅበረ ቅዱሳን ግንኙነት አጀንዳ በቀረበበት አኳኋን ሳይሆን በ11 ተራ ቁጥር መካተቱ ተመልክቷል፡፡ አሁን ባለው የስብሰባው አካሄድ ግን በቅደም ተከተል ወደኋላ የተቀመጡ አጀንዳዎች በአግባቡ የመታየት ዕድል እንደማይኖራቸው በመገመቱ ጉባኤው በቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥርዐት መሠረት የፓትርያኩን ማንአለብኝነት በመግራት የቅዱስ ሲኖዶሱ የበላይነት ተከብሮ የተያዙት አጀንዳዎች ውጤታማ አመራር እንዲያገኙ ከማድረግ ሊዘናጋ እንደማይገባ የስብሰባው ተከታታዮች ሐሳብ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን የስብሰባ ሥርዐት አንቀጽ 10 ንኡስ አንቀጽ 5/ሀ መሠረት እንዲህ ያሉት አስተዳደራዊ ጉዳዮች በአጀንዳነት ይያዙ ዘንድ ከተገኙት አባላት ከግማሽ በላይ በሆኑት መደገፍ ብቻ የሚበቃቸው ናቸው፡፡ በአንቀጽ 9 ንኡስ አንቀጽ 1 እና በአንቀጽ 15 ንኡስ አንቀጽ 2 መሠረት ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነው ፓትርያኩ ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት በአግባቡ የመምራት፣ ይህን በብቃት ማድረግ ካልቻሉ ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከመካከላቸው የሹመት ቅድምና ያለውን አባት መርጠው ርእሰ መንበር በማድረግ ስብሰባውን በጤናማ መንገድ የመቀጠል ሥልጣን እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡

ከተለያዩ ምንጮች እንደተሰማው ከስብሰባው ውጭ ለፓትርያኩ ያልተስማሙ የሚመስሉ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች እንዳይፈቱ በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና “ሊቀ ካህናት” ጌታቸው ዶኒ የሚደረጉ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ “ሊቀ ካህናት” ጌታቸው ዶኒ ራሳቸውን በራሳቸው “ቃለ መጠይቅ” አድርገው በሳምንታዊው አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ እንዲወጣላቸው ወደ ቢሮው ባመሩበት ወቅት ድርጊቱ ከጋዜጠኛነት አሠራር ውጭ መሆኑ ከተግሣጽ ጋራ ተነግሯቸው በምትኩ በዝግጅት ክፍሉ የተዘጋጀ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል ከተዘረዘሩት አጀንዳዎች አንዳንዶቹ (በተለይ የሲዳሞ ሀ/ስብከት ችግር) በምልአተ ጉባኤው እንዳይያዝ ግፊት ያደረጉት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ በመጪው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት በተለይም የሐዋሳ ምእመናንን ጥያቄ የሚያጣጥል እና ማኅበረ ቅዱሳንን የሚወነጅል፣ ነገር ግን ስሙ እንዳይጠቀስ ያሳሰቡበትን ቃለ ምልልስ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡


በሌላ በኩል የስብሰባው የተጋጋለ አካሄድ በቀጣይ የሚፈጥራቸው አዲስ ሁኔታዎች ያሰጋው የጥቅመኛ እና ጨለማ ቡድን ኮሚሽን የተደረጉ ኀይሎች “ውስጥ ለውስጥ ነገር ያጦዛሉ፤ ጳጳሳቱን ያሳድማሉ”  በሚል እንደ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ሊቀ ጳጳስ ዘኢየሩሳሌም፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እና ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ያሉ ብፁዓን አባቶችን ላይ እንደ ሐምሌ 2001 ዓ.ም ይነቱን ድርጊት የመፈጸም ጋት እንዳለ ተነግሯል፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)