May 19, 2011

የቅ/ሲኖዶስ መጀመሪያ ቀን ከሰዓት በኋላ ውሎ (ሪፖርታዥ)

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ። 
  • አቡነ ጳውሎስ የሲዳሞ ሀ/ስብከት ችግር እና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ያለው ግንኙነት በአጀንዳነት መያዙን ተቃወሙ
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 19/2011):- ትናንት ጠዋት የተጀመረው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በአጀንዳ አርቃቂነት የሠየማቸው ሰባት ሊቃነ ጳጳሳት(ብፁዕ አቡነ ናትናኤል - በሰብሳቢነት፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ - በፀሃፊነት፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እና ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአባልነት) ባቀረቧቸው ዘጠኝ አጀንዳዎች እና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የቀረቡ አምስት አጀንዳዎችን በአጠቃላይ ዐሥራ አራት የመነጋገሪያ ነጥቦችን ካቀረበ በኋላ በእያንዳንዳቸው ላይ ተነጋግሮ በማጽደቅ ወደ ውይይት እንደሚገባ ተጠብቆ ነበር፡፡ ከቀትር በኋላ በነበረው የስብሰባው ውሎ ግን ፓትርያርኩ ባልተስሟሙባቸው ሁለት አጀንዳዎች ሳቢያ ወደ ውይይት ሳይገባ ለዛሬ ለማሳደር ተገዷል፡፡


ትናንት በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የጉባኤውን አብዛኛውን ሰዓት የወሰደው፣ “የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ችግር በቋሚ ሲኖዶስ እየታየ በመሆኑ፣ ወደፊትም ስለሚታይ በምልአተ ጉባኤው ላይ መነሣቱ አስፈላጊ አይደለም” ባሉት በፓትርያርኩ እና “ችግሩ በራሳችን እየወሰንን እንድንሠራ ባለመደረጉ የመጣና ይፋ የወጣ” በመሆኑ መቋጫ እንዲበጅለት በሚሹ በብዙኀኑ የምልአተ ጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ከፍተኛ ክርክር በማስነሣቱ ነው፡፡ የኋላ ኋላ ፓትርያርኩ የብዙኀኑን ሐሳብ በመቀበል በአጀንዳው መያዝ የተስማሙ ቢመስልም ይህ አቋማቸው የዘለቀው ግን ከቀትር በኋላ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና በማኅበረ ቅዱሳን ግንኙነት ዙሪያ የተያዘው የአርቃቂ ኮሚቴው አጀንዳ ይጸድቅ ዘንድ እስኪቀርብ ነበር፡፡

“ስለ አጀንዳው ባለቤት ሆኖ የቀረበ አልያም ይያዝልኝ ብሎ የጠየቀ አካል የለም” በሚል የአጀንዳውን መያዝ ተቃውመዋል - ፓትርያርኩ፡፡ እንደወትሮው ሁሉ የትት በስቲያውንም የሐዋሳ ምእመናን ጠንካራ የአቤቱታ አቀራረብ “የማኅበሩ ተጽዕኖ በማያጣው አልያም ማኅበሩ ባቀነባበረው ተቃውሞ በአደባባይ ተሰድቤያለሁ” ብለው የሚያስቡት አቡነ ጳውሎስ ይህን አጀንዳ ለመቃወም ምክንያት እንደሚሆናቸው የጉባኤው ተከታታዮች ያስረዳሉ፡፡ በዚህ አቋማቸው በውስጥ እንደ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል እና ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ያሉት አባቶች ግልጽ ድጋፍ  በውጭ ጉዳዩ በአጀንዳነት እንዳይያዝ በማድረግ ‹ጀርባቸውን ለማዳን› ሲተጉ የዋሉት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ፣ የወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና “ሊቀ ካህናት” ጌታቸው ዶኒ ምክር እና ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እና የተቀሩት ብዙኅን የምልአተ ጉባኤው አባላት ጉዳዩን ማኅበረ ቅዱሳን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እንዲሁም ለእያንዳንዳቸው አስቀድሞ ባሰራጨው ደብዳቤ ላይ በማኅበሩ እና በመምሪያው መካከል እንደ ችግር ሆነው ያሉት ዋና እና ምክትል ሓላፊው እንዲነሡ መጠየቁ ለአጀንዳው መያዝ በቂ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ተከራክረው ነበር፡፡ የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል “ከተማሩት ልጆችዎ ጋራ ካልሠሩ ከማን ጋራ ሊሠሩ ነው” በማለት ፓትርያርኩን እስከ መማፀን ደርሰው እንደነበረም ተነግሯል፡፡ ሂደቱ በዚህ መልክ የጠበቀባቸው ፓትርያርኩ “እንዲህስ ከሆነ” በሚል ጠዋት በማንገራገር ተቀብለውት የነበረውን “የሲዳሞ ሀገረ ስብከትንም አጀንዳ አልስማማበትም” ወደሚል አቋም መጠቅለላቸው ተነግሯል - በታዛቢዎች አስተያየት ለፓትርያርኩ አንዱ አጀንዳ የሌላው ማፍረሻ አልያም ‹ከሁለቱ አንዱን ምረጡ› ይመስላል በሚል የፓትርያርኩን አቋም ያብራሩታል፡፡ ትናንት ከሰዓት በአቡነ ጳውሎስ የታየውን የአቋም አያያዝ በ2001 ዓ.ም ከተካሄደው የግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የነበራቸውን “የማንም አያዝዘኝም” አቋም ጋራ ተመሳስሎ የፈጠረባቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡

በዚህ መልኩ ማምሻውን ከተጠናቀቀው የጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ በኋላ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በተለያዩ ቡድኖች በመሆን ንት በስቲያኛ በሐዋሳውያኑ የተሰራጨውን የአንድ ሰዓት ከ18 ደቂቃ ቪሲዲ በመመልከት መመርመራቸው ተዘግቧል፡፡

ለጉባኤው የቀረቡት ዐሥራ አራት አጀንዳዎች ዝርዝር በጠቅላላው ሲታዩ፡-
1) የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጉባኤ መክፈቻ ንግግር፣
2) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት፣
3) የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ምርጫ፣
4) ማእከላዊነትን ያልጠበቀ አሠራርና ተግባራዊ ያልተደረጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፣
5) ዝውውር የጠየቁ ሊቃነ ጳጳሳት ጉዳይ፣
6) የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ጉዳይ፣
7) የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ እና የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ፣
8) በቅርቡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ጉዳይ፣
9) የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥራ አፈጻጸም፣
 10) የስብከተ ወንጌል ጉዳይ (በዚህ ውስጥ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አደጋ እና ያልተገታው የሕገ ወጥ ሰባክያን ጉዳይ አጀንዳ እንደሚሆን ተገምቷል)
11) ልማትን በተመለከተ፣
12) መንፈሳዊ ተቋማትን በተመለከተ፣
13)የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ/ ግንብ ግንባታን በተመለከተ እና
14) ልዩ ልዩ የሚሉ ናቸው፡፡

ጉባኤውን አስመልክቶ የመንበረ ፓትርያርኩ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ስታሊን ገብረ ሥላሴ ለሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ሬዲዮ በሰጡት መግለጫ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ከግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ጋራ በስልክ መወያየታቸውን፣ በውይይታቸውም ባለፉት ሳምንታት የግብፅ ሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን እና የግብፅ መንግሥት ልኡካን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ በተገናኙበት ወቅት ኢትዮጵያ ግብፃውያን ምርጫ አካሂደው መንግሥት እስኪመሠረቱ ድረስ የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን ስምምነት በምክር ቤቷ ከማጽደቅ ለማዘግየት የወሰደችውን አቋም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ማድነቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ባስተላለፍነው ዘገባ የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ጥያቄ ውድቅ የሆነው ከምልአተ ጉባኤው ስብሰባ በፊት በቋሚ ሲኖዶስ በተወሰደው አቋም ስለነበር ፓትርያርኩ ለምልአተ ጉባኤው በአጀንዳ እንዲያዙ ባቀረቧቸው አምስት ነጥቦች ውስጥ አለመካተቱን ከጉባኤው ምንጮች የእርምት ሐሳብ ተሰጥቷል፡፡

በጉባኤው ከ56 ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከ38 ያላነሱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በስብሰባው ተገኝተዋል፡፡ ከእኒህም ውስጥ በውጭ ካሉት 10 ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ሦስቱ (የካናዳው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ፣ የኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ እንዲሁም በሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል) ይገኙባቸዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በምልአተ ጉባኤው አለመሳተፋቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)