May 18, 2011

በቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ዋዜማ ምን ተከናወነ፣ ምን ይጠበቃል?

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።
  • የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የመክፈቻ ጸሎት ተካሄደ::
  • “የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ይግባኝ የለውም፤ የሚያወጣቸውን ሕጎች ሁሉም ተፈጻሚ የማድረግ ግዴታ አለባቸው” (ብፁዕ አቡነ ገሪማ)
  • ማልደው ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ የነበሩት የሐዋሳ ምእመናን መኪና ዱከም ላይ “በጸጥታ ምክንያት” በሚል ለአራት ሰዓታት በፖሊስ ታገተ፤ ከሰዓታት እገታው በኋላ ከተፈቀደላቸው ጥቂት ምእመናን በተጨማሪ በእግር በማቆራረጥ እና በተለያዩ ማጓጓዣዎች ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቅጽር ለመድረስ የቻሉት ምእመናኑ ተንበርክከው በማልቀስ ለሲኖዶሱ ስብሰባ የመክፈቻ ጸሎት ለተገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ለፓትርያርኩ ጥያቄያቸውን በንባብ አሰምተዋል፤ በጋሻው ደሳለኝ፣ ያሬድ አደመ፣ እጅጋየሁ በየነ እና ጌታቸው ዶኒ የፈጸሟቸውን በደሎች የሚያስረዳውን ቪሲዲ ለብፁዓን አባቶች እና ለምእመናን አሰራጭተዋል::  
  • ፓትርያርኩ “በአቡነ ገብርኤል ላይ ባላቸው ቂም እና ማኅበረ ቅዱሳንን ለመምታት” በሚል በሲዳሞ ሀገረ ስብከት ላይ ከሚያደርጓቸው አግባብነት የሌላቸው ድርጊቶች እና ተጽዕኖዎች እንዲቆጠቡ ምእመናኑ ቅዱስ ሲኖዶስን ጠይቀዋል፤
  • “ሊቀ ካህናት” ጌታቸው ዶኒ “የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን” እና “የቅን ልቦና የመንፈሳዊ እና ፈውስ አገልግሎት” የእምነት ተቋም መሥራች እና አባል ሆነው ሳለ ፓትርያርኩን በጭፍን ስለደገፉ ብቻ ሥራ አስኪያጅ ተደርገው መሾማቸውን እንቃወማለን፤ እንኳንስ ሥራ አስኪያጅ ሊሆኑ የእምነቱ ተከታይ አይደሉምና ተገቢው ሃይማኖታዊ ውሳኔ ይሰጥበት፤
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 18/2011)፦ የ2003 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የመክፈቻ ጸሎት ትናንት ማምሻውን በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተካሂዷል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ጨምሮ 29 ያህል ብፁዓን አባቶች በተገኙበት በዚሁ የመክፈቻ ጸሎት መጠናቀቂያ ላይ ቃለ ምዕዳን የሰጡት የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በኢየሩሳሌም ከተደረገው የመጀመሪያው የቅዱሳን ሐዋርያት ጉባኤ በመነሣት ያለውን የቅዱስ ሲኖዶስ ታሪካዊ አመጣጥ በስፋት አስረድተዋል፡፡ “የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጳጳሳት ናቸው” ያሉት ብፁዕነታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛው አስተዳደራዊ አካል እንደ መሆኑ “ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን ከእኛ የሚጠብቁትን ሐላፊነት በሕግ እና በሥርዐት መፈጸም ይገባናል” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ይግባኝ የሌለው” በመሆኑ የሚያወጣቸውን ሕጎች እና የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች ሁሉም ተፈጻሚ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በትምህርታቸው ማጠቃለያም ቤተ ክርስቲያን በመከናወን ላይ የሚገኘውን “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ/ግንብ ግንባታ በአንክሮ ታየዋለች፤ የበኩሏንም አስተዋፅኦ ታደርጋለች” ብለዋል፡፡

ከውጭ አህጉረ ስብከት በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ፣ የሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ከተገኙበት ከዚሁ የመክፈቻ ጸሎት በኋላ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅጽሩ ምሥራቃዊ በር ተንበርክከው እና አሰምተው እያለቀሱ ወደሚጠብቋቸው የሐዋሳ ምእመናን አምርተዋል፡፡ ምእመናኑ የመግለጫቸውን ቅጂ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ስም ጥቅም ስለሚያሳድደው የ“ተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማኅበር” ማንነት፣ ስለ ቀድሞው ሊቀ ጳጳስ እና ሥራ አስኪያጃቸው አስተዳደራዊ በደል፤ ያሬድ አደመ፣ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና በጋሻው ደሳለኝ በየጊዜው እየፈጠሩት ያሉትን ምእመኑን የማወክ እና የመከፋፈል ተግባር፣ የ“መናፍቁ፣ አጭበርባሪው እና ሽጉጥ ታጣቂው”ን የጌታቸው ዶኒን ማንነት እና በሥራ አስኪያጅነት መሾም የሚያሳዩ በሰነድ፣ ድምፅ እና ምስል የታገዙ ገለጻዎች ይገኙበታል፡፡ (ምእመናኑ ከዚህ በፊት ያቀረቧቸው አቤቱታዎች)


የምእመናኑ ተወካይ የብዙዎቹን ሰማዕያን ቀልብ በገዛ መልኩ በንባብ ባሰሙት መግለጫቸው፣ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የተሾሙላቸው ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ወደ ሀገረ ስብከታቸው እንዳይመለሱ፣ ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ መደረጉን ኮንነው ምክንያቱንም ያሬድ አደመ በሰጠው ቃል አስረድተዋል - “አንድም - ቅዱስነታቸው የቆየ ቂም በአቡነ ገብርኤል ላይ ስላላቸው፤ በሌላም በኩል - እኛን (ያሬድ፣ በጋሻው እና ጓደኞቹ) በማስደሰት እንደ ዱላ ተጠቅመው ማኅበረ ቅዱሳንን ለመምታት!!”

ከዚህ ጋራ በማያያዝ ምእመናኑ “እስከ መቼ ይሆን የሕዝብ ጥያቄ ሁሉ ‹የማኅበረ ቅዱሳን› የሚል ታፔላ እየተለጠፈበት እንዲቀበር የሚፈለገው? ለመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳንን እናንተ አይደላችሁም ወይ ዕውቅና የሰጣችሁት? የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው የሲዳሞ ሀገረ ስብከት አይመለከታቸውም እንዴ?” በማለት ጠይቀዋል፡፡ “እኛ የሀገረ ስብከቱ ምእመናን[ግን] ማኅበረ ቅዱሳን አለመሆናችንን ተረድታችሁ ቅዱስነታቸው ከሚፈጽሟቸው አግባብነት የሌላቸው ተፅዕኖዎች እና ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እንድታደርጉልን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን” ሲሉ ተማፅኗቸውን አቅርበዋል፡፡

በምእመናኑ ጥብዐት የተመላበት አቀራረብ የተቆጡና ምናልባትም በቅርብ ባለሟሎቻቸው መጋለጥ የተከፉ የሚመስሉት ፓትርያርኩም ብዙም ጎልቶ ባልተሰማው ንግግራቸው፣ “ከጓደኞቼ ጋራ አታጣሉኝ፤ ብቻዬን የወሰንሁት ነገር የለም፤ አሉባልታ ነው፤…ጥያቄያችሁን ቀስ ብለን እናየዋለን” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ብፁዕ አቡነ ማቲያስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ተንበርክከው የሚያለቅሱትን ምእመናን ተጠግተው በግልጽ ሲያረጋጉ የታዩ ሲሆን ከመክፈቻው ጸሎት እንደ ወጡ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ፣ ለእንግልት ተዳርጎ መጥቶ በፊታቸው ወድቆ የሚያለቅሰውን ምእመን ሐዘን በአባትነታቸው ዞረው ሳይመለከቱ እና ጆሮ ሳይሰጡ በቀጥታ ወደማረፊያቸው የሄዱ፣ ድንጋጤም የሚታይባቸው አባቶች እንደ ነበሩ ተዘግቧል፡፡

ዛሬ እንደሚጀመር በሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አጀንዳዎችን ለማርቀቅ ባለፈው ሳምንት ዓርብ እና ትናንት ስብሰባ የተቀመጠው ቋሚ ሲኖዶስ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም እና ለሹመቱ ባቀረቧቸው ቆሞሳት/መነኮሳት/ ዝርዝር ላይ መነጋገሩ ተሰምቷል፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጋራ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስን፣ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆምን፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስን እና ብፁዕ አቡነ ዳንኤልን በያዘው በቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ የቀረበው የፓትርያርኩ የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት አጀንዳ ጠንካራ ተቃውሞ እንደ ገጠመው ተመልክቷል፡፡

በጥቂት የመንበረ ፓትርያርኩ ታዛቢዎች አስተያየት፡- የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እና የሥራ ክፍሎቿ ከመስፋፋታቸው፣ ጥቂት የማይባሉ አባቶች በሞተ ዕረፍት በመለየታቸው አንዳንድ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አህጉረ ስብከትን ደርበው እያስተዳደሩ መሆናቸው ለአሠራር ከሚፈጥረው ጫና፣ ከዕርግና እና ሕመም የተነሣ ዝውውር እና ዕረፍት የሚሹ አባቶች እንዳሉ መነገሩ የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳትን ጥያቄ አግባብ ያደርገዋል፤ ጉዳዩን የመመዘን እና የመወሰን ሥልጣንም “የቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው” ይላሉ፡፡

የእኒህን ሁኔታዎች ነባራዊነት የሚቀበሉ ሌሎች ወገኖች ደግሞ የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳቱን ሹመት አስፈላጊነት ቢቀበሉም “ይሁንና ወቅቱ አይደለም” በማለት ይቃወማሉ፡፡ ለእነዚህ ወገኖች ተጨማሪ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ከመፈጸሙ በፊት ከሚከተሉት አማራጮች ቢያንስ አንዱ ተፈጻሚ መሆን ይኖርበታል፡፡ የ1991 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ከወቅቱ ችግር አንጻር - የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥልጣን እና ተግባር እንዲሁም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደራዊ መዋቅር ከመ ጤፍ የማይቆጥረውን የአቡነ ጳውሎስን ዐምባገነናዊ አሠራር ለመግታት፤ ከዘለቄታው አኳያ - የተተኪውን ፓትርያርክ እና ለኤጲስ ቆጶስነት ሹመት የተገቡ መነኮሳትን ምርጫ በተጨባጭ ለማከናወን የሚያስችል አሠራር በዝርዝር ሊያመላክት በሚያስችል አኳኋን ማሻሻልን እንደ ቀዳሚ አማራጭ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያዳግት ከሆነ በዚሁ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 16 ንኡስ አንቀጽ 1/ሀ - ሐ እንደ ተደነገገው፡- በ18 ዓመት ዘመነ ፕትርክናቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን ቀኖና ባለመጠበቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፉ ተግባራትን በመፈጸም በምሬት የሚነገርባቸው፣  በአጠቃላይ በካህናት እና ምእመናን ዘንድ በታማኝነታቸው እና መንፈሳዊ አባትነታቸው ተቀባይነት እያጡ መሆናቸው እየተረጋገጠባቸው የሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከሥልጣናቸው ተገልለው በምትካቸው ሌላ ተመርጦ እንዲሾም ይጠይቃሉ፡፡

ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ በፓትርያርኩ የቀረበው የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት አጀንዳ አቡነ ጳውሎስ በቋሚ ሲኖዶሱ እና በምልአተ ጉባኤው ተግዳሮት እየገጠመው የመጣውን ተጽዕኗቸውን ሚዛን ከማስጠበቅ ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው እኒህ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም በላይ በፓትርያርኩ ከታሰቡት ተሿሚዎች ጥቂት የማይባሉት በሥነ ምግባር ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም አለባቸው የሚባለው ነቅ ሲታይ ጉዳዩን የተጽዕኖ ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ ህልውና እና ማንነት ቀጣይነት ጥያቄ ያደርገዋል፤ “ነገ በቅዱስ ሲኖዶስ መንበር ተቀምጠው ሕግ የሚያወጡት፣ ዐበይት ውሳኔዎችን የሚያሳልፉት፣ ሌሎች ኤጲስ ቆጶሳትን እና ካህናትን የሚሾሙት የዛሬዎቹ ‹ምርጦች› ናቸውና፡፡”

በየጊዜው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ ባለመሆናቸው ሳቢያ የምእመናን ግፊት የበረታበት ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርኩን እና በየደረጃው ያሉ ሐላፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ መጀመሩም አቡነ ጳውሎስ እንዲህ ያሉ አወዛጋቢ አጀንዳዎችን እንደ ማስቀየሻ ስልት (diversionary tactic) እንዲፈጥሩ ሳያስገድዳቸው እንደማይቀር እኒሁ ወገኖች ይገምታሉ፡፡ ለዚህም በጉልሕ ማሳያነት የሚጠቅሱት የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ይዞታ ያሳሰባቸው ታዋቂ ምእመናን ከረዥም ቀጠሮ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ ከፓትርያርኩ ጋራ ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት ያጋጠመው ሁኔታ ነው፡፡

ታዋቂ ምእመናኑ ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በየጊዜው የሚሰሙት ነገር እንደሚያስጨነቃቸው፣ በፓትርያርኩ ዙሪያ ያሉት ሰዎች ማንነት እንደሚያሳስባቸው እና የመሳሰሉትን ነጥቦች በመዘርዘር ፕሮቴስታንታዊው-የተሐድሶ-ኑፋቄ የደቀነውን አደጋ በአስረጅነት ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ አነጋገር አቡነ ጳውሎስ በእጅጉ በመቆጣት “ተሐድሶ በተጨባጭ የሌለ የማኅበረ ቅዱሳን ፈጠራ ነው” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ ታዋቂ ምእመናኑ በአቡነ ጳውሎስ ቁጣ ሳይደናገጡ “የተሐድሶ ኑፋቄ እውነት ነው፤ ተሐድሷዊ ኑፋቄማ አለ” በማለታቸው ከአቅራቢያቸው ከሚገኘው ድልብ ዶሴ ሁለት ገጽ ያለው ሰነድ ስበው አወጡ፤ ሰነዱ በራስጌው ልሙጥ ሆኖ በግርጌው “የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊን ስም እና ፊርማ ከማኅበሩ ማኅተም” ጋራ ይዟል፡፡ “እነርሱ ልጆቼ ናቸው፤ ባርኬ፣ አሳድጌ፣ በእኔው ጊዜ ሕንፃ እና ሀብት አፍርተው ተመልሰው በእኔው ላይ ተነሡብኝ፤ ይህ ሰነድ ማኅበሩ የእኔ በሚላቸው ጳጳሳት ሲኖዶሱን በመቆጣጠር የራሱን ፓትርያርክ ለመሾም ያወጣውን የ25 ዓመት ዕቅድ ያሳያል” - ተናገሩ ፓትርያርኩ፡፡

ሰነዱ ከታዋቂዎቹ ምእመናን በአንዱ ለሁሉም በንባብ ከተሰማ በኋላ ግን “ለወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን በምን መልክ ግዴታችንን እንወጣ፤ ምን እናግዝ፤ ምን እንርዳ” የሚል ተልእኮ ከመንፈሳዊ አባታቸው ለመቀበል በመጡቱ የውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጥ ሊደበቅ የማይችል፣ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚጋባ የኀፍረት ስሜት ነገሠ፡፡ በፓትርያርክነታቸው ርእሰ አበው በመሆን ውስብስቡን/ጥልቁን ይመረምሩ ዘንድ በከፍተኛው መንፈሳዊ ማዕርግ የተቀመጡ አባት እንዲህ ያለውን የፈጠራ ሰነድ ለከባድ ክሳቸው ማስረጃ አድርገው በማቅረብ መገመታቸው እና መቅለላቸው በእውነትም አንገት የሚያስደፋ ነበር፡፡ ወሬው ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች ከደረሰ በኋላ ማኅበሩን በሒስ በመጎንተል የሚታወቁ አንድ አባት  የፓትርያርኩን “ማስረጃ” “የማኅበሩን ወዳጆች ይቅርና ጠላቶቹን ሳይቀር ያሳዘነ እና ያላሳመነ” ሲሉ ድርጊቱ ባለማወቅ ያይደለ ይሁነኝ ተብሎ የሚፈጸም እንደ ሆነ በመግለጽ የተሰማቸውን ብስጭት መግለጣቸው ተሰምቷል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የኤጲስ ቆጶሳቱን ሹመት አምርረው የሚቃወሙ ወገኖች ሁኔታው በራሱ አሳዛኝ ቢሆንም መልካም አጋጣሚነቱንም ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡ ይኸውም ፓትርያርኩ “ስለ ልዩ ልዩ ድርጅቶች እና ማኅበራት ጉዳይ” በሚል ለማስያዝ በጣሩት አጀንዳ ሰነዱን  እንደ ዱብ ዕዳ አቅርበው “ድንገተኛነትን” በማትረፍ - አንድም የተሰብሳቢዎቹን አባቶች ቀልብ ለጥጦ እና ወጥሮ ትኩረታቸውን ከዋናው አጀንዳ ለመክፈል ያላቸው የማስቀየሻ ዕቅድ አስቀድሞ በመታወቁ፤ ከተሳካላቸውም “እኔው አሳድጌዋለሁ፤ እኔው ቀብሬው እሄዳለሁ” እያሉ እንደሚዝቱበት የሚነገረውን ማኅበር ለማፍረስ ሰነዱ ያለው ጉልበት በመክሸፉ፣ የመንግሥትም አካል ይህን ያረጋገጠበት ዕድል በመፈጠሩ ነው፡፡

ይህ ዜና እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ታዋቂ ምእመናኑ የተጭበረበረውን ሰነድ የትመጣ አጣርተው የፈጠራ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ከፓትርያርኩ ጋራ የተቋረጠውን ውይይታቸውን ዳግመኛ ለመቀጠል በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ትናንት ከቀትር በኋላ የቅዱስ ሲኖዶስን ስብሰባ አስመልክቶ ለኅትመት በበቃው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ልዩ እትም ላይ “በእንተ ጦማረ ሐሰት” በሚል ርእስ ማኅበሩ በሰጠው መግለጫ ሰነዱ “ድንግል ማርያም” በተሰኘ ፌስ ቡክ ላይ የተገኘ መሆኑን ገልጧል፡፡ የሃያ ዓመት የአገልግሎት ልምድ ያዳበረው ማኅበረ ቅዱሳን በ55 ገጾች ያዘጋጀው፣ ለሚመለታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት በማሳወቅ የሚተገብረው የአራት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ ያለው መሆኑን ያመለከተው መግለጫው የሐሰት ሰነዱ በይዘቱ ይሁን በገለጻው በምንም ዐይነት የማኅበሩ እንዳልሆነ በራሱ የሚያረጋግጥ እንደሆነ አሳውቋል፡፡ ማኅበሩ ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች ጋራ በመቀናጀት ፀረ-ተሐድሶ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን መግለጫው አስታውሶ የሐሰት ሰነዱ በፀረ-ተሐድሶው እንቅስቃሴ “ማምለጫ እስኪያጡ ድረስ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት፣ በመሸማቀቅ በቁማቸው ያለቁት፣ ሳያስቡት የመጣባቸውን እውነት ለመጋፈጥ የሚያስችል ተክለ ሰውነት ያጡት የመልካም ዘር ፀሮች የሆኑ የሃይማኖት ጠላቶች ሤራ” እንደ ሆነ አመልክቷል፡፡

የሹመቱ ተቃዋሚዎች ሌላው ስጋት በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙት አባቶች ጋራ በተጀመረውና በቅርቡ ዳግመኛ እንደሚቀጥል በሚጠበቀው የእርቅ ሂደት ላይ የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ይኖረዋል የሚሉት የአደናቃፊነት ሚና ነው፡፡ በዕርቁ ሂደት የተጨማሪ ሹመት አለመፈጸምን እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል የሚባለው አካል በዚህ ሳቢያ በሚወስደው ተመሳሳይ ርምጃ በተስፋ የሚጠበቀው የቤተ ክርስቲያን አንድነት ጨርሶ ሊከስም እንደሚችል ተፈርቷል፡፡ ቀድሞም ቢሆን ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለዕርቁ ሂደት ያላቸው አዎንታዊ አቋም የእምነት ሳይሆን በሲኖዶሱ አንጋፋ አባላት ጫና ላይ የተመሠረተ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ እንደ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ያሉት ግለሰቦች ዕርቁን በመቃወም ፓትርያርኩ አስቀድመው በአገር ቤት ባሉት አባቶች ተጽዕኗቸውን እንዲያጠናክሩ በመምከር አሉታዊ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ተገልጧል፡፡

በቅርቡ የተደረገውን ማስተካከያ መሠረት በማድረግ በጵጵስና ማዕርግ ላሉት አባቶች እስከ ብር 5000 ደመወዝ እንደሚከፈል የሚጠቅሰው የተቃዋሚዎቹ አስተያየት፣ በአሁኑ ወቅት በቁጥር እስከ 30 ይደርሳሉ ለሚባሉት አዲስ ተሿሚዎች ያለውን በጀት የመመደብ አቅም፣ ከማዕረጉም ከፍተኛነት አኳያ የሚመጥን የማረፊያ ቤት/መንበረ ጵጵስና/ መሰናዶ እና ውጤታማ የሥራ ክፍሎች ዝግጅት መደረጉ ያጠራጥራቸዋል፡፡ በአባቶች ሞተ ዕረፍት፣ ዕርግና እና ሕመም ሳቢያ ክፍተት የተፈጠረባቸውን አህጉረ ስብከት ጨምሮ መመሪያዎችን፣ ድርጅቶችን፣ ታላላቅ ገዳማትን እና አድባራትን ሳይቀር ፓትርያርኩ ባቀረቧቸው ተሿሚዎች እንዲመሩ መታሰቡ ነው የሚነገረው፡፡

በሌላ በኩል “ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት እጥረት የለባትም” በሚል የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳቱን ሹመት የሚቃወም የአባቶች አስተያየት ተደምጧል፡፡ በእኒህ አባቶች አስተያየት በፓትርያርኩ ተመርጠው ከመጡት ጥቂት የማይባሉቱ በተለያዩ አህጉረ ስብከት ምዝበራ ሲፈጽሙ፣ ምእመናንን ሲከፋፍሉ እና ሲበጠብጡ የነበሩ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈውን ውሳኔ (የአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ ተነሥቶ በሙዝየም እንዲቀመጥ መወሰኑን) በመቃወም ሲያሳድሙ የነበሩ፣ የሥነ ምግባሩ ነገር ይቆየንና በቂ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እና አገልግሎት እንኳ የሌላቸው ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ይኸው ከፍተኛ ማዕርግ እንደ ጥንቱ ሥርዐት ተሿሚዎቹ መነኮሳት ባገለገሉባቸው እና እነርሱን በቅርበት በሚያውቁ ካህናት እና ምእመናን “አኪዎስ አኪዎስ /ይደልዎ ይደልዎ/” ያልተባለበት፣ “ከበጣም መጥፎ” የሚያስመርጡ ጥቂቶች ቢኖሩበት እንኳ በአብዛኛው በክፉ ለታወቁ አባቶች መሰጠቱ የሲኖዶሱን ክብር በማሳነስ፣ የሹመቱን ፈላጊዎች ጽነት በቀጣይነት ወደ አቡነ ጳውሎስ በማድረግ ዐምባገነንነታቸውን ስለሚያጠናከር መጥፎ አርኣያነት እንደሚተው ያስጠነቅቃሉ፡፡

የመጨረሻዎቹን አስተያየት ሰጪ አባቶች ሐሳብ የሚጋሩ የሚመስሉት ከቋሚ ሲኖዶሱ አባላት መካከል አንዳንዶቹ (ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል) ብፁዕ አቡነ ማቲያስ በአንድ ወቅት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የተናገሩትን በሚያስታውስ አኳኋን “ያለነውስ መቼ ሠራንላትና ነው ሌላ የሚሾመው?” እስከማለት መድረሳቸው ተሰምቷል፤ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ እና ብፁዕ አቡነ ፊልጶስም “በዝምታ (ድጋፍ ባለመስጠት) ተቃውመውታል” ተብሏል፡፡ የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ባለፈው ሳምንት ዓርብ እና ከትናንት በስቲያ ሰኞ ባደረጉት ተደጋጋሚ ውይይት አጀንዳውን እንዳልተቀበሉት ከታወቀ በኋላ ጉዳዩን ምልአተ ጉባኤው በሚሠይማቸው የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ አማካይነት ለማስገባት በፓትርያርኩ እና በተሿሚዎች ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ አጀንዳውን በከፍተኛ ደረጃ ሊቃወሙ ይችላሉ በተባሉት የተመረጡ አባቶች (ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል) ላይም በውስጥ እና በውጭ ከወዲሁ “የሚያከላክሏችሁ፣ ሌላውን የሚያሳድሙባችሁ እነኝህ ናቸው” በሚል የአሉባልታ ዘመቻ እና ሥነ ልቡናዊ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑ ተገልጧል፡፡

በዚሁ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በሲዳማ ጌዴኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት እና በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ያልተቋጩት አስተዳደራዊ ችግሮች ሌሎች የመነጋገሪያ አጀንዳዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ቋሚ ሲኖዶስ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከትን ቤተ ዘመዳዊ አሠራር፣ የሙስና እና የሥነ ምግባር ችግር ለማጣራት የላካቸውን ሦስት ልኡካን ሪፖርት ተመልክቶ ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ “ሥራ አስኪያጅነቴ ከቆመ ቆይቷል፤ የኔን ሥራ የሚሠሩት አባ ጳውሎስ ናቸው” እስከማለት ደርሰው የተማረሩበት፣ የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከሓላፊነታቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ እስከ ማቅረብ ደርሰው የወሰኑበት የሐዋሳው ችግር አያያዝ ከፍተኛ የስብሰባው አጀንዳ እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡ 

ብፁዕ ዋና ጸሐፊው የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው ወደ ሀገረ ስብከታቸው ዞር ባሉበት የትንሣኤ በዓል ሳምንት ቋሚ ሲኖዶስ የመረጠውን ወደ ጎን በማለት ገለጻ በማያሻው አኳኋን ግዙፍ የሃይማኖት፣ የሥርዐት እና የምግባር ችግር ያለበት “ሊቀ ካህናት” ጌታቸው ዶኒ በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ትእዛዝ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ፊርማ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ መሾሙ ችግሩ መፍትሔ እንዳያገኝ ያለውን የጠነነ ፍላጎት ማሳያ ሆኗል፡፡ ይህን ተከትሎ “ሊቀ ካህናት” ጌታቸው ዶኒ ወደ ሐዋሳ በማምራት በየቢሮው በመዞር የተሾመበትን ደብዳቤ ቢያሳይም ቀናዕያን ምእመናኑ ከጥንቱም እምነቱ የሌላ የሆነ ከሐዲ ሊመራቸው እንደማይችል ለክልሉ መንግሥት በተጨባጭ በማስረዳት ወደ የትኛውም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለመግባት ቢሞክር የመጨረሻውን ርምጃ እንደሚወስዱበት ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል፡፡ ስለ እርሱ እና የክሕደት አጋሮቹ ማንነት የሚገልጡ በርካታ ማስረጃዎችም በሐዋሳ፣ ዲላ፣ ይርጋለም እና ነገሌ ቦረና ከተሞች ለምእመናን አቅርበዋል………….የተባለ የጡመራ መድረክም ችግሩን የሚያስገነዝቡ፣ ምእመናን በአንድነት እንዲነሡ ጥሪ የሚያቀርቡ የተለያዩ ጽሑፎችን በማስነበብ ላይ ይገኛሉ፡፡

“ሊቀ ካህናት” ጌታቸው ዶኒ
“ሊቀ ካህናት” ጌታቸው ዶኒ ለሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሐላፊ በእጅ የጻፉት እና ሐላፊው በያዙት ሥልጣን አማካይነት በሰንበት ት/ቤቶች የተደራጀውን ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ለፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ለማመቻቸት የወጠኑትን ሐሳብ የያዘ ሰነድ በደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ መነበቡ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመምሪያው ሐላፊ “የጥናት ጽሑፍ” በሚል በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያዘጋጁትን ባለ25 ገጽ ከመጋቢት 22 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለክፍለ ከተማው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ አስተባባሪዎች፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ እና ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሠራተኞች በማቅረብ የውንጀላ እና የብጥብጥ አፋልጉኝን ዘመቻቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ታውቋል፡፡

ሐላፊው በቅርቡ በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ስም እና ፊርማ በማስመሰል የተሰራጨው የፈጠራ ሰነድ ከያዛቸው መልእክቶች ጋራ አንድ እና ያው የሆነና በስመ ጥናት የሚያሰሟቸውን ውንጀላቸውን ባካሄዱባቸው መድረኮች ሁሉ ጥቂት ደጋፊዎችን ባያጡም በአመዛኙ ኀፍረት የሚያከናንብ የተሳታፊዎች አስተያየት እንደገጠማቸው ተመልክቷል፡፡ “ለማኅበሩ ከለላ ይሰጣሉ፤ ከማኅበሩ ደመወዝ ይከፈላቸዋል” ያሏቸውን አባቶች (ያረፉትን ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅን ጭምር) እና ሐላፊዎች ሳይቀር ወርፈዋል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ያጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ “ማኅበሩን ሌላው ቤተ ክህነት በማድረግ ገቢዋን ጠቅልሎ እንዲወስድባት አድርጓል” በሚል “ምን ዐይነት ሲኖዶስ እንደነበረ አላውቅም፣ እንዲህ ዐይነት ደንብ ማጽደቅ አልነበረበትም” በማለት መዋቅሩን በንጽጽር እያቀረቡ ተችተዋል፡፡ መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በቆረጣ የተወሰነውን ባለአምስት ነጥብ (ማኅበሩ በቤተ ክህነቱ ሞዴላሞዴል እንዲጠቀም በገዛ ሥልጣናቸው ስድስተኛ አድርገው የጨመሩትን በማከል) “እኔ ስድስቱ ቃላተ ወንጌል ብዬ የምጠራቸውን እኒህን ውሳኔዎች ማስፈጸም ዋነኛ ዕላማችን ነው” ብለዋል፡፡

“ማኅበረ ቅዱሳን የሠራውን ያህል መምሪያው ሠርቷል ወይ? ሥራን በሥራ መቃወም አይበጅም ወይ? በየዓመቱ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከሚቀርበው የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ውስጥ ማኅበሩ አገልግሎቱን የማይፈጽምበት የሀገሪቱ ክፍል እንደሌለ ተረድተናል፤ መምሪያው ግን ሰንበት ት/ቤቶችን ያላደራጀባቸው አጥቢያዎች በርካታ ናቸው፤ ይልቅዬ ለምን በአጠቃላዩ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ በድክመት በተገመገማችሁባት በዚህች የማደራጀት እጥረታችሁ ላይ አተኩራችሁ በመመካከር አትሠሩም? በአንድ በኩል በየቦታው ያለውን ብጥብጥ ማኅበረ ቅዱሳን ነው የሚያሥነሳው ትላላችሁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተሐድሶን መኖር ትክዳላችሁ፤ እናንተ ልትቆጣጠሯቸው ሲገባ ልትመሯቸው ያልቻልችኋቸው ብዙ ሺሕ የወጣት ማኅበራት እያሉ በብጥብጡ የተሐድሶዎች እጅ ስላለመኖሩ ወይም እንደ አነጋገራችሁ የሚበጠብጠው ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ስለ መሆኑ እንዴት ርግጠኞች  ሆናችሁ? ማኅበረ ቅዱሳን እኮ በዚሁ በእኛው ቤት ያለ፣ ቢሳሳት ልናርመው የምንችለው ልጃችን ነው፤ ይህስ ይሁን - ማኅበረ ቅዱሳንን ለመቃወም ከተሐድሶዎች ጋራ መተባበሩ ለምን አስፈለጋችሁ? እኛን ምን አድርጉ ትሉናላችሁ፤ ማኅበረ ቅዱሳን አጥፍቷል ካላችሁ ለምን እዚያው ደንቡን አጽድቆ ከሰጠው ሲኖዶስ ጋራ ተነጋግራችሁ ርምጃ አትወስዱም?” የሚሉ ጥያቄዎች በአብዛሃዊ መድረኮች ለሓላፊው የቀረቡ ጥያቄ አዘል ተቃውሞዎች ነበሩ፡፡

የመምሪያው ሓላፊ ግን በዚሁ ካፈርሁ አይመልሰኝ ሳይሉ ማኅበሩ ከሌሎች የአገልግሎት ማኅበራት ጋራ በመተባበር የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ንቅናቄው በመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴው የደረሰበትን ገመገም (አድማስ) ቁልጭ አድርጎ በሚያሳይ አኳኋን ሰፋፊ ዐውደ ጥናት ነክ ጉባኤያት ባካሄደባቸው ሕዝባዊ መድረኮች ፈቃድ የሰጡትን መንግሥታዊ ባለሥልጣናት ጭምር በማደራጃ መምሪያው ስም የቅሬታ ደብዳቤ እያበረሩ እና በየቢሯቸው እየዞሩ ለማስጠንቀቅ ቃጥቷቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል በኤግዚቢሽን ማእከል እና የገበያ ልማት ድርጅት እና በሬዲዮ ፋና ለማኅበሩ የተሰጡትን መድረኮች በመቃወም ለአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍ እና የስብሰባ ፈቃድ ማሳወቂያ ጽ/ቤት እንዲሁም ለሬዲዮ ፋና ያቀረቧቸው ተቃውሞዎች ይጠቀሳሉ - አልበጃቸውም እንጂ፡፡ ይህ ሁሉ የሓላፊው ሽር ጉድ እንግዲህ በሰሞኗ የፓትርያርኩ የተሿሚዎች መዝገብ ላይ ለመስፈር እንደ ነበር ነው ቢባል ስሕተት አይሆንም፡፡
አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
ማኅበረ ቅዱሳን በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በጻፈውና ለመላው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሰራጨው ደብዳቤ በስድስት ዓመታት ውስጥ ከክስ በቀር ረብ ያለው ሥራ ያልሠሩት የማደራጃ መምሪያው ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እና ምክትል ሓላፊው ከቦታቸው ተነሥተው በምትካቸው የኢትዮጵያን ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ለመምራት ሞያው ያላቸው ሓላፊዎች እንዲሾሙ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡ የታሰበው የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመትም የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና በሚያስጠብቅ አኳኋን በጥናት እንዲከናወን፣ የቅዱስ ሲኖዶስ የበላይነት ተከብሮ ውሳኔዎቹ ተፈጻሚነት እንዲያኙ እንዲደረግ፣ የተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ መኖሩ ታምኖበት ለመከላከል የሚያስችል አቅጣጫ በቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲሰጥም መጠየቁ ተዘግቧል፡፡
______________________________________________________________
ሲኖዶስ የጽርዕ ቋንቋ ነው፡፡ በአንድ መልኩ ዐቢይ ጉባኤ፣ ሸንጎ፤ የፓትርያርክ፣ የጳጳሳት እና የሊቃውንት ማኅበር፤ እከባ፣ ስብሰባ ማለት ሲሆን በሌላ ገጹ ደግሞ አበው ጳጳሳት በጉባኤ የወሰኑትን፣ ያገጉትን፣ የደነገጉትን ሕግ፣ ሥርዐት እና ቀኖና ሃይማኖት የያዘው መጽሐፍ ስያሜ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ለዋጃት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እረኛ አድርጎ የሾማቸው አበው ኤጲስ ቆጶሳት፣ ጳጳሳት እና ሊቃነ ጳጳሳት ለቤተ ክርስቲያን ዶግማዊ፣ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ችግር መፍትሔ ለማበጀት፣ መሠረተ እምነትን ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በጉባኤ ይሰበሰቡ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ በ51 ዓ.ም በኢየሩሳሌም፣ በ325 ዓ.ም በኒቂያ፣ በ381 ዓ.ም በቊስጥንጥንያ እና በ431 ዓ.ም በኤፌሶን የተሰበሰቡት አበው ጉባኤያት ዛሬም በመንፈስ ቅዱስ ለሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ መሠረቶች ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችን እና መመሪያዎችን የማውጣት የዳኝነት ሥልጣን አለው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማ፡- ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ፣ አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ፣ ሃይማኖት እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዳይፋለስ ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ፣ ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት፣ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት እና ለማጠናከር፣ ወጣቶች ከአበው የተቀበሉትን ሃይማኖት እና ሥርዐት ጠብቀው፣ በትምህርት እና በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ ሰንበት ት/ቤትን ለማጠናከር እና ለማስፋፋት፣ የሰው ዘር ሁሉ ከርኀብ፣ ከእርዛት፣ ከበሽታ እና ከድንቁርና ተላቆ በሰላም እና በአንድነት፣ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖር ማስተማር እና መጸለይ መሆኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 1 - 6 ላይ ተመልክቷል፡፡

የኒቂያ ጉባኤ ካሳለፋቸው ሃያ ቀኖናዎች መካከል የየሀገረ ስብከቱ ኤጲስ ቆጶሳት በዓመት ሁለት ጊዜ መሰብሰብ እንደሚኖርባቸው፣ ከእኒህም አንዱ ከዐቢይ ጾም በፊት ለእግዚአብሔር ንጹሕ ስጦታ ለማቅረብ ሁለተኛው ደግሞ በመጸው እንደሚሆን የሚደነግገው ይገኝበታል፡፡ በዚህም መሠረት በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 10 ንኡስ አንቀጽ 1/ሀ እና ለ እንደተመለከተው የመጀመሪያው ጉባኤ በየዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን፣ የሁለተኛው ጉባኤ ትንሣኤ በዋለ በሃያ አምስተኛው ቀን/በርክበ ካህናት/ ይካሄዳል፡፡ ምልአተ ጉባኤ የሚባለውም ከአቅም በላይ የሆነ እክል ካላጋጠመ በስተቀር መላው አባላት/አሁን ከ52 ያላነሱ/ የተገኙበት ጉባኤ ሲሆን ነው፡፡

______________________________________
ለቅዱስ ሲኖዶስ ቅሬታ ሊያቀርቡ የመጡ ከ200 በላይ ሰዎች ዱከም ላይ በፖሊስ ታገቱ

 (ሪፖርተር ጋዜጣ /Wednesday, 18 May 2011 06:41):-  ከደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከሐዋሳ ከተማ በሰባት አውቶቡስ ተሰባስበው ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ አዲስ አበባ ያመሩት የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አገልጋዮችና የእምነቱ ተከታዮች ምዕመናን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በምትገኘው ዱከም ከተማ ላይ ሲደርሱ በፖሊስ መታገታቸውን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የከተማው ፖሊስ ሕገወጥ ሰልፍ ስለማይፈቅድ መሆኑን ገልጿል፡፡

በትናንትናው ዕለት ረፋዱ ላይ ተነስተው ከሰዓት በኋላ በግምት ስምንት ሰዓት ተኩል አካባቢ ዱከም ከተማ ላይ ሲደርሱ፣ በፖሊስ የታገቱት ቁጥራቸው ከ200 በላይ እንደሚሆኑ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ቅሬታቸው ሚያዚያ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. የክልሉ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው በፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የተሾሙትን ግለሰብ በመቃወም ነው፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት የሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲሠሩ የነበሩት አቡነ ፋኑኤል ተነስተው፣ አቡነ ገብርኤል የተሾሙ ቢሆንም፣ በሐዋሳ የሚገኘው በማኀበረ ቅዱሳንና በተስፋ ኪዳነ ምሕረት ማኅበር መካከል ግጭት ከመነሳቱም በተጨማሪ የአቡነ ገብርኤልን መሾም በመቃወማቸው የክልሉን ሀገረ ስብከት እንዲያስተዳድሩ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ በመሾማቸው ነው፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደገለጹት፣ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ የሌላ እምነት ተከታይ ናቸው፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆን የቪዲዮና የጽሑፍ ማስረጃ ለቅዱስ ፓትርያርኩና ለቤተ ክህነት አስገብተዋል፡፡ ምላሽ ግን አላገኙም፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ በሚጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ቅሬታቸውን ለማቅረብ በትናንትናው ዕለት በሰባት አውቶቡስ ተሳፍረው ከ200 በላይ ቅሬታ አቅራቢዎች ዱከም ሲደርሱ ወደ አዲስ አበባ እንዳያልፉ ተከልክለዋል፡፡ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ‹‹ሰልፍ ማድረግ አትችሉም›› ተብለዋል፡፡ ሁሉንም ይወክላሉ የተባሉ 40 ሰዎች ተመርጠው በአንድ አውቶቡስ ብቻ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ ተደርጎ ሌሎቹ ዱከም ከተማ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡

ተቃዋሚዎቹ ያለምንም ግርግርና ሌላ እንቅስቃሴ በመጓዝ ላይ እያሉና የክልሉ መንግሥት (የሐዋሳ) ፈቅዶላቸው በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ መከልከላቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ሀገረ ስብከት በሊቀ ጳጳስ እንዳይመራ የተፈለገበትንና አንድ አባት ሲሾም የሃይማኖቱ ሁኔታና ያለው የትምህርት ብቃት ሳይረጋገጥ ዝም ብሎ መሾም ለምን እንዳስፈለገ ከሚያነሷቸው ጥቂቶች ጥያቄዎቻቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የዱከም ከተማ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር መንግሥቱ ተካን አነጋግረናቸው፤ ‹‹ከ200 በላይ ሰው በአንድ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አይችልም›› ካሉ በኋላ፣ ሕጋዊ መንገዱን ጠብቀው እንዲሄዱ በማድረግ 40 ሰዎችን መርጠው ጉዳያቸውን እንዲያደርሱ መላካቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹የታገተ ማንም የለም፡፡ አምስት መኪና ሞልተው ከ200 በላይ ሆነው ማለፋቸው ሳይሆን ያሳሰበን፣ ከሐዋሳ ተነስተው ዱከም እስከሚደርሱ ድረስ ለደህንነታቸውም አለማሰባቸው ነው፤›› ያሉት ምክትል ኮማንደሩ፣ በሰላማዊ መንገድ ቅሬታን ለማቅረብም ቢሆን ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ደጋግመው አስታውቀዋል፡፡ በሰላማዊ ሁኔታ መንገዱን ይዞ የሚንቀሳቀስን ተሽከርካሪ ሰልፍ መሆን አለመሆኑን እንዴት እንዳወቁ ጠይቀናቸው ‹‹መረጃ ደርሶን ነው›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሕዝቅኤልን አነጋግረናቸው፤ ‹‹በጉዳዩ ላይ እየተነጋገርነበት ነው፡፡ አሁን ፀሎት ላይ ስለሆንኩ ከዚህ በላይ ማለት አልችልም፤›› በማለታቸው ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልቻልንም፡፡

በሐዋሳ ክልል የሲዳማ፣ የአማሮና የአካባቢው ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሚያዝያ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. የተመደቡትንና ቅሬታ የተነሳባቸውን ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒን አነጋግረናቸው፤ ‹‹ችግሩ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን ኢላማ ያደረገ ነው›› ካሉ በኋላ፤ እሳቸው የቢሮ ሥራ እንጂ ከምዕመናኑ ጋር የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

የእሳቸው መሾምና ወደ ሐዋሳ ክልል መሄድ ያላስደሰታቸው ሰዎች ሳይኖሩ እንዳልቀሩና ስማቸውንም በተለያዩ ፎርጂድ ማስረጃዎች እያጠፉ እንደሚገኙ ሊቀ ካህናት ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት በመንበረ ፓትርያርክ ተመድበው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ያሉ ሁለት አቢያተ ክርስቲያናትን ሲያስተዳድሩ በነበረበት ወቅት ከሕዝብ ጋር ሲገናኙ ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥማቸው፤ አሁን ከሕዝብ ጋር የማያገናኝ ሥራ ሲይዙ ለምን ይህ ችግር እንደተፈጠረ እንዳልገባቸው የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ ‹‹ስሜን የሚያጠፉትን በሕግ እየጠየቅኩኝ ነው፡፡ ቀሪዎቹንም በቀጣይ ሕግን ተጠቅሜ እጠይቃለሁ፡፡ የሕግ የበላይነትንም አሳያቸዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ሊቀ ካህናት ጌታቸው ሐዋሳ ክልል የተመደቡበትን ዋና ዓላማና ምክንያት እንደገለጹት ከሆነ፤ ቀደም ባሉት ወራቶች በሐዋሳ ማኅበረ ቅዱሳን አባላትና በተስፋ ኪዳነ ምሕረት ማኅበር አባላት መካከል ተነሰቶ የነበረውን ግጭትና ሲኖዶሱ በአጣሪ ኮሚቴ መርምሮና አጣርቶ ውሳኔ የሰጠበትን ውሳኔ ለማስፈጸም ነው፡፡ ኮሚቴው በውሳኔው የሁለቱ ማኅበራት ተመራጮች የፀቡ መነሻ በመሆናቸው በአገልግሎትም ሆነ በሌላ ሥራ እንዳይገቡ ታግደዋል፡፡ ከሁለቱም ማኅበራት ንክኪ የሌለው አዲስ የሰበካ ጉባዔ እንዲመረጥ ተወስኗል፡፡ የገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት ለፀቡ መንስዔ አንዱ አካል በመሆኑና አመራሮቹ እንዲወርዱ ተደርገዋል፡፡ ከሀገረ ስብከቱ አላግባብ የታገዱ አባላት በእሳቸው አማካይነት ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ እሳቸውም ይህንኑ እየሠሩ ነው፡፡

የሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ፋኑኤል ከተነሱ በኋላ አቡነ ገብርኤል የተሾሙ ቢሆንም፤ ከምዕመናኑ መልካም አቀባበል ባለማግኘታቸው አዲስ አበባ ተመልሰው በቤተ ክህነት መሆናቸውንና በዓመት ሁለት ጊዜ የትንሳኤ በዓል ባለፈ በ25ኛ ቀን (ረክበ ካሕናት) እና በጥቅምት ወር የሚሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ዛሬ ስለሚጀመር አቡነ ገብርኤልን አንስቶ ሌላ ሊሾም እንደሚችል የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በታምሩ ጽጌ

11 comments:

Anonymous said...

በእንባ አነበብኩት እስቲ ቢቆጠርልኝ

Weyra said...

Reporter's news is fully twisted article. Why didn't the reporter ask Getachew Doni himself about his religion? How come the reporter said Abune Gebre'el was not welcome by the people?

T/selase said...

አይ ፈተና፣ ካልደፈረሠ አይጠራም በጣም ይገርማል ፖሊስ፣ ጌታችው ዶኒ፣ አባ ሰረቀ፣ በጋሻው፣ አደመ፣ መናፍቃን፣ ሌሎችም እ/ር ሁሉንም ያጥራልን

yrdaw said...

ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቀርበት አንጥፉልኝ አለ አሉ አይጌታቸው ዶኒ ስለአንተማ አንተ ሳትሆን ስር መሰረትህን
የሚያውቀው የመቂ ሕዝብ ሳይገባህ ተሹመህ የሰራህበት የእንጦጦ
የአቃቂ ሕዝብ ቢናገር ይሻላል። ምን ያህል ጳትርያርኩ ቤተ ክርስቲያንን ለመጉዳት እንደተነሱ ያየሁትና ለእር ሳቸው የነበረኝን
አመለካከት የከፋ እንዲሆን ያደረገኝ ያንተ የእሳቸው የሕግ ጠበቃ ሆነህ መነሳትህና አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ የአዋሳ አገረ ስበከት ሥራ
አስኪያጅ መሆንህን ስሰማ ቤተ ክርስቲያን ምንያህል አደጋ ውስጥ
እንዳለች ተረዳው። ቀድሞ ብዙ የማላውቀውን ማኅበረ ቅዱሳን
አሁን ግን ሳውቀው ለካ እየታገለ ያለው ከአንተና አንተን መሰሎች
ጋር መሆኑን ስረዳ ለቤተ ክርስቲያኔና ለአገረ ሥል መኅበሩን በሚገባ አጥንቼ በተቻለኝ ሁሉ ርኩስ የሆነ ሥራህን ለመታገል ከአዋሳ ምእመናንጋር እቆማለሁ። ሰለጌታቸው ምንነት ለማወቅ መቂ
እንጦጦና አቃቂ ምን እንደሰራ መጠየቁ በቂ መረጃ ነው። በእርግጥ ጌታቸው ዶኒ በቤ ትክርስቲያን ስም ብቻ ሳይሆን በመንግስትም ስም የሚነግድ አጭበርባሪ ነው። የመንግስት የቅርብ ተጠሪ እንደሆነ ራሱን ያቀርባል ለምን ዓለማ እንደቆሙ የማያውቁ የመንግስት ካዴሪዎችን በገንዘብ እየደለለ በሄደበት ቦታ ሁሉ ያላሳሰረው የሰነበት ትምህርት ቤት ወጣት የለም። ያን ዘዴውን ተጠቅሞ ይመስለኛል ዱከም ላይ አሁንም መኪናቸውን ያስመለሰው። መንግስት እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ማንነት በሚገባ ሊረዳ ያስፈልካል በስሙ የሚነግዱ ካሕናት ያልሆኑ ወረ በሎች ቤተ ክርስቲያንን ወረዋታል። አቤቱ እሰከመቼ እንዲህ ይሆን

Anonymous said...

It would have been better, if it were seen seriously on time, even now is the right time to take measure.

Kidusan kidist leminulun
God bless Ethiopia

Anonymous said...

It would have been better, if it were seen seriously on time, even now is the right time to take measure.

Kidusan kidist leminulun
God bless Ethiopia

Anonymous said...

It would have been better, if it were seen seriously on time, even now is the right time to take measure.

Kidusan kidist leminulun
God bless Ethiopia

Anonymous said...

የምንለው የለም የአንተ ድንቅ ሥራ ይገለጽ በአባቶቻችን አድረህ ለዚች ቤተ ክርስቲያን የሚበጀውን አምጣ በአባቶቻችን አድረህ ቀናውን መንገድ ግለጽ

Anonymous said...

የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር እስኪ ከእናንተ ጋር ይሁን
ወይ እናቴ ቤተ ክርስቲያን!!!

Anonymous said...

mahibere kidusan yetemseretew besew fekad ayidelemna menkat matsifat ayichalim be kidusan sewoch be egiziabher fekadi new yemseraw le church new lehager new lewgen new menafikan binesu tehadiso binesu yitsefalu ye mahibere kidusanin agelgilot lemawek keketema wede getser wetsa bilo mayet new yetezegu gedamatina adibarat kefito kahin setsito megareja zebib gezito menafikanin tekakumo yalew mahiberu new kesashoch tekawamiwoch menafikan ye felegewin bilu liyatsefut ayichilum siraw bebirhan yemitay new

Anonymous said...

Egziabher minew Tinsae betekirstiyann Azegeyehew... Lemiknyat Yihon?????

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)