June 2, 2011

ከሐዋሳ የመጡ የጌታቸው ዶኒ ልዑካን ጳጳሳትን ሲሰድቡ ዋሉ

To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDF ለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።

(ደጀ ሰላም፤ ጁን 1/2011)፦ ትናንት ከቀትር በፊት የአባ ሰረቀን ጋዜጣዊ መግለጫ ያስተናገደው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ሕንፃ በሌላው የስብከተ ወንጌል አዳራሹ ደግሞ ጌታቸው ዶኒ አላግባብ ከተሰጠው የሥራ አስኪያጅነት ሥልጣን በቅዱስ ሲኖዶስ መወገዱን ለመቃወም ነው በሚል የመጡ ቡድኖች ከአቡነ ጳውሎስ እና ከአራት ሊቃነ ጳጳሳት (ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ) ጋራ ያካሄዱትን ዛቻ እና ኀይለ ቃል የተመላበት ስብሰባ እያስተናገደ ነበር፡፡


በሐዋሳው ውዝግብ በድብደባ ወንጀል በተመሠረተባቸው ክስ ፍርዳቸውን የሚጠባበቁትና የ”ተስፋ ኪዳነ ምሕረት” ማኅበር አመራር አባላት በሆኑ ግለሰቦች ተቀስቅሰው የመጡት እኒህ ቡድኖች ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ሊያነጋግሯቸው የመጡትን ብፁዓን አባቶች፡- “እናንተ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊና ጉዳይ አስፈጻሚ ጳጳሳት ናችሁ፤ ተሐድሶም ጴንጤም የሚባል የለም፤ ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው ነው፤ አቡነ ናትናኤል የማኅበረ ቅዱሳን-ደጀ ሰላም ሪፖርተር ናቸው፤ የሚገባ መሥዋዕትነት ባይሆንም አቡነ ገብርኤል ወደ ሐዋሳ የሚመጣ ከሆነ እንገድለዋለን፤” የሚሉ በገዛ ጭብጨባቸው የታጀቡ የዛቻ እና የዘለፋ ንግግሮች ሲያሰሙ መዋላቸው ተገልጧል፡፡

በሁኔታው ያዘኑት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ “ቅዱስ አባታችን፣ እዚህ የመጣሁት ልሰደብ አይደለም” በሚል ወጥተው ሲሄዱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልም ተከትለዋቸዋል፤ ይሁንና ሁለቱም አባቶች በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ልመና ከበር ተመልሰው እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ ወዲያውም ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል “የት ነው የተማራችሁት? ማን ነው ስድብ ያስተማራችሁ? እናንተንኮ አናውቃችሁም” በሚል ገሥጸዋቸዋል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ከጎናቸው አስቀምጠው ሲያሰድቡ የዋሉት ፓትርያርኩም “እንደዚህ ነው የመከርኳችሁ? እንዴት እንዲህ ባለ ኀይለ ቃል ትናገራላችሁ?” ማለታቸው ነገሩ አስቀድሞ በእርሳቸውና በጌታቸው ዶኒ መቀናጆ የተፈጠረ እንዳስመሰለው ውይይቱን የተከታተሉ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡ ተቃዋሚ ተብዬዎቹ “አባቶቼ ከወሰኑት የተለየ ውሳኔ አትጠብቁ፤ የሚኖር ከሆነ ወደፊት እግራችኋለን” በሚለውና በእጅጉ እንደተበሳጩበት በተገለጸው የአቡነ ጳውሎስ ንግግር ቢሰናበቱም ፓትርያርኩ “መምጣት አልነበረባችሁም” ማለታቸውን ግን ታዛቢዎቹ “የማይጥም ቀልድ” ብለውታል፡፡


የተቃውሞ መቀናጆው የሐዋሳ ምእመናን ግንቦት 9 ቀን በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተገኝተው ብዙዎችን ያሳመነውን የቪሲዲ ማስረጃቸውንና መግለጫቸውን በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፊት በማቅረብ ለአቡነ ጳውሎስ የመጨረሻ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት ፓትርያርኩ የተሰማቸውን ብስጭትና እርሱን ተከትሎ በጌታቸው ዶኒ መወገድ ጠንካራ አቋም የያዙትን አባቶች በመዝለፍ ለመበቀል ያለመ እንደሆነ ተገምቷል፡፡

በምእመናኑ አስተባባሪዎች ላይ ክስ የመሠረተው ጌታቸው ዶኒ “መነሣቴ ካልቀረ” በሚል በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ላይ የስም ማጥፋት የሚሰነዝር ጽሑፍ በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ላይ ለማውጣት ተዘጋጅቶ እንደነበር ለደጀ ሰላም የደረሰውና ከወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋራ የተነጋገረበት የድምፅ ማስረጃ ይጠቁማል፡፡

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል መልአከ ብርሃን ይትባረክ ታጠቅን የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ መምረጣቸው የተመለከተ ሲሆን እኚህ አባት ከዚህ ቀደም በአርሲ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በሰላሌ-ፍቼ፣ በደቡብ ኦሞ-ጂንካ እና በደቡብ ወሎ-ደሴ አህጉረ ስብከት በሥራ አስኪያጅነት የሠሩ ሲሆን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ምክትል ሐላፊ ሆነው መቆየታቸው ታውቋል፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)