May 15, 2011

“ደጀ ሰላም” በኢትዮጵያ እንዳትነበብ ለማድረግ እየተሞከረ ነው

(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 15/ 2011)፦  ብዙ ደጀ ሰላማውያን በተደጋጋሚ እየገለፁልን እንዳሉትና እናም እንዳረጋገጥነው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዋዜማ “ደጀ ሰላም” ለአንባብያን እንዳትደርስ የማደናቀፍ ሥራ እየተሠራባት ነው። ጉዳዩ ከዚህ በፊትም ሲሞከር የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን በተጠናከር መልኩ ቀጥሏል። ይህንን የሚያደርገው ማን/እነማን እንደሆነ/ኑ ለጊዜው እገሌ/ እነ እገሌ ነው/ናቸው ለማለት ባንፈልግም ሌሎቹ ጣታቸውን እንደሚጠቁሙት “መንግሥት እንዲህ እያደረገብን ነው” ለማለት አንፈልግም። ነገር ግን መንግሥት በሰጣቸው ኃላፊነት በኢትዮጵያ ያለውን የኢንተርኔት መስመር እና ሥርጭት የማወቅ ዕድል ያላቸው ሰዎች እጅ እንዳለበት ግን እርግጠኞች ነን።


በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የጡመራ መድረካችን ከምእመናን ዓይን እንዳትደርስ ለማድረስ የመሞከሩ ተግባር ለጊዜው ያደናቅፈን ካልሆነ በስተቀር መረጃችንን ለሕዝብ ከማድረስ ግን ሊገታን አይችልም። ዕድሜ ለቴክኖሎጂ፣ የአባቶቻችን አምላክ እየረዳን በቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ማድረግ ያለብንን ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም።

አንባብያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የደጀ ሰላም ድምጽ ሆነው ከሚፈለገው ሥፍራ ሁሉ ያደርሷታል። አበው በተረታቸው ያሉትን በመስማት ትምህርት መውሰድ ቢቻል ጥሩ ነበር። ሰውየው ሁል ጊዜ ወደ በረቱ እየመጣ ከብቶቹን የሚጎትትበት አንድ አንበሳ ነበረ አሉ። እናም አንድ ቀን ጠብቆ በጦር ወግቶ ሊገድለው ፈለገ። እንዳለውም አንበሳውን ለመግደል ጦሩን ቢወረውር ከማቁሰል ውጪ ሳይጎዳው ይቀራል። ወዳጁ በበነጋው ሲጠይቀው “አንበሳውን ገደልከው ወይ?” ይለዋል። እርሱም “አልቀናኝም፤ አፉን ነው የወጋሁት” ብሎ ይመልሳል። ጓደኛውም “አዪዪዪ፤ ታዲያ ምኑን ጎዳኸው፤ አፉን የበለጠ አሰፋኸው እንጂ” ሲል ዘበተበት አሉ። አሁንም የሆነው እንዲሁ ነው። መስኮቱን ለመዝጋት ስትሞክሩ ብዙ በሮች ትከፍቱልናላችሁ።

ውድ ደጀ ሰላማውያንም፣ በቀጥታው ንባብ ላይ ብቻ ሳትመረኮዙ፣ በተለያዩ መስመሮች ማለትም በፌስ ቡክ ገጾቻችን እንዲሁም በተለያዩ ድረ ገጾች እና የዜና ማሰራጫዎች እንድትከታተሉን፤ ካነበባችሁ በኋላ ኮፒ በማድረግ ላላነበቡ ሰዎች እንድታዳርሱ ያስፈልጋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኢ-ሜይል አገልግሎታችንን እንድትጠቀሙ፣ ካቃታችሁ ደግሞ ኢ-ሜይላችሁን ወደ እኛ በመላክ ጽሑፎቹን ታገኙ ዘንድ ከወዲሁ እናስታውቃለን።

ደጀ ሰላምን አሁን ለመዝጋት እና ድምጿን ለማጥፋት የተሞከረው ሰሞኑን በሚጀመረው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚወሳውን እና የሚወሰነውን የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ኦርቶዶክሳዊ እንዳያውቅ ለማድረግ፣ የሚደበድቡትንም አባት፣ የሚያስፈራሩትንም ወገን፣ የሚዘርፉትንም ሀብት ያለምንም ከልካይ እንደፈቀዳቸው ለማድረግ ስለሚፈልጉ ነው። ለጵጵስና ክብር ሊበቁ የማይገባቸውን ሰዎች ለመሾም፣ የእምነት ሕጸጽ ያለባቸውን ሰዎች በአበው የጵጵስና መንበር ለማስቀመጥ በጉቦ እና በእጅ መንሻ የሚደረገውን የሰሞኑን ሩጫ ደጀ ሰላም ትቃወማለች። ዝም ማለት በሚገባን ወቅት ዝም ብለናል። መናገር ባለብን በዚህ ወቅት፣ እንዲያውም መጮኽ ባለን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እንናጋራለን፣ እንዲያውም እንጮኻለን።

መንግሥት እና ጉዳዩ የሚመለከተው የቴሌኮሙኒኬሽን ክፍል የዜግነት ድምጻችንን ለማፈን የሚሞክሩትን ወንጀለኞች ሃይ ሊልልን ይገባል። ዓላማችን እና ፍላጎታችን ፖለቲካ አይደለም። ዓላማችን እና አጀንዳችን ቤተ ክርስቲያናችን ናት። ይህንን ብሶታችንን በተገቢው መንገድ እንዳናቀርብ  ልንታገድ አይገባንም። በዚህ ዘመን፣ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ የሰውን ልጅ ድምጽ ለማፈን መሞከር ነፋስን እንደማባረር ነው። አይቻልም!!!

በመጨረሻ፣ ይህንን ችግር ለተገቢው የመንግሥት አካል ማሳወቅ በምንችልበት በዚሁ የጡመራ መድረክ ለመግለጽ እንድንችል ደጀ ሰላማውያን ያላችሁበትን አካባቢያችሁን እና የገጠማችሁን የማንበብ ችግር፤ ከመቼ ጀምሮ እንዳስቸገራችሁ በመግለጽ ኢ-ሜይል እንድታደርጉል እየጠየቅን፤ በድምጽ መልእክቶቻችሁን መተው ለምትፈልጉም እንደከዚህ በፊቱ በነጻ በመደወል ሐሳባችሁን ትሰጡ ዘንድ እንጠይቃለን።

አሁን ቤተ ክርስቲያን ያለባት ችግር ሀ/ስብከት የሌላቸውና የማይኖራቸው አዳዲስ ጳጳሳትን መሾም አይደለም። በቁጥር ደረጃ በቂ ቁጥር ያላቸው አባቶች አሉን። ያሉትን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በእንክብካቤ እና በአክብሮት ሳንይዝ ሌሎችን በመሾም አሁን የተጀመረውን የሙስና እና የሥርዓት አልበኝነት አስተዳደር ለማስቀጠል ድጋፍ ማሰባሰቢያ ለማድረግ የሚደረገውን ሩጫ እንቃወማለን።

የጥቅምቱ የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ የወሰናቸው ውሳኔዎች ለምን አልተተገበሩም፣ ሐውልቱ ለምን አልፈረሰም፣ የቤተ ክርስቲያን ዝርፊያ ለምን አልቆመም፤ አህጉረ ስብከት ላይ ያሉ ችግሮች ከእጅ እየወጡ ወደ ብጥብጥ እንዲኬድ የሚደረገው ሙከራ ለምን አስፈለገ፣ የአቡነ ጳውሎስ ሥርዓት አልበኝነት የሚገታው መቼ ነው፣ ወይዛዝርቱ ከሳሎን አልፈው በቅ/ሲኖዶስ አስተዳደር ውስጥ ዕድል ፈንታ ማግኘታቸው የሚቆመው መቼ ነው?  ወዘተ ወዘተ ……

አሁንም እንጠይቃለን!!!!!!
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)