May 11, 2011

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የተባባሰው አለመግባባት


  • ቋሚ ሲኖዶስ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የተባባሰውን አለመግባባት የሚያጠና ልኡክ ሠየመ
  • “አለመግባባቱን በውይይት እና በምክክር ለመፍታት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል” (የዞኑ ፍትሕ ጽ/ቤት)
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 10/2011) በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በቤተ ዘመዳዊ አሠራር ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸመውን ሙስና፣ አስተዳደራዊ በደል እና ሥነ ምግባራዊ ጉድለት በመቃወም ችግሩ እልባት እንዲሰጠው የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሯል፡፡ ቀደም ሲል በተቃውሞ እንቅስቃሴው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና የወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች በአንድነት፣ “ጥሩ ሥነ ምግባር እና የጸዳ ሃይማኖት የለውም፤ በመንፈሳዊ አገልግሎታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አድርሶብናል፤ በተጭበረበረ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቶ ዲፕሎማ በመያዝ ቤተ ክርስቲያንን ደፍሯል፤ መንግሥትን አታልሏል” ባሉት የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤት ክፍል ሓላፊ ላይ ርምጃ እንዲወስድ (የቴዎሎጂ ዲፕሎማው እንዲሰረዝ እና የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያውቁት) ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ቢያመለክቱም ጽ/ቤቱ ወገንተኛ አቋም በመያዝ ሕገ ወጡን ተግባር ለማስተባበል ከደብረ ብርሃን እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ድረስ መማጠንን መርጧል ተብሏል፡፡


የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤት ክፍል ሓላፊ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ያቀረበው የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የትምህርት ማስረጃ የተጭበረበረ ስለመሆኑ በሀገር ዓቀፍ ፈተናዎች ድርጅት በመረጋገጡ በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶበት በሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ብርሃን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 25 ቀን 2003 ዓ.ም ባዋለው ችሎት የብር 500 የገንዘብ ቅጣት ተወስኖበታል፡፡ ይሁንና ግለሰቡ ከሚፈጽመው እና በማስረጃ ተረጋግጧል ከተባለው “በድግምት የማታለል ተግባር” ጋራ ሲነጻጸር የተወሰነው የገንዘብ ቅጣት ተመጣጣኝ አይደለም በሚል ውሳኔው በዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ተጠይቆበታል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና የወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች የሀገረ ስብከቱ ሒሳብ እና በጀት ክፍል ሓላፊ ከታላላቅ ገዳማት እና አድባራት አለቆች ጋራ በፈጠሩት ትስስር ይፈጽሙታል ያሉትን ሥር የሰደደ የገንዘብ ዝርፊያ እና ብኩንነት አጋልጠዋል ተብሏል፡፡ በደብረ ምጥማቅ ጻድቃኔ ማርያም እና ደብረ በልበሊት ኢየሱስ ገዳማት የሚገኙት ማኅበረ መነኮሳት የገዳማቱ አስተዳዳሪዎች ካለባቸው የከፋ ምግባራዊ ችግር የተነሣ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡላቸው የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት ጠይቀዋል፡፡

በዕድሜ አረጋዊ ለሆኑት ሊቀ ጳጳስ ክፉ ምክር እየሰጡ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ ያደርጋሉ የተባሉት የሒሳብ እና በጀት ክፍል ሓላፊ በቅርቡ የሀገረ ስብከቱን ስብከተ ወንጌል እና አስተዳደር ክፍል ሓላፊነት ደራርበው እንዲይዙ በመደረጉ ቤተ ዘመዳዊ አሠራሩ ሲጠናከር፣ ውዝግቡ እየተባባሰ ሄዷል የሚለው ስሞታ ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ ግለሰቡ የሊቀ ጳጳሱ እኅት ልጅ በመሆናቸው ብቻ የቢትወደድነት ሚና ይጫወታሉ፣ አራጊውን ደግ አባትም ያሳስታሉ ተብሏል።

በውዝግቡ መሃል በርካታ ምእመናንን የሚገኙበት እና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቀጥሎ ለመንበረ ፓትርያርኩ ፈሰስ ከሚያደርገው ከፍተኛ ፐርሰንት አኳያ ከሌሎች አህጉረ ስብከት ባልተናነሰ የተጠናከረ ትምህርተ ወንጌል፣ ሰፊ የማኅበራዊ እና ልማታዊ አገልግሎት የሚገባው የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ካለው ቅምጥ አቅም በተፃራሪ በተዳከመ ይዞታ ላይ ይገኛል፡፡

በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ከሊቀ ጳጳሱ ከብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ጋራ በውይይት እና ምክክር ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው ተመልክቷል፡፡ ስለ ሁኔታው ከዘገብንበት ጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም ወዲህ እንኳን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የሰሜን ምዕራብ ሸዋ-ሰላሌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ከሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ (በጠቅላይ ቤተ ክህነት የዕቅድ እና ልማት መምሪያ ምክትል ሓላፊ) እና ከሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ መኩሪያ ጋራ የሽምግልና ጥረት ቢደረግም ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤፍሬም “ከሳሾቼ መኪናዬን በፖሊስ አስፈትሸዋል፤ ስሜን በኢንተርኔት አጥፍተዋል፤ ቁስሉ አይሽርም” በሚል በእንቢታ ጸንተዋል፡፡

በተመሳሳይ አኳኋን የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን የገለጹት የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ፍትሕ ጽ/ቤት እና የደብረ ብርሃን ወረዳ ፍትሕ እና ጸጥታ ጽ/ቤት “አለመግባባቱን በውይይት እና ምክክር ለመፍታት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን” በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጡት ደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡ በአድራሻ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተላከው ይኸው የዞኑ መስተዳደር ፍትሕ ጽ/ቤት ደብዳቤ ችግሩ ለአካባቢው ሰላም እና ልማት ዕንቅፋት በመፍጠሩ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የበላይ አካል አማካይነት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ጥያቄው እና የችግሩ አሳሳቢነት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ከታየ በኋላ ሦስት አባላት ያሉት አጣሪ ልኡክ ተቋቁሟል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ሰብሳቢነት የሚመራው አጣሪ ልኡኩ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊውን (መጋቤ ካህናቱን) ሊቀ ማእምራን ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁን እና የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊውን አባ ኀይለ ማርያም መለሰን በአባልነት ይዟል፡፡
ወደ ደብረ ብርሃን ያቀናው ልኡክ ባለፈው እሑድ ከሰንበት ቅዳሴ በኋላ ከዞኑ ባለሥልጣናት ጋራ ስብሰባ መቀመጡ ተዘግቧል፡፡ በዚሁ ምሽት ፍትሕ ከተጠሙት የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች እና የከተማው ነዋሪዎች እንደ ሆነ የተገመተ፣ “ፍርድ የሚሰጡ ባለሥልጣናት ስለ መጡ የድጋፍ ሰልፍ እንድትወጡ” የሚል ደብዳቤ በከተማይቱ የተሰራጨ ሲሆን በአጠፌታው ከእሑድ ጠዋቱ ቅዳሴ በኋላ ምእመኑ ለድጋፍ ሰልፍ እንዲወጣ የተላለፈው ጥሪ ሐሰት በመሆኑ ምእመኑ እንዳይቀበል የሚያሳስብ ማስታወቂያ በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ተከላካዮች አማካይነት በየአጥቢያው ሲነገር መደመጡን ታዛቢዎች ለደጀ ሰላም ገልጸዋል፡፡

የአጣሪ ልኡኩ ወደ ደብረ ብርሃን መሔዱ ከመታወቁ በፊት የዞኑ ባለሥልጣናት መላውን የሀገረ ስብከቱን ሠራተኞች ስብሰባ በመጥራት አነጋግረዋቸዋል፡፡ በስብሰባው የወቅቱ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ተከላካዮች እና የሊቀ ጳጳሱ የሥጋ ዘመዶች ሳይቀሩ በአሰላለፍ “ገለልተኛ” መሆናቸውን ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ በምንጃር ወረዳ የምትገኘዋ የአረርቲ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ መልክ ትሠራ ዘንድ እብነ መሠረት ለመጣልና በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ ለመገኘት በጉዞ ላይ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የስብሰባውን ውሎ እና የአጣሪ ልኡኩን መምጣት እንደተነገራቸው መንገዳቸውን በማቋረጥ ወደ ደብረ ብርሃን መመለሳቸው ተገልጧል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ልሳን እንደሆነ የሚነገረው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ የየካቲት-መጋቢት 56 ዓመት ቁጥር 118 እትሙ ይህንኑ ጉዳይ በመዘገብ፣ ከሁሉም አህጉረ ስብከት በላቀ ሁኔታ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እና ልማት ድጋፍ ሰጪ የሆነው የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት መጽዳት እና መስተካከል እንደሚገባው በመጠቆም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብርቱ ቁጥጥር እና አሰሳ እንዲያደርግበት ማሳሰቡ ታውቋል፡፡

3 comments:

Anonymous said...

Dear Dejeselam! I knew about North shewa Hagere sibket few things.I was working around them &sometimes I participated in their preaching.all most all wereda hagere sibket staffs have strong relation with Abune Efrem.I think some mistakes came from the head.

Anonymous said...

why do you think you guys from ethiopian orthodox church? you remebered , you wrote one article about abune epherem spoiled job, he awarded one car from the people.Please remember this , " leaders lead by example" we don't have any orthodox father who leads our church by example . Check your patriric , how he abuses your church. you will see more than this if you live well

Anonymous said...

I was in Debre birehan before one year but currently I am in hawassa i saw similar problems in both town there was some tahadisos's group in debre birehan St. Gorge church. I think peoples around that knows those tahadisos's people so that try to find those people from our church unless there will be a big problem in the feature.
from hawassa

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)