May 2, 2011

የማታ ማታ …፤ ቢን ላደን ተገድሏል


(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 2/2011)፦ ላለፉት 10 ዓመታት በሰማይ - በምድር፣ በአየር - በባሕር ሲፈለግ ነበር። መግቢያው አልተገኘም ነበር። በአፍጋኒስታን ቦራቦራ ተራሮች ልብ ውስጥ ተደብቆ ይሆናል ተብሎ ብዙ የአሜሪካ ልጆች ደማቸውን አፍስሰዋል። ዛሬም በየቀኑ በቢንላደን ምክንያት ብዙ የሰው ልጅ ደም ይፈሳል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሪ እና ከ6 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከጨፈጨፈው ከሒትለር ወዲህ አሜሪካውያን እንደ ቢን ላደን የሚጠሉት ሰው እንደሌለ ትናንት እሑድ መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ ሰምቻለኹ። ይገባቸዋል። ቢን ላደን በዓለም ልዕለ ኃያል አገር በአሜሪካ ተፈልጎ ባለመገኘቱ፣ ያውም 10 ዓመት፣ ቢን ላደን የሚባል ሰው የለም፣ እንደ ጭራቅ ለማስፈራሪያነት የተፈጠረ ነው የሚሉ ሰዎች ነበሩ።


ቢን ላደን እንደ አንድ ሰውነቱ ሳይሆን የዓለምን የሰላም ሚዛን፣ የኢኮኖሚ እና የሰው-ለሰው ግንኙነት ሚዛን ያዛባ የዘመናችን አንድ ጉድ ነበር። አሜሪካ እንደምትናገረው ከመስከረም 11/2000 ጀምሮ ያለው አሜሪካውያን ሕይወት በጠቅላላው የተለመወጠ ሲሆን በየአውሮፕላን ማረፊያው ያለው የጸጥታ ጥበቃ እና ጭንቀት ያንን ሰላማዊ አገር እና ሕዝብ ቀይሮታል። በዚህም ምክንያት ምንም ያላጠፉ ንፁሐን ሙስሊሞች ሳይቀሩ የገፈቱ ቀማሽ ሆነዋል። ሙስሊም መሆን ብቻ እንኳን በሌላው ሰው የሚያስጠረጥርበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

ከቢን ላደን ጥቃት በኋላ የቡሽ አስተዳደር በኢራቅ ላይ ባካሄደው ዘመቻ ምክንያት ብዙ አሜሪካውያን ወታደሮች እና ሰላማውያን ኢራቃውያን ሕይወታቸውን እና ኑሯቸውን ያጡ ሰሆን በተለይ ደግሞ በዚያች ጥንታዊት የባቢሎን ምድር የነበሩ ክርስቲያኖች ዘር ማጥፋት ሊባል በሚችል መልኩ የአክራሪዎች ጥቃት ሰለባ ሊሆኑ ችለዋል። በሳዳም ሁሴን ዘመን እንኳን ደርሶባቸው የማያውቀው ዓይነት ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል። በዚህ አሥር ዓመት ውስጥ ክርስትና ከነምልክቱ ከኢራቅ ሊጠፋ ምንም አልቀረውም።

ዋነኛው ጦርነት ሊካሄድበት ሲገባ ዘግይቶ እና በመጠኑ በተጀመረበት በአፍጋኒስታንም ንፁሐን ሰዎች በየቀኑ ሕይወታቸውን እያጡ ነው፤ ሕጻናት እና ሴቶች ሰለባዎች ሆነዋል። አክራሪዎቹ ሰፊ የአደንዛዥ ዕጽ ማሳዎችን በማዘጋጀት፣ ዕፁን በማስፋፋት እና ገንዘባቸውን በመሰብሰብ እጥፍ ድርብ ወንጀል ሲሰሩ ቆይተዋል። የዚህ ሁሉ ግንባር ቀደም ምልክት እና መሪ ደግሞ ቢን ላደን ነበር። ይህ ላለፉት 10 ዓመታት ሲፈለግ የነበረ ቁጥር አንድ ወንጀለኛ የሚገባውን አግኝቷል። ግን የእርሱ መሞት ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣ ይሆን?

ብዙ መሪዎች ሲሞቱ እንደሚሆነው ሁሉ የቢን ላደን መገደል “የእባቡን ጭንቅላት” መምታት ተደርጎ እየተቆጠረ ነው። ነገር ግን ይህ አሸባሪ ግለሰብ የዘራው ክፉ ዘር ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ሶማሊያ ብሎም በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች እስካሉ ተከታዮቹ ድረስ ሰርጎ የገባ በመሆኑ መሞቱ አሸባሪነትን ሙሉ በሙሉ ያጠፋዋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።

አክራሪነት በየዘመኑ የነበረ አስተሳሰብ ነው። በተለይም እስልምናን ተገን ያደረገው አክራሪነት ግብ አድርጎ የያዘው በኃይል እስልምናን በመላው ዓለም መጫን ብሎም ዓለምን በሸሪዓ ማስተዳደር በመሆኑ እስከመቼውም የሚጠፋ አይሆንም። አንዳንድ የዋህ ሙስሊሞችን ወደ ዓላማው በማሰለፍ በኩልም ቀላል የማይባል ርምጃ ተራምዷል።

ነገር ግን ቢን ላደን በቦንቦቹ እና ደም በማፍሰሱ ለእስልምናው ዓለም ካስገኘው ጥቅም ይልቅ አንዲት ጥይት ያልተኮሱት የቱኒዚያ እና የታህሪር አደባባይ ግብጻውያን ወጣቶች ያመጡት ለውጥ ይበልጣል። ቢን ላደን ኒኩሊየር ቢታጠቅም ሊያመጣ የማይችለውን ውጤት ሰላማዊ ትግል ያደረጉ እና የሕዝባቸው ኑሮ እንዲሻሻል የተሟገቱ ወጣቶች እና የፌስቡክ ትውልዶች ያመጡት ለውጥ ይገዝፋል።

በመላው ዓለም ያሉት አክራሪዎች የቢንላደን ክፉ አሟሟት የሚያስተምራቸው ብዙ ነገር ይኖራል ብዬ እገምታለሁ። የሰውን ልጅ ንፁሕ ደም የሚያፈሱ በሙሉ የማታ ማታ እንዲህ የአጋግን ዓይነት መራር የሞት ጽዋ መጎንጨታቸው አይቀርም።  የማታ ማታ እውነት ይረታ ማለት ይኸው ነው።
ይቆየን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)