May 16, 2011

ቁጥራቸው 30 የሚደርስ መነኮሳት ለጵጵስና ታጭተዋል


  • 300,000 እስከ 500,000 ቀብድ የሰጡ አሉ፤
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 16/ 2011)፦  ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ ያደረሱን ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን በዚህ የግንቦት ቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ በፓትርያርኩ አቅራቢነት ከ30 የማያንሱ መነኮሳት ለጵጵስና መቅረባቸውን የሚያትት ነው። ዜናው የሹመቱ ጉዳይ አይደለም። ለዚህ ማዕረግ ከቀረቡት መካከል እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ጉቦ የሰጡ መኖራቸው ግን እጅግ አስደንጋጭ ነገር ነው። ይህንን ጽሑፍ ባናስነብባችሁ ደስታችን ነበር፤ ይህንን ጉድ ላለማውጣት። ከዚህ ውጪ ግን ምንም አማራጭ ሊኖረን አልቻለም። 

መተ ሲሞን:- ሲመት /ሹመት/ ለተለየ ተልዕኮ የሚሰጥ በገንዘብ፣ በንብረት እና በሰው  ሀብት ላይ የማዘዝ እና የማስተዳደር ሥልጣን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ መንፈሳዊ ሲመት ሲሆን ምድራዊ ላይደለ ሰማያዊ ተልዕኮ የሚሰጥ ሥልጣን በመሆኑ ለዚሁ መግቦት /አገልግሎት/ በትምህርታቸው ልቀት በመንፈሳዊነታቸው ብቃት እና በሃይማኖታቸው ጽናት ለተመረጡ አገልጋዮች እንደየ ደረጃቸው እና ማዕረጋቸው የሚሠጥ የሥራ ድርሻ ነው፡፡


ሐዋርያት የተሰበሰቧት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ጀምራ እስከ አሁንም ድረስ ከዲቁና እስከ ጵጵስና ለተመረጡ አገልጋዮቿ ሥርዓተ ሲመት ስትፈጽም ኑራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለች የእግዚአብሔር እንደራሴ የፀጋው ግምጃ ቤት እንደመሆኗ ምእመናንን ለመጠበቅ እና ለማሠማራት እንድትችል ሥልጣነ ክህነት የምትሰጥበትን ጥብቅ ቀኖና በፍትሕ መንፈሳዊ በመደንገግ እና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ በማዘጋጀት በትምህርታቸው የበሰሉትን በሃይማኖታቸው ነቅ በምግባራቸው ጠንቅ የሌለባቸውን አገልጋዮች ስትሾም ኖራለች ወደፊትም ትኖራለች!

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ቤተ ክርስቲያናችን በታሪኳ አይታውም ሰምታውም የማታውቀው የሥልጣን ሽሚያ መድረክ ሆናለች፡፡ በፍቅረ ሲመት የነደዱ ከአገልግሎቱ ይልቅ ጥቅማጥቅሙን በመናፈቅ ያበዱ ጥቂት የማይባሉ ግብረበላዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥልጣነ ክህነት ለመቆናጠጥ የማይምሱት ስር እና የማይበጥሱት ቅጠል የለም፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን ደግሞ ይባስ ብለው በመንፈሳዊው ዓለም ትልቁን እና እጅግ የከበረውን ሲመተ ጵጵስና ለመቀራመት በግል እና በቡድን በመደራጀት ጆሮ የሚሰቀጥጥ ዘመቻ ላይ ናቸው፡፡

እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?
በቅዱስ መጽሐፍ በሐዋርያት አበው የሚደረገው ገቢረ ዓምራት በሃይማኖት እና በግብረ መንፈስ ቅዱስ የተገለጠ መሆኑን በመዘንጋት ሲሞን (የሐዋ. 8፤9) የተባለ ጠንቋይ ብዙ ብርና ወርቅ በማምጣት ሐዋርያት አበውን «እናንተ የምታደርጉትን የመሠለ ድውይን የመፈወስ ሙት የማስነሳት ሥልጣን ስጡኝ» ብሏቸው ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ከዋጃት መድኃዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ መንጋውን የመጠበቅ የማሠማራት እና የመመገብ ሰማያዊ አደራ የተቀበሉት ቅዱሳን ሐዋርያት ግን ሲሞን ያመጣው ርና ወርቅ ሳያስጎመጃቸው አንተ እና ብርህ አንድ ላይ ጥፉ በማለት ረግመው እና አዋርደው መልሰውታል፡፡

ልብ በሉ! ሲሞን የጠየቀው ሲመት (ሥልጣነ ክህነት) ዓላማው ምእመናን በነፍስ በሥጋ መጠበቅ እና ማጽናናት ለመንግሥተ ወንጌል ማብቃት ሳይሆን ሥልጣኑን መከታ በማድረግ ምእመናንን በሥጋ ገንዘባቸውን በመንፈስ ነፍሳቸውን ለመንጠቅ ነው፡፡

ዛሬስ?
ዛሬም ሲሞናውያን በቁጥር በርክተው በዓ ረቅቀው መንበረ ጵጵስናውን እና ታላቁን የሐዋርያት ጉባኤ ቅዱስ ሲኖዶስን ለመቆጣጠር ከተቻለም ሙሉ በሙሉ በመውረር ሐዋርያዊቷን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመረከብ ለዓይኖቻቸው እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቻቸው እረፍት አጥተው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ሲሞናውያን እንዲህ ለቁጥር በርክተው በገነኑበት ዘመን የሚያመጡትን መደለያ እና ጥቅማ ጥቅም «እርም» አድርጎ የሚያሳፍር በእነ ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የተቀመጠ ሐዋርያዊ አባት መኖሩን ግን እንጠራጠራለን፡፡ ጥርጣሬያችን ደግሞ እንዲሁ የመጣ ሳይሆን ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ጵጵስናን ያህል ታላቅ ማዕረግ የገንዘብ ጉቦ በመቀበል የመሾም ጉዳይ ለአባ ጳውሎስ ብዙም የማያስገርም አሠራር እየሆነ መምጣቱን ከማየት የመነጨ ነው፡፡

ምሳሌ ከዚህ በፊት ከደቡብ ኦሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት የ“ጵስና ሹሙልን የድጋፍ ደብዳቤ በማጻፍ  የመሾም ጥረት አድርገው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውድቅ ሲያደርገባቸው ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም እንዲሉ 150,000 ብር ለአቡነ ጳውሎስ ጉቦ በመክፈል ሁለተኛ ዙር ሙከራ ያደረጉትንና አሁን ጋምቤላ ሀ/ስብከት የሚገኙትን አንድ ግለሰብ መጥቀስ ይቻላል። ፓትርያርኩ ብሩን ተቀብለው ነገር ግን ሲመቱን ሳይሰጡ ዝም በማለታቸው በመበሳጨ ወይ ብሬን ወይ ሹመቴን በማለት ለሦስተኛ ዙር በአቡነ ጳውሎስ የሲመት ዝርዝር ውስጥ ሊገ ለዋል፡፡ (እንደ አስፈላጊነቱ ስማቸውን እና ማስረጃውን እናቀርባለን)

በዘንድሮው ሲመተ ጰጵስና 300,000 እስከ 500,000 ብር (ብሩ ከምእመናን የተሰበሰበ መሆኑን ሳንዘነጋ) ቀብድ የሰጡ 30 ያላነሱ ተሿሚዎች በአባ ጳውሎስ ፊታውራሪነት ፀጉራቸውን ተላጭተው ፈረጂያ አሰፍተው አስኬማ ወልውለው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ከመስማት በላይ ልብ የሚሰብር ዜና ከየት ይመጣ ይሆን? ጉዳዩን የበለጠ አስደንጋጭ የሚያደርገው ደግሞ አንደኛው የማፍያ የጥቅም ቡድን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ መዋቅር በአምቻ፣ በጋብቻ እና በጉቦ ጠቅልሎ ለመረከብ ሲረባረብ ሁለተኛውና እና እጅግ አደገኛው የተሐድሶ ክንፍ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ቅዱሱን የጳጳሳቱን ጉባኤ ሊቀላቀ ዝግጅቱን ጨርሶ የአባ ጳውሎስን ቡራኬ በመጠባበቅ ላይ መሆኑ መሰማቱ ነው፡፡

ጵጵስና ትልቁ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊው የሹመት ደረጃ እንደመሆኑ ለዚህ ሹመት የሚታጩ አገልጋዮች በእውቀት የሚታሙ መሆን እንደሌለባቸው በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተደነገገ ጉዳይ ቢሆኑም የአባ ጳውሎስ አዲሶቹ ተሿሚዎች ግን «ድንግል በክልኤ» (በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው እዚህ ግባ የሚባል ትምህርት የሌላቸው) ጨዋዎች መሆናቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ሌላኛው የጰጵስና ማዕረግ ዕጨኑት መመዘኛ ሴት ርቆ ንጽሕ ጠብቆ የመኖር ጉዳይ በአንዳንዶቹ ዘንድ የማይታወቅ በመሆኑ ዘርተው የቃሙ ደው የሳሙ መሆናቸውን ለሚያውቅ ምእመን መልእክቱ ግልጽ ነው፡፡

ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በመጣስ ምእመናንን ተስፋ ማስቆረጥ ቅዱስንም ሲኖዶስ የወለዱ እና ከበዱ ማፍያዎች መሰብሰቢያ ማድረግ በመጨረሻም መንጋውን መበተን ነው፡፡ ሲሞናውያንን የምግባር ብልሹነት በተወሰነ ደረጃ መታገስ ይቻል ይሆናል፡፡ የሃይማኖት ሕጸጻቸውን ግን ድርድር ለማቅረብ መሞከር ሳይሆን ማሰብ እንኳን የሚቻል አይመስለንም

በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸችውን ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን በተድሶ ኑፋቄ ሥርዓ አምልኮቷን የነገረ መለኮት ትምህርቷን በመበረዝ እና በመለወጥ ጠቅሎ የመረከብ አንዱ ስልታቸው በባሌም በቦሌም ጵጵስናውን መቀበል ነው፡፡ በዚህ ዓመት አባ ጳውሎስ የሹመት ዝርዝር ውስጥ ካካተቷቸው 30 ያላነሱ ዕጩዎች ጥቂት የማይባሉ የተሃድሶ ግርፎች እና ደጋፊዎች መኖራቸውን የሚታወቅ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ባገኘነው ጊዜ ለምእመናን መረጃውን በግልጽ የምናሳውቅ መሆኑን እየገለጽን የተወሰኑ ማሳያዎችን ግን እንደማስጠንቀቂያ ደውል ማሳየት ተገቢ ሁኖ አግኝተነዋል፡፡

የግርግሩ አትራፊው ማነው?
በዚህ ሁሉ የሲመተ ሲሞን ግርግር ተጠቃሚው ማነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ የመፍትሔ ጠቋሚ አንዳች ረብ ይኖረዋል፡፡
  1. አቡነ ጳውሎስ በምእመናንም ሆነ በሚሰበሰቡት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚደርሳቸውን ተደጋጋሚ ተግሳጽ እና የሥራ መመሪያ በመናቅ እና በማጣጣል የሚታወቁ ሲሆን በቅርቡ እንኳን በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቦሌ መድኃዓለም ካቴድራል በር ላይ ያቆሙትን ሐውልተ ስምዕ (ሐውልታቸውን) እንዲያፈርሱ፣ ወደ አባቶች ማረፊያ የሚግተለቱሉትን ወይዛዝርት እና ባልቴቶች እንዲያስታግሱ የተሰጣቸው መመሪያ እንኳንስ ሊተገብሩ ይበሉ ይበርቱ የተባሉ ይመስል ብልሹ አሠራራቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታ፡፡ ከዚህም የተነሳ የግንቦቱ ቅ/ሲኖዶስ ይዞ የሚመጣውን ቁጣ በመፍራት ከዕውቀት፣ ከምግባር እና ከሃይማኖት የራቁ ግብረ በላዎችን ሲመት ጉዳይ ወደ መድረክ ይዘው በመምጣት አጀንዳ ለማስቀየር በዚህም አትራፊ ለመሆን ስላል፡፡
  2. ግበረ በላዎች፡ ቤተክህነት ውስጥ በአምቻና በጋብቻ በዘመድ አዝማድ መጠቃቀም ላይ የተመሠረተ የቤተሰብ አስተዳደር በማስፈን የምእመናንን መባዕ ያለ ከልካይ ለመዝረፍ ያሰፈሰፉ መጽሐፍ «እለ ከርሶሙ አምላኮሙ» የሚላቸው እነ ሆድ አምላኩ ገበታቸው አይጉደል እንጂ ቤተክርስቲያኒቱ በአፍጢሟ ብትደፋ ግድ የሚሰጣቸው አይደሉም።
  3. ተሐድሶዎች፦ ቤተ ክህነትን መቆጣጠር ምእመናንን መቆጣጠር መሆኑን በውል የተረዱት ተሐድሶዎች ያለ የሌለ ኃይላቸውን በማሰባሰብ ሲመተ ጵጵስናውን ለመቆጣጠር የሞት የሽረት ትግል በማድረግ ላይ ናቸው። የአቡነ ጳውሎስ ብልሹ አስተዳደርም ለሴራቸው ከለላ በመስጠት ትብብሩን ስላልነፈጋቸው ሊሆን አይችልም ለማለት ይከብዳል።

በቀጣይ ዝርዝር መረጃዎች እስከምናገኝ፤ ሰላም።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)