April 14, 2011

የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ ተጠናቀቀ


  • እነ ንቡረ እድ ኤልያስ በአጣሪ ኮሚቴው ስም ባቀረቡት ሪፖርት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከሐዋሳ እንዲነሡ፣ በማኅበረ ቅዱሳን የሓዋሳ ማእከል እንዲዘጋ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።
  • ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ጠንካራ ሥራ አስኪያጅ ከሁለት ረዳቶች ጋራ ተመድቦላቸው ባሉበት ሀገረ ስብከት ይቀጥላሉ፤
  • ሦስት የአጣሪ ኮሚቴው አባላት ማኅበረ ቅዱሳንን የቤተ ክርስቲያን ካልሆኑ አካላት ጋራ ደምረው ለመክሰስ ያደረጉትን ሙከራ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ እና ሌሎች ብፁዓን አባቶች ተቃወሙ፤
  • “በሓላፊነቴ የራሴ መረጃ አለኝ፤ ለምንድን ነው ማኅበሩን የችግር ምሕዋር ውስጥ የምትከቱት?” (ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ)
  • በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና ደቀ መዛሙርት ስም በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የቀረበው የክስ አቤቱታ በኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ፣ ምክትል አካዳሚክ ዲን እና ሌሎች ተማሪዎች ተቃውሞ ገጠመው
  • “ፕሮቴስታንታዊውን የተሐድሶ ኑፋቄ ወጥመድ የሚያጋልጠው ሰነድ ሲም የተባለ የተሐድሶ ድርጅት በአጭር ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ለመውረስ የቴዎሎጂ ት/ቤቶችን ማእከል አድርጎ ለመንቀሳቀስ የያዘውን ዓላማ የሚያጋልጥ እንጂ ኮሌጁን እንደ ተቋም የሚወነጅል እንዳልሆነ በበለጠ ግልጽነት ሊሠራበት ይገባል፡፡”(ብዙኀን የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት)
(ደጀ ሰላም፤ ኤፕሪል 14/2011)፦  በአስቸኳይ የተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የምልአተ ጉባኤውን ሥልጣን እና ክብር የሚያስጠብቁ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ማምሻውን ተጠናቀቀ፡፡ ከሃያ ያላነሱ አባላት በተገኙበት ረቡዕ ጠዋት በተከፈተው አስቸኳይ ስብሰባ መጀመሪያ ላይ በዐባይ ወንዝ ላይ ለሚሠራው ለታላቁ ሚሌኒየም ግድብ ግንባታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የአንድ ወር ሙሉ ደመወዛቸውን ለማበርከት ተስማምተዋል፤ በዚህ ረገድ ምእመናን እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በቀጣይነት በተለያየ መልክ የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ለማበረታት ተወስኗል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሲዳማ ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት የተፈጠረውን አስተዳደራዊ ክፍተት እና በሐዋሳ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያለውን ውዝግብ በተመለከተ በቋሚ ሲኖዶሱ የተሠየመው አጣሪ ኮሚቴ አባላት የተስማሙበት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ሪፖርቱ ተጠናቆ ባለማለቁ አጀንዳው ውሳኔ ሳይሰጥበት ሊቀር ችሏል።


“በሓላፊነቴ የራሴ መረጃ አለኝ፤ ለምንድን ነው ማኅበሩን የችግር ምሕዋር ውስጥ የምትከቱት?”           (ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ)
ይሁን እንጂ ሪፖርቱ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ወደ ጉባኤው በአስረጅነት የተጋበዙት የኮሚቴው አባላት ማለትም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ እና የሊቃውንት ጉባኤ አባሉ መምህር አእመረ አሸብር የራሳቸውን ሪፖርት በንባብ ማሰማታቸው ታውቋል። ነገር ግን “ይህንን ሪፖርት አናውቀውም፤ በጓዳ ተሠርቶ የቀረበ ነው” የሚል ብርቱ ተቃውሞ የአጣሪ ኮሚቴው አባላት ከሆኑት ከብፁዕ አቡነ ያሬድ እና ከብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ገጥሞታል ተብሏል፡፡

ስለ ጉባኤው ዝርዝር ሪፖርታዥ እንደደረሰልን ለማቅረብ እንሞክራለን።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)