April 27, 2011

በዓባይ ወንዝ ላይ ቤተ ክርስቲያን የነበራት ታሪካዊ ሚና ምን ነበር፤ አሁንስ ምን ዓይነት ሚና መጫወት ትችላለች???

(በፍቅር ለይኩን  ከደቡብ አፍሪካ):- የታሪክ መዛግብትና ሊቃውንት የሚነግሩን ታላላቅ የዓለማችን ሥልጣኔዎች መነሻ ወንዞች እንደሆኑ ነው። በዚህም በዓለማችን ታሪክ በግንባር ቀደምትነት ከመዘገባቸው ታላላቅ ሥልጣኔዎች (The Great World Civilizations) መካከል የሜሴፖታሚያ፣ የፋርስ፣ የባቢሎን፣ የግብጽ፣ የቻይና፣ የአሲሪያን፣ የግብጽና የእኛይቱ ኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች መነሻ ወንዞች እንደሆኑ ልብ ይሏል። ለእነዚህ ግዙፍ ሥልጣኔዎች ከፍተኛውን ሚና ካበረከቱት ወንዞች መካከል የኤፍራጥስና የጤግሮስ፣ ያንጊቲዝና የቢጫ፣ አማዞንና ዓባይ/ናይል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
መጽሀፍ ቅዱስም ሰለ ኤደን ገነት ሲተርክ የኦሪት መጽሀፍ ጸሀፊ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በገነት ዙሪያ ስላሉት ወንዞች በዘፍጥረት መጽሀፍ እንዲህ ገልጾታል፦

". . .ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከኤደን ይወጣ ነበር፤ የንደኛው ስም ፊሶን ነው፤ የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፣ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል። የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፣ እርሱም በአሶር ምስራቅ የሚሄድ ነው። አራተኛውም ወንዝ ኤፍርጥስ ነው።"
                                                                                         ዘፍጥረት ፪፥፲_፲፬

በተለምዶ የታሪክ አባት (The Father of History) ተብሎ የሚጠራው ግሪካዊው  ሊቅ ሄሮዶቱስ ሰለዓለማችን ታላላቅ ሥልጣኔዎች በጻፈው የታሪክ ድርሳን ውስጥ ግብጽን የዓባይ ስጦታ (The Gift of Nile) ሲል ጠቅሷታል፤ ሰለ ኢትዮጵያ በጻፈው የታሪክ ዘገባ ላይም ሰለሀገራችንና ሰለ ህዝባችን ሲናገር፦ “የተፈጥሮን ውብትና ሀብት የታደሉ፣ የቅዱሳን አማልእክት ሀገር፣ ሰዎቻቸው ጥበበኞችና መልከመልካሞች፣ ወንዞቻቸው በተራራ ላይ የሚፈሱ፣ ፈውስና መድኃኒት ናቸው” በማለት ዘግቦአል፤ በእርግጥም ሄሮዶቱስ እንዳለው በዓለማችን ረዥሙ የሆነው የናይል ወንዝ፣ በዓለማችን ታሪክ የሰው ልጅ ያለፈበትን እጅግ ታላላቅና ውስብስብ የሆኑ ሥልጣኔዎችን ለተቀረው ዓለም በማበርከት ረገድ ለግብጾች ከባለውለታ በላይ ነው ቢባል ያንሰበታል እንጂ አይበዛበትም።

ዛሬ በዓለማችን ካሉ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ ሀገሮች ግብጽን ቁንጮ እንድትሆን ያደረጋት የዚሁ የዓባይ ወንዝ ትንግርታዊ በረከት ነው፣ ብቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2011 ከ14 ሚሊዮን በላይ በሚቆጠሩ ቱሪስቶች የግብጽን ምድር እንደረገጡና በዚህም ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደቻለች መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ በተጨማሪም የናይልን ወንዝ ተፋሰስ ተከትሎ እየተካሄደ ያለው የእርሻ ምርት፣ የመስኖውን እና የኃይል ማመንጫ የግድቦቿን ብዛት ለሚታዘብ ሰው ዓባይ ለግብጻውያን ሕይወታቸው ወይም እስትንፋሳቸው ነው የሚለው አባባል ምን ያህል እውነታ እንዳለው ምንም ሊታዘበው የሚችለው ሀቅ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት የግብጽንና የመካከለኛው ምስራቅን የፖለቲካ ታሪክ ያስተምሩን የነበሩት ፕሮፌስር በወቅቱ የናይል ወንዝ፣ የግብጽንና የተፋሰሱ ሀገራትንና እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅን ፖለቲካዊ ትኩሳት በማናርም ሆነ በማረጋጋት ረገድ የናይል ስጦታ የሆንችው ግብጽ የምትጫወተውንን ሚና እያስረዱን በነበረበት ወቅት ባዛው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ፕሮፌሰር የሥራ ባልደረባቸው ‘The Hydro politics of Nile’ በሚል በዓባይ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የነበረውን ፍጥጫ፣ ግጭት፣ ውሎችና ፖለቲካዊም ሆኑ ኢኮኖሚ አንድምታዎች የተነተኑበት መጽሀፋቸውን በመጥቀስ፣ ግብጽ በከፍተኛ ደረጃ በአሜሪካና በአውሮፓ ባሉ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ዜጎችዋ በዋነኛነት የሚያጠኑት ትምህርት Hydrology እና Water Engineering እንደሆነ ከዚሁ መጽሀፍ በመጥቀስ የሰጡን መረጃ ግብጻውያን በዓባይ ጉዳይ ምን ያህል ቁርጠኛና የማያወላውል አቋም እንዳላቸው ያስገነዘበን ነበረ በወቅቱ።

በናይል ወንዝ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አንድምታ ዙሪያ ላይ ብዙ ጥናት ያደረጉት እኚሁ ምሁር ምናልባትም የሶስተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ወንዞች ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ስጋታቸውን የገለጹበት ሁናቴ ነበር፤ እንዲሁም the influential head of the Environment Research Institute World Watch, ተጠሪ የሆኑት Lester Brown, በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር "water scarcity, and that Egypt is unlikely to take kindly to losing out to Ethiopia."

እንዲሁም Dr Mohammad El Salim የተባሉ በካይሮ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ "Ethiopia’s ambitious development plans, if implemented, will pose a grave threat to Egypt before the end of the century" በማለት በዓባይ ውኃ ዙሪያ በሚታቀዱ ልማቶች ላይ ሀገራቸው ያላትን ስጋት በግልጽ አስቀምጠውታል። ክቡራን አንባቢዎቼ ግብጽ ለዘመናት በዓባይ ዙሪያ የነበራትን ስጋት፣ ስሱነትና ማስፈራራት በበለጠ ለመረዳትና በዓባይ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ለማግኘት ከላይ የጠቀስኩትን መጽሀፍና ሌሎች በርካታ የሆኑ ጥናታዊ ጹሁፎችን ማንበብ እንደምትችሉ በመጠቆም ወደ ጹሁፌ ዋና ጭብጥ ላምራ።መቼም በዓባይ ወንዝ ላይ ግብጻውያን ያላቸው የማያወላውል አቋም ምን ያህል ጥንካራና ብሄራዊ ስሜትን የተላበሰ እንደሆነ ብዙዎቻችን እንረዳለን ብዬ አስባለሁ። በዓባይ ዙሪያ የእስልምና ተከታዮችም ሆኑ በክርስትና እምነት የምንዛመዳቸው ወንድሞቻችን በዓባይ ዙሪያ ምንም ለድረድር የሚቀርብ ነገር እንደሌለ ፊት ለፊት ሲነግሩን እንደነበረ በበርካታ አጋጣሚዎች መጥቀስ እንችላለን። በክርስትና ሃይማኖት ምክንያት ለብዙ ዘመናት የተወዳጀናቸውና በተደጋጋሚ ለበርካታ ዘመናት በእስልምና እምነት ተከታዮች ለሚደርስባቸው መከራና ግፍ  አብዝተን የጮኽንላቸው ክርስቲያን ግብጻውያኑም ሆኑ ለእስልምና ሀይማኖት ታላቅ ባለውለታ የሆነችው ኢትዮጵያችን በናይል ዙሪያ እነዚህ የወዳጅነት ውለታዎች ምንም ሚና የሌላቸው በዚሮ የተባዙ እንደሆኑ በበርካታ አጋጣሚዎች ለመገንዘብ ችለናል። ስለዚህም መብታችንን ለማስከበር ወሳኙ ነገር አቅምን ማዳበርና የኢኮኖሚያችንን ኃይል ማጠናከር እንደሆነ ከተረዳን ውለን አድረናል።

እንዲህ በዓለም ዙሪያ በጦርነት፣ በርሃብ እና በድርቅ በድህነት ጥቁር መዝገብ ከመስፈራችንና ጩኸታችን ሁሉ ሰሚ ያጣ ከመሆኑ በፊት የዓባይ ውሃ፣ ግብጽ በእስልምና መዳፍ ስር ከዋለች በኃላ በአናሳዎቹ ክርስቲያን ግብጾች ሙስሊሞቹ ለሚያደርሱባቸው መከራና ሰደት በኢትዮጵያውያኑ ነገስታት እንደማስፈራሪያ ይጠቀሙበት እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ። ዓለማውያኑም ሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ አዋቂዎች እንደሚነግሩን በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ነገስታት ዓባይን በመገደብ ወይም የወንዙን አቅጣጫ በማስቀየር ክርስቲያን ወንድሞቻቸውን ለመከላከል እንደማስፈራሪያ ይጠቀሙበት እንደነበር ብዙ ማስረጃዎች አሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለ1600 ዓመታት ጳጳስ ታሰመጣ የነበረው ከግብጽ ስለነበር እነዚህን አባቶች የማግኘት ጥያቄና የግብጻውያኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ጸጥታንና ድኅነት ጉዳይ በከፊልም ቢሆን ከዓባይ ጋር ተያያዥነት እንደነበረው ብዙ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ብጹእ አቡነ ጎርጎሪዮስ(ቀዳማይ) በጻፉት "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" መጽሀፋቸው በዛግዌ ዘመነ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ተልከው የነበሩት ጳጳስ አቡነ ሳዊሮስ በግብጽ ሲኖዶስ የተመረጡ ሳይሆን በእስላማዊው ንጉስ በበድር አል ጀማል ትእዛዝ የተላኩ ጳጳስ እንደነበሩና ከሀገራቸው ንጉሱ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረትም፤ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ሥራ ከመጀመራችው በፊት በኢትዮጵያ ለሚኖሩ አርብ እስላሞች መስጊዶች እንዲሰሩ አደረጉ።

እስላሞቹም በኢትዮጵያ ላይ ሃይማኖታቸውን እንዲያስፋፉ የሐሳብ ድጋፍ ይሰጧቸው ጀመር፤ በእርግጥ እኚህ አባት ይሄን ያደረጉበት ዋንኛው ምክንያት እንደ አቡነ ጎርጎሪዮስ ገለጻ በግብጽ ያሉ ክርስቲያን ወገኖቻቸው የመከራ ቀንበር እንዲቀልላቸው ብለው እንደሆነ ያስረዳሉ፤ ይሁን እንጂ በወቅቱ ከኢየሩሳሌም በመቀጠል ቅዱስ የክርስቲያን ምድር ተብላ በምትጠራው በኢትዮጵያ ምድር መስጊዶች መታነጻቸው ያላስደሰታቸው ክርስቲያኖችና ንጉሱ በአስቸኳይ መስጊዶቹ እንዲፈርሱ በማድረጋቸው ይሄን ዜና የሰማው የግብጽ ንጉስ ለኢትዮጵያው ንጉስ ለግርማ ሥዩም በላከው አስቸኳይ መልእክት፦

"በሀገርህ የፈረሱት መስጊዶቻችን እንደገና ካልተሰሩ እኔም በግብጽ የሚገኙትን የኮፕት አብያተ ክርስቲያናትን እንዳልነበሩ አድርጋቸዋለሁ" በማለት ዛቻ የተቀላቀለበት መልክት ላደረሳቸው የግብጽ ንጉሥ የኢትዮጵያዊው ንጉሥ በላኩት የአጸፋ መልእክት፥ "ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ድንጋይ ብታነሳ መካ ተሻግሬ የካአባን ድንጋይ አመድ አድርጌ ትቢያውን ካይሮ እልክልሃለሁ" በማለት ምላሽ እንደሰጡት አቡነ ጎርጎርዮስ በመጽሀፋቸው ገልጸውታል።

በሌላ በኩል አንዳንድ የአረብ ታሪክ ጸሀፊዎች እንደዘገቡት ደግሞ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ "ከመካ የመስጊዱን ድንጋይ አስመጥቼ የፈረሱትን መስጊዶች አሰራልሃለሁ" በማለት የምጸት ምላሽ እንደሰጡት ዘግበዋል፤ በግብጽ ክርስቲያኖችና በኢትዮጵያውያኑ ክርስቲያኖች መካከል ለረጅም ዘመናት የቆየው ግንኙነት በመጥፎም በመልካም የሚነሱ ብዙ ታሪካዊ እውነታዎች ቢኖሩም በዋንኛነት ግን ግብጽ በእስላሞች እጅ ከወደቀች በኃላ ክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችም ሆኑ ነገሥታቱ በዝምታ ያለፉበት ጊዜ እንደሌለ ከበቂ በላይ የታሪክ ማስረጃዎች እንዳሉ አንባቢያን እንዲያውቁት  መጠቆም እፈልጋለሁ።

ግብጻውያኑ ሙስሊሞች በክርስቲያኑ ላይ ያደርሱት ለነበረው ግፍ በዋንኛነት የግብጽ እስትንፋስ የሆነው የዓባይ ወንዝ ክርስቲያኖቹ ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ ለመከላከል ከማስፈራሪያነት ባሻገር በተግባር ዓባይን ለመገደብና የውኃውን አቅጣጫ ለማስቀየር የሞከሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል። በጉልህ የሚጠቀሱትም ንጉሥ ይምርሐነ፣ ንጉሥ ሐርቤ፣ አጼ አምደ ጽዮን፣ አጼ ዳዊትና አጼ ዘርያአቆብ ናቸው። በተለይ ንጉሥ ይምርሀነ ዓባይን የመገደብ ሥራ በመጀመሩ በእጅጉ የተደናገጡት ግብጻውያን ወደ ኢትዮጵያ በላኳቸው መልእክተኞች ዓባይን መገደብ የሚያለቁት ግብጻውያን እስላሞች ብቻ ሳይሆኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁም ጭምር ናቸው በማለት የተማጽኖ መልእክት በእስክንድሪያው ሊቀ ጳጳስ በአቡነ ሚካኤል በኩል ተልኮ እንደነበረ የታሪክ መስረጃዎች ይጠቁማሉ።

እንዲሁም አጼ ዘርያእቆብ በዘመናቸው በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ ለመበቀል የዓባይን ወንዝ ለመገደብና የውኃውን አቅጣጫ ለማስቀየር ባደረጉት ሙከራ ግራ የተጋቡት ግብጻውያን ወደ ንጉሡ በላኳቸው ከፍተኛ የእስልምና ታላላቅ አባቶች የተመራ ልኡካን ለአጼ ዘርያቆብ ብዙ ስጦታዎች፣ ብርና ወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮች እንዲሁም የተማጽኖ መልእክት ይዘው መጥተው ለነበሩት መልእክተኞች ባስተላለፉት መልእክት፦

"...ያመጣችሁት ብርና ወርቅ እንዲሁም ሌሎች ስጦታዎቻችሁ ለራሳችሁ ይሁኑ፣ እኔ የክርስቲያን ንጉሥ ነኝ ነገሥታቶቻችሁ በተደጋጋሚ በግብጻውያን ክርስቲያን ወንድሞቻቻን ላይ ለሚያደርሱት ግፍ በቀልን ላድርግ ብል እጅግ የከፋ ነገር ላደርስባችሁ እችል ነበር፤ ግና ሕዝቤና እኔ በንጹህ ኅሊና የምናመልከው ጌታዬ፣ አምላኬና ንጉሤ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር አምላክ ነውና ያስተማርኝ ቀኝ ጉንጭህን ለሚመታህ ግራውን ደግሞ አዙርለት ስለሚል ስለአምላኬ ፍቅርና ውለታ ስል ያሰብኩትን ሁሉ ትቼያለሁ መንግስታችሁ በክርስቲያን ግብጻውያን ወንድሞቻችን ላይ የሚያደረሰውን ግፍ ብቻ እንዲያቆም ንገሩት..." በማለት መልእክተኞቹን በሰላም ማሰናበታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በአውሮፓ ሀገራት ማየቱን ለትምህርት በዛ የቆየ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል። ቤተ ክርስቲያኒቱም ሆኑ ነገሥታቱ ለዘመናት የግብጽ ክርስቲያኖችን ለመታደግ እንደማስፈራሪያ ይጠቀሙበት የነበረው የዓባይ ወንዝን የመገደብና አቅጣጫ የማስቀየር ሙከራን አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በዛን ወቅት ምን ያህል የኢኮኖሚ አቅም፣ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ወይም ባለሙያ ብርቱ ወኔና የበላይነት እንደነበራቸው የሚያሳይ ነው።

የውኃ ምህንድስና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት እንኳን ዓባይን ያህል ግዙፍ ወንዝ ቀርቶ አነስተኛ ወንዞችን ለመገደብም ሆነ የፈሰት አቅጣጫቸውን ለመቀየር ብዙ አቅምና ባለሙያ እንደሚጥይቅ ያስረዳሉ፣ ታዲያ በዛን ጊዜ ይሄን ለማድረግ የሚያስችል እውቀቱም ሆነ ሀብቱ ነበር ወይ ብዬ ራሴን ስጠይቅ... በእርግጥም ከታላላቅ የአለት ተራራዎች እነዛን እስከዛሬም ድረስ በምን ዓይነት ቴክኖሎጂና ጥበብ እንደተሰሩ ምላሽ ያላገኙትን፣ የሰው ልጅ የስልጣኔ ታሪካዊ ትንግርት (Wonders of the World) የሆኑትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያነጹ፣ እነዛን ግዙፍ የሆኑ ሰማይ ጠቀስ የአክሱምን ሀውልቶች የቀረጹ ትውልዶች በነበሩባት ኢትዮጵያ ዓባይን የመገደብ ሂደት ከሚገባው በላይ ሊቀላቸው እንደሚችል በዘመኑ ከነበረው የምንህድስና የአርክቴክቸር ጥበብ አንጻር ልንገምት እንችላለን።

የሚገርመው ከቡዙ ዘመናት በኃላ ዛሬ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ ላለው ህዝባችን በደጁ በነጋ ጠባ የሚፈሱትን ወንዞች እንኳ በመስኖ በመጥለፍ ራሳችንንና ህዝባችንን ለመታደግ ያልቻልንበትን እንቆቅልሽ ሳስብ ግርም ይለኛል፤ ባለፉት ዘመናት ዓባይን ሰለመገደብ አይደለም ሰለዓባይ ኢትዮጵያዊነት ማውራት የግብጻውያኑን ዓይን ደም እንዲለብስ የሚያስደርግ በማንኛውም ሁኔታ ዓባይ ላይ ሀገራችን የምታነሳው ፍትሃዊ ጥያቄ ሁሉ ለድርድር የማይበቃበት ከንቱ ጩኸት ወደ ሆነበት፣ ከመፈራትና ከክብር ታሪካችን ተምዘግዝገን ወደ ታች የዘቀጥንበትን እውነታ እየመረረንም ቢሆን ለመቀበል የተገደድንበት አሳፋሪ ዘመናትን አሳልፈናል።

በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ የዓለምን ህዝብ ሁሉ ጉድ ባሰኘና እንባ ባራጨ ረሃብ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝባችን በርሃብ መርገፉ ልባቸውን የነካቸው ኢትዮጵያውያን የውሃ ሀብት ምህንድስና የምጣኔ ሀብት ምሁራኖች እንዲህ ዓይነቱ ዘግናኝ እልቂት በሀገራችው እንዳይደረስና በምግብ እህል ራስን ለመቻል በጣና ዙሪያ አካባቢ ጥናት እየተደረገ የመሆኑ ዜና የደረሳቸው የወቅቱ የግብጽ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት ባደረጉት ንግግር እንዲህ ነበር ያሉት፦
“Any action that would endanger the waters of the Blue Nile will be faced with a firm reaction on the part Egypt, even if that action should lead to war. As the Nile waters issue is one of the life and death for my people, I feel I must urge the United States to speed up the delivery of the promised military aid so that Egypt might not be caught napping.”

ዛሬ ግብጽ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ካላት ከፍተኛ ተሰሚነትና በአረቡ ዓለምና በመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ፍጥጫ ከምትጫወተው የማረጋጋት ወሳኝ ሚና የተነሳ የተናገሩት ሁሉ የሚሰማ፣ ያዘዙት ሁሉ የሚፈጸምላቸው ወደ መሆን የክብር ሰገነት የተሸጋገሩ በመሆናቸው ሀገራችን በዲፕሎማሲም ሆነ በኃይል በዓለም መድረክ ሳንሸማቀቅ መብታችንን የምናስከብርበት የኃይል ሚዛን ምን ያህል ወደግብጾች እንዳዘነበለ ሁላችንም የምንረዳው ሐቅ ነው። ያም ብቻ ሳይሆን በግብጽ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ክርስቲያኖቹም ሆኑ ሙስሊሙ የግብጽ ሕዝብ ምን ያህል ትብብር እንዳላቸው በቅርቡ አምባገነኑን የኦስኒ ሙባረክን መንግስት ለመጣል በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ያሳዩት ትብብር ምን ያህል ለብሔራዊ ጥቅማቸው በአንድነት የሚቆሙ እንደሆኑ የተረዳንበት የታሪክ አጋጣሚ ነው።

ከብዙ ዘመናት በኃላ ባነን የተነሳንበት ዓባይን የመገደብና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብት ለብዙ መቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብጻውያኑ ጋር ከነበራት የታሪክ ቁርኝት አንጻር ዛሬ ዘግይተንም ቢሆን ለተነሳንበት የዓባይን ውኃ የመጠቀም መሰረታዊና ፍትሃዊ ጥያቄዎች ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወሳኝ የሆነ ሚና መጫወት እንደምትችል ለማሳሰብ እወዳለሁ፤ በተለይ በግብጽ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸውን ከርስቲያን ግብጻውያን ወንድሞቻችንን በዲፕሎማሳዊም ሆነ በክርስቲያናዊ ወርቃማ የፍቅር ህግ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ሀገራችን በገዛ ሀብቷ ባይተዋር የሆነችበት የታሪክ ምእራፍ ይዘጋ ዘንድ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ በማድረግ ጥረታችንን መቀጠል ይገባናል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች ከግብጻውያን አባቶችና ክርስቲያን ፖለቲካኞችና ሙሁራን ጋር በመነጋገር ሀገሪቷ በዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭ ወንዞች ህግ ስምምነት መሰረት (Cross Country Rivers Treaties) ከዓባይ ወንዝ መጠቀም ያለባትን ሁሉ መጠቀም እንድትችል የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ትልቅ የሆነ ታሪካዊ ኃላፊነት የሚወስዱበት ወቅት እንደሆነ ለመጠቆም እሻለሁ። ምንም እንኳን በተደጋጋሚ በታሪክ አጋጣሚ እንዳየነው ክርስቲያኖቹ ግብጻውያን በብሔራዊ ጥቅማቸው ዙሪያ ያላቸው ግትር አቋምና ለዘመናት በሁለቱ ሕዝቦችና አብያተ ክርስቲያናት መካከል የንበረው አለመስማማትና አልፎ አልፎ የነበሩት ግጭቶች በመጠኑም ቢሆን ተወግደው አንጻራዊ በሆነ መልኩ ግንኙነታችን እየተሻሻለ ቢሆንም፤ ግብጻውያኑ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ግትር አቋም በማለዘብ አኳያ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች የጀመሩትን ግንኙነት በማጠናከር ወሳኝ ሚና መጫወት ያለባቸው ይመስለኛል።

ለዚህም በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነት በሳል የሆነ እውቀትና ልምድ ያካበቱት ፓትርያሪክ አቡነ ፓውሎስ ያላቸውን ከፍተኛ ተደማጭነት በመጠቀምና እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ህብረትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም ፕሬዝዳንት እንደመሆናቸውም ጭምር ትልቅ ጫና መፈጠር እንደሚችሉ እገምታለሁ። እንዲሁም በሀገራችን በሃይማኖቶች መካከል መልካም ግንኙነትና መከባበር እንዲኖርና፣ በአንድነት በመሆን ለሀገር ክብርና ጥቅም እንዲሁም ልማት መጫወት የሚችሉትን ሚና ለማጠናከር በተከታታይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ በካቶሊክ፣ በእስልምና እምነት ሃይማኖት አባቶችና በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መካከል በመቻቻቻልና በአንድነት ለሀገራችንና ለህዝባችን ብልጽግና የተጀመሩትን መልካም ውይይቶች አጠናክሮ በመቀጠል ሀገራችን ወደተሻለ የኢኮኖሚና የልማት ጉዞ ወደ ፊት መሄድ እንድትችል እንዲሁም በወቅታዊነት በገዛ ውኃችን የበይ ተመልካች የሆንበት የዓባይ የዘመናት እንቆቅልሽ ይፈታ ዘንድ በርቱ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል።

ስለዚህም ነጋ ጠባ ወንዞቻችን በዓይናችን ፊት እየፈሰሱ በርሃብ አለንጋ የምንገርፍበት ዘመን ያበቃ ዘንድና ሳንሳቀቅ ቢያንስ በቀን ሶስቴ የምንበላበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ሁላችንም ልዩነታችንን አጥብበን ለብሔራዊ ጥቅማችን በጋራ ልንቆም የገባናል። ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች "ከዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው!" ተረት ወጥተን ከዓባይ በረከት ጠጥተን ወደ ምንረካበት የታሪክ ምእራፍ እንሻገር ዘንድ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንነሳበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል።
ሰላም! ሻሎም!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! ለግብጻውያኑ ወንድሞቻችንም ቅን ልብ ይስጥልን!!!


References:
  1.   ሔሮዶቱስ ፫ና መጽሀፍ ምእራፍ ፳_፩፻፲፬ 
  2.  Spencer Trimingham, Islam in Ethiopia, (London: Oxford University Press, 1952), 70-71.  
  3. Akhbar El Yom (Cairo) May 13th, 1978.
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)