April 16, 2011

በዴር ሡልጣን ገዳም መንግሥታዊ ትእዛዝ የተሰጣቸው አቡነ ማቲያስ ከባለሥልጣናት እና ፖሊሶች ጋራ እየተከራከሩ ነው


  • ሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ጥሪ ቀርቧል
አቡነ ማቲያስ
(ደጀ ሰላም፤ ኤፕሪል 16/2011)፦  በዴር ሡልጣን ገዳም “የኮፕት መነኩሴ በቀዳም ስዑር ሻማ አብርቶ ይዞ ይለፍ” የሚል መንግሥታዊ ትእዛዝ የተሰጣቸው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲያስ ከመንግሥት ባለሥልጣናት እና ፖሊሶች ጋራ እየተከራከሩ ነው:: በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ እና ማኅበር አባላት ግብጻዊው የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መነኩሴ በበዓለ ትንሣኤ ዋዜማ (ቀዳም ሥዑር) ከጎልጎታ - የጌታ መቃብር ሻማ አብርቶ ይዞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ይዞታ በሆነው በዴር ሡልጣን ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በኩል ገብቶ በመድኃኔ ዓለም እና አርባዕቱ እንስሳ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለውስጥ አልፎ ወደ ኮፕቲክ ገዳም እንዲገባ ፈቃድ እንዲሰጠው ካዘዙት የእስራኤል መንግሥት ባለሥልጣናት እና ትእዛዙን በግድ ለማስፈጸም ከሚዝቱት የብሉይ ከተማ ኢየሩሳሌም ፖሊሶች ጋራ እየተከራከሩ መሆናቸው ተገለጸ፡፡ ትእዛዙ በነባሩ የስታተስ'ኮ ሕግ ያልነበረ እና ሕጉን የሚጥስ፣ በትንሽ በትልቁ ለኮፕቶቹ ጥያቄ ከሚሰጠው ልዩ ትኩረት እና መረባረብ በተፃራሪ በኢየሩሳሌም ተመሳሳይ በሌለው አስከፊ ሁኔታ ከሰብአዊ ፍጡር በታች እንዲኖሩ በተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ላይ በብሉይ ከተማ ኢየሩሳሌም ባለሥልጣናት እየተደረገ ያለው ጫና ቀጣይ ሂደት እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ጥንተ ይዞታ የነጠቁት ኮፕቶች በተጽዕኖ ብዛት ማኅበረ መነኮሳቱን ከቦታው በማጥፋት ገዳሙን ሙሉ በሙሉ ለመንጠቅ ያላቸው ሕልም አካል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

The stone huts of Deir al Sultan monastery in Jerusalem are at the heart of the row between Ethiopia and Egypt  [Photo: BBC]
በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ለብዙኀን መገናኛ ባሰራጩት ባለሦስት ገጽ መግለጫ እንዳብራሩት፣ ከመጋቢት 21 ቀን 2003 ዓ.ም (30/302011) ጀምሮ ባልተጠበቀ ሁኔታ የተለያየ ማዕርግ እና የሥራ ድርሻ ባላቸው ሰባት የብሉይ ከተማ ኢየሩሳሌም (Old City of Jerusalem) የእስራኤል ፖሊሶች፣ ከሃይማኖት ጉዳይ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሦስት ባለሥልጣናት በተከታታይ ሰዓታት ወደ ኢትዮጵያ ገዳም መንበረ ጵጵስና በመምጣት “በበዓለ ትንሣኤ ዋዜማ ግብጻዊው መነኩሴ ሻማ አብርቶ ይዞ በእናንተ ይዞታ እንዲያልፍ ፍቀዱ አለበለዚያ እ.አ.አ በ1971 የተላለፈውን ውሳኔ በሥራ ላይ የማዋል ግዴታ ስላለብን በግድ በፖሊስ ኀይል እናሳልፈዋለን” እንዳሏቸው አስረድተዋል፡፡ በባለሥልጣናቱ የተገለጸው ውሳኔ ኖረም አልኖረም መተላለፊያው ኮፕቲኮችም ሆኑ የዓለም ቱሪስቶች ዓመት እስከ ዓመት በየቀኑና በየሰዓቱ የሚመላለሱበት ቢሆንም ኮፕቲኮች ሻማ አብርተው በዴር ሡልጣን ያልፉ እንደ ነበር የሚያገልጽ ማስረጃ ከቶ የለም፤ አልፈው አያውቁም፣ በታሪክም የለም፡፡ ብፁዕነታቸው በመግለጫቸው እንዳሉት “ኮፕቲኮች ለጭካኔያቸው ገደብ የላቸውም፤ ውሳኔው ቢኖርማ ኑሮ ስንኳን 40 ዓመት 40 ሰዓት አይጠብቁም ነበር፡፡”

ኮፕቲክ መነኮሳቱ በየዕለቱ ከሌሊቱ 10 ሰዓት(4፡00 ኤ.ኤም) ወደ ጎልጎታ እንዲያልፉበት “የመድኃኔዓለምንና የአርባዕቱ እንስሳ እንዲሁም የቅዱስ ሚካኤልን በሮች ክፈቱላቸው” የሚል ውትወታ ሁልጊዜ እንደሚደርሳቸው ያመለከቱት ብፁዕነታቸው፣ “እኛ ግን በተቃራኒው በዓለ ሆሣእናን፣ በዓለ ትንሣኤን፣ በዓለ መስቀልን እና የመሳሰሉትን ዐበይት በዓላት በዐውደ ምሕረት ላይ በምናከብርበት ጊዜ በዚህ በኩል ብቻ እንጂ በዚያ በኩል መብራት እንዳታበሩ፣ የድምፅ ማጉያ እንዳትጠቀሙ፣ ሳትጮሁ ቀስ ብላችሁ ዘምሩ. . .ወዘተ እያሉ በየጊዜው ተጽዕኖ ማሳረፍ የተለመደ ነው” ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሁለት ጊዜ ያህል ከብሉይ ከተማ ኢየሩሳሌም ባለሥልጣናት ጋራ ስብሰባ መደረጉን ያሰፈረው የብፁዕነታቸው መግለጫ ባለሥልጣናቱ ለሚጠቅሱት ውሳኔ በገዳሙ ማኅበር አባላት በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት እ.አ.አ በ1971 የተላለፈ ነው ያሉትን ውሳኔ ሁለት ገጽ የእንግሊዝኛ ደብዳቤ በተመሳሳይ ዕለት አምጥተው መስጠታቸውን ያሳያል፡፡ ደብዳቤው ግን በአድራሻ የተጻፈው በዘመኑ ለነበሩት ለኮፕቲኩ ሊቀ ጳጳስ ለአባ ባስልዮስ እንጂ ለኢትዮጵያ ገዳም እንዳልነበረ፣ በደብዳቤው ላይ የሰፈረው ኀይለ ቃል “ቁልፎቹ እና የቦታው ይዞታ በኢትዮጵያውያን እጅ ቢሆንም ነጻ መተላለፊያው (free access) ለኮፕቲክ ማኅበረሰብ ተጠብቆላቸዋል” ይላል እንጂ “ኮፕቲኮች ሻማ ይዘው ይለፉ” የሚል ትእዛዝ እንደሌለው፤ በመሠረቱ በይዘቱ ሚኒስትሮቹ ለመንግሥት ያቀረቡት ሓሳብ እንጂ ውሳኔ እንዳልሆነ፣ በምንም መልኩ መንበረ ጵጵስናውን እንደማይመለከት፣ ፖሊሶቹም “የመንግሥትን ትእዛዝ እናስፈጽማለን” ያሉት የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሆነ ግልጽ እንዳይደለ፣ ኮፕቲኮቹ ደብዳቤው የሚጠቅማቸው ሆኖ ቢያገኙት ኑሮ 40 ዓመታት ሙሉ ሸሽገውት እንደማይኖሩ በኢትዮጵያ ገዳማት ማኅበር መመርመሩን የብፁዕ አቡነ ማቲያስ ደብዳቤ ያትታል፡፡

ሚያዝያ 16 ቀን 2003 ዓ.ም የሚከበረው የትንሣኤ በዓል በመቃረቡ “ንግግሩ ከትንሣኤ በኋላ ቢቀጥል” የሚል ሓሳብ ሁለት ጊዜ ተመላልሰው ለመጡት የእስራኤል ባለሥልጣናት እና ፖሊሶች የቀረበ ሲሆን “በምንም ዐይነት፤ ዛሬውኑ ማለቅ አለበት” ማለታቸው ተገልጧል፡፡ ይህም እንደ ብፁዕነታቸው መግለጫ፣ “በድንገት ሳይታሰብ በሁለት አቅጣጫ የተረባረቡብን ሳናስብበት የይሁንታ ቃል ከአፋችን ለመንጠቅ ነበር፤ ሁለቱም ግሩፖች (ኮፕቲኮቹ እና ባለሥልጣናቱ) በደንብ ተዘጋጅተው ነበር የመጡት፤ እኛ በዚህ ሰዓት ሄደን እናስጨንቃቸዋለን፤ እናንተ ደግሞ ተከታትላችሁ መጥታችሁ ተጫኗቸው ተባብለው እንደ መጡ በግልጽ ይታይ ነበር፣ እነርሱም ይህን አልሸሸጉም” ብለዋል፡፡

ከዛሬ 240 ዓመታት በፊት ኮፕቲኮች ዋናውን ገዳማቸውን ሲቀሟቸው በዘመኑ የነበሩት ኢትዮጵያውያን መናኞች መነኮሳት እና መነኮሳዪያት የተነጠቁትን ገዳም ለማስመለስ በነበራቸው ተስፋ ኃይላቸውን እስኪያጠናክሩ ድረስ ከሩቅ ቦታ ድንጋይ እና ውኃ እየተሸከሙ በሠሯቸው መቃብር ቤት መሰል የጭቃ ጎጆዎች እስከ አሁን ይኖራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በእነዚህ ጉድጓዶች እንኳን ሰው አውሬም አይኖርባቸውም፤ ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገፋ መጥቶ ለሰው ሕይወት ጠንቅ እስከ መሆን ደርሷል፤ ቤተ መነኮሳቱ አየር ማስገቢያ የለውም፤ መጸዳጃ የለውም፤ በጠቅላላ በቆሻሻነቱ በኢየሩሳሌም ከተማ ተመሳሳይነት የሌለው የመጨረሻ አስከፊ ቦታ ነው፡፡

ችግሩን በተገኘው አጋጣሚ በብሉይ ከተማ ኢየሩሳሌም ለሚሾሙት የእስራኤል ኮማንደሮች እና ልዩ ልዩ የፖሊስ አዛዦች በዐይን እንዲያዩት ስናደርግ ‹ቤቶቹን› በርግጥ ሰው ሊኖርባቸው እንደማይገባና አስቸኳይ ጥገና እንደሚያስፈልጋቸው ይመሰክራሉ፤ ነገር ግን በተግባር አይተረጉሙትም፡፡ የኢትዮጵያውያን የታሪክ እና የቅድስና ቦታ በመሆኑ ብቻ አባቶቻችን እና እናቶቻችን መከራውን በጸጋ ተቀብለውት እንዳለፉ ሁሉ እኛም እንደነርሱ ችግሩን ተሸክመን እንኖራለን፤ የዴር ሡልጣን ቤተ መቅደሶች እና ቤተ መነኮሳት በመነኮሳቱ ላይ ከመፍረሱ በፊት ይታደስ ዘንድ ማመልከቻ ከቀረበ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ሆኖታል፡፡ ከኢትዮጵያ ገዳም፣ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ከኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የተውጣጣ “የዴር ሡልጣን እድሳት ኮሚቴ” በ2000 ዓ.ም ተቋቁሞ ያደረገው ጥረት እና የለፋው ልፋት እጅግ ብዙ ሲሆን እስከ አሁን የቃል ተስፋ ከመስጠት በቀር አንድም የተደረገ ነገር የለም፡፡ ግን እስከ መቼ? በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ዴር ሡልጣን ላይ የተደቀነው ችግር ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ ነው፤ ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው የሆነብን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ሰዎች ነን፤ አገር አለን፤ መንግሥት አለን፤ ሕዝብ አለን፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ እውነተኛው ዳኛ እግዚአብሔር አለ፤ ሰብአዊ ፍጡሮች ነንና ሰብአዊ መብታችን ይከበርልን፡፡

ችግሩ ይህን ያህል በከፋበት ሁኔታ የሰውን ሕይወት ለማዳን በማሰብ እና በመጨነቅ ፈንታ “ኮፕቲኮች ሻማ ይዘው ካለፉ ሞተን እንገኛለን” ብሎ መጨነቅ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ጭምር መሆኑን አምርረን አሰምተናቸው ተጽዕኖ ያደረጉብን የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፖሊስ ሠራዊቱ ለጊዜው ምንም ሳያደርጉ መመለሳቸውን የሚያስረዳው የብፁዕነታቸው መግለጫ “ይሁን እንጂ የፖሊሶቹን ሁኔታ እንደ ተመለከትነው በኃይል ከማስገባት ወደኋላ የሚሉ አይመስሉምና ብርቱ ጥንቃቄ እና አስቸኳይ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል” ሲል ያሳስባል፡፡ በመሆኑም “በሀገር ውስጥም ሆነ ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቃውሞውን ማሰማት አለበት፤ በተለይ በቴል አቪቭ የሚገኘው ኤምባሲያችን እንደተለመደው ከፍተኛ ጥረት የማድረግ ሓላፊነት አለበት” በማለት የተማኅፅኖ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል አባቶቻችን እና እናቶቻችን ኢትዮጵያውያን ተጓዧች ለዘመናት በባሕር እና በአሠቃቂ የበርሓ ጉዞ ማይልሶችን እያቋረጡ የቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የቅድስና እና የታሪክ ይዞታችንን ሲያስጠብቁ የኖሩበት ጽናት መንፈሳዊ ወራሽ በመሆን ለዓመታት ሲሠራ የኖረውን የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት በማናወጥ እና በማዳከም “ቀራንዮ በኢየሩሳሌም አስጎብኚ የጉዞ ወኪል” የተባለ የግላቸውን ድርጅት ባቋቋሙት /ዝርዝሩን በደጀ ብርሃን የጡመራ መድረክ http://www.dejeberhan.org/2010/10/blog-post.html ላይ ይመልከቱ/ በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ በኩል ተመዝግበዋል የተባሉ ተጓዦች ትናንት አርብ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በፓትርያርኩ ሽኝት እንደ ተደረገላቸው ተገልጧል፡፡ በጉዞው አምስት ያህል ሊቃነ ጳጳሳት አብረው በመሄድ “ተጓዡን በማስተማር እንዲያስተባብሩ እና እንዲሳተፉ” በፓትርያርኩ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ተብሏል - ከአቡነ ሳዊሮስ እና ከአንድ ሌላ ብፁዕ አባት በቀር፡፡  ከወይዘሮዋ ጋራ አብረው በመጓዝ በባር ዱባይ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በተቋቋመው “ጉባኤ ያካሂዳሉ” የተባሉት እነ በጋሻው ደሳለኝ የጉዟቸውን ወጭ ለመሸፈን ሳይሆን እንደማይቀር የተገመተ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ሚያዝያ አንድ ቀን 2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ ደሳለኝ ሆቴል ማካሄዳቸው ተዘግቧል፡፡

ስለዚሁ የሆቴል ጉባኤ አስተያየታቸውን በጽሑፍ የሰጡ ደጀ-ሰላማዊ “የጉባኤው ዓላማ ቅድስት ገርን በወንጌል መድስ የሚልና ከተለያየ ለም የሚመጣውን ዝብ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የተሳሳ መረጃ ለመስጠት የተዘጋጀ ነው። የፋይናስ ድጋፉን ከኤልዛቤል በተጨማሪ በአስግድ ሳህሌ የኑፋቁ ራ ራሳቸውን ያቦ ትዳራችውን የፈቱና ለማዊ ዝና ማግት ቢያቅታችው ኑፋቄ ሚገኝ ዝና ቤተ ክርስቲያንን ለመበጥብጥ በተዘጋጁ ወይዘሮዎቸ በተለይም ለም መረሳና በዱባይ የምትኖረው መንበረ መለስ ድጋፍ ያደርጉበታል ።” ብለዋል።

ይሁንና ባለፉት ወራት በአቡዳቢ መድኃኔዓለም፣ በአላየን ቅዱስ ገብርኤል፣ በሻርጂያ ሰዓሊተ ምሕረት እና ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እንዲሁም በቃጣር በተከታታይ በተካሄዱት የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ መከላከል ጥረት ሕገ ወጦቹ በሚገኙበት ባር ዱባይ እና አካባቢው የሚኖረው ምእመን “ለምን ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አትጠብቁም?” በሚል የቡድኑን አባላት ወጥሮ መያዙ ታውቋል፡፡ የቡድኑን ዓላማ ባለማወቅ ተደናግረው የነበሩ በርካታ ምእመናንም ንስሐ ገብተው እና ቀኖና ተቀብለው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ላይ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ በዚህ ሳቢያ ሕገ ወጦቹ  ሲያጭበረበሯቸው እና ሲበዘብዟቸው የኖሩትን ምእመናን ቁጣ ለማስታገሥ ከአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ጋራ “ዕርቅ ለመፈጸም ሞክረናል” ያሉበትን ደብዳቤ በማሰራጨት ላይ እንደ ሆኑ ተነግሯል፡፡ “በቅድሚያ የመሠረታችሁትን ተቋም አስረክቡ” በሚል ከአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “የስብከተ ወንጌሉን አገልግሎት በራሳችን ለማካሄድ፣ ያስቀመጥነው አስተዳዳሪ እንዲቀጥል እንስማማ” የሚሉ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ይልቅ የቡድን ጥቅማቸውን እና ዓላማቸውን ለማስጠበቅ እና ለማስቀጠል የሚያስችላቸውን ነጥቦች እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል፡፡

እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ እና በጋሻው ደሳለኝ ከኢየሩሳሌም መልስም ይሁን ከዚያ በፊት ወደዚሁ ሕገ ወጥ ጉባኤ በመሄድ ጥቅማቸውን ለማሳደድ ቢያስቡም ምእመኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለ ማንነታቸው በተፈጠረለት ኦሬንቴሽን ግንዛቤ በመጨበጡ በግልጽ እንደሚቋቋማቸው ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ የተቋቋመው የሰባክያኑ ጥምረት ሰብሳቢ መምህር ዳንኤል ግርማ ቀደም ብሎ ወደ ስፍራው በማምራት በነገረ ማርያም፣ በነገረ ቅዱሳን፣ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እና በነገረ ድኅነት ላይ ባተኮሩ ርእሰ ጉዳዮች በየሳምንቱ ዓርብ፣ ቅዳሜ፣ እሑድ፣ ሰኞ እና ማክሰኞ በአቡዳቢ መድኃኔዓለም፣ በአላየን ቅዱስ ገብርኤል፣ በሻርጂያ ሰዓሊተ ምሕረት እና ቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም በአዲስ መልክ በተተከለው የራስ አልኬማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተከታታይ ትምህርት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሆሳዕና በአርያም፡፡

(by Negussay  Ayele)
http://www.ethiopians.com/Views/NegussayAyele_on_Deir_Sultan.htm
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)