April 15, 2011

የቅ/ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ እና የመ/ኮሌጅ ደቀመዛሙርት ደብዳቤ (ሪፖርታዥ)


  • ማኅበረ ቅዱሳን ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ጋራ ለመወያየት የኮሌጁን አስተዳደር ጠየቀ
  • “ፕሮቴስታንታዊውን የተሐድሶ ኑፋቄ ወጥመድ የሚያጋልጠው ሰነድ ሲም የተባለ የተሐድሶ ድርጅት በአጭር ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ለመውረስ የቴዎሎጂ ት/ቤቶችን ማእከል አድርጎ ለመንቀሳቀስ የያዘውን ዓላማ የሚያጋልጥ እንጂ ኮሌጁን እንደ ተቋም የሚወነጅል እንዳልሆነ በበለጠ ግልጽነት ሊሠራበት ይገባል፡፡” (ብዙኀን የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት)
(ደጀ ሰላም፤ ኤፕሪል 15/2011)፦  ረቡዕ፣ ሚያዝያ አምስት ቀን 2003 ዓ.ም በአስቸኳይ የተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የምልአተ ጉባኤውን ሥልጣን እና ክብር የሚያስጠብቁ አንፀባራቂ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን ከተጠናቀቀ በኋላ ቁጥራቸው ከ40 ያላነሱ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት በፓትርያርኩ ጽ/ቤት በመገኘት ባለስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ዝርዝሩ እነሆ።

ደቀ መዛሙርቱ በአቋም መግለጫቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነት እና ክርስቲያናዊ ትውፊት እንዲያስጠብቅ በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተፈቀደለት ማኅበረ ቅዱሳን የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን በማጋለጥ የሚያከናውነውን ሕጋዊ እና ተገቢ የመከላከል አገልግሎት “በፈጠራ ወሬ የኮሌጁን እና የደቀ መዛሙርቱን ስም በማጥፋት” ወንጀል በመፈረጅ በማኅበሩ እና የዚህ ተግባር ተባባሪ ናቸው ባሏቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ሠራተኞች፣ አገልጋዮች እና “ባለቤትነቱ ለጊዜው አልታወቀም” ባሉት በደጀ ሰላም ብሎግ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ለምእመናን፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ለመንግሥት በማሳወቅ ርምጃ እንዲወሰድበት ጠይቀዋል፡፡  

በቅርቡ በእንቅስቃሴ መልክ ከተጀመረው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን የመከላከል ጥረት ጋራ በተያያዘ “ማኅበረ ቅዱሳን የኮሌጁን እና የደቀ መዛሙርቱን ስም እያጠፋ ነው፤ በዐውደ ምሕረት ማገልገል አልቻልንም፤ ከአባቶች እና ምእመናን ጋራ አጋጭቶናል” በሚል እና “የመረጥነው የተማሪዎች ካውንስል በኮሌጁ አስተዳደር ጉባኤ እንዳይጸድቅልን ሚና ተጫውቷል” በሚሉ ሰበቦች በመነሣሣት 40 የሚደርሱ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ከትናንት በስቲያ አንሥቶ “ለሲኖዶሱ ይቀርባል” የተባለ የክስ አቤቱታ ሲያጠናቅሩ ቆይተዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በአባ ሰረቀ ደብዳቤ መነሻነት በየካቲት ወር ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የጻፉትን ደብዳቤ ለደቀ መዛሙርቱ በማሰራጨት ያነሣሱት አባ ሰረቀ፣ ከእርሳቸውም ጋራ መናፍቁ አሰግድ ሣህሌ ከኮሌጁ በመታገዱ በፍ/ቤት በመሠረተው ክስ ለኮሌጁ በጥብቅና የቆሙት የሕግ ባለሞያ “የማኅበረ ቅዱሳን አባል በመሆናቸው” እና በስም የሚታወቁ ሦስት የኮሌጁ መምህራን በየመማሪያ ክፍሉ “ስማችሁ እየጠፋ ነው፤ ምን ትሠራላችሁ” በሚል ለክስ አቤቱታ አቀራረብ በቀስቃሽነት እንደተሳተፉበት ተገልጧል፡፡ የክስ አቤቱታው በመመሥረቻ ነጥቦቹ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት “የኮሌጁን እና የደቀ መዛሙርቱን ስም ከማጥፋት”፣ “በሕዝቡ መካከል ውዥንብር ከመፍጠር”፣ “አባቶችን ግራ ከማጋባት”፣ “በፈጠራ ወሬ ሕዝቡን በማወዛገብ ከፍተኛ ረብሻ እና ብጥብጥ ከማነሣሣት” እና “ቅዱስነታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ራሷን ችላ ከጥገኝነት እና ኋላ ቀርነት ተላቅቃ እንድትቆም በማድረጋቸው እና ከዚህም በላይ በዓለም ደረጃ ቤተ ክርስቲያኗን በመወከል የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ቁንጮ እና ታላቅ አባት መሆንዎት ሰላም የነሣቸው” ክፉዎች ቀናተኞች ተግባር ጋራ ያተካክለዋል፡፡ እነዚህ ነጥቦች ላይ በመመርኮዝ፡-  
  •  “የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ መዋቅር እና የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ወደ ጎን በመተው፣ በመናቅ የኮሌጁን ስም የማጥፋት ተግባር እየፈጸመ ባለው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰድ”
  • “የስም ማጥፋት ዘመቻውን እያስፋፋ እና የፈጠራ ወሬውን የፈጠረው አቶ ያረጋል አበጋዝ በጥናታዊ ጽሑፍ መልክ በመላው ሃገሪቱ በመዘዋወር ‹መንፈሳዊ ኮሌጆች የተሐድሶ መፈልፈያ ናቸው” በማለት ችግር የፈጠረ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያኗ የበላይ ሓላፊዎች ተጠርቶ ከዚህ ተግባር እንዲቆጠብ እና ከዚህ ቀደም ላደረጋቸው ድርጊቶች ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድበት” (እነርሱ አቶ ያሉት ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ የአካውንቲንግ መምህር፣ የንግድ አስተዳደር እና ፋይናንስ፣ የአቋቋም እና ቅኔ ባለሞያ፣ የደቡብ አፍሪካው ዩኒሳ ዩኒቨርስቲ የፒ.ኤች.ዲ ዕጩ፣ የግእዝ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች አቀላጣፊ፣ ጸሐፊ እና ተርጓሚ፣ ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ እና ኤሌክትሮኒክስ ዋና ክፍል ምክትል ሓላፊ፣ የሐመር መጽሔት ምክትል ዋና አዘጋጅ፣ በሰባክያኑ ጥምረት ውስጥ የተመሰገነ ተሳትፎ የሚያደርግ እና በማታው መርሐ ግብር በመንፈሳዊ ኮሌጁ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኝ፣ በፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ንቅናቄው indefensible ምሁርነቱ እና irrefutable ክሂሉ ነጥሮ የወጣ ተጋዳይ አገልጋይ ነው] 
  • “ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ሲገባቸው በመዋቅሯ ውስጥ መሽገው ለዚህ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተባባሪ የሆኑ፣ ራሳቸውን የማኅበር አባል ያደረጉ በኮሌጆቻችን እና በጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎች ያሉ አገልጋዮች ከዚህ ሥራ እንዲቆጠቡ፣ ሁኔታው ተጣርቶ አስፈላጊው አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው”
  • “በቅዱስነትዎ እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ እንዲሁም በመምሪያ ሓላፊዎች እና በመንፈሳዊ ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ደጀ ሰላም  የሚል ብሎግ (ዌብ ሳይት) እየተደረገ ያለው ቤተ ክርስቲያናችን የማይወክል እና በቅዱስ ሲኖዶስ የማይታወቅ በመሆኑ የዚህ ብሎግ ከፋች እና ባለቤት ቀርቦ እንዲጠየቅ እና ቅዱስ ሲኖዶስ ለምእመናን እና ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲሁም ለመንግሥት በማሳወቅ ጉዳዩን የሚያከናውኑት ግለሰቦች ሆኑ ማኅበሩ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ”፤
  • “ከከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጆች እና ከአብነት ት/ቤቶች ውጭ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ውጭ ማስተማር የማይቻል መሆኑ ተገልጾ በየሀገረ ስብከቱ እና ወረዳ ቤተ ክህነቶች እንዲሁም ለእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን secular ደብዳቤ እንዲተላለፍልን እና ለመምህራኑም ሕጋዊ የሆነ የሚታደስ መታወቂያ እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን”፤
የሚል የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡ አቋማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚታይ ለክስ አቅራቢዎቹ የተነገራቸው ሳይሳካ ቀርቶ ረቡዕ ማምሻውን ከአስቸኳይ ስብሰባው መገባደድ በኋላ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ የተገናኙት ደቀ መዛሙርቱ፣ “እናንተም እነርሱም ልጆቼ ናችሁ፤ ዐዋቂ ሰው እንዴት እንዲህ ይሳሳታል፤ እንደተባለው የሃይማኖት ችግር የለባችሁም፤ ጥያቄያችሁን ወደፊት እናየዋለን” በሚል እንደተሸኙ ተነግሯል፡፡

በቁጥር 40 ያህል የሚሆኑትንና በፍርሃትም በግዳጅም ከተሰለፉት ደቀ መዛሙርት በተለየ ብዙኀን ደቀ መዛሙርት ከወጣው የአቋም መግለጫ በመለየት፣ “የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ መኖር የሚዳሰስ እና የሚጨበጥ እውነታ ሆኖ ኮሌጁ ታላላቅ ምሁራንን ያፈራ እንደመሆኑ መጠን ደግሞ የኑፋቄውን ወጥመድ በሚያጋልጠው መረጃ በሚገለጽበት ወቅት ጥንቃቄ ሊደረግ፣ የተፈጸመ ስሕተት ካለም ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል፤ ከመናፍቃን ጋራ ግንኙነት ያላቸው፣ በጾም ቀን እንኳ በግልጽ እንደሚበሉ የምናውቃቸው ደቀ መዛሙርት ተለይተው ይውጡ እንጂ ብዙኀኑ ሐቀኞች ከጥቂት ችግር ፈጣሪዎች ጋራ ተጃምለው ሊጠረጠሩ አይገባም፤ በዚህ ረገድ የተፈጸመ ስሕተት ካለም ይታረም” ማለታቸው ተመልክቷል፡፡

የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የኮሌጁ አካዳሚክ ዲን መምህር ፍሥሓ ጽዮን ደሞዝ “ጥቂት ደቀ መዛሙርት እንዳሉት የኮሌጁ ስም ጠፍቶ ከሆነ የሚመለከተው አስተዳደሩን እንጂ እነርሱን አይደለም” በሚል በተማሪዎቹ ወጣ የተባለውን የአቋም መግለጫ ውድቅ አድርገውታል ተብሏል፡፡ ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ቅሬታቸውን ከኮሌጁ አስተዳደር ጀምሮ ለምን በየደረጃው እንዳላቀረቡ ለተሰነዘረው የታዛቢዎች ጥያቄ “አስተዳደሩ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ነው” በሚለው የእነ አባ ሰረቀ እና አባ ሱራፌል (የፓትርያርኩ ዘመድ ናቸው ይባላል) ግፊት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ሳቢያ የሰሞኑ አደዝዳዥነት ያልያዘላቸው እነ አባ ሰረቀ በኮሌጁ አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ የዓላማ ተጋሪዎቻቸው ጋራ በመተጋገዝ ለፓትርያርኩ የከሰሷቸው መምህር ፍሥሓ ጽዮን ካላቸው ሓላፊነት ሊነሡ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል፡፡ 

በተያያዘ ዜና ከኮሌጁ እንደተሰማው፡- የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት ከመላው ደቀ መዛሙርት እና ከኮሌጁ ማኅበረሰብ ጋራ በቀረቡት አቤቱታዎች እና በወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ ፊት ለፊት ለመወያየት ለኮሌጁ አስተዳደር ያቀረበውን ጥያቄ ለማስፈጸም አዳጋች እንደሆነ ተገልጧል፡፡ የዚህም ዋናው ምክንያት የፕሮቴስታንታዊ- ተሐድሶ-ኑፋቄውን ወጥመድ አስመልክቶ ቀደም ሲል ከኮሌጁ መምህራን፣ የኮሌጁ ምሩቃን እና ደቀ መዛሙርት የሆኑ የሰባክያን ጥምረት ጋራ በኮሌጁ የጸሎት ቤት የተካሄደውን ውይይት “ፊት እየሰጣችሁ ነው” በሚል በተቆጡት እና “እኔ ሳልፈቅድ አንዳችም ስብሰባ በኮሌጁ እንዳይካሄድ” የሚል መምሪያ ሰጥተዋል በተባሉት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ትእዛዝ ምክንያት መሆኑ ተዘግቧል፡፡

የሐዋሳ ጉዳይ …
ከደቀ መዛሙርቱ አቤቱታ አቀራረብ ቀደም ሲል ለአንድ ቀን የተካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ ዋና ዋና የውሳኔ ሐሳቦች በመዘገብ ዝርዝሩን በቆይታ እንደምናቀርብ መግለጻችን ይታወሳል፡፡ በአስቸኳዩ ስብሰባ ላይ በሲዳማ ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት የተፈጠረውን አስተዳደራዊ ክፍተት እና በሐዋሳ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያለውን ውዝግብ በተመለከተ በቋሚ ሲኖዶሱ የተሠየመው አጣሪ ኮሚቴ አባላት በኀባር የተስማሙበት ሪፖርት ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ወደ ጉባኤው በአስረጅነት የተጋበዙት የኮሚቴው አባላት (የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ እና የሊቃውንት ጉባኤ አባሉ መምህር አእመረ አሸብር) በንባብ ያሰሙት ሪፖርት ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

የአጣሪ ኮሚቴው አባላት የሆኑት ብፁዕ አቡነ ያሬድ እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ “ይህን አግበስብሳችሁ ያመጣችሁትን ሪፖርት አናውቀውም፤ በጓዳ ተሠርቶ የቀረበ ነው፤ አልተስማማንበትም” በማለት በአቋም መለየታቸውን በግልጽ አሰምተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ግን ችግር ፈጣሪው ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን በመጥቀስ በሐዋሳ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከል ከተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት ፀረ-ኤድስ ማኅበር ጋራ “እንዲታገሥ” የከሰሰውን የእነ ንቡረ እድ ኤልያስን ‹ድርሰት› በመደገፍ፣ “እነርሱ በገለጹት መጠንም ባይሆን ማኅበረ ቅዱሳንም በችግሩ እጁ እንዳለበት የሚያሳዩ ነገሮች አሉ” ብለዋል፡፡ እነ ንቡረ እድ ኤልያስ በ‹ድርስ ሪፖርታቸው› በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከሀገረ ስብከቱ እንዲነሡም ጠይቀው ነበር፡፡

ብፁዕ አቡነ ያሬድ እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የእነ ንቡረ እድ ኤልያስን ‹ድርስ ሪፖርት› እና የአቡነ ጎርጎርዮስን አስተያየት በመቃወም “የራሳችንን አካል መልሰን አንከስም” በማለት የሰጡትን ማስተባበያ ተከትሎ በርካታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጠንካራ የተቃውሞ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውጥረት የሰፈነበት ጉባኤው ለተሲዓቱ ጸሎተ ቅዳሴው ከተነሣ በኋላ ዳግመኛ ከቀኑ 10፡00 ላይ ተመልሶ ተቀምጧል፡፡

በዚህ ጊዜ የጠዋቱን የድርሰት ‹ሪፖርት› በጸጥታ የታዘቡትና በጉዳዩ ዙሪያ በርካታ መረጃዎችን ሲመረምሩ መቆየታቸውን የተናገሩት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ “ማኅበረ ቅዱሳን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ትላላችሁ፤ በሓዋሳው የምእመናን ተወካዮች ውስጥ የሚገኙት በቀድሞው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር እንደ ምእመንነታቸው እንዲያገለግሉ የተጠሩ ሁለት [ስማቸውን እየጠሩ] የማኅበሩ አባላት ብቻ መሆናቸውን ባለብኝ ሓላፊነት መጠን ተከታትዬ አረጋግጫለሁ፡፡ እኔ የማላውቀው ችግር እርሱ ምንድን ነው? ለምንድነው ማኅበሩን ወደ ችግር ምሕዋር እንዲገባ የምትገፉት? ‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ-ኤድስ ማኅበር› ስለሚባለው ከክልሉ መንግሥት ዕውቅና ያገኘበት ሠርተፊኬት [ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ፍትሕ እና ጸጥታ ቢሮ በመዝገብ ተራ ቁጥር 131/10/97 በቀን 08/09/97 የተሰጠውን ምስክር ወረቀት እያሳዩ] አግኝቻለሁ፡፡ የዚህን ማኅበር መተዳደሪያ ደንብ መርምሮ የሕግ ዕውቅና የሰጠው የክልሉ መንግሥት በመሆኑ ከእኛ የሥልጣን ክልል ውጭ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ከማገድ ውጭ እንደተባለው ሌላ ርምጃ ልንወስድበት አንችልም” በማለት በእነ ንቡረ እድ ኤልያስ በተነበበው ክስ እና ርምጃ ላይ ኀያል ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡  

ከብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋራ በደቡብ ትግራይ የማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የወቅቱን የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ለመምራት ወደ መቐለ የአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ በርዳታ ስም የገባውን ሲም የተባለ የተሐድሶ አራማጅ ድርጅት የፈጠረውን ችግር በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ በማጋለጣቸው በአቀንቃኞቹ እንደተከሰሱ በፓትርያርኩ የነገራቸው ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ እና የሲዳማ ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “የቤተ ክርስቲያን ልጆችን የቤተ ክርስቲያን ካልሆኑት ጋራ ደምሮ ማየት” አግባብ አለመሆኑን አስተንክረው በመናገር የእነ ንቡረ እድ ኤልያስን የድርሰት ‹ሪፖርት› ተቃውመዋል - ንቡረ እድ ኤልያስ በቁጣ ሊመልሱላቸው ቢሞክሩም፡፡

በመጨረሻም አስቸኳይ ጉባኤው በቋሚ ሲኖዶስ ከተሠየመው አጣሪ ኮሚቴ ሙሉ ስምምነት ውጭ በእነ ንቡረ እድ ኤልያስ የቀረበውን “ድርስ ሪፖርት” ውድቅ በማድረግ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በሀገረ ስብከቱ ያለው ችግር እስኪረጋጋ በዚሁ ሆነው እየተከታተሉ ከተመደቡላቸው ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ ጋራ በሓላፊነት እንዲቀጥሉ፣ የጽ/ቤቱን ሥራ የሚመሩት ሥራ አስኪያጁም ሌሎች ሁለት ጠንካራ ረዳቶች እንዲጨመሩላቸው ወስኗል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)