April 11, 2011

ቋሚ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያስጠብቅ እና ሕዝቡን የሚያረጋጋ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ የሐዋሳ ምእመናን ተወካዮች ጠየቁ

  •   ቋሚ ሲኖዶስ ረቡዕ በዚህ ጉዳይ እንደሚነጋገር ይጠበቃል፤
(ደጀ ሰላም፤ ኤፕሪል 11/2011)፦ በጥቂቶች ማስፈራሪያ ተልእኮውን ሳያጠናቅቅ የተመለሰው አጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ መፍትሔ እንዲፈለግ አለመደረጉ የሐዋሳን ምእመን እና ውጤቱን በገለልተኛነት የሚጠባበቀውን የክልሉን መንግሥት በእጅጉ እንዳሳዘነ የሐዋሳ ምእመናን ተወካዮች ገለጹ፡፡ “ጉዳዩን እንዲያጣራ የተላከው የጳጳሳት ኮሚቴ ለአምስት ቀናት ብቻ ቆይታ በማድረግ የማጣራት ሥራውን ሠርቶ በተከታዩ ሦስት ቀናት ውስጥ ምላሽ ታገኛላችሁ ቢልም ሀገረ ስብከቱ ያለ መሪ ባዶውን እንደሚገኝ” ተወካዮቹ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በንባብ ባሰሙት ባለአራት ገጽ የጽሑፍ ማሳሰቢያ ላይ አመልክተዋል፡፡ አድራሻቸው እና ማንነታቸው በግልጽ ከሚታወቁ ከስድስት ሺሕ በላይ የከተማው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ምእመናን የተላኩት ተወካዮቹ፣ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም በቋሚ ሲኖዶሱ የተላለፉት ውሳኔዎች በአብዛኛው ተፈጻሚነት ባለማግኘታቸው በከፍተኛ ደረጃ ተባብሶ እየቀጠለ ለሚገኘው ሁከት እና ብጥብጥ መፍትሔ እንዲፈለግለት ጠይቀዋል፡፡

በቁጥር ከ26 ያላነሱ የሐዋሳ ምእመናን ተወካዮች መጋቢት 28 ቀን 2003 ዓ.ም በፓትርያርኩ ጽ/ቤት በመገኘት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ባቀረቡት ጥያቄ በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተፈጠረው የአስተዳደር ክፍተት እና ብልሹ አሠራር መነሻነት በተከሠተው ከፍተኛ ቀውስ፣ በጥቅመኛ ግለሰቦች ድጋፍ እየተባባሰ በመጣው ሁከት ሳቢያ ምእመኑ ሥርዐተ አምልኮውን የመፈጸም መብቱን ተነፍጓል፤ የአካባቢው ኅብረተሰብ ሰላማዊ ኑሮ ተናግቷል፤ የመንግሥት የጸጥታ ሥራ በንጹሐን ምእመናን ላይ በገሃድ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙትን ነውጠኞች ዕለታዊ ተግባር በመከታተል ታውኳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የከተማው ነዋሪ እና ተላላፊ እንግዳ በግልጽ በሚታዘበው አኳኋን ምእመኑ (በተለይም የነውጠኞቹን እኩይ ተግባር የሚቃወሙ ምእመናን ሕይወት እና ደኅንነት) ከአደጋ ተጠብቆ የሚገኘው ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሚደረግለት ጥበቃ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነት እና በክልሉ መንግሥት የጸጥታ ኀይል እገዛ መሆኑን ምእመናኑ አመልክተዋል፡፡ በተፈጠረው ትርምስ ለዘመናት ተጠብቆ የቆየው የእምነታችን ክብር እና ህልውና በእጅጉ አደጋ ላይ መውደቁን ያስረዱት የምእመናኑ ተወካዮች፣ የሌሎች ተሣልቆ (“ለኦርቶዶክሶች እንጸልያላቸው” በሚሉት ፕሮቴስታንቶች ጭምር) እያሳፈራቸው እና አንገታቸውን እያስደፋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተወካዮቹ አበክረው እንደተናገሩት፣ ምእመኑ በአንድነቱ እና በእምነቱ ጸንቶ እንዲኖር ማድረግ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሓላፊነት ነው፡፡ ይህን በመገንዘብ ቋሚ ሲኖዶሱ እና ቅዱስ ፓትርያርኩ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትም ሆነ በሐዋሳ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ የቅድስት ሥላሴ እና የሞኖፖል ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ደረጃ ተሰግስገው የተሳሳተ እና አፍራሽ መረጃ እየሰጡ የሰፊው ምእመን ጥያቄ እንዲታፈን፣ ጥያቄውንም የማኅበረ ቅዱሳን በማስመሰል ብጥብጡ እንዲቀጥል በማድረግ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ለሚሹት ለእነ ያሬድ አደመ እና መሰሎቹ፣ በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ደረጃም በማያገባቸው ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚታወቁት እንደ ታዋቂዋ ወይዘሮ ላሉት ግለሰቦች ጆሮ ሳይሰጥ በድጋሚ በቀረበው መንፈሳዊ የፍትሕ ጥያቄ መሠረት ሕዝቡን የሚያረጋጉ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጠብቁ ዘለቄታዊ እና ተግባራዊ ርምጃዎች እንዲወስዱ በተወካዮቹ ተጠይቀዋል፡፡

“ከዚህ በኋላ በአስቸኳይ መወሰድ የሚገባው የመፍትሔ ርምጃ ለአንድም ቀን ቢሆን መዘግየቱ ችግሩን በፍጥነት እያባባሰ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሁከት እና ትርምስ ሊያስከትል እንደሚችል ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል” እንደ ምእመናኑ ተወካዮች ማሳሰቢያ፡፡ ተወካዮቹ በጥያቄያቸው፣ ቋሚ ሲኖዶሱ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም ውይይት ያደረገባቸው ነጥቦች እና ያሳለፋቸው ውሳኔዎች “ውስን እና እጅግም መሠረታዊ ያልነበሩ” መሆናቸውን ተችተዋል፡፡ ይሁንና ውሳኔውን አክብረን በመቀበል የመጨረሻውን ውጤት ስንጠባበቅ የቆየን ቢሆንም ከውሳኔው መካከል የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሓላፊ ከመነሣታቸው እና በምትካቸው የተሠየሙት አዲስ ሓላፊ እስከ አሁን መጥተው ጽ/ቤቱን ካለመረከባቸው፣ ሊቃነ ጳጳሳት እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር አካላት የሚገኙበት አጣሪ ኮሚቴ በቅርቡ ችግሩን አይቶ ከመመለሱ ውጭ ዘላቂ መረጋጋት የሚያመጣ ተግባራዊ ርምጃ ካለመወሰዱ ጋራ በተያያዘ ቀውሱ እና አለመረጋጋቱ በተባባሰ ሁኔታ መቀጠሉ ተገልጧል፡፡
ይኸው ያልተገባ አካሄድ በአፋጣኝ እንዲያበቃ ሆኖ፡-
1) በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ አገላለጽ “ተፎካካሪ ናቸው” ከተባሉት ማኅበራት ውስጥ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ ያልተገባ ከለላ እየተሰጠው የሰንበት ት/ቤቱን አዳራሽ ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ለብጥብጥ እየተጠቀመበት የሚገኘው፣ በመመሥረቻ ደንቡም መሠረት ዋና ተግባሩ የልማት እና ፀረ-ኤድስ ሥራ እንጂ መንፈሳዊ አገልግሎት ያልሆነው “የተስፋ ኪዳነ ምሕረት ፀረ-ኤድስ ማኅበር” አፍራሽ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ፣ በቃለ ዐዋዲው መሠረት ሕጋዊነት ያለው ሰንበት ት/ቤት ወደ ፊት በሚደራጀው ሰበካ ጉባኤ አማካይነት እስኪቋቋም ድረስ አዳራሹ ተዘግቶ እንዲቆይ እንዲደረግልን፤
2) የገዳሙን ህልውና በከፍተኛ አደጋ ውስጥ እየጣለ፣ ምእመኑን በተሳሳተ መረጃ እየከፋፈለ ወደ ከፍተኛ እልቂት እየመራ ለሚገኘው “ለተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ-ኤድስ ማኅበር” ሽፋን በመስጠት ኢ-መንፈሳዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙት የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ በአስቸኳይ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፤
3) ሀገረ ስብከቱን እንዲመሩ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል እና በቋሚ ሲኖዶሱ አማካይነት በድጋሚ የተመረጡት ሥራ አስኪያጁ ወደ ምድብ ሥራቸው በመምጣት ምእመኑን የማረጋጋት፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱ በቃለ ዐዋዲው መሠረት እንዲቀጥል፤
4) ከቃለ ዐዋዲው በተቃራኒ በጊዜያዊነት እንዲያገለግል በሚል ሽፋን ያለምእመኑ ፈቃድ እና ዕውቅና በሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል የግል ፍላጎት ብቻ የተሠየመው እና በአሁኑ ሰዓትም ከገዳሙ አስተዳዳሪ ጋራ በመሆን የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ባለማክበር ሥልጣኑን አልለቅም ብሎ የሕዝቡን ገንዘብ ከሕዝቡ ዕውቅና ውጭ እያንቀሳቀሰ የሚገኘው ሰበካ ጉባኤ በአስቸኳይ እንዲነሣ፣ በምትኩም አዲስ እና ሕጋዊ የሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው መሠረት እንዲመረጥ፤
5) ከሕዝብ የሚሰበሰበውን የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ለግል ፍላጎታቸው መጠቀሚያ ለማድረግ በማሰብ ተባብሶ ለቀጠለው ከፍተኛ ነውጥ ምክንያት የሆኑት የሦስቱ አብያተ ክርስቲያን(የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ የቅድስት ሥላሴ እና የሞኖፖል ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት) አለቆች ችግሩ በምእመኑ ሕይወት እና ደኅንነት ላይ ያልተፈለገ አደጋ አደጋ ከማስከተሉ በፊት ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከሓፊነታቸው እንዲነሡ፣ በምትካቸው ሃይማኖትን የሚጠብቁ፣ በመንፈሳዊ ብቃታቸው የተፈተኑ፣ በሥነ ምግባራቸው የታነጹ እና በምእመኑ አንድነት የሚያምኑ መንፈሳዊ አባቶች እንዲተኩ የምእመናኑ ተወካዮች በአጽንዖት ጠይቀዋል፡፡

መጋቢት 28 ቀን 2003 ዓ.ም ማለዳ ከሐዋሳ ተነሥተው ጠዋት 3፡30 ላይ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተገኙት የምእመናኑ ተወካዮች አቡነ ጳውሎስን ለማግኘት እስከ ቀኑ 10፡20 ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ፓትርያርኩ “እነርሱን የማናግርበት ፕሮግራም አልያዝሁም” በሚል የያዙትን አቋም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አግባቢነት እስኪለውጡ ድረስ ተወካዮቹ በቅድሚያ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከዚያም ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ ተወያይተዋል፡፡

  “ዮዋ
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የአጣሪ ኮሚቴው አባል በመሆን ጉዳዩን አጥንተው ቢመለሱም በአጣሪ ኮሚቴው አባላት መካከል የሐሳብ መለያየት መኖሩንና የነገሩ ቁልፍ ያለው በፓትርያርኩ እጅ መሆኑን ለተወካዮች ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ ቀትር ላይ ከብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጋራ በመሆን ተወካዮቹን በአስተዳደር ጉባኤ አዳራሽ ካናገሩት አንዱ የሆኑት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአጣሪ ኮሚቴው አባል ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ “ሁለት ገመድ ነው አዋሳ ላይ ያለው፤ የተቸገርነው ሁለታችሁንም ከኋላችሁ በሚጎትቷችሁ በእነዚህ ገመዶች ነው” ብለው በመናገራቸው ተወካዮቹን አስቆጥተዋል፡፡ የንግግራቸውን አሊጎሪ በፍጥነት በተረዳች አንዲት ምእመንትም “ገመዱ ያለው እዚሁ ነው፤ የማይገናኝ ነገር አያገናኙ፤ አቋምዎን ያስተካክሉ፤ እኛ ማኅበረ ቅዱሳን አይደለንም፤ ማኅበረ ቅዱሳንን ከተስፋ ኪዳነ ምሕረት ጋራ ማነጻጸር ተገቢ አይደለም፤ ጉዳያችንን ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በማቀላቀል አያዳፍኑ” በሚል ተገሥጸዋል፡፡ ምእመናኑ በገጠማቸው ማዘናቸውን የገለጹት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ግን ከጥር 20 - 22 ቀን 2003 ዓ.ም በሐዋሳ መስቀል አደባባይ ሕገ ወጥ ‹ሰባክያኑ› እንዳያስተምሩ በመጻፋቸው መወቀሳቸውን አስታውሰው ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ለተወካዮቹ አስረድተዋል፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን በማናገርም ከቀትር በኋላ ቀጠሮ እንዲያዝላቸው አድርገዋል፡፡

ከቀኑ 10፡20 ላይ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ በጽ/ቤታቸው በመገናኘት ከሁለት ሰዓታት በላይ የተነጋገሩት የምእመናን ተወካዮቹ፣ “በድጋሚ እና ለመጨረሻ ጊዜ” በሚል በንባብ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች ተከትሎ ቁጣ እና ተማጽኖ የተፈራረቀባቸው የሐሳብ ልውውጦች ተካሂደዋል፡፡ በምእመናኑ ተወካዮች በኩል በተለይም ካለፈው ሳምንት እሑድ ጀምሮ በውሳኔዎች አለመተግበር ሳቢያ ውጥረቱ እየተባባሰ በመሆኑ “በፓትርያርኩ ነው የተሾምኩት” በሚል በደል ማድረሳቸውን የቀጠሉትን የገዳሙን አስተዳዳሪ ከሌሎቹ ሁለት አጥቢያዎች አለቆች እና ችግር ፈጣሪዎች ጋራ “ጠራርገን እናስወጣለን” ብሎ የተነሣሣውን ምእመን በማረጋጋት ለመጨረሻ ጊዜ ችግሩን ለማስታመም መምጣታቸው፣ ያለመፍትሔ ሊሄዱ እንደማይችሉ አጽንዖት የተሰጠበት ጉዳይ ነበር፡፡

ሱባኤው ሳይገባ መፍትሔ እንዲፈለግ ተናግረው እንደነበር፣ 10 አባላት ያሉትን አጣሪ ኮሚቴ ከብር 30,000 በጀት ጋራ መስደዳቸውን፣ ይሁንና ሪፖርቱ ተጠናቅቆ ስላልቀረበላቸው ባላለቀ ሥራ ለብቻቸው የሚሰጡት መፍትሔ እንደማይኖር የተናገሩት ቅዱስ ፓትርያርኩ በበኩላቸው፣ “ሰላም እንዳጣችሁ ዐውቃለሁ፤ ጊዜያችሁን በማባከናችሁ አዝኛለሁ፤ ሕዝቡ እንደተሠቃየ ከመንግሥትም ደርሶኛል፤ አትፈቱትም እንዴ ተብዬአለሁ፤ መልካም እና ክፉ ጠባይ ያላቸው ልጆች ቢኖሩም ሁሉም ልጆቼ ናቸው፤ እናንተ አንዱን ክፍል ደገፋችሁ፣ እነዚያም አንድ ክፍል ደግፈው መጡ፤ ሁለታችሁንም ነው የምንፈልገው፤ አንዱ እያለቀሰ ለሌላው አልፈርድም፤ ሌሎች ልጆቼን ነጥዬ መልስ አልሰጥም፤ አስታራቂዎችን ስንልክ እርስ በርሳችሁ በኀይል ትፎካከራላችሁ፤ ሰላም ከተፈለገ እና ፈቃደኞች ብትሆኑ ሽማግሌ አያስፈልግም ነበር፤. . . ዛሬውኑ መፍትሔ መስጠት ይቻላልን? ሁለታችሁም ተስማምታችሁ የምትኖሩበት መፍትሔ ይሻላል ወይስ ሌላ?” የሚሉ ዐረፍተ ነገሮችን በብዙ መልክ እና ቃና ሲደጋግሙ ተደምጠዋል፡፡

መልሰው ደግሞ “ነገሩ እንዲቀጥል የምታደርጉት እናንተ ናችሁ፤ ዕርቅ ማለት የሚተወውን መተው ማለት ነው፤ እገሌ ይውጣ፣ እገሌ ይሻር አትበሉ” ብለዋል፡፡ ተወካዮቹም ብዙኀኑን ምእመን በመወከል ለስድስት ወራት እየተመላለሱ ምላሽ እንዲሰጧቸው ያቀረቡላቸውን ተማፅኖ ሳያስተናግዱ ምንም ዐይነት ውክልና ለሌላቸው ወሮበሎች መሠረተ ቢስ ክስ ቋሚ ሲኖዶሱን ስብሰባ በመጥራት በሁለት ቀን ውስጥ ውሳኔ ማስተላለፋቸው አባታችሁ ነኝ፤ ገለልተኛ ነኝ የሚለውን ቃላቸውን አጠራጣሪ እንደሚያደርገው አብራርተውላቸዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ግን ውሳኔው የተላለፈበትን የቋሚ ሲኖዶሱን ቃለ ጉባኤ እንደማያውቁት በመናገር ተወካዮቹን አስደንግጠዋል፤ አስደምመዋል - “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ቃለ ጉባኤ አላውቀውም፡፡”

አቡነ ገብርኤል
በሌላ በኩል ስለ ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መመለስ፣ አቡነ ገብርኤል ከሀገረ ስብከቱ ባይነሡም “ውጡ ተብለው መውጣታቸውን” አስመልክቶ ሲያስረዱ፣ “አባ ገብርኤል ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዲመለሱ እዘዝ ተብዬአለሁ፤ አላዝዝም! እንገድልዎታለን እየተባለ መላክ አልችልም፤ ሪፖርቱን ቋሚ ሲኖዶሱ አይቶ እስኪወስን ድረስ እኔ ብቻዬን መላክ አልችልም” ብለዋል፡፡ የሐዋሳ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እንዴት አንድን ሊቀ ጳጳስ ሊደበድብ ይችላል ሲሉ ለጠየቁት ተወካዮች ሲመልሱም “አባ ገብርኤልን ጥቁር ጨርቅ እያውለበለበ የተቀበላቸው ሕዝቡ ስለጠላቸው አይደለ፤ ራሳቸው ‹በጥቁር መሐረብ ተቀበሉኝ› ብለውኛል፤ ‹ከሐዋሳ ውጣ፣ እናርድሃለን› ተብለው ነው የወጡት፤ ይህን አሳዛኝ ነገር ያደረገው የአዋሳ ሕዝብ ነው፤ መፍትሔ የሌለው ነገር ይዛችሁ በመምጣችሁ አዝኛለሁ፤ እናንተ የአንድ አባት ልጆች ናችሁ፤ የፋኑኤል፣ የገብርኤል አትበሉ፤ በጳጳሳት መካከል ልዩነት እንደሌለ ነግሬያችኋለሁ፤ አቡነ ገብርኤል ወይም አቡነ ፋኑኤል ይምጡ ቢባል በሰላም ትኖራላችሁ ወይ? ለሰላም ጊዜ አልሰጠነውም” ብለዋቸዋል፡፡

በፓትርያርኩ አነጋገር በጣም ማዘናቸውን የገለጹት ተወካዮቹ፡- ምእመኑን በግ እና ፍየል እያደረጉ ሲከፋፍሉ የቆዩትን አቡነ ፋኑኤልን እንኳ ለሦስት ዓመት የታገሡትን ያህል ለአቡነ ገብርኤልም ዕድል እንዲሰጣቸው፣ ያለአባት የራሳችሁ ጉዳይ ተብለው ምእመኑን በሃይማኖቱ ለማጽናት እንደሚያዳግታቸው፣ አቡነ ገብርኤልም መከራ ቢኖር እንኳን ፈርተው እንዲሸሹ ሳይሆን ምእመኑን በመባረክ እና በማረጋጋት ያገለግሉ ዘንድ ክርስትናቸው እንደሚያስገድዳቸው ለዚህም ተንበርክከው እንደሚለምኗቸው፣ ስለ ደኅንነታቸውም ምእመኑ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግ ለፓትርያርኩ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ የመጡትን የአጣሪ ኮሚቴ አባላት ሌባ ብለው ከመሳደብም በላይ ያረፉበትን ቤት በር በመደብደብ ኮሚቴው ተልእኮውን ሳያጠናቅቅ እንዲመለስ ያደረጉት፣ በሌላ ቦታ ለማቃጠል የሚከብድ ቆሻሻ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ እስከ ማቃጠል የሚደፍሩትን፣ ማታ ማታ በአጥር እየዘለሉ በመግባት ከገዳሙ አስተዳዳሪ ጋራ በሊቀ ጳጳሱ ላይ እየዶለቱ ዐምባጓሮ የሚፈጥሩትን ከ30 የማይልቁ ነውጠኞችን እንደ ፓትርያርኩ አነጋገር “የቤተ ክርስቲያን ልጆች ናቸው” ለማለት እንደማይቻል፣ ይህም ሆኖ ከእነርሱ ጋራ ፊት ለፊት ለመነጋገር ለአጣሪ ኮሚቴው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘም አስረድተዋል፡፡

በዚህ መልኩ በቀጠለው ውይይት መሐል ፓትርያርኩ የተወካዮቹን ቀልብ የሳበ አንድ ምክር ሰጥተዋል - “ሐቁን እየተከተሉ ከተበደሉ ክብር እንጂ ውርደት አይደለም፤ እኔ ብዙ ፈተና ደርሶብኛል፤ በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሰይፍ ተመዞብኝ ለአንገቴ የተሰነዘረው ትክሻዬ ላይ ዐርፏል፤ ልብሴ ተቀዷል፤ ወደ እስራኤል ለሕክምና ሄጄ ሞቷል ብለው ያስወሩብኝ ሰዎች ስመለስ ቆመው ተቀብለውኛል፤ ድንጋይ ተወርውሮብኛል፤. . .የአሁኑ ፈተና በእናንተ መካከል የመጣ ፈተና ነው፤ እንዲህ የሚያደርገው ጸላኤ ሠናይ እንጂ የሰው ጉድለት አይደለም፡፡”

በምክሩ ያሰቡበት የምእመናኑ ተወካዮችም “እርስዎ ሰይፍ ተቃጣብኝ ብለው ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ከመሄድ አልተከለከሉም፤ እንግዲያስ ምነዋ በሐዋሳ ሕዝብ ስም የጠሯቸው እፍኝ የማይሞሉ ወሮበሎች በአቡነ ገብርኤል ላይ ጥቁር ጨርቅ አውለብልበዋል ብለው እንዳይሄዱ መከልከልዎ?” ፓትርያርኩም መለሱ፤ እንዲህም አሉ፡- “የእኔ ችግር ከዚህ ጋራ የሚያያዝ አይደለም፤ እስኪ የሚያደርጉትን ልይ ብዬ በልጆቼ መካከል አባ ገብርኤልን አልሰድም፡፡”

ብዙ የተወካዮቹ እጆች ወጡ፤ ይሁንና “በቃን፣ በቃን፣ ይብቃን” የሚለውን ሹክሹክታ ተከትሎ “ሕዝቡ ችግር ፈጣሪዎችን በኀይል ጠራርገን እናስወጣ ሲለን ለመጨረሻ ጊዜ ታገሡ፤ ሄደን እንለምን ብለን ነው የመጣነው፤ ከአሁን በኋላ ወደ እርስዎ አንመጣም፤ ምናልባትም እርስዎ ወደ እኛ ይመጡ ይሆናል፤ በዚህ ለሚፈጠረው ሁሉ ሓላፊነቱን ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይወስዳል” የሚሉ ማሳሰቢያዎች ተሰምተዋል፡፡ “ሪፖርቱ ነገ ይደርስሃል ተብዬአለሁ፤ ውጤቱን ነገ ወይም ከነገ ወዲያ (ያለፈው ሳምንት ዓርብ እና ቅዳሜ) እንዲቀርብ አደርጋለሁ” - ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፡፡

ኀሙስ ማምሻውን ከተጠናቀቀው ከዚህ ዐይነቱ ውይይት በኋላ ወደ ሊቀ ጳጳሳቸው ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ቤት ያመሩት የምእመናኑ ተወካዮች ‹አግድም ነው፣ አንድ ወገን ነው› ባሉት የፓትርያርኩ ንግግር በእጅጉ እያዘኑ ነበር፡፡ የምእመንነት ግዴታቸውን እየተወጡ ከዚህ በኋላ ሂደቱን በቀጥታ ለመንግሥት ለማሳወቅ ማሰባቸውም አልቀረም፡፡ በያዟቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች እነ ያሬድ አደመ እና “የተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ-ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ማኅበር” የቀድሞው ተጠሪ ገዛኸኝ አበራ አሳስተው በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ያሠማሯቸውን አብዛኞቹን ‹ቴኳንዶዎች› ጭምር አስረድተው በማሳመን ለሃይማኖታቸው ጥብቅና የሚቆሙ አድርገዋቸዋል፡፡ በሲዳማ ባህል አዳራሽ እና በጂምናዝየም የስብሰባ አዳራሽ ከ1500 በላይ ለሆኑ ምእመናን ባደረጓቸው በማስረጃ የተደገፉ ገለጻዎች በሀገረ ስብከቱ የተፈጠረውን አስተዳደራዊ ክፍተት እና ብልሹ አሠራር ለብዙኀኑ ምእመን በማስረዳት ከጎናቸው ለማሰለፍ ችለዋል፤ ማስረጃዎች ርእሰ መስተዳድሩ ቢሮም ደርሰዋል፡፡ በዚህም “ጾም አያስፈልግም፤ ጳጳስ አያስፈልግም፤ ዋናው ኢየሱስ ነው፤ ክርስቶስን አስኳል አድርገን እንሰብካለን” እያለ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ የሚወሸክተው፣ ሥዕለ ማርያምን ቀድዶ እስከመጣል እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን “አሮጊቷ ሣራ” በሚል የሚዘልፈው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ጎራ እንዲመናመን ተደርጓል፡፡

ይህን መሠረት በማድረግ ነው ለብፁዕነታቸው፣ “ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ወስነን ነው የመጣነው፤ ለ19 ዓመት ከ19 ቀን ለፍተን ባቀናነው ገዳም ከአባቶቻችን የወረስነውን ለልጆቻችን እንዳናወርስ ውጡ እየተባልን የታወጀብንን አስቸጋሪ ነገር አስወግደነዋል፤ ሕዝቡ ተሸንፈው እንዲቀሩ ሳይሆን እንዲመጡ ይፈልጋል፤ አስፈላጊውን ከለላ እና ጥበቃም ያደርጋል፤ ለእኛ የሚጠቅመን የእርስዎ ጥንካሬ ነው፤ በእርስዎ አለመምጣት ብዙ ክፍተት ይፈጠራል፤ የሚመለሱበትን ቀን ቆርጠን ሕዝቡ የሚቀበልበትን ቀን ብናመቻች፤ ከዚህ በኋላ በዚህ ጉዳይ ወዲህ መምጣት አንፈልግም” ያሏቸው፡፡ “እናንተን ማገልገልም ግዴታዬ ነው” ያሉት ብፁዕነታቸውም ስጋት ተስፋ የተመላበት ምላሽ ሰጥተዋቸዋል - “ሕዝቡ አንድ ከሆነ ለመመለስ ዝግጁ ነኝ፤ ትልቁ ነገር ሰላሙ ነው፤ መንቀሳቀስ የምችለው ግን እርሳቸው ሲፈቅዱልኝ ነው፤ የሴትዮዋ ተጽዕኖ ከባድ ነው፤ እኔን ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በመፈረጅ ከማኅበረ ቅዱሳን ገለልተኛ የሆነ ጳጳስ ይመደብ እየተባለ ነው፤ ይህ መሠረት የሌለው ክስ ነው፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ለምን ብዬ እጠይቃለሁ፤ በሆያ ሆዬ ሓላፊነቴን አልተውም፤. . .ቤተ ክርስቲያን በፈተና ላይ ፈተና፣ የፈተና ፈተና ነው የገጠማት፤ የግንቦቱ ሲኖዶስ ችግሩን ሳይፈታ ካለፈ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሸጠዋታል ማለት ነው፡፡”
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)