April 5, 2011

ስለ እግዚአብሔር ክብር…


ሁሉም በአግባቡና በሥርዐት ይሁን፡፡  (1ኛ ቆሮ.14፥40)
(ወልደ ያሬድ አበ ማቱሳላ):- የአድዋ ድል መታሰቢያ ዕለት ነው፤ በጾም ወራት መንገድ ከመሔድም መጾም ይገባል ብዬ እኔ መንገደኛው ወደ መንፈሳዊ ጉባኤ ታደምሁ፡፡ ቀኑ ብሔራዊ በዓል በመሆኑ ሥራና ትምህርት ስለሌለ ጉባኤው በጊዜ እንዲጀመርና ብዙ ምእመናን እንዲታደሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ ጉባኤው ከተጀመረ በመድረሴ የመጀመሪያው ትምህርት ወደ መጠናቀቁ ነበር፡፡ መርሐግብር መሪው ዐውደ ምሕረቱን እንደተረከቡና መዝሙር መዘመር እንደተጀመረ ግን ግራ የሚያጋባ ነገር ገጠመኝ፡፡

ዕልልታና ጭብጨባው ከዳር እስከዳር ያስተጋባ ጀመር፡፡ ግራ ገባኝ “ዐቢይ ጾም ገብቶ የለም እንዴ? …” አልኩኝ ለራሴ፡፡ አጠገቤ የነበረውን ሰው ቀስ ብዬ ጠየቅሁት “ምን ችግር አለው? ለእግዚአብሔር ክብር ነው!” አለና በእልህ የበለጠ ማጨብጨብ ጀመረ፡፡ በእጁ ጣውላ ይዞ የሚያጨበጭብ ይመስል ጭብጨባው በጣም ይጮኽ ነበር፡፡ በነገሩ ግራ መጋባቱን ያስተዋለው በቀኜ የተቀመጠ ጎልማሳ አንገቱን ወደ ጆሮዬ አስግጎ “ከሀገረ ስብከቱ እንዲጨበጨብና ዕልል እንዲባል ተፈቅዶአል!” አለኝ፡፡ ወዲያውም መርሐ ግብር መሪው “ምእመናን እርግጥ ነው ዐቢይ ጾም ቢሆንም ለእግዚአብሔር ክብር እልል በሉ፣ አጨብጭቡ፤ እስከ ሰሙነ ሕማማት ይቻላል!!” አያለ ማበረታቱን ቀጠለ፤ ከአንዳንድ አረጋዊያንና በሰል ካሉ ሰዎች በስተቀር ከታዘዝን ምን አስጨነቀን ያሉት ምእመናን “ፈቃድ የተሰጠውን እልልታና ጭብጨባ” አቀለጡት”፡፡

የእኔ ልብ ግን ጥያቄውን አላቋረጠም “ለእግዚአብሔር ክብር አጨብጭቡ የሚባለው ለምን ይሆን? አባቶቻችን በዐቢይ ጾም እልልታና ጭብጨባ እንዳይደረግ ሥርዓት የሠሩት ለእግዚአብሔር ንቀት ስለነበራቸው ነበር እንዴ? ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንስ ያለ አንዳች አሳማኝና አስገዳጅ ሁኔታ ሰው ደስ ይበለው ተብሎ በፈቃድ መጣስ ይቻላል እንዴ? ከቅዳሴ በላይ እግዚአብሔር የሚከብርበት ልዩ ሥርዓት የለም፡፡ ታዲያ ቅዳሴ ላይ የቱ ጋር ነው “እልልታና ጭብጨባ ያለው? “ ጥያቄው በዚህ የሚያቆም አይደለም “ለእግዚአብሔር ክብር በሚል ሥርዓት መሻር ከተቻለ “ለእግዚአብሔር ክብር ብለን የምንበላው ምግብ ውስጥስ ትንሽ ቅቤ ጣል ቢደረግበት..? ለእግዚአብሔር ክብር..?” በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የነበሩት አባቶቻችን በዐቢይ ጾም ሳያጨበጭቡ፣ ሳያሸበሽቡ የኖሩት የእኛን ያህል ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት ሳያውቁ ነበር?፣ ወይስ በእነዚያ ዘመናት የነበሩት አበው ፈቃድ መስጠትን ሳያውቁበት ቀርተው ነው? መርሐ ግብር መሪው እንደነገረን “እስከ ሰሙነ ሕማማት ድረስ ለእግዚአብሔር ክብር የሚጨበጨብ” ከሆነ በሰሙነ ሕማማትስ ለምን ይከለከላል? በሰሙነ ሕማማት ለእግዚአብሔር ክብር አይሰጥም እንዴ?” ይህን ጥያቄ ውስጤ ከመጠየቅ አላርፍ አለኝ እንጂ እኔ እንኳን በተሰጠው ፍቃድ ተጠቅሜ እልል ለማለት ፈቃደኛ ነበርሁ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ በዐቢይ ጾም ጭብጨባ መስማት ከተጀመረ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ግራ በመጋባት ፈራ ተባ እያለ ሲያጨበጭብ ከራርሞ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ግራ መጋባት እየቀረ ማጨብጨብም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ለብዙ ዓመታት የቆየን ክርስቲያናዊ ትውፊት እንደ ዋዛ ማፍረስ ቢቻልም በቀላሉ የማይመለስ /unrepairable/ መሆኑ ግን መታወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን ያፈረሰው አካል ሁል ጊዜ የታሪክ ተወቃሽ መሆኑ አይቀርም፡፡

በጉባኤው የታደምኩበት ዕለት የዓድዋ ድል ቀን መሆኑን ብዙ ነገር አስታወሰኝ፡፡ የዐድዋ አርበኞች የጦር ሜዳ ውጊያ አርበኞች ብቻ ሳይሆኑ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የመታመን አርበኞች ነበሩ፡፡ እንደ ሚታወቀው የዐድዋ ጦርነት የተካሔደው በዐቢይ ጾም ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ጾመው መዋጋት ስለሚከብዳቸው ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ እንዲፈቷቸውና ከጦርነቱ በኋላ እንዲጾሙ አጤ ምኒልክ ጠይቀው ነበር፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ግን ይህንን ፈቃድ ለመስጠት እምቢ አሉ፡፡ /አንዳንድ ጸሐፍት ኢትዮጵያዊ ስላልሆኑ ነው ይላሉ/ በዚህ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትእዛዝ ላለመተላለፍ ኢትዮጵያውያን እየጾሙ ተዋግተው ድል ነሡ፡፡ እንዲያው ለድምዳሜ ቸኮልክ አትበሉኝ እንጂ ለድሉ አንዱ ምክንያት ጾማቸው ነው ለማለት እገደዳለሁ፡፡ እነዚህ ወታደሮች ጾሙን ለማፍረስ አሳማኝ ሊባል የሚችል ምክንያት ማቅረብ ይችሉ ነበር፤ ግን አላደረጉትም፡፡ በየዘመናቱ በተከሰተው ድርቅ ጊዜም በዐቢይ ጾም ከብቶቻቸውን አርደው ላለመብላት ብለው ታምነው በረሃብ የሞቱትን ኢትዮጵያውያን፣ ተራብን ብለው የቤተ መቅደሱን የመገበሪያ ስንዴ ያልነኩ አባቶቻችን ጉዳይም ውል አለኝ፡፡ የልጅ ልጆቻቸው ግን “ለእግዚአብሔር ክብር እያልን ሥርዓት እንጥሳለን!” ምን አገናኘው እነርሱ የጾሙት ከምግብ የሚል ይኖራል፡፡ ሆድ ከምግብ ሲጾም እጅ ከጭብጨባ፣ አንደበት ከእልልታ መከልከሉስ አብሮ የተሠራ ሥርዓት አልነበረም?

እግዚአብሔር ካልጮኹ የማይሰማ፣ ካላደመቁ የማያይ አምላክ አይደለም፡፡ ከመላእክት ወገን እንኳን በአርምሞ /በዝምታ/ የሚያመሰግኑት አሉ፡፡ የእኛም ነፍስ ለማመስገን የግድ አንደበትና እጅ እንዲያግዟት አትሻም፡፡ ከኦሪት መጽሐፍ አንድ ታሪክ እናንሣ ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ይዞ ከባሕረ ኤርትራ ሲደርስ ከኋላ የፈርኦን ሠራዊት መጣባቸው፡፡ ሕዝቡ ሙሴ ላይ ጮኸበት፡፡ ነቢዩ ግን “እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርጋትን ማዳን እዩ!” ብሎ ሕዝቡን አረጋጋ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን፡- “ለምን ትጮኽብኛለህ” አለው፡፡ የሚያስደንቀው ነገር ሙሴ እንኳን እርሱ ሊጮኽ የሚጮኹትንም ሰዎች ያረጋጋው እርሱ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ለምን ትጮኽብኛለህ ያሰኘው የሙሴ የልቡ ጩኸት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያለ ጩኸት ያለ እልልታ ያለ ጭብጨባ የሚሰማ አምላክ ነው፡፡ መናገር የተሳናቸውን ሰዎችም ጸሎት ከሁሉ ይልቅ ያዳምጣል፡፡ ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያን በታላቁ ጾም በእርጋታና በጸጥታ ከፈጣሪ እንድንገናኝ ሥርዓት የሠራችው፡፡ ወቅቱም ራስን በእርጋታ የመመልከቻ፣ የጽማዌ፣ የተዘክሮ /meditation/ ጊዜ እንጂ የግርግርታ ጊዜ አይደለም፡፡ ስለ ጌታችን ጭምትነት የተጻፈው “አይጮኽም አይከራከርም፤ በአደባባይ ድምጹን የሚሰማ የለም፤ የተቀጠቀጠ ሸንበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስ የጥዋፍን ክርም አያጠፋም” ተብሎ ነው፤ በገዳመ ቆሮንቶስም በእርጋታና በጸሎት እንጂ በጩኸት እንደቆየ አልተጻፈም፡፡ በዓመት ለሁለት ወራት ብቻ እንኳን መረጋጋት የከበደው ሰው መንፈሳዊነቱ ምኑ ላይ ነው?

 /ምንጭሐመር ፣18ኛ ዓመት፣ ቁጥር 12 ፣ መጋቢት 2003ዓ.ም/
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)