March 29, 2011

አቡነ ጳውሎስ እና ፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ-ኑፋቄን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ እየፈጠሩ ያሉት ጫና (ጥልቅ ሪፖርታዥ)

   (ደጀ ሰላም፤ ማርች 29/2011)፦ ማክሰኞ፣ የካቲት 14 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀትር በኋላ፤ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ስልክ የተመታላቸው አንድ የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት ከፍተኛ ሓላፊ መረጃ የሚቀበሉ የደኅንነት መኰንኖችን በአስቸኳይ እንዲልኩ ይጠየቃሉ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁለት የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት አባላት ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊት ይገኛሉ፡፡ ከጥቂት የመግባቢያ ጭውውት በኋላ ፓትርያርኩ፣ “ለመሆኑ ምን እየሠራችሁ ነው? ሰሞኑን ወጣቶቹ [ማኅበረ ቅዱሳን] ምን እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ ታውቃላችሁ? እንዴ፣ የዐረቦቹ ብጥብጥ'ኮ የተነሣው በወጣቱ ነው?” ሲሉ ልብ እና ማስተዋላቸውን ይገዛል ያሉትን አገባብ ተጠቀሙ፡፡

   “ምን አደረጉ?” ጠየቁ መኰንኖቹ፡፡ “ማኅበሩ ሰንበት ት/ቤቶችን፣ ሰባክያንን፣ ምሁራንን፣ ነጋዴዎችን እየሰበሰበ ቅስቀሳ እያካሄደ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ለውጥ እንደሚያስፈልጋት እኛ ብናምንም ሊያሠሩን አልቻሉም፡፡ ‹ተሐድሶ› እያሉ ለለውጥ የቆሙ አባቶችን እና ወንድሞችን እያስፈራሩብን ነው፡፡ በተለይ መቐለ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ ላይ ልናስተዳድር አልቻልንም፤ ከውጭ የመጡ ወንድሞቻችንን ‹ተሐድሶ› ናቸው በማለት እያሸማቀቁብን ነው” በማለት ‹መረጃ ነው› ያሉትን አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ የመረጃ መኰንኖቹስ መች የዋዛ ናቸው፤ “ማስረጃ ሊሰጡን ይችላሉ?” ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡

   የካቲት 11 ቀን 2003 ዓ.ም በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከ60 በላይ ከሚሆኑ ማኅበራት ለተውጣጡ 300 ያህል ወጣቶች (በራሳቸው አጠራር ‹የጥምቀት በዓል ተመላሽ ወጣቶች ማኅበራት›) የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ወጥመድ በሚያጋልጠው ሰነድ ላይ በሰንበት ት/ቤቱ እገዛ ሁለት የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ገለጻ ከሰጡ በኋላ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ ገለጻው እና ውይይቱ ቤተ ክርስቲያኗ “ተሐድሶ ያስፈልጋታል” በሚል ሽፋን ትምህርተ ሃይማኖቷን፣ ሥርዐተ እምነቷን እና ክርስቲያናዊ ትውፊቷን በአጠቃላይ እርሷነቷን ለመለወጥ እና ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ በተለየ ስልት የተዘረጋውን ወጥመድ ለመሥበር የሚካሄደውን ፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ንቅናቄ የጦሩ ጫፍ ሆኖ በማስተባበር እና በመምራት ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በመላው አህጉረ ስብከት በስፋት ከዘረጋቸው የቅስቀሳ እና ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች አንዱ ነበር፡፡ እንግዲህ ፓትርያርኩ ‹መረጃቸውን› በማስረጃ እንዲያስደግፉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ይህን የገለጻ እና ውይይት መርሐ ግብር ነው ከዐረቡ ዓለም ሕዝባዊ መነሣሣት (Popular Arab Uprising) ጋራ በማመሳሰል በማሳያነት እንደጠቀሱት የሚነገረው፡፡ ይህም የንቅናቄውን ዓላማ በመሠረቱ የሚጻረሩ ውስጠ ተኩላዎች ነገር ለነገር በማገናኘት አምታተው እና አማስለው ለፓትርያርኩ ያቀረቡላቸው ሸውክ፣ ፓትርያርኩም እንዲህ ያለውን ስብቀት እና ሰብቀኞች በማንኛውም ጊዜ ለመቀበል ያላቸው ጽነት ውጤት መሆኑ ነው የተመለከተው፡፡
   የመረጃ ላእካኑ ግን “እኛም እዚያው [ገለጻው በተደረገበት ልደታ አዳራሽ] ነበርን” በማለት ፓትርያርኩ የጠቀሷቸውን ውይይቶች እንደሚያውቋቸውና በሰነድ የተደገፈ ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ ካላቸው እንዲሰጧቸው ይጠይቋቸዋል፡፡ እርሳቸውም “እንዴት ተደርጎ ከእነርሱ [ማኅበረ ቅዱሳን] ላይ ሰነድ ይገኛል? እናንተው ቢሯቸውን ፈትሻችሁ አግኙ እንጂ” ብለው ነገሩን ለማጦዝ ይሞክራሉ፤ አክለውም “ዝም አትበሉ!! እስከ የካቲት 30 ድረስ አንድ ርምጃ ካልወሰዳችሁ ለበላይ አካል በደብዳቤ አሳውቃለሁ” በማለት ይዝታሉ፡፡ የመረጃ ላእካኑን ጭነው ለመላክ ግልጽ ዝንባሌ ያሳዩት ፓትርያርኩ ባጋጠማቸው ጥንቁቅ አቀራረብ (cautious approach) ምናልባትም የጸጥታ ሠራተኞቹን “በማኅበረ ቅዱሳንነት” ሳይጠረጥሯቸውም አልቀረ፡፡

   አቡነ ጳውሎስ - ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ!!

   አቡነ ጳውሎስ ርምጃቸውን ለየካቲት 30 ቀን ያራዝሙት እንጂ ከዚህ ቀደም ሲል በቁጥር ል/ጽ/252/2959/2003 በቀን 07/06/2003 ዓ.ም ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ በሠባራ እና ሠንጣራው ሰበብ እየፈለጉ ማኅበረ ቅዱሳንን የሚከሱበትን “የቤተ ክርስቲያኒቱን የሥልጣን ተዋረድ መዋቅር አለመጠበቅ” እና “በማይመለከተው ጉዳይ ጣልቃ መግባት” የሚሉትን አሠራር አሁንም ደግመው አንሥተዋል፡፡ በዚህ ደብዳቤያቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊወስዷቸው ይገባሉ ያሏቸውን “የማስተካከያ እርምት” በመዘርዘር እስከ የካቲት 30 ቀን ድረስ የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያደርሷቸው አስታውቀው ነበር፡፡ በግልባጭ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለሊቃውንት ጉባኤ እና ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ለተላከው ለዚሁ ደብዳቤ መጻፍ የቅርብ መንሥኤ ሆኖ የተጠቀሰው የማኅበሩ “የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቅስቀሳ እና ገቢ አሰባሰብ አገልግሎት”  ክፍል “ሁለት ልብሶች ያሉት. . .” በሚለው ኀይለ ቃል ከጥር 22 - 29 ቀን 2003 ዓ.ም በዋናው ማእከል ጽ/ቤት ያዘጋጀው ልዩ የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

   ማኅበሩ በ25 ገዳማት እና አድባራት ያሉ 750 መነኮሳትን እና በ50 ታላላቅ የአብነት ት/ቤቶች የሚገኙ 3500 መምህራን እና ተማሪዎችን ችግር በጊዜያዊነት ለመቅረፍ በሚል ባዘጋጀው በዚሁ መርሐ ግብር፣ ከ5000 በላይ ምእመናን እንደሚሳተፉበት እና 15 ሰንበት ት/ቤቶች ማእከል ሆነው እንደሚያገለግሉበት ስለ መርሐ ግብሩ ባሰራጨው በራሪ ወረቀት ላይ ገልጧል፡፡ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው ማኅበሩ ይህ ችግር መኖሩን ቢያውቅ እንኳ የቅርብ ተጠሪው ለሆነው የበላይ አካል (የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ) በሪፖርት ከማሳወቅ በቀር “በባለቤትነት ስሜት መንቀሳቀስ አልነበረበትም፡፡” ማኅበሩ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚሆን ልብስ ለሌላቸው ገዳማውያን መነኮሳት፣ ለቅፈፉም ለትምህርቱም ለመኝታውም በአንዲት መደረቢያ ጨርቅ ተጣብቀው ለሚኖሩ የቤተ ጉባኤ ተማሪዎች የአልባሳት ድጋፍ ማድረግን በማስለመድ “ታርዤ አልብሳችሁኛልና” የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ለማስፈጸም ያደረገው እንቅስቃሴ “የቤተ ክርስቲያኒቱን ማእከላዊ አስተዳደር ተክቶ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት አጉልቶ የሚያሳይ ነው” አስብሏል።

   ሐምሌ 10 ቀን 1994 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ “ኅብረተሰቡ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያውቃት፣ በዕውቀቱ፣ በገንዘቡ እና በጉልበቱ እንዲያገለግላት አስፈላጊውን ሁሉ ማመቻቸት” /አንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ 7/፤ “በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ የማኅበሩ አባላት ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ሞያቸውን በማቀናጀት ለገጠር አብያተ ክርስቲያን፣ ለገዳማት፣ ለአድባራት እና ለአብነት ት/ቤቶች መንፈሳዊ ድጋፍ እና አገልግሎት እንዲያበረክቱ፣ ሰብአዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያደርጉ ማድረግ እና ማበረታት በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምትመራው መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት የመሳተፍ መብት ተሰጥቶታል፡፡

   በዚህ ረገድ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 29 ላይ እንደተገለጸው ማኅበሩ በሞያ አገልግሎት እና ተራድኦ ክፍሉ በጎ አድራጊ ምእመናን ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን አስተባብረው ገዳማትን፣ አድባራትን፣ የአብነት ት/ቤቶችን እና ችግረኞችን በተቀናጀ መንገድ እንዲረዱ የማስተባበር፣ ለአፈጻጸሙም እገዛውን ከሚያደርግባቸው አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ መመሪያ በመቀበል አስፈላጊ ሁኔታዎችን እያመቻቸ እስከ ወረዳ ማእከል ድረስ በተዘረጉት መዋቅሮቹ አማካይነት የምግባረ ሠናይ ተልእኮውን ይወጣል፡፡ የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት ደግሞ የተራድኦው ተግባር ከሚመለከተው የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ስለ ምግባረ ሠናይ ተልእኮው የሚቀርብለትን ዕቅድ እና አፈጻጸም እንደሌላው አገልግሎት ሁሉ የቅርብ ተጠሪው ለሆነው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በየስድስት ወሩ በጽሑፍ ሪፖርት ያሳውቃል፤ እንደ አስፈላጊነቱም በየወቅቱ ዝርዝር ዕቅዶቹን ይሁን አፈጻጸሞቹን የተመለከቱ ማብራሪያዎችን ለመምሪያው ሊቀ ጳጳስ እና የሥራ ሓላፊዎች ይሰጣል፡፡

   ይሁንና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ከመምሪያው ሊቀ ጳጳስ እና ባልደረቦች በተለየ አኳኋን ሞያቸው አስመስለው የያዙትን በማኅበሩ ላይ የክስ ዶሴ ማከማቸት በመቀጠል ተግባቦቱን እያወኩ ይገኛሉ - በራሳቸው አነጋገር በመምሪያው የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን “የግል ማኅደር” መምሪያው በሚጽፋቸው “የእርምት ርምጃ” ጥያቄዎች እና ለጥያቄው በአባሪነት በሚያያይዛቸው “የማስረጃ ፎቶ ኮፒዎች” ተጣቦ ይገኛል፡፡ ከላይ ለተጠቀሰው የፓትርያርኩ ደብዳቤ መነሻ የሆነው እና በቁጥር 101/3/2003 በቀን 30/05/2003 ዓ.ም የተጻፈው የሓላፊው ክስም ከዚሁ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ግን በሓላፊው አካሄድ ላይ አስገራሚ ናቸው ያሏቸውን ሁለት ነጥቦችን በመጥቀስ ግብዝነታቸውን ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ ሓላፊው እንዲህ ያሉትን ደብዳቤዎች የሚጽፉት እንደ ጓሮ ጎመን ወደሚቆጥሩት የአሜሪካ “ፕሮጀክታቸው” ለመሄድ ሲነሣሱ ነው፤ እጅ መንሻቸውም እንደሆነ ለጊዜው ባይታወቅም በግልባጭ ለመምሪያው የተላከው የፓትርያርኩ ደብዳቤ ግን በአንድ የመፍቀሬ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ድረ ገጽ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለጥፎ መታየቱ “የማኅበሩን የግል ማኅደር ያጣበቡ” ዶሴዎችን ዋነኛ ማጠንጠኛ ጠቁሞ የማሳየት ያህል ነገሩን ግልጽ ያደርግልናል፡፡

   ሁለተኛው የምንጮቹ ነጥብ ደግሞ ሓላፊው፣ “የጉዞ መሥመሩን አሻቅቦ ከሥልጣን ክሂሎቱ በላይ አልፎ ተገኝቷል፤ በዚህም የቤተ ክርስቲኒቱን ሁለንተናዊ አቅም ወደ ራሱ አመራር አዙሯል” በማለት ማኅበረ ቅዱሳንን በጥር ሠላሳው ደብዳቤያቸው የመክሰሳቸውን ያህል ራሳቸውም የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ሳያውቁት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን እንዲሁም የአስተዳደር ዘርፎች ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁን አቶ ልዑል ሰገድ ግርማን በከፍታ ዝላይ ተሻግሮ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ‹ቅሬታ ማቅረባቸው› ነው፡፡ እዚያው ሳለም ፓትርያርኩ ራሳቸው ደረጃውን ጠብቆ ያልቀረበ ‹ቅሬታ›ን መቀበላቸው ሳይበቃ “የማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት ድርጅታዊ መዋቅሩን አለቦታው በመጠቀም የቤተ ክርስቲያኒቱን የሥልጣን ተዋረድ እየሸረሸረ እና እየጣሰ መሥራትን በስፋት እንደተያያዘው” ለመናገር እንደምን ይችላሉ?

   የማኅበሩ የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍልስ ቅዱስ ሲኖዶስ ባጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን መንፈሳዊ፣ ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት በተሟላ መንገድ ለመፈጸም የሚያስችለንን የዕውቀት በረከት የሚያስገኙልን የአብነት ት/ቤቶቻችን እና መናብርተ ጥበብ የሆኑ ዐይናማ መምህራን እንዳይነጥፉ ከዘርፉ ብዙ ችግራቸው አንዱ የሆነውን የአልባሳት መታረዝ ለዚያውም በጊዜያዊነት ለመቅረፍ ጥረት ማድረጉ የማንን ክብር ይነካል? የጥቅምቱ 29ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርት እንደገመገመው፣ የገዳማት አስተዳደር ሥራ በሰው ኀይል እና በበጀት እጥረት ቀዝቅዞ በሚታይበት በአሁኑ ወቅት ገዳማውያን መነኮሳት ተራቁተው ለፍልሰት እንዳይዳረጉ በጎ አድራጊ ምእመናንን በማረባረብ እገዛ ማድረግ እንዴት ነው “በማይመለከተው ጉዳይ ጣልቃ መግባት” ሊባል የሚችለው? ሌላው ይቅርና የማደራጃ መምሪያው ሓላፊ ማኅበሩ “የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን” አድርገው ያቀረቡት ክስ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ላይም መስተጋባቱ የማኅበሩን አገልግሎት በአስተዳደራዊ ጫና ለመገደብ ብሎም ህልውናውን ለማቋረጥ የተኬደበትን ርቀት እንደሚያሳይ ተነግሯል፡፡

   ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ
   ስለዚህ ምክንያት ይሆን ደብዳቤው በአድራሻ የተጻፈላቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ደብዳቤው “ተንኮል ያለበት” በመሆኑ ለአፈጻጸም እንደማይመሩት፣ የአስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ ደግሞ “በማያውቁት ጉዳይ እንደማይፈርሙ” መናገራቸው? እነርሱ እንዲህ ቢሉም የፓትርያርኩ ደብዳቤ “አርኪቴክት” እንደሆኑ የሚነገርላቸውና ጉዳዩ ጨርሶ የማይመለከታቸው የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ መች ወደኋላ ይላሉ፤ የተላኩበትን ለማስፈጸም በመጀመሪያ ምክትል ሥራ አስኪያጁን፣ ለጥቆም ብፁዕ ሥራ አስኪያጁን ለመሞገት መሞከራቸው ተመልክቷል፡፡ ብፁዕነታቸውም ቀደም ሲል የማደራጃ መምሪያው ሓላፊ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ላይ የዘረዘሯቸውን ጥያቄዎች ለማስፈጸም የታቀደው በምክክር እንጂ ቅቡልነትም ቅንነትም በሚጎደለው አኳኋን አለመሆኑን አስታውሰው ንቡረ እዱ በውትወታ የሚጫኗቸው ከሆነ ደግሞ ከሓላፊነታቸው እንደሚለቁ እና ይህንንም ይፋ እንደሚያደርጉ አሳስበዋቸዋል ተብሏል፡፡

   ወደ ዝርዝር መግባት ሳያስፈልግ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ተፈጥሮ በነበረው አስተዳደራዊ ችግር ሳቢያ መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በተደረገው ውይይት ላይ የማኅበሩን የኅትመት ውጤቶች በመጥቀስ “ማኅበሩ ወደ ነቀፋ እና ፖሊቲካ ያዘነብላል” በሚል ባቀረቡት ክሳቸው ይታወሳሉ፡፡ እርሳቸው በጠቀሷቸው ኅትመቶች ላይ የተስተናገዱት ጽሑፎች ግን ቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊ እና ክህነታዊ ሥልጣኗ እንዲሁም ከታሪካዊነቷ የተነሣ አገራዊ የማስታረቅ ሚናዋን እንድትወጣ የሚያሳስቡ፣ የእምነት ልዩነትን ሰበብ በማድረግ የሚፈጸመው ግብረ-ሽበራ ተቀባይነት እንደሌለው የሚመክሩ እንደነበሩ ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡

   በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የማደራጃ መምሪያው ሓላፊ ማኅበረ ቅዱሳን፣ “ሕገ ደንቡን በመጣስ ይሠራል፤ የዕዝ ሰንሰለት አይጠብቅም፤ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ ይገባል፤ ሀብት እና ንብረቱ፣ የአባላቱ ቁጥር እና የገቢ ምንጩ አይታወቅም፤ ተንኳሽ ኅትመቶችን ያወጣል፤ ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል” በሚል ክሳቸውን አሰምተው ነበር፡፡ ክሶቹ ግን በሚገባ ያልተደራጁ እና በማስረጃም ያልተደገፉ ስለነበር በሓላፊነታቸው መጠን መፍታት የሚገባቸውን ችግር ለዚህ በማድረሳቸው እንደ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ባሉት ብፁዓን አባቶች በድክመት ተገሥጸዋል፡፡ በወቅቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅም (ነፍሳቸውን ይማርልን) ጉዳዩን የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ ለችግሩ መፍትሔ እያፈላለገ ባለበት ሁኔታ እንዲህ ዐይነቱ ስብሰባ መጠራቱ ድንገተኛ እንደሆነባቸው ገልጸው ነበር፡፡

   በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ ዘጠኝ መሠረት መምሪያው የማኅበሩን የአገልግሎት እና የሥራ ዕቅድ በመገምገም ተገቢውን መምሪያ እና አስተያየት የመስጠት፣ ማኅበሩ ከሦስተኛ አካላት ጋራ የሚያደርገውን ግንኙነት የማመቻቸት፣ የሚገጥሙት ችግሮች እና ዕንቅፋቶች እንዲወገዱ ተገቢውን ጥረት የማድረግ ሓላፊነት ቢኖርበትም ይህንኑ በአግባቡ እንዳይወጣ ሓላፊው ተመልሰው ያደሩ ጥያቄዎችን ሁሉ በብዙ መልክ እና ቃና መላልሰው በማንሣት ችግሩን የሚያባበስ አካሄድ መምረጣቸውን ነው የጉዳዩ ተከታታዮች የሚናገሩት፡፡ ለአብነት ያህል በፓትርያርኩ ደብዳቤ ላይ ከተመለከቱት ውስጥ በቁጥር ል/ጽ/594/2002 በቀን 16/11/2002 ዓ.ም “ማኅበረ ቅዱሳን ሊሠራበት ከሚገባው ውስጠ ደንብ ውጭ እየሠራ ችግር በማስከተሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ማእከላዊ አስተዳደር መርሕ ተከትሎ ይሠራ ዘንድ ውሳኔ እንዲተላለፍ” የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ለታዘዘበት ደብዳቤ ማኅበሩ በቁጥር ማ/ቅ/ሥ/አ/158/2003 በቀን 20/11/2003 ምላሽ ሰጥቷል። የመምሪያው ሊቀ ጳጳስም ማኅበሩ “ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጭ ሠርቷቸዋል” የተባሉት ስሕተቶች ግር ቢያሰኛቸውም ከላይ የተገለጸውን እንዲፈጽሙ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በቁጥር 452/16187/03 በቀን 19/2/2003 ዓ.ም በተጻፈላቸው ደብዳቤ በታዘዙት መሠረት፣ “ማኅበሩ ሊተዳደርበት ከሚገባው ውስጠ ደንብ ውጭ እየሠራ ችግር አስከትሎ ከሆነ ከሕግ አግባብ ውጭ በመሆኑ መታረም እንደሚገባው ታውቆ ወደፊትም ቢሆን ሊተዳደርበት ከተሰጠው የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ ውጭ መሥራት እንደሌለበት” አሳስበው ነበር፡፡

   የመምሪያው ሓላፊ ጥር ሠላሳ ቀን ደረጃውን ሳይጠብቁ ለፓትርያርኩ ከጻፉ በኋላ እንደተለመደው ወደ አሜሪካ በመብረር ውጤቱን ቢጠባበቁም ቀደም ሲል በተገለጹት ምክንያቶች በዋና ሥራ አስኪያጁ በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ውድቅ ተደርጓል፡፡ የማደራጃ መምሪያው ምንጮች እንደሚናገሩት ይህ መርዶ የሆነባቸው ሓላፊው ካሉበት አሜሪካ ወደ መምሪያው ሠራተኞች ስልክ በመደወል ከፓትርያርኩ የተጻፈው ደብዳቤ በመምሪያው ድረ ገጽ ላይ እንዲለጠፍ ቢያዙም ትእዛዛቸው ተፈጻሚ አልሆነም፡፡ ፓትርያርኩ በበኩላቸው ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ስልክ በመደወል እና በአካል በመጥራት ጫና ቢፈጥሩም ብፁዕነታቸው አቋማቸው የማይለወጥ ሆኖ ተገኝቷል፤ በፓትርያርኩ የተጠሩት አራት የመምሪያው ሠራተኞችም በደብዳቤው የተገለጸውን እንዲያስፈጽሙ - የማያስፈጽሙ ከሆነ ሥራቸውን እንዲለቁ በውግዘት ቀረሽ ኀይለ ቃሎች ቢያስጠነቅቋቸውም “ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ለመፈጸም እና ለማስፈጸም እንቸገራለን” በማለታቸው ደብዳቤው ግዳጁን ሊፈጽም የማይችል ሆኖ ታይቷል፡፡

   ውጥኑ ስንዝር ሳይራመድ የጠበቃቸው የማደራጃ መምሪያው ሓላፊ ከአንድ ሳምንት በፊት ከአሜሪካ ጉዟቸው ሲመለሱ የመምሪያ ባልደረቦቻቸውን በኀይለ ቃል በመዝለፍ ስለ መንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሆነው ያረቀቁትን የአፈጻጸም ደብዳቤ በመያዝ ወደ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በመቅረብ ፊርማቸው እንዲያኖሩበት ይጠይቋቸዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም በዚህ ጉዳይ መነጋገር የሚሹት ከመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋራ እንጂ ከእርሳቸው ጋራ አለመሆኑን በመግለጽ እንደማይፈርሙ አስረግጠው ይነግሯቸዋል፡፡ ሓላፊው ቀደም ሲል ከማኅበሩ ቅዱሳን ጋራ ለመሥራት እንደማይችሉ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት ያሳወቁ በመሆናቸው አንድም ፓትርያርኩ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን በመጫን ትእዛዙን ለማደራጃ መምሪያው እንዲጽፉ የተለያዩ የማስገደጃ መንገዶችን ይጠቀማሉ አልያም ከዚህ በፊት ማኅበሩን በአሸባሪነት እና በፖሊቲከኛነት በመክሰስ እንደጻፉት ሁሉ ለመንግሥት አካል ማኅበሩን በመወንጀል ይጽፉ ይሆናል፡፡

   ይህንንም በማኅበሩ የርዳታ አልባሳት መርሐ ግብር ማሰባሰቢያ ሰሞን የማኅበሩን ዋና ጸሐፊ በመጥራት በሰጡት ማስጠንቀቂያ አሳይተዋል፡፡ በርግጥም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መዋቅሮች የራሳቸው ፈቃድ ፈጻሚ አድርገው በማሽመድመድ (de-institutionalized bureaucratic  authoritarianism) “ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ አውጪም ሕግ አስፈጻሚም ሕግ ተርጓሚም ነዎት” የሚለውን ማባበያ እና ውዳሴ ያለእርማት ለሚቀበሉት አቡነ ጳውሎስ ደግሞ ይህን ለማድረግ የሚያግራቸው እና የሚያክራቸው አካል ያለ መስሎ አይታይም፡፡

   የአቤቱታ አቅራቢዎች ግንባር - የምጥ ዋዜማ

   ፓትርያርኩ ማኅበሩ ለሚሠራው የምግባረ ሠናይ አገልግሎት ተደጋጋሚ ተግዳሮት የሆኑትን ያህል ከሰሞኑ እንኳ ኤልሻዳይ ሪሊፍ የሚባለው ከቤተ ክርስቲያኗ ውጭ የሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ልመናን ከአዲስ አበባ ለማጥፋት” በሚል ከእያንዳንዱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ እና ሰንበት ት/ቤቶች ከብር 300,000 - 700,000 ለመሰብሰብ አስቧል ለተባለው ፕሮጀክት ሙሉ ስምምነታቸውን መስጠታቸው የመንበረ ፓትርያርኩን ምንጮች ያስደምማቸዋል፡፡ ወትሮም ቢሆን በየአጥቢያቸው ስም የሰበካ አስተዳደር ጉባኤያት የማያውቋቸው በርካታ የሒሳብ መዝገቦች (በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ስም አራት የአስተዳደር ጉባኤው የማያውቀው አራት አካውንት ተገኝቷል) በተለያዩ ባንኮች ውስጥ እየተገኙ መሆኑ ለሚያሳዝናቸው፣ እስከ መቶ ሺሕ ብር ድረስ ወጪ እየተደረገ  ለፓትርያርኩ በስጦታ እና በመዋጮ መልክ የሚፈጸመው ብኩንነት እርስ በርስ ለሚያወዛግባቸው የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት የሀብት ጥንተ መሠረቱ የአንድ የፕሮቴስታንት ድርጅት የነበረው የበጎ አድራጎት ተቋሙ ሐሳብ ክፉኛ አሳስቧቸዋል፡፡

   (በነገራችን ላይ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ስም አራት የአስተዳደር ጉባኤው የማያውቀው አራት አካውንት ተገኝቷል፤ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልየዐሥር ሚልዮን ብር ዕዳ አለበት፤ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ግን ለፓትርያርኩ ሽልማት ለመስጠት አልሰነፉም።)  

   “ልመናን ከአዲስ አበባ ለማጥፋት” በሚለው በዚህ ፕሮጀክት ሐሳብ መሠረት በመሐል ከተማ የሚገኙትንና ተነጻጻሪ አቅም ያላቸውን አድባራት ትተን በከተማዋ ዳርቻ ከሚገኙት አጥቢያዎች አንዱ የሆነው የደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እንኳ ብር 300,000 (ከዚህ ውስጥ ብር 80,000 የተጠየቀው ሰንበት ት/ቤቱ ነው) የማዋጣት ሓላፊነት ተጥሎበታል፡፡ የድህነት ውጤት የሆነውን ልመናን ማስወገድ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚሻ ግልጽ ቢሆንም በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያኒቱ በእያንዳንዱ ምእመን ቤት የምትደርስባቸውን መዋቅሮች ከዘረፋ እና ሙስና አጽድቶ በሙሉ አቅማቸው ማንቀሳቀስ እየተቻለ ሐሜት ከበዛበት የአፍኣ ተቋም ጋራ መጣበቅ ውጤታማነቱን አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡

   አሁን ስለ ፓትርያርኩ ደብዳቤ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የሚገኘው ከላይ በቅርብ መንሥኤነት የተገለጸው የማኅበረ ቅዱሳን የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አይደለም፡፡ እንደ ማኅበሩ ምንጮች ከሆነ ለአንድ ሳምንት በተካሄደው የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር 22‚000 ልዩ ልዩ አልባሳት እና ከብር 80‚000 በላይ ተገኝቷል፡፡ አልባሳቱ ታጥበው እና ተተኩሰው በአራቱም ማእዘናት ወደተመረጡ ገዳማት እና አድባራት ወዳሉ 750 መነኮሳት፣ በታላላቅ የአብነት ት/ቤቶች ወደሚገኙ 3500 መምህራን እና ተማሪዎች ከየአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጋራ በመተባበር ለማከፋፈል በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ምንጮቹ አመልክተዋል፡፡

   ይልቁንስ የፓትርያርኩ ደብዳቤ ዋነኛ መንሥኤ፣ ከወራት በፊት የተቀጣጠለውን የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ንቅናቄ ማኅበረ ቅዱሳን ማእከል እና መሠረት ሆኖ የማስተባበሩ ጉዳይ የግል እና የቡድን ጥቅማቸውን የሚያሳጣቸው እና ሐቀኛ ማንነታቸውን የሚያጋልጥባቸው የፓትርያርኩ ባለሟሎች (በነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ቃል አቆላማጮች/አሽቃባጮች) ባልተሰጣቸው ሥልጣን ከፓትርያርኩ ያተረፉትን ቅርበት በመጠቀም በልዩ ልዩ መልክ ከሚያደርጓቸው አስተዳደራዊ ጫናዎች አንድ መገለጫ ሆኖ ተወስዷል፡፡

   A cartoon characterized King Leopold of the Belgians as a monstrous snake crushing the life out of the black population of the Congo Free State, which was under the personal rule of the Belgian king from 1885 to 1908.
   የማኅበሩን አገልግሎት በአስተዳደራዊ ጫና በመገደብ በሂደት ህልውናውን ለማቋረጥ በተጠናከረ መልኩ በተያዘው ምስነት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደራዊ መዋቅር በኩል ያደረጉት ሙከራ ብዙም ያልተራመደላቸው ፓትርያርኩ ከየአህጉረ ስብከቱ “ማኅበረ ቅዱሳን እየበጠበጠን ነው” በሚል ክስ የሚያቀርቡ የአቤቱታ አቅራቢዎች ግንባር እንዲፈጠር በመጣር ላይ ይገኛሉ፡፡ የክስ አቤቱታዎቹ ጋጋታ “ለጳጳሳቱ አጀንዳ እየሰጠ ያስወጋኛል” የሚሉትን እና አባታዊ ክብካቤያቸውን ከነፈጉት ውሎ ያደረውን ማኅበር ለመድፈቅ ከተሳካላቸውም ለማፍረስ ለያዙት ምስነት ሕጋዊ መሠረት ለመስጠት የሚደረግ መሆኑ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ እና በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ ሳይቀር ግልጽ ሆኗል ተብሏል፡፡

   ፓትርያርኩ በዚህ ምስነታቸው ከሁለት ዓመት በፊት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ነጥለው ባስቀሩበት ስልት ማኅበረ ቅዱሳን በታዛዥነት የሚያገለግላቸው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳደሮች፣ መንፈሳውያን ማኅበራት እና አገልጋዮች ደንብረው እንዲሸሹት፣ ዐይን እና ናጫ እንዲሆኑ በማድረግ አገልግሎቱን ያደናቅፋሉ፤ በዚህም በወረዳ ማእከላት እና በማእከላት የሚገኙ የቅርንጫፍ መዋቅሮቹን አገልግሎት በማዳከም በሂደት በዋናው ማእከል ደረጃ ብቻ እንዲወሰን አልያም ተቋማዊ ቀብሩ በዚያው እንዲጠናቀቅ ያደርጋሉ፡፡

   ከማእከል ወደ ዋናው ጽ/ቤት ማኅበሩን ሸርሽሮ ለማጥቃት ለየቅል የሆኑ ቅራኔዎችን አስተባብረው በፈጠሩት ግንባር በቤተ ክርስቲያኒቱ የፋይናንስ እና አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ የፈጸሙት ሙስና እንዳይጋለጥባቸው፣ በዚህም መንገድ የሚያገኙትን ጥቅም እስከ ወዲያኛው ለማስጠበቅ ከእርሳቸው ጋራ ውኃ እና ወተት ከሆኑት አንዳንድ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች እና ሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት ጀምሮ በስውርም በገሃድም የሚረዷቸው አልጠፉም፡፡ የማደራጃ መምሪያው ሓላፊ እና ጸሐፊ፣ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት እና ኤጲስ ቆጶስነትን በመንፈሳዊ ብቃት ያይደለ በደጅ ጥናት ለመሸመት የሚሹ ቆሞሳት፣ ከአቆላማጮቹም እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና የእርሳቸው አሽቃባጭነት የሽፋን ተኩስ የሚሰጣቸው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኞች እንደ ቅደም ተከተላቸው የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ረድፍ ተሰላፊዎች ሆነዋል፡፡

   ሰሞኑን ቀድሞ የአቡነ ሳዊሮስ ሀገረ ስብከት ከነበረው ከነገሌ ቦረና ሀገረ ስብከት አንዳንድ ከተሞች (ሻኪሶ፣ ክብረ መንግሥት እና ሀገረ ማርያም) የማኅበረ ቅዱሳን ወረዳ ማእከላት እንዲዘጉ የሚጠይቁ አቤቱታ አቅራቢ ነን ባዮች በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ አስተባባሪነት ወደ ቋሚ ሲኖዶሱ መቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ በተለይም ከሻኪሶ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መምጣታቸውን የሚናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎች፡- የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እና መሪጌታ እንዲነሡ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የቦረና ማእከል የሻኪሶ ወረዳ ማእከል እንዲታገድላቸው መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ ከፍተኛ ገቢ እንዳለው የሚነገረው ይህ አጥቢያ ከሀገረ ስብከቱ የቀድሞ ሊቀ ጳጳስ ጋራ ከአቡነ ሳዊሮስ ጋር የጥቅም ትስስር በፈጠሩት የአሁኑ አቤቱታ አቅራቢ ነን ባዮች መበዝበዙ ይነገራል፡፡ ይህን በተመለከተ የሒሳብ መዝገብ ምርመራ /ኦዲት/ ጥያቄ የቀረበው ደግሞ አሁን ሀገረ ስብከቱን ከሲዳማ ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ጋራ ደርበው ለሚመሩት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ነው፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ ያላግባብ ከሓላፊነታቸው በተነሡበት ወቅት ከጉዳዩ ጋራ በተያያዘ በዚያው በነገሌ ቦረና የሳምንታት ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ይኸው የሀገረ ስብከቱ የተጠናከረ አያያዝ ያሰጋቸው ጥቅመኞች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ አቤቱታ በማቅረብ ስም ለመሸፈን የሚሹት ይህን ጥፋታቸውን ነው - “እንዴት የአንድ ወገን አቤቱታ ይዘን እንወስናለን? ሰው ልከን እናጣራለን እንጂ” ብለው በተቃወሙ አንድ የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ለጊዜው ተገታ እንጂ፡፡

   ሌላም አለ፤ ከመስከረም 9 - 11 ቀን 2001 ዓ.ም በዚሁ አጥቢያ የቀድሞው ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በተካሄደው ጉባኤ በጋሻው ደሳለኝ ምእመናኑ ችግሮቻቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቆ ነበር፡፡ በጥያቄው ግር ያለው ምእመንም ግራ ይጋባል፡፡ በጋሻው በዐይነ ደረቅነት የጥያቄ ያለህ ሲል ይቆይና ራሱ ያደራጃቸውና በምእመኑ ውስጥ ያሰረጋቸው ግብረ በላዎቹ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር የዘርፌን እና የምርትነሽን ‹መዝሙር› እንዳይዘምሩ እንደሚከለክላቸው የሚከስ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

   በዚህ ጥያቄ መነሻ ያገኘው በጋሻውም ወደ ሊቀ ጳጳሱ ዞሮ፣ “የዘርፌን መዝሙር ዘፈን ነው የሚሉ ሐሜተኞች አሉ፤ እንኳን ዘፍና ዘምራ ሕዝብን ካመጣች ምን ክፋት አለው፤ ብፁዕ አባታችን ይህን ሕዝብ ከእስራት መፍታት አለብዎት፤ ይህን ሰበካ ጉባኤ ከሥልጣን ማውረድ አለብዎት፤ ወሳኙ ሕዝቡ ነው” ይላል፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ከእርሱ ብሰው፣ “ምእመናን ከነገ ጀምሮ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ እንድታደርጉ፡፡ አዎ፣ መጋቤ ሐዲስ በጋሻው ‹የዘርፌን መዝሙር ዘፈን ነው የሚሉ ሐሜተኞች አሉ፤ እንኳን ዘምራ ዘፍና ሕዝብን ካመጣች ምን ክፋት አለው› ብሏል፤ እኔም በዚህ እስማማለሁ፡፡ በእኔ ሀገረ ስብከት የሚያገባው የለም” በማለት ምእመኑን ያስደነግጣሉ፡፡ ወዲያም በጋሻው ድምፅ ማጉያውን ተቀብሎ፣ “ብፁዕነታቸው አስተዳደር ውስጥ እንድንገባ ፈቅደውልናል፤ ከነገ ጀምሮ የእነርሱን (በማኅበረ ቅዱሳን የሻኪሶ ወረዳ ማእከልን) ታፔላቸውን አንሡ፤ ከዚህ ወረዳ ይውጡ፤. . .በእውነት አሁን አባታችን የሚሄዱበት መኪና መኪና ነው፤ በሌላ ሀገረ ስብከት ያሉት ጳጳሳት በሁለት ሚልዮን ብር መኪና'ኮ ነው የሚሄዱት፤ ሲሆን ለሥራ አስኪያጁም መግዛት ይገባ ነበር፤ የአቅም ችግር ስላለ በአዲስ አበባ ያሉ ሰዎችን አስተባብረን ለብፁዕ አባታችን አንድ መኪና በስጦታ እንገዛለን” ሲል ሊቀ ጳጳሱም “ከዚህ በኋላ እነ መጋቤ ሐዲስ በጋሻውን ማማት አይቻልም፤ ሰበካ ጉባኤውን አውርጃለሁ” በማለት ስምምነታቸውን በዐዋጅ ያሳውቃሉ፡፡

   የመኪና ስጦታው ሳይሳካ ቀርቶ በ2600 ብር የእጅ መስቀል ቢተካም በጋሻው በሻኪሶ ወረዳ በጥያቄ መልክ የጀመረውን ሕዝቡን ከእስራት የመፍታት ‹ነጻ አውጭነት› እስከ ወሊሶ ድረስ በመውሰድ በወሊሶ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ በሁዳዴው ጨፍሮ የጾሙን ቀኖና በመሻር ‹ነጻነቱን› በራሱ ዐውጆታል፡፡ ከእርሱም ጋራ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ-ወሊሶ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በአካል በመገኘት ይሁን ፈቃዳቸውን በመስጠትም አብረውት እንደነበሩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

   በርግጥም ሊቀ ጳጳሱ እንደተናገሩት በሀገረ ስብከታቸው ማንም ጣልቃ የመግባት ሥልጣን ባይኖረውም ይህ የሚሆነው ግን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን እና ቃለ ዐዋዲውን ጠብቀው እስካስጠበቁ ድረስ ብቻ ነው፡፡

   የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ተክለ ሃይማኖትም ከዚህ ተለይተው ሊታዩ አይችሉም፡፡ በሀገረ ስብከቱ መዠንግር ዞን ጎደሬ ወረዳ ቶሊ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል እና ጌቴሰማኒ መድኃኔዓለም አብያተ ክርስቲያን ከአንድ ወር በላይ በዘለቀው ጉባኤ አይሉት ዳንኪራ ሥራ አስኪያጁ በዐውደ ምሕረቱ በተቀመጡበት የጾሙን ቀኖና በሚሽር አኳኋን ሲጨበጨብ እና እልልታው ሲቀልጥ ከርሟል፡፡ በዐውደ ምሕረቱ የድርጊቱ ፈጻሚዎች የነበሩት ደበበ እስጢፋኖስ፣ ዕዝራ ኀይለ ሚካኤል (ሕፃን?) እና ሌሎች ሁለት ሰባኪ እና ዘማሪ ነን ባይ ጆቢራዎች ናቸው፡፡ ሥራ አስኪያጁ ድርጊቱን የሚቃወሙ ሁሉ የመውጊያውን ብረት መርገጥ እንደሚሆንባቸው በማስጠንቀቅ በፖሊቲከኛነት ወንጅለዋቸዋል፤ ወደ እስር ቤትም እንደሚያስወረውሯቸው ዝተዋል፤ ራሳቸውን የሰላም እና ልማት አርበኛ በማድረግም ፓትርያርኩን በተደጋጋሚ እያወደሱ በቅርቡ ሀገረ ስብከቱን እንደሚጎበኙ ገልጸዋል፡፡

   ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ሳዊሮስ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ወደ ወሊሶ ከተዘዋወሩ በኋላ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ሥራ አስኪያጁ ደርበው በያዙት ነገሌ ቦረና ሀገረ ስብከት እንደ ልቡ መፈንጨት ያልተቻለው በጋሻው በቅርቡ ለአንድ መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ ሁለቱንም በአንተታ ጠርቶ ዘልፏቸዋል፡፡ በጋሻው በዚሁ ቃለ ምልልስ “የነበረው ሥራ አስኪያጅ ሕዝቡን ስላስቆጣ ሲኖዶሱ ይሄንን ተቀብሎ ሥራ አስኪያጁን አንሥቶታል” ካለ በኋላ ስለ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም “አሁን ደግሞ የሕዝቡ ጥያቄ ሊቀ ጳጳሱ ካልተነሡልን ነው፤ ምክንያቱም ሕዝቡን እያገለገለ አይደለም” ብሏል፡፡

   በቅርቡ በሲዳማ እና ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት በተፈጠረው የአስተዳደር ችግር አቤቱታውን በተደጋጋሚ ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት እና ለክልሉ መንግሥት በማሰማት “ሕግ ይከበር” እያለ የሚገኘው ቀናዒው የሐዋሳ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ሆኖ ሳለ የችግሩ ምክንያት “የተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ ኤድስ ማኅበር ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና ደጋፊዎች ጋራ የሚያደርጉት ፉክክር ነው” በሚል ቋሚ ሲኖዶስ አስተላልፎታል በተባለው ውሳኔ የማኅበሩ የሐዋሳ ማእከል “በቤተ ክርስቲያኒቱ መድረክ እንዳያስተምር” የሚያግድ ውሳኔ ወጥቷል፡፡

   ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ተቋም ተጠርቶ ባልተጠየቀበት ሁኔታ የችግሩ አካል እንደሆነ ተደርጎ በተጠቀሰው አኳኋን የተደረሰበት ውሳኔ እንዳሳዘነው የገለጸው የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት፣ በቁጥር ማቅሥአመ/09/02/ለ/03 በቀን 09/06/03 ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ የማኅበሩን ስም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በአደባባይ በማጥፋት ላይ የተሰማሩትን እና ይህንንም ተግባር እያበረታቱ በሚገኙት አካላት ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ በማከታተልም በቁጥር ማቅሥአመ/08/02/ለ/03 በቀን 21/06/03 በአድራሻ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፈው ደብዳቤ ተላለፈ የተባለው ውሳኔ በሀገረ ስብከቱ ቤተ ክርስቲያንን እና የአካባቢውን ሕዝብ ሁከት ውስጥ እየጨመሩ የሚገኙ አካላትን የሚያበረታታ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

   ስለዚህም “የተጻፈው ደብዳቤ በአስቸኳይ እንዲሻር እና በሁከት ፈጣሪዎቹ ላይ ርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን” በሚል ጥያቄውን አጠናክሮ አቅርቧል፡፡ በቋሚ ሲኖዶሱ ተላለፈ የተባለው ውሳኔ ቃለ ጉባኤ ምናልባትም በሸኚ ደብዳቤ እንዲደርሰው ተደርጎ በሪፖርተር ጋዜጣ የካቲት 20 ቀን 2003 ዓ.ም እትም ላይ ለተላለፈው ዘገባም የማኅበሩ ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ተመሳሳይ የማስተባበያ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከሌሎች ቀናዒ አገልጋዮች እና የምእመናን ማኅበራት ጋራ በመሆን በጀመረው የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ንቅናቄ ላይ የሚስተዋለው አስተዳደራዊ ጫና ይኸው ምልልስ በፓትርያርኩ እና በዙሪያቸው በተጠለሉ ጥቅመኞች ዘንድ የፈጠረው እልክ እና ስጋት ሊሆን እንደሚችል ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት ትዝብት ነው፡፡

   ቁም ነገሩ ግን “ቤተ ክርስቲያንን እና የአካባቢውን ሕዝብ ሁከት ውስጥ እየጨመሩ ናቸው” የተባሉት አካላት ጎጠኝነትን የመጨረሻ ምሽጋቸው ያደረጉ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ መረማመጃዎች እና የግል ጥቅም አሳዳጆች መሆናቸው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎትም ይሁን ከዲቁና እስከ ጵጵስና ባለው የክህነት ሢመት የታወጀ /ሥርዐታዊ የሆነ/ አድልዎ እና ጭቆና በሌለበት ሁኔታ በተወላጅነት መብት ስም ጭፍን ስሜቶችን ለማጋጋል መሞከር ጠባብነት ነው፡፡ በፖሊቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ገጹ ጠባብነት - የጥገኝነት መሣሪያ ነው፤ ጠባብነት - መዋቅራዊ ውስንነቶችን እና ጥገኛ አመለካከቶችን በመበዝበዝ፣ የታሪክ ቁርሾዎችን በማራገብ ወሳኙን እና መሠረታዊውን ሐቅ (በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ቤተ ክርስቲያኒቱን አዳክሞ የመውረስ ወይም ከፍሎ የመረከብ) ለመሸፈን የሚደረግ ርብርብ ነው፡፡ ጠባብነት - ሥልጣንን ተቆናጠው አልያም ሥልጣን በያዙት ተጠልለው ለመበልጸግ የሚሹ ጥገኞችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በመሆኑም ከብዙኀኑ ምእመን መብት እና ጥቅም ጋራ ምንም ትስስር የሌለው ብቻ ሳይሆን የምእመኑን ሃይማኖታዊ መብት ከሚፃረሩ ጅቦች ጋራ ተሰልፎም ቢሆን ከንቱ ውዳሴን ለመሸመት እና ያልተገባ ጥቅምን ለማግበስበስ ያለባቸውን ሰቀቀን ለመሸፈን የሚጠቀሙበት ጭምብል ነው፡፡

   ዛሬ በሐዋሳ “የሲዳማ ቄስ እና ጳጳስ የለም፤ በቋንቋችን እንዳናስተምር ተከለከልን” በሚል አዲስ መፈክር ያነገቡት ወገኖች ከጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም በፊት ይህ ዐይነቱ ጥያቄ አልነበራቸውም፡፡ በወቅቱ በነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ግን መንበረ ጵጵስናው ከብር 50‚000 ያላነሰ ወጪ ይታይበት ነበር፡፡ ለነዳጅ እስከ ብር 80‚000፣ ለአንድ ጊዜ የመኪና እድሳት እስከ ብር 181‚000 ወጪ ተመዝግቧል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ጠቅላላ ዓመታዊ ደመወዝ ብር 60‚000 ሆኖ ሳለ “ልዩ ልዩ ወጪዎች” በሚል በሊቀ ጳጳሱ የተመዘገበው ወጪ ብር 240‚000 እንደነበር የሒሳብ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

   የቀድሞው የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል በመንበረ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት የሚከፈላቸው ብር 5000 ደመወዝ ሳያንስ በሐዋሳ ከተማ ከሚገኙ አድባራት ከእያንዳንዳቸው ብር 800 በየወሩ ሲወስዱ፣ ሜሮን እና ቅብዐ ቅዱስ ሲሸጡ፣ በየአጥቢያው ታቦት እንዲደረብ በማድረግ ገንዘብ ሲቀበሉ፣ በአዲስ አበባ የሚገኘውንና በብዙ ሺሕ ብር ያከራዩትን ቤት እንዲያስጨርስላቸው 20‚000 ስኩዬር ሜትር የሆነውን የባሕረ ጥምቀት ቦታ ለአንድ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሸጡ ጎልቶ የተሰማ ተቃውሞ አልነበረም፡፡

   ሊቀ ጳጳሱ ከሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ምእመናን የልማት ኮሚቴ ጋራ አለመግባባት ከፈጠሩባቸው ምክንያቶች አንዱ የልማት ኮሚቴው ያሠራው ባለአራት ፎቅ ሕንፃ እንዲሁም በዓመት ከ5 - 6 ሚልዮን ብር በሚያስገኘው የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ገቢ አስተዳደር አላላውስ ስላላቸው ነበር፡፡ የቀድሞውን የገዳሙን አስተዳዳሪ በማንሣት የሀገረ ስብከቱን መመሪያ ባለማስፈጸም፣ ቃለ ዐዋዲውን ባለማስጠበቅ እና ለአሁኑ ሊቀ ጳጳስ ባለመታዘዝ [ከሁከት ፈጣሪው ቡድን ጋራ የሚመክሩበትን የገዳሙን የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ እንዲዘጋ ለመከረው የርእሰ መስተዳድሩ ቢሮ ጭምር እምቢታን በመምረጥ] በገዳሙ ለተፈጠረው ሁከት ምክንያት የሆኑትና ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ ጥያቄ የቀረበባቸውን የአሁኑን አስተዳዳሪ የሾሙት ደግሞ ፓትርያርኩ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ የቀድሞው ሊቀ ጳጳስ በቋሚ ሲኖዶሱ ቃለ ጉባኤ ላይ እንደተመለከተው፣ ከክህነቱ ተሽሮ በውጭ እንዲያገለግል የተወሰነበትን ግለሰብ ከጋብቻ ውጭ ልጅ እንዳለው እያወቁ በሥርዐተ ተክሊል በማጋባት ለሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ግድ እንደሌላቸው ያሳዩ ናቸው፡፡

   እንግዲህ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም ቋሚ ሲኖዶሱ ወስኖታል በተባለው መሠረት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ተውጣጥቶ በሀገረ ስብከቱ የተፈጠረውን ያለመግባባት ችግር አጥንቶ ለመፍታት እና ከክልሉ መስተዳድር ጋራ በመተባበር የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት በሀገረ ስብከቱ ለተገኘው ኮሚቴ 2ሜxበ1ሜ በሆኑ ሁለት ሸራዎች ላይ የቀድሞውን ሊቀ ጳጳስ ሥዕል በመያዝ “የልማት አባት” ያሰኙት ወገኖች ይህን አያውቁም አልያም ከዚህ ተጠቃሚ አልነበሩም ማለት አይቻልም። “ና፣ ና፤ ፋኑኤል ና ና፣ ተጨንቀናልና” ተብሎም ተዘምሮላቸዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት እሑድ ከመጻጉዕ ሰንበት ቅዳሴ በኋላ ሕፃናት እና ሴቶች የሚበዙባቸው እነዚሁ የእነ ያሬድ አደመ መልእክተኞች ባሳዩት ድርጊት ለማስተማር በዐውደ ምሕረቱ ላይ በነበሩትና የልኡካን ቡድኑ መሪ በሆኑት በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ “የሐዋሳ ሕዝብ ድሮ ስናውቀው አንድ መንፈስ የነበረውና ይህን ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ያሠራ ነው፡፡ ሕዝቡ አባትን ያከብራል ብዬ ነው የመጣሁት፤ አባትን መውደድ ጥሩ ነው፤ በዚህ መልኩ መሆን ግን የለበትም” በሚል ተመክረዋል፡፡

   በደብዳቤ ቁጥር 274/2069/03 በቀን 22/06/03 ዓ.ም የተሠየመውና ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴው፡- ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድን፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን፣ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን፣ አቶ ልዑል ሰገድ ግርማን፣ በኩረ ትጉሃን ዓለም አታላይን (የጠቅ/ቤ/ክ የቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊ)፣ መምህር አእመረ አሸብርን (የሊቃውንት ጉባኤ አባል) እና አቶ ይሥሓቅ ተስፋዬን (የሕግ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊን) ያቀፈ ነው፡፡ ከልኡካን ቡድኑ ጋራ ያላግባብ ከሓላፊነታቸው በተነሡት የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ ቦታ የተተኩት ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ አብረው ተጉዘዋል፡፡

   ይሁን እንጂ ለኮሚቴው ሥራ መሟላት የግድ መገኘት የነበረባቸው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም ሆነ የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና ጸሐፊ በሀገረ ስብከቱ አለመኖራቸው ኮሚቴው “ያለባለቤቱ” ምን ዐይነት ማጣራት (ማረጋጋት) እንደሚያካሂድ ለብዙዎች አደናጋሪ ነበር፡፡ የቀድሞው አጣሪ ኮሚቴ ተልእኮውን የፈጸመው ግን በስምሪቱ ወቅት በአሜሪካ የነበሩትን የአቡነ ፋኑኤል መምጣት እንዲጠብቅ ተደርጎ ነበር፡፡

   በአንዳንድ ምንጮች ጥቆማ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “ጉዳት ይደርስብዎታል፣ ዐርፈው እዚሁ ይቀመጡ” በሚል ወደ ሓዋሳ እንዳይሄዱ ማስፈራሪያ ተደርጎባቸው ነበር፡፡ ይሁንና ብፁዕነታቸው “ሲኖዶሱ እስከ መደበኝ ድረስ ሄጄ መሥራት አለብኝ” ብለው ወደ ሓዋሳ ከተመለሱ በኋላ ቁጥራቸው 40 የሚደርሱ ዑላ በሚል የተደራጁ የቀን ሠራተኞች ቡድን ጥቁር ጨርቅ በመያዝ፣ “አባ ጳውሎስ እንዳትሄድ እያሉህ ለምን መጣህ፤ እናርድሃለን ውጣ” በሚሉ አሳዛኝ ንግሮች መዝለፋቸው ተሰምቷል፡፡ ጥር 25 ቀን 2003 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ ምእመናን እና ሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ስም በፓትርያርኩ እና በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ አበረታችነት ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መጥተው ለቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መነሻ የሆነውን የአስተዳደር ችግር አቀረቡ የተባሉት በዚህ መልኩ ሊቀ ጳጳሱን የዘለፉ፣ ሥራ አስኪያጁን የከሰሱ እና ማኅበረ ቅዱሳንን የወነጀሉ ወገኖች ናቸው፤ በመመለሻቸውም ላይ ፓትርያርኩ 5000 ብር ለ‹ሻይ› የሰጧቸው መሆኑን በዚያው መድረክ ላይ የተናገሩ ሲሆን ከተጓጓዙባቸው ዐሥር ያህል መኪኖች የሁለቱ የመጓጓዣ ወጪ የተሸፈነው በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ነበር፡፡

   በአንጻሩ ጥር 30 ቀን 2003 ዓ.ም በእኒህ ጋጠ ወጦች ሁከት ሳቢያ በገዳሙ ማስቀደስ፣ መማር እና መንፈሳዊ አገልግሎት መፈጸም አለመቻላቸውን ለመግለጽ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ፓትርያርኩ የቀረቡ 24 የአገር ሽማግሌዎች፣ “እናንተ ቤተ ክርስቲያን ሠርታችኋል፤ ከዚህ በኋላ ለምን ዐርፋችሁ ቤታችሁ አትቀመጡም” በሚለው የአቡነ ጳውሎስ ንግግር አፍረው እና አዝነው እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ዛሬ በሀገረ ስብከቱ ያለውን የአስተዳደር ጉባኤ እና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የመምራት ሓላፊነት ያለባቸው፣ በሀገረ ስብከቱ ለሚገኙት ገዳማት እና አድባራት መንፈሳዊ አባት የሆኑት ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በሀገረ ስብከታቸው የሉም፡፡ ፊት የባሌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በኋላም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት አባል፣ በጡረታ እና ሬከርድ ክፍል ሓላፊ ሆነው መሥራታቸው የሚነገርላቸው አዲሱ ሥራ አስኪያጅም አሁን በምን መልኩ እንደተሾሙ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡

   አንድ ነገር ግን ርግጥ ነው - ከመጋቢት 8 - 14 ቀን 2003 ዓ.ም በሐዋሳ ቆይታ ያደረገው ልኡክ ፓትርያርኩን ተገን ያደረጉት የእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ ጫና እና ክትትል እንዳለበት (የማጣራቱን ሂደት በቀጥታ የስልክ ግንኙነት ሞኒተር እስከ ማድረግ ድረስ)፡፡ በጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም ተሠማርቶ ለነበረው አጣሪ ልኡክ 76 ገጽ የሰነድ፣ ስድስት የኦዲዮ ቪዥዋል ማስረጃዎችን አቅርበው ሳለ “እርባና የሌለው” በሚል ተጥሎባቸው ፍትሕ ያጡት የአገር ሽማግሌዎች ባለፈው ሳምንት እሑድ ከኮሚቴው አባላት ጋራ ሲወያዩ ቅሬታቸውን በሚከተለው መልኩ የገለጹት ይህን በመረዳት ይመስላል፡-”አሁን የመጣችሁት የአቡነ ጳውሎስን ፈቃድ ለማስፈጸም ቢሆንም፣ የሥራ አስኪያጁ መነሣት ኢፍትሐዊ ቢሆንም አባቶቻችን ናችሁና እንቀበላችኋለን፤ ጉብዝናችሁን ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ የሰጣችሁ ሰዎች ናችሁ፤ በምንኩስና ከማዕርገ ጵጵስና ደርሳችኋል፤ ምንድን ነው የምትፈሩት?”

   የአገር ሽማግሌዎቹን እንዲህ ለማምረር ያበቃቸው የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ነው በተባለው ቃለ ጉባኤ ላይ ማስረጃዎቻቸው የተመዘነበት እና የተደረሰበት ውሳኔ የፈጠረባቸው ቅሬታ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይሁንና ዋናው መንሥኤ ግን ከዚህም ያልፋል፡፡ ይኸውም የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት የደረሱበት ውሳኔ በቃለ ጉባኤው ላይ በሰፈረው መልክ አለመሆኑ መታወቁ አንደኛው ነው፡፡ ከአሁኑ ኮሚቴ አባላት በተለይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ወደ ፓትርያርኩ ቢሮ ተጠርተው የኮሚቴው አባል ሆነው እንዲሄዱ መመደባቸው ሲነገራቸው፣ “በሐዋሳ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ ሥራ አስኪያጅ እና ጸሐፊ በሌለበት መሄዳችን አግባብ አይደለም፤ ያለፈው አጣሪ ኮሚቴ ሪፖርትም በቅጡ አልታየም” በማለት ለመሄድ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ በሚገልጹበት ወቅት ቀድሞም በቢሮው ውስጥ የነበሩት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ “ይሄዳሉ፤ መሄድ አለብዎት” በማለት ጥልቅ ይላሉ፡፡ ብፁዕነታቸውም “አንቺ አታዥኝም” በማለት ቢሮውን ለቀው ይወጣሉ፡፡ ወዲያው ሦስት ብፁዓን አባቶች እና አምስት የጠቅላይ ቤተ ክህነት የአስተዳደር ሓላፊዎችን ዝርዝር የያዘው ደብዳቤ ከመዝገብ ቤት ገብቶ ወጪ ሳይደረግ በወይዘሮዋ አማካይነት ወደ ሐዋሳ ግብረ በላዎቻቸው በፋክስ ተልኳል፡፡ ይህ መረጃ የደረሳቸው የሐዋሳ የአገር ሽማግሌዎች የአሁኑ አጣሪ ተልእኮ ቀድሞ በቋሚ ሲኖዶስ ተወስኗል ተብሎ ቅሬታ ለቀረበበት የፓትርያርኩ የብቻቸው ውሳኔ ሕጋዊ ልባስ ለመስጠት የሚደረግ ነው ብለው በማመናቸው ነው የተቆጡት፡፡ ፓትርያርኩ በዚህ መልክ በፈተኑት ቋሚ ሲኖዶስ ማኅበረ ቅዱሳን የሚዘጋበትን አልያም አገልግሎቱን በቅልጥፍና ለመፈጸም በማያስችለው የቤተ ክህነቱ ቢሮክራሲያዊ ማነቆ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ ውሳኔ እንዳያሳልፉ ተሰግቷል፡፡

   ይህ ጉዳይ በመንበረ ፓትርያርኩ የከፍተኛ አስተዳደራዊ አካል ውሳኔ አሰጣጥ ሴትዮዋ በፓትርያርኩ ላይ አላቸው ስለሚባለው ተጽዕኖም በቂ ማረጋገጫ ሆኖ ታይቷቸዋል፡፡ አሳዛኙ ነገር ጥር 30 ቀን 2003 ዓ.ም ፓትርያርኩን አነጋግረው የነበረው 24ቱ የሐዋሳ የአገር ሽማግሌዎች በችግሩ ውስጥ ወይዘሮ እጅጋየሁ ስላላቸው ሚና ሲያነሡ አቡነ ጳውሎስ፣ “እኔ ወይዘሮዋን ካየኋቸው ወራት አልፈውኛል፤ ለምን ስም ታጠፋላችሁ፤ ኀጢአት ይሆንባችኋል” ብለዋቸው ነበር፡፡ ይሁንና ሰሞኑን በግልጽ እየወጡ እየገቡ መታየታቸው ያስጨነቃቸው ወገኖች ፓትርያርኩ ዘንድ ቀርበው የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ለምን አይከበርም በማለት ሲጠይቋቸው፣ “ይህ (ያሉበትን ሕንፃ መሆኑ ነው) ቤቴ ነው፤ በቤቴ መስተናገድ ይችላሉ፤ እናንተ በመኖሪያ ቤታችሁ እንግዳ አትቀበሉም እንዴ?” ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰውላቸዋል፡፡

   ከአጣሪ ኮሚቴው ጋራ እሑድ መጋቢት 11 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገው ውይይት “አዲስ ነገር ባንጠብቅም ያለንን ትክክለኛ ሚና በማስገንዘብ ቤተ ክርስቲያናችንን ከጥቅመኞች እና መናፍቃን በመከላከል ማስከበር እንደምንችል ማሳመን ዋነኛ ፍላጎታችን ነበር” ብለዋል ከምእመናን ተወካዮች አንዱ፡፡ መጋቢት 8 እና 9 ቀን 2003 ዓ.ም የምእመናን ተወካዮቹ ከማስረጃዎቻቸው የተመረጡ ክፍሎችን ከአንድ ሺሕ ላለነሱ ሰዎች በአዳራሽ ገለጻ በመስጠት የተቀሰቀሰው ምእመን መጋቢት 10 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በገዳሙ ቅጥር ግቢ በብዛት ተገኝቷል፡፡ በሁኔታው የተደናገጠው እና ሕዝባዊ ድጋፍ እንደ ከዳው በአጣሪ ኮሚቴው ፊት የተጋለጠበት የእነ ያሬድ አደመ ቡድን በገዳሙ ቅጽር ግቢ እና ከውጭ ሳይቀር የወዳደቁ ቁሳቁሶችን እያግበሰበሰ ከምሮ በማቃጠል “ቢንቢዎቹን ለማስወጣት” በሚል የተሰበሰቡትን ምእመናን በጭስ ለመበተን ጥረት ቢያደርግም ሁኔታውን በከፍተኛ ትእግሥት እና ዝምታ በተከታተለው ምእመን ብርታት ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ በወቅቱ አጣሪ ኮሚቴው የአምስቱን አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ሰብስቦ በማወያየት ላይ የነበረ ቢሆንም የገዳሙ አስተዳዳሪም ይሁኑ ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተል የቆየው ፖሊስ ድርጊቱን ለመግታት የወሰዱት ርምጃ አልነበረም፡፡

   ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2003 ዓ.ም የዚህን ሁከተኛ ቡድን ተወካዮች ያነጋገረው አጣሪ ኮሚቴ በቡድኑ አባላት ግብረ ገብ የለሽነት ማዘናቸው ተመልክቷል፡፡ ከቡድኑ አባላት አንዳንዶቹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ሳይቀር “ክህነታችሁን እንጠራጠራለን” እስከማለት መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ገደብ ያለፈ አነጋገር በያሬድ አደመ አዝማችነት በሁለት ቡድን ተደራጅተው ከገቡት ምእመናን አንዳንዶቹ በመደናገጥ፣ “እኛ እንዲህ የሚሉ አልመሰለንም፡፡ እነዚህ ሰዎች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች መሆናቸውን እንጠራጠራለን” በሚል በአጣሪ ኮሚቴው አባላት ፊት እርስበርስ መካሰሳቸው ታውቋል፡፡ የኮሚቴው አባላት የሆኑት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የጋጠ ወጦቹን ንግግር በመታገሥ ምክር ከሰጧቸው በኋላ ጥቂቶቹ ተንበርክከው እያለቀሱ ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ የምእመናኑ ተወካዮች በበኩላቸው ለቀደመው አጣሪ ኮሚቴ ያቀረቧቸውን ማስረጃዎች በማስታወስ በተለይም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከመጡ በኋላ በተደረገው ጥረት በታኅሣሥ ወር መጨረሻ ተደርሶበት ስለነበረው ዕርቀ ሰላም፣ የዕርቀ ሰላሙ ስምምነት በተለይም ከጥር ሰባት ጀምሮ እንደምን እየተጣሰ እንደመጣ፣ ቋሚ ሲኖዶስ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አስተላልፎታል የተባለውን ውሳኔ ለመቀበል አዳጋች እንደሆነ ትኩረት ሰጥተው ማስረዳታቸው ታውቋል፡፡

   ኮሚቴው እሑድ ዕለት ከምእመናን ተወካዮች ጋራ ካደረገው ውይይት ባሻገር ከማኅበረ ካህናት፣ ከአምስቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ከ24ቱ የአገር ሽማግሌዎች (ዕርቀ ሰላም ኮሚቴ አባላት)፣ ሁከት ፈጣሪው በሁለት ቡድን አደራጅቶ ከላካቸው መልእክተኞች እንዲሁም ከደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋራ መወያየቱ ታውቋል፡፡ ኮሚቴው ከርእሰ መስተዳድሩ ጋራ  ባደረገው ውይይት ችግሩ በአስቸኳይ በሚቋጭበት ሁኔታ ላይ መምከሩ ተገልጧል፡፡ ከአምስቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ጋራ በተደረገው ውይይት የዳቶ ኪዳነ ምሕረት እና የባለወልድ አድባራት አለቆች “ችግሩ እኛ ካህናት የሚገባንን ያህል ባለመሥራታችን የተፈጠረ ነው” ሲሉ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ መልአከ ኀይል አባ ኀይለ ጊዮርጊስ፣ የቅድስት ሥላሴው አባ ናትናኤል እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ አባ ሲሳይ ደግሞ “የችግሩ ሁሉ መንሥኤ ማኅበረ ቅዱሳን ነው” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የሐዋሳ ማእከል ሥራ አስፈጻሚ አባላት በበኩላቸው በአቡነ ጎርጎርዮስ የሚመራው ልኡክ ማኅበሩ ተጠርቶ ሳይጠየቅ ያለተግባሩ በሚወነጀልበት ጉዳይ ላይ እንዲያነጋግሯቸው በደብዳቤ ጭምር ቢጠይቋቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ተዘግቧል፡፡

   ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት ከምእመናን በቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ መሠረት የምእመናን ተወካዮች ለአጣሪ ኮሚቴው ሲያቀርቧቸው የቆዩትን ማስረጃዎች በሙሉ በገዳሙ ቅጽር ግቢ በኤል.ሲ.ዲ ፕሮጀክተር ለማቅረብ ቀጠሮ ይዘው የነበረው ቢሆንም ሁከት ለመፍጠር ላሰፈሰፉት የእነ ያሬድ አደመ መልእከተኞች ምክንያት ላለመስጠት እና በአጣሪ ኮሚቴው ምክር መርሐ ግብሩ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ይሁንና በዚሁ ዕለት ምሽት በገዳሙ የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ የመሸጉት ሁከት ፈጣሪዎች በመንበረ ጵጵስናው ወዳረፉት የአጣሪ ኮሚቴ አባላት በማምራት በራቸውን በኀይል ሲደበድቡ መቆየታቸው ታውቋል፡፡ ይህን ተከትሎ የአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ “ማስረጃውን ለምእመኑ ይፋ አደርጋለሁ ብሎ ሁከት የቀሰቀሰው ማኅበረ ቅዱሳን በመሆኑ የችግሩ መንሥኤ ማኅበረ ቅዱሳን ነው” በሚል ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ሐሳብ ያቀርባሉ፤ ሐሳቡን ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ይቃወማሉ፡፡ በመሐል ከፓትርያርኩ በተደወለ ስልክ የተጠሩት የአጣሪ ኮሚቴው አባላት ተልእኳቸውን በውል ሳያጠናቅቁ ረቡዕ ጠዋት ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ተገልጧል፡፡ በእነያሬድ አደመ በኩል ከጅምሩ አንሥቶ የነበረው ጥረት፣ የአጣሪ ኮሚቴው አባላት በፍቅረ ንዋይ ተለክፎ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አሽከር የሆነውን ቡድን ሐቀኛ ማንነት በርጋታ አጢነው እንዳያጋልጡት በዚህ መልኩ የጸጥታ ስጋት ፈጥሮ አልያም አበሳጭቶ ከጊዜው በፊት እንዲመለሱ ማድረግ እንደነበር የምእመናን ተወካዮቹ አስረድተዋል፡፡

   አጣሪ ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ የአጣሪ ኮሚቴውን በድንገት ከሐዋሳ መልቀቅ የሰሙት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የምእመናን ተወካዮች ለሕዝቡ ሊያሳይ ስለነበረው ማስረጃ ምንነት በመረዳት፣ “ከዚህ በኋላ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት መፍትሔ ያፈላልጋል የምንለው ሰው አንጠብቅም፤ ሂደቱ የክልሉ መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ መስጠት እንደማይችል የሚያስመስል ነው፤ ከዚህ በኋላ ጉዳዩን ራሳችን እያጣራን ርምጃ እንወስዳለን” ማለታቸው ተመልክቷል፡፡ የአጣሪ ቡድኑ መሪ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም በዚያው ሐሳባቸው ጸንተው በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የቅሬታ አቁማዳ ለከፈቱት ፓትርያርክ ማጠናከሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማጣራቱ ሂደት የስድብ ናዳ ሲወርድባቸው የነበሩት እንደ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ያሉት አባቶች ደግሞ “ችግሩ ላይኛው ቤት እንደሆነ ዐውቄአለሁ፤ ሰውዬው የሚፈልጉት ማኅበሩን እንድንከስላቸው እና እንድናፈርስላቸው ነው፤ አቡነ ይሥሓቅ ከነሓሳባቸው እንደሞቱት እኔም ከነሓሳቤ መቃብር እገባለሁ እንጂ በዚህ አልተባበርም፤ ልጆቼን አሳልፌ አልሰጥም” ማለታቸው ታውቋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በተለይም የአቡነ ጳውሎስን ሐውልተ ስምዕ አስመልክቶ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ የአማርኛ አገልግሎት የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያስተላለፈውን ውሳኔ ይፋ ካደረጉ ወዲህ በፓትርያርኩ በሚሰነዘርባቸው ማንጓጠጦች ምክንያት የፓትርያርኩ ቢሮ ከሚገኝበት ሕንጻ እንዲወጡ ተደርገው ወጥተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ቢሮዎች ወደሚገኙበት ሕንጻ ተዛውረዋል፡፡ በዚህ ወቅት አቡነ ጳውሎስ እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፡- “እኔ ሳልፍ እዚህች መንበረ ፓትርያርክ ውስጥ ማንም ፓትርያርክ አይገባም፤ እኔ የምታሰብበት ሙዚየም ነው የሚሆነው፡፡”

   ከቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የተሰማው ፀረ ተሐድሶ ደወል

   በሌላ በኩል ኅዳር 12 ቀን ወር 2003 ዓ.ም አንሥቶ በስፋት ተጀምሮ በጥልቀት በመፈጸም ላይ የሚገኘው ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን የመከላከል ጥረት አስተዳደራዊ ጫናዎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ማንነት በማስጠበቅ ጽኑ መንፈስ እና ሙሉ ፍላጎት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የሰባክያነ ወንጌል ጥምረት በተለይም ከየካቲት 27 - 30 ቀን 2003 ዓ.ም በቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ያካሄደው የትምህርተ ወንጌል ጉባኤ ስኬት በኑፋቄ አቀንቃኞቹ ጎራ የፈጠረው ድንጋጤ ለአስተዳደራዊ ጫናዎቹ መጠናከር በምክንያትነት እየተጠቀሰ ነው፡፡

   ጥምረቱ በዚህ ደብር ለአራት ቀናት ባከናወነው 12ው ዙር የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ከ17 ያላነሱ መምህራን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን እና ነገረ ማርያምን ርእሰ ጉዳይ በማድረግ ምእመናን ከወቅታዊው የኑፋቄ ንፋስ የሚጠበቁበትን ትምህርተ ወንጌል በመስጠት ተሳትፈዋል፤ የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶው ንቅናቄ አጋር በመሆን በየመድረኩ የተሰለፈውና በዕውቅ ተዋንያን የሚመራው ማኅበረ ላሊበላ ተዋሕዶ” የተሰኘውን መምህራኑ ከመላው ጉባኤተኛ ጋራ በቁጭት እንባ የታጠቡበትን መንፈሳዊ ተውኔት አሳይቷል፤ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄውን ወጥመድ የሚያጋልጠው ገለጻ በኤል.ሲ.ዲ ፕሮጀክተር ተደግፎ ቀርቧል፡፡ በደብሩ የስብከተ ወንጌል ታሪክ ባልተለመደ አኳኋን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምእመን የተከታተለው ይኸው ጉባኤ፣ “ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን ቃና በድምፅ ለይተው እንዲያውቁ እና ኦርቶዶክሳዊ መሠረታቸውን እንዲያጠናክሩ” የሚያስችል እንደሆነ የደብሩ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ “በመጀመሪያው ቀን የነበረው ምእመን በሁለተኛው ቀን ዕጥፍ ሆኖ መጣ፡፡ ያሉን 1500 ወንበሮች ቦታ ስለሚያጣብቡብን እነርሱን አንሥተን ምእመኑ መሬት ላይ ተጠጋግቶ ተቀምጦ ጉባኤውን እንዲከታተል አድርገናል” ይላል ከደብሩ አገልጋዮች አንዱ፡፡ የአጥቢያው ምእመናን እንደሚናገሩት ከዚህ ቀደም በዐውደ ምሕረቱ ላይ በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኝነት የሚጠረጠሩ ግለሰቦች በአስተዳዳሪው እየተጋበዙ ‹ያስተምሩ› ነበር፡፡

   ምእመናኑ አያይዘውም ክብረ ቅዱሳንን በመቃወም እና “ነፍስ እግዚአብሔር ናት” በሚለው የተሳሳተ ትምህርታቸው ከሚለዩዋቸው ሰባክያን ነን ባዮች በተጨማሪ በደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ሓላፊ የሚጠሩት እነበጋሻው ደሳለኝ፣ “ሚካኤል [ቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል] ሙጃ በቅሎበታል፤ የኢየሱስ ጠላቶች [የቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች እነ መምህር ፍሬ ስብሐት እና መምህር አፈወርቅ] እዚያ አሉ፤ እንጸልያላቸው” በማለት ይናገሩ እንደነበር መስክረዋል፡፡ በርግጥ እነበጋሻው በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው እንዲህ የሚዘልፉት ምስጉን መምህራነ ወንጌልን ብቻ ሳይሆን  እነርሱ በየአዳራሹ እና በተለያዩ አጥቢያዎች ከሚያካሂዷቸው ሕገ ወጥ ጉባኤዎች እንዲታገዱ ቅዱስ ሲኖዶስ የካቲት 12 ቀን 2001 ዓ.ም ያሳለፈውን ውሳኔ በጥብቅ ለማስፈጸም የጣሩትን የቀድሞውን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅን ጭምር ነው፡፡ ብፁዕነታቸው የካቲት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በድንገተኛ ሕመም ማረፋቸው እንደተሰማ በጋሻው ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እንዲህ አጫውቷቸው ነበር - “አንድ የኢየሱስ ጠላት ሞተ፡፡”

   ጉባኤው ተጀምሮ እስከተጠናቀቀበት የካቲት 30 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት ድረስ የደብሩን ሰባክያነ ወንጌል ሲያበረታቱ የቆዩት አስተዳዳሪ በዚሁ ቀን ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የጻፉት ደብዳቤ ግን የማበረታቻ አልነበረም፡፡ በቤተ መቅደሱ አገልግሎት እና በዐውደ ምሕረቱ ለፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኞች ፈቃድ ከመስጠትም በላይ በምእመናን ፊት እስከ ማሞካሸት የሚደፍሩት የደብሩ አስተዳዳሪ ከየካቲት 27 - 30 ቀን 2003 ዓ.ም በአጥቢያው የተካሄደው ጉባኤ፣ በጉባኤው የተሳተፉት መምህራን እና የመናፍቃኑን ወጥመድ የሚያጋልጠው ገለጻ ምእመኑን ለሁለት ከፍሎ ብጥብጥ ሊያሥነሳ እንደነበር፣ እርሳቸው የጠሩት የፖሊስ ኀይል ግን ከስፍራው ደርሶ ብጥብጡን ለማስቀረት እንደተቻለ የሚገልጽ ፍጹም ሐሰተኛ ደብዳቤ ነበር፡፡ በየጊዜው እየጠነከረ በመሄድ ላይ ያለው የሰባክያነ ወንጌሉ ጥምረት ከቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ስብከተ ወንጌል ኮሚቴ ጋራ በመቀናጀት ያከናወነው ስኬታማ ጉባኤ ከደብሩ ዐውደ ምሕረት ተሻግሮ በደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ከሚፈነጩበት መድረክ እንደሚያስወግዳቸው የሰጉት የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኞቹ ጫና ለመፍጠር የተንቀሳቀሱት አስተዳዳሪውን እንዲህ ያለ አሳሳች ደብዳቤ እንዲጽፉ በማድረግ ብቻ አይደለም፡፡

   የኑፋቄ አቀንቃኞቹ እና የጥቅም አሳዳጆቹ ረጅም እጅ በሆኑት በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ አማካይነት በአስተዳዳሪው ደብዳቤ ላይ የተገለጸው ተመሳሳይ መልእክት የደረሳቸው ፓትርያርኩ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊውን አባ ኀይለ ማርያም መለሰን ማነጋገራቸው አልቀረም፡፡ አባ ኀይለ ማርያም መለሰ ከዚህም በፊት ከሐምራዊ መጽሔት የወርኀ የካቲት እትም ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር” የሚባለው ቡድን በመምሪያው የተጣለበት እግድ እንደጸና ስለመሆኑ፣ ከሚሌኒየም አዳራሽ ‹ጉባኤ› የመግቢያ ትኬት ሽያጭ እና ከስፖንሰርሽፕ የተገኘውን በሚልዮን የሚቆጠር ብር ይዞ ‹መሰወሩን› በማጋለጣቸው በፓትርያርኩ ተጠርተው ተመሳሳይ ተግሣጽ አግኝቷቸው ነበር፡፡

   ጫናው የበረታባቸው የመምሪያው ሓላፊ በቁጥር 2783/2789/2003 በቀን 06/07/2003 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ “በአሁኑ ሰዓት ራሳቸውን ያደራጁ ሰባክያን ምእመናንን ለንስሐ፣ ለጾም፣ ለጸሎት፣ ለሰላም እና ፍቅር በማዘጋጀት ፈንታ በሁለት ግሩፕ በመሆን ምእመናንን ግራ በማጋባት ላይ መሆናቸውን ባለን መረጃ ለማወቅ ተችሏል” የሚል ለፍርድ ያስቸገረ አገላለጽ ተጥቅመዋል፡፡ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ጉዳዩን በጥልቀት እየመረመረው እንደሚገኝ የገለጹት ሓላፊው ለጉዳዩ እልባት እስከሚሰጠው ድረስ “በማንኛውም መድረክ ላይ ከመደበኛ የቦታው ሰባክያን እና የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከሚያሰማራቸው በስተቀር በዐውደ ምሕረቱ ላይ የተለየ ጉባኤ ማድረግ የማይቻል” እንደሆነ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትም በቁጥር 3160/90/03 በቀን 13/07/03 ዓ.ም ትእዛዙ ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ ለመላው የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በጥብቅ አስታውቋል፡፡ የትእዛዙን መውጣት ተከትሎ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊው 23 አባላት ካሉት የሰባክያነ ወንጌል ጥምረት እና “የአገልጋዮች ኅብረት” በሚል ከተደራጀው አካል ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጋራ በተናጠል መወያየታቸው ታውቋል፡፡

   በሰባክያኑ ጥምረት ጋራ በተደረገው ውይይት ሓላፊው ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ እና መዋቅሯን የሚያዳክም ማንኛውንም የመድረክ እንቅስቃሴ እንደሚያግዱ ቢያስጠንቅቁም የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ወጥመድ የሚያጋልጠው እና በኤል.ሲ.ዲ ፕሮጀክተር እየተደገፈ ከስብከተ ወንጌሉ ጋራ በመቀናጀት በዐውደ ምሕረት ሲቀርብ የቆየው ገለጻ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አባ ኀይለ ማርያም ስለ ገለጻው ያላቸውን ስጋት ሲያስረዱም፣ “ቁጭት አንድ ነገር ቢሆንም ውጤቱም ሊታሰብበት ይገባል፤ አባቶች ዝም ብለዋል፤ ካለማወቅ አይደለም፤ ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገብቷቸዋል፤ እንዲህ ያለ ነገር በዘመናቸው ገጥሟቸው አያውቅም፤ ፍርሃትም ይኖራል፤ ትውልዱ ሥሡ ነው፤ ይህን ነገር መሸከም የሚችልበት ደረጃ ላይ አልደረሰም፤ በሐዋሳ ያየነው ዐይነት ድንጋይ መወራወር እንዳያመጣ ሁሉንም ነገር በአግባቡ እና በፈሊጥ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴው ግን ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሹ፣ እርሳቸውም አመቺ በሆኑ አጋጣሚዎች ሁሉ አብረው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ከመምሪያው የወጣው ደብዳቤ ማንን እንደሚመለከት ከሰባክያኑ ለቀረበላቸው ጥያቄም “እናንተን ቤተ ክርስቲያኒቱ በተቋሟ አስተምራ የቀጠረቻችሁ በመሆኑ፣ ከየሀገረ ስብከቱ ስለ አገልግሎታችሁ በተደጋጋሚ ወደ መምሪያው የሚመጡት አስተያየቶች መልካም በመሆናቸው እና መምሪያውም እየመደባችሁ ስታገለግሉ የነበራችሁ በመሆናችሁ ደብዳቤው እናንተን አይመለከትም” ብለዋቸዋል፡፡

   ሓላፊው ይህን ይበሉ እንጂ በመምሪያው ደብዳቤ ላይ “ራሳቸውን ያደራጁ እና በሁለት ግሩፕ በመሆን ምእመናንን ግራ የሚያጋቡ” የሚለው ሐሳብ ጥያቄ እንደሆነባቸው ቀርቷል፡፡ በግሩፕ ተደራጅቶ ምእመናንን ግራ ማጋባት የጀመረው ማን ነው? እንዲህ ዐይነቱ ትእዛዝ የሚወጣውስ የቤተ ክርስቲያናችን መድረክ በመናፍቃን መወረሩ ያሳሰበን ልጆቿ ተጠራርተን መመከት ስንጀምር ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን እንዲያነሡ አስገድዷቸዋል፡፡ በቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በእጅጉ የረኩበት የአራት ቀናት የተሳካ ጉባኤ ባካሄዱበት ማግሥት ከደብሩ ሦስት ምድብ ሰባክያን መካከል ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት የአቋቋሙ ባለሞያ እና ማሕሌታዊው መምህር አፈወርቅ ወደ መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና መዛወራቸውም ጥርጣሬያቸውን አጠናክሮታል፤ “በደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ችግር ያለባቸው ሰባክያን እያሉ ምስጉኑ መምህር ከቦሌ ሚካኤል መነሣታቸው ተገቢ አይሆንም” በማለት ቅሬታቸውን ለሓላፊው የገለጹት ሰባክያኑ የጀመሩት ተግባር የደመወዝ ጉዳይ ሳይሆን የሃይማኖት በመሆኑ በያሉበት እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ግልጽ አድርገውላቸዋል፡፡

   የመምሪያው ሓላፊ ከሰባክያኑ በተሰጠው ጥቆማ መሠረት በደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ዘንድ ያለውን ችግር ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጋራ በመሆን እንደሚያጤኑት፣ በቅርቡ ምናልባትም በቀጣዩ ሳምንት በስብከተ ወንጌል ሓላፊው የተጋበዙት እነበጋሻው በቦሌው የቅዱስ ሚካኤል ጉባኤ ስኬት ሳቢያ በአካባቢው ሰሚ በማጣታቸው በክርስትና እምነት ስም የሚጠራውን የማንኛውንም እምነት ተከታይ [ወትሮም ቢሆን ዓላማቸው “በተረዳንበት እምነት እንቅረብ፤ እዚያ ያሉ ወደዚህ እዚህ ያሉ ወደዚያ እንዲሄዱ አይደለም ትምህርታችን” የሚል ነበርና] በማግተልተል ለማካሄድ ያቀዱትን ጉባኤ እንደሚያስቆሙ ማሳወቃቸው ተጠቁሟል፡፡

   በጋሻው ደሳለኝ ከአንድ መጽሔት ጋራ ባደረገው ቃለ ምልልስ የቀቢጸ ተስፋ ምላሽ የሰጠው ይህን በመረዳት ይመስላል - “በኢ.ቢ.ኤስ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚያስተላልፉት ዝግጅት የቤተ ክርስቲያኗ የመምሪያ ሓላፊዎች ያውቁታል ወይ?. . .የስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊ አባ ኀይለ ማርያም ቤተ ክርስቲያኗ እንደማታውቀው ገልጸው ነበር” በሚል ለቀረበለት ጥያቄ በጋሻው በሰጠው ምላሽ፣ “በመጀመሪያ ዶ/ር ብለህ ስለጨመርከው ቅጽል እኔ ማስተካከያ ልስጥህ፤ እኔ ሰውዬው ዶክተር መሆናቸውን አላውቅም፡፡ ምናልባትም ግን መነኩሴ ይመስሉኛል. . .” በማለት በሽሙጥ (ቧልት) መልክ በመናገር ለጥያቄው ቀጥተኛ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡ ዶክተርነትም ይሁን ምንኩስና ለበጋሻው የራቁ እና የከበዱ ቢሆኑም በዚህ ንግግሩ ምንኩስናን መዝለፊያ ዶክተርነትን ማመስገኛ ላለማድረጉ ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም፤ በእርሱ ደረጃ ሌብነቱን ያጋለጡበትን የመምሪያ ሓላፊ ያመሰግናቸዋል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ እርሱ ለሌላው ስመ ማዕርግ እርማት ሲሰጥና የሌላውን ምንኩስና ሲጠራጠር በአጠፌታው የራሱን ውሎ እና አዳር ለሰው ቢናገሩት ለሰሚው የሚያምር አይሆንም፡፡ በጋሻው ዲቁናውን ያረከሰ፣ የኮሌጅ ደቀ መዛሙርት እንደሚናገሩት በአካዳሚያዊ ዝለት በ‹ፍላት የወጣ› ‹ዘረ ቆርጥም› ከመሆኑ በቀር በሜዳ የሸመተውን የእርሱን “መጋቤ ሐዲስ”ነትስ ማን ያውቅለታል? መቼም ጎጋው በጋሻው ልብ የለውምና ይኸው ንግግሩ “ሳይታወቀኝ በስሜት የተናገርኩት ነው” በማለት አባ ኀይለ ማርያም ይቅርታ እንዲያደርጉለት አማላጅ እንደላከባቸው ሰምተናል፡፡ በወጉ መሠረት አባ ኀይለ ማርያም የጽሑፉን ስሕተት በጽሑፍ በማስተባበል የይቅርታህን ጥያቄ ፈጽም እንደሚሉት ተስፋ እናደርጋለን፡፡

   በየአጥቢያው ከዐውደ ምሕረት በውርደት የመባረር ዕጣ የገጠመው በጋሻው የወይኑን ማማ ዘላ ዘላ ልትደርስበት ባለመቻሏ “ፍሬው መራራ ነው” ብላ የተወችውን ቀበሮ ብሂል የሚያስታውስ ነገርም በቃለ ምልልሱ ላይ ተናግሯል - “ወደ ቤተ ክርስቲያን የሄዱ አማኞች ቁጥር እየጨመረ የሄደበት ወቅት ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግን ምእመኑ በተፈጠረበት ውዥንብር ሳይቀንስ የሚቀር ይመስልሃል?” የሚል ‹በልኩ የተሰፋ› የሚመስል ጥያቄ የቀረበለት በጋሻው እንዲህ ብሏል - “በመሠረቱ በንጽጽር ንገረኝ የምትል ከሆነ ከዘንድሮው የአምናው ይሻላል፡፡ እነዚህን ሁለት ዓመታት በየቤተ ክርስቲያኑ ስናይ ያለፉት ዓመታት ይሻል ነበር፡፡ ትላንት ወጣቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ነቅሎ መጥቶ ነበር፡፡ አሁን ትንሽ ቀዝቅዟል፡፡”

   ራሱን “የሠርክ ጉባኤ፣ የፈውስ እና ዝማሬ አብዮተኛ” አድርጎ ያለኀፍረት ለሚያወራው በጋሻው ሃይማኖታዊ ‹ሙቀት› እና ‹ቅዝቃዜ› በምን ያህል ምእመን ቁጥር መገኘት ይለካ ይሆን? በጋሻው ምእመናን ስለተቀዛቀዙበት ምክንያት ሲጠየቅ በሰጠው ምላሽ ጾም፣ ጸሎት እና ቆሞ ማስቀደስ እየራሳቸው በተግባራዊ ክርስትና ካላቸው መንፈሳዊ ዋጋ በማውጣት ከምሽት ጉባኤዎች ጋራ ወደረኛ የሚያደርግ ምላሽ ሰጥቷል - “በመሀል በተፈጠሩ አለመግባባቶች ሕዝቡንም ውዥንብርና መደናገር ውስጥ የሚያስገቡ ወሬዎች ይወሩ ስለነበር ሕዝቡን እነዚያ መሠረት የሌላቸው ወሬዎች አዝለውታል፡፡ ሃይማኖታዊ መነቃቃቱ ወርዷል፡፡ ሆኖም መጾም መጸለያችን በራሱ ፍቅር ካልተጨመረበት ይላል - ምእመኑም፡፡ ከዘንድሮው የአምናው ይሻላል፡፡ በእርግጥ ዘንድሮም ጥሩ ነው፡፡ ምናልባት ግን አብዛኛው ሰው በሥራም በግል ጉዳይም የከሰዓቱን ቅዳሴ ቆሞ ላያስቀድስ ይችላል፡፡ ምሽት ላይ የሚደረጉ ጉባኤዎች ግን ጥሩዎች ናቸው፡፡”

   ትምህርት ጤፉ በጋሻው ይህን ወደ መሰለው የ”እኔ ከሞትሁ ሠርዶ አይብቀል” ግዙፍ ድምዳሜ ለመድረስ በንጽጽሩ ምን ያህል ቦታዎችን በመነሻነት እንደወሰደ አይታወቅም፡፡ የሚታወቅ ነገር ቢኖር መምህረ ሃይማኖት ባሕታዊ ኀይለ ጊዮርጊስ የተባሉ ሰባኬ ወንጌል እንደተናገሩት፣ በጋሻው እና “የሞንታርቦ ወንድሞቹ” ትውልዱ ማንነቱን ለይቶ በማያውቅበት የምሽት ጉባኤዎች ድብልቅልቅ በማደንዘዝ ሀብቱን እየበዘበዙ፣ እናት ቤተ ክርስቲያኑን በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አዳክሞ ለመውረስ አልያም ከፍሎ ለመረከብ ላሰፈሰፉ ኀይሎች በሎሌነት እያገለገሉ መሆናቸው ነው፡፡

   ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና የፍግ እሳት ነው፤ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና አልቀዘቀዘም፤ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና አይቀዘቅዝም!! የቀዘቀዘው፣ ዕርቃኑ የወጣው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋለጠ ያለው የበጋሻው ማንነት እና ቀድሞ በየዋሃን ምእመናን ገንዘብ የደለበው ኪሱ ነው - ዛሬ እርሱን በሚያሠማሩት አጽራረ ቤተ ክርስቲያን እየተሞላ ቢሆንም፡፡  በጋሻው በዚህ አነጋገሩ ባነገበው የኑፋቄ ተልእኮ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሂደት እንድትገባበት የፈለገውን ማጥ ያጋልጥ እንደሆን እንጂ በቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እንደሚካሄዱት ያሉትን ጉባኤያት እንደማይመለከት ግልጽ ነው፡፡

   እርሱ እንደተናገረው ሕዝቡ ውዥንብር እና መደናገር ውስጥ ገብቶ ከሆነም የውዥንብሩ እና መደናገሩ አንዱ መንሥኤ እርሱ እና እንደ እርሱ ባልተገባቸው ሰበካ የቆሙ [ሥራ ክቡር ነውና በጋሻው የጋራዥ ጎሚስታ የነበረ መሆኑ ሰውነቱን ባያሳንሰውም] ግብዞች ፓትርያርኩን ተተግነው የሚፈጽሙት ደባ መሆኑን በተለይ ዛሬ የሚስተው አይኖርም፡፡ “በአጠቃላይ ሳንጠነቀቅ መንፈስ እንዳዘዘን እናስተምራለን” ከሚል “የዘመኑ ሐዋርያ ነኝ” ባይ ምእመኑ ምን ይማራል? “ንጉሣችን ቅልጥ አድርጎ ይዘምራል፤ አባባ ሲተኛ እኛ እንነቃለን፣ እኛ ስንተኛ እርሱ ይሠራል፤ ሥላሴ ሲያጫውቱ ያሥቃሉ፣ እሺ፤ በጣም ነው የሚያጫውቱት፤ ተባበሩኝ ብለው የሚያሥቁ ኮሜዲያን አሉ፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንደዛ አይደሉም፤ ለማርያም ከበሮ አይመታም ለጌታ እንጂ፤ ከጸበሉ ይልቅ የሚያጽናናቸው ቃሉ ብቻ ነው፤ በአንድ ወቅት በራስ ቅል ኮረብታ ላይ ኢየሱስ እና ዲያቢሎስ ቁማር ተጫወቱ…ዲያቢሎስም በጨበጣ ገባ፤ እኛ ሕዝቡን ጨፍረን እናምጣው፣ እናንተ መዝሙር አስተምሩት፤ እኛ ሕዝቡን ደንሰን እናምጣው፤ እናንተ ሥርዐት አስተምሩት፤ እኛ ሕዝቡን ጨፍረን እናምጣው እናንተ ሃይማኖት አስተምሩት፤ ይሄ ሕዝብ እኛ ሳንወድቅ ወድቋል፤ እኛ የምናምነው በፈውስ፣ በዝማሬ በጸጋ ነው፤ ‹በተሰጠኝ ጸጋ ሰይጣን ፎቶዬን ሲያይ መጮህ ጀምሯል› [ጋሞጎፋ ሳውላ ኪዳነ ምሕረት]” የሚል ሰባኪ ነኝ ባይ ዋልጌ የግል ተክለ ሰብእናውን ከመገንባት ውጭ እንደምን ምእመኑን በሃይማኖቱ ለማጽናት ይቻለዋል?

   ከስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ ጋራ ሰባክያኑ ወዳደረጉት ውይይት ስንመለስ፣ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን በሚያጋልጠው ሰነድ ገለጻ መቀጠል ላይ አንድ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል አባል የሰጡት አስተያየት የሓላፊውን ስጋት እና የአስተዳዳሪውን ክስ የሚያስተባብል ነው፤ እንዲህም ብለዋል፡-”አሁን ሁለት ቀርተናል፤ እኛንም እስኪቀይሩን ድረስ ወደኋላ የምንልበት ነገር አይኖርም፤ የስብከተ ወንጌል ኮሚቴው በቃለ ዐዋዲው መሠረት የዐውደ ምሕረት ጉባኤን የጥቅም በር ያደረጉትን ሳይሆን በሥራ ላይ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጋብዞ ጉባኤ የማዘጋጀት ሓላፊነት አለበት፡፡ አስተዳዳሪው የጠሯቸው ፖሊሶች ጉባኤው ሰላማዊ መሆኑን አይተው ነው የተመለሱት፡፡ እርሳቸው አሁንም ‹ጉባኤውን አስቆማለሁ› እያሉ በመዛት ላይ ናቸው፤ ከእኛ የማሳወቅ እጥረት እንጂ ሕዝቡ በእነዚህ የሚጭበረበር አልነበረም፤ ‹እስከ ዛሬ ስለምን ይህን ዐይነቱን ገለጻ አልሰጣችሁንም፤ እነርሱ ወደ አዳራሽ ስለሄዱ እኛ ቤተ ክርስቲያናችንን አልተውንም› ይለናል፡፡ ጉባኤው ከተካሄደ ከቀናት በኋላ እንኳ ‹መቀዛቀዝ እየታየባችሁ ነው› በሚል ጣመን ድገሙን እያለን ነው፡፡”

   ደብዳቤው የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊው “የፓትርያርኩን ፈቃድ በመፈጸም እና የሰባክያኑን ጠንካራ እንቅስቃሴ በመምራት አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን አሳይቶናል” ያሉት የአንዳንድ አጥቢያዎች የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊዎች የወጣውን ትእዛዝ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ ትእዛዙ መተላለፉ ጥቅምም ጉዳትም ይኖረዋል - ጥቅሙ ቀድሞም ቢሆን ቅሬታ የሚያሳድርብንን ከሜዳ ላይ የሚመጡ ሰባክያንን የምር የሚያስቀር ከሆነ ነው፤ ጉዳቱ ደግሞ አፈጻጸሙ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎችን በማስፈራራት እና የደብር አስተዳዳሪዎችን በጥቅም በመደለል አድልዎ የሚፈጸምበት እና ለሌሎች በር የሚከፍት ከሆነ ነው፡፡

   አሰግድ እና እጅጋየሁ

   የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን በመከላከሉ የጋራ ጥረት ላይ አስተዳደራዊ ጫና መፍጠር ስንል ለኑፋቄ ወጥመዱ አካላት እና አባላት ሽፋን በመስጠት በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ መሽገው የሚቆዩበትን ሁኔታዎች ማመቻቸትን ይጨምራል፡፡ በዚህ ረገድ ፓትርያርኩ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የማንኛውም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አባል እንዳልሆነ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደብዳቤ ለጻፈበት አሰግድ ሣህሉ ሰሞኑን ለፍርድ ቤት ጻፉት የተባለው ደብዳቤ ሌላው ጉልሕ ማሳያ ነው፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኞች ግንባር ቀደም የሆነው አሰግድ የተቋሙን የቅበላ መስፈርት ሳያሟላ በተጭበረበረ አኳኋን መመዝገቡን በማረጋገጥ ከትምህርት ገበታ አግዶት ነበር፡፡ ይሁንና ቤተ ክርስቲያኒቱ በሃይማኖታዊ ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት ያላትን ሥልጣን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ አኳኋን በአዲስ አበባ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት ኮሌጁን የከሰሰው አሰግድ ውሳኔ እስኪሰጠው ድረስ እየተማረ እንዲቆይና ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 6 ቀን 2003 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና ዳኛዋ መዝገቡን መርምረው ባለማጠናቀቃቸው ቀጠሮው ለመጋቢት 21 ቀን ተራዝሟል፡፡

   አሰግድ ክሱን በአሸናፊነት ለመወጣት በሚያደርገው አፈሳ እና ዳበሳ ከሰሞኑ ወ/ሮ እጅጋየሁን የሙጥኝ ብሎ ይዟል፡፡ ወይዘሮዋ በልዩ ባለሟልነታቸው አሰግድን ወደ ፓትርያርኩ አቅርበው የአሰግድን መልካም ሰውነት በማስረዳት ክሱ እንዲቋርጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ ጽፈዋል፤ አሰግድም ይህንኑ ደብዳቤ መጋቢት 6 ቀን 2003 ዓ.ም በነበረው የችሎት ውሎ እርሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዱትን የኮሌጁን ጠበቃ ሲሟገት ታይቷል፡፡ ብዙዎችን ያስደመመው ሐቅ ግን አሰግድ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ እንዲያመጣ ለጠየቀው ኮሌጅ ከደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን በሙስና ያጻፈውን “የንስሐ አባቱን” እና የሰበካ ጉባኤ ደብዳቤዎች በደብዳቤ ወደሻሩበት የደብሩ አስተዳዳሪ ስልክ በመደወል፣ “ቅዱስ ፓትርያርኩ ያናግሩሃል፤ ሥራ አስኪያጁ እና ሊቀ ጳጳሱ አስገድደውኝ ነው ደብዳቤ የጻፍሁት ለፍርድ ቤቱ መስክር” ማለቱ ነው፡፡

   ምን ይሄ ብቻ - በዚህ መካከል የኮሌጁ የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ምዝገባ ይካሄዳል፡፡ የልብ ልብ የተሰማው አሰግድ አስቀድሞ በማጭበርበር ተመዝግቦ የነበረው በማታው መርሐ ግብር ሆኖ ሳለ በምዝገባው ወቅት የቀን ተማሪዎችን ስሊፕ በመውሰድ መመዝገብ ከሚገባው /14/ ክሬዲት አወር በላይ በ20 ክሬዲት አወር የሞላውን ቅጽ ለቀንና ማታ መርሐ ግብር ሓላፊው አስፈርሞ ወደ ሬጅስትራሩ ሲደርስ ተነቅቶበት ተከልክሏል ተብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ተመዝግቦ መማር የሚችለው በማታው መርሐ ግብር እንደሆነ በገለጹለት ሬጅስትራር ላይ የዛተው አሰግድ ማንነታቸው የማይታወቁ ሁለት ግለሰቦችን አስከትሎ በመምጣት አስፈራርቷቸዋል፡፡

   ሬጅስትራሩ ጉዳዩን ለኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በማሳወቅ አስቸኳይ ስብሰባ በተጠራው የአስተዳደር ጉባኤው ላይ ቀርቦ ታይቷል፡፡ በዚህም በተጭበረበረው ስሊፕ ላይ በመፈረም ወደ ሬጅስትራሩ የመሩት የቀን እና ማታ መርሐ ግብር ሓላፊው ክፉኛ ‹ቢደነግጡም› ከፍተኛ ተግሣጽ አግኝቷቸዋል፡፡ አሠራሩን እያወቁ እንደምን እንዲህ ያለ ግዙፍ ስሕተት እንደ ፈጸሙ ለተጠየቁት ሲመልሱም “ስሊፑ ከብዙ ዶክመንቶች ጋራ ሆኖ ስለቀረበ በተመሳሳይ መልኩ አይቼው ነው” ብለዋል፡፡ ታዛቢዎች ግን የሓላፊውን እና የአሰግድን ስልት፣ “ቢያዩኝ እሥቅ ባያዩኝ እሰርቅ” በማለት ተርተውበታል፡፡ ከጅምሩም አሰግድ በማታው መርሐ ግብር መስፈርቱን ሳያሟላ ስለ መመዝገቡ እኚሁ ሓላፊ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ይህንኑ ተመሳሳይ ምክንያት ያጣቀሰ ነበር፡፡ በአንድ ዘዴ አንድ ጊዜ እንጂ ስንቴ ማሞኘት ይቻላል? አሰግድም በማታው መርሐ ግብር ተመዝግቦ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

   በሀገር ቤት ይህን ያህል ተጽዕኖ ያላቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ እጃቸውን በማስረዘም ሰሞኑን አንድ የትብብር ደብዳቤ ከፓትርያርኩ ለማጻፍ ችለዋል፡፡ ወይዘሮዋ በየዓመቱ በጌታችን ልደት እና ትንሣኤ በዓላት ተሳላሚ ምእመናንን በመያዝ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ይዞ በመጓዝ የሚታወቀውን አንጋፋውን የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ለሁለት ከፍለዋል፤ በኋላም “ቀራንዮ በኢየሩሳሌም አስጎብኚ የጉዞ ወኪል” የተባለ ድርጅት አቋቋመዋል /ዝርዝሩን ደጀ ብርሃን  የተባለ የጡመራ መድረክ ማውጣቱ ይታወሳል http://www.dejeberhan.org/2010/10/blog-post.html/፡፡ ሚያዝያ 16 ቀን 2003 ዓ.ም የሚከበረውን የጌታችን በዓለ ትንሣኤ ምክንያት በማድረግ ተሳላሚዎች ወደ እስራኤል ጉዞ እንደሚያደርጉ የሚገልጸው የፓትርያርኩ ደብዳቤ ተሳላሚዎችን በማስተባበር እና በማስተማር መርሐ ግብሩን እንዲያስፈጽሙ ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ለብፁዕ አቡነ ያሬድ ያስታውቃል፡፡ በቁጥር 262/540/03 በቀን 18/6/2003 ዓ.ም በፓትርያርኩ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ በግልባጭ እንዲደርሳቸው ከተደረጉት ውስጥ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ይገኙበታል፡፡ ብፁዕነታቸው ግን ወ/ሮ እጅጋየሁ ባቋቋሙት ድርጅት የሚመጡትን ተሳላሚዎች እንደማያስተናግዱ በመጥቀስ ለእስራኤል ኤምባሲ በማሳወቃቸው ኤምባሲው ወ/ሮ እጅጋየሁ ተሳላሚዎችን በማጓጓዝ ለማፈስ የፈለጉትን ጥቅም አስተጓጉሎባቸው ቆይቷል፡፡

   እዚህ ላይ በዋናነት ለማውሳት የተፈለገው ቁምነገር ግን በዚህ የተሳላሚዎች ጉዞ ወይዘሮዋ በጋሻው ደሳለኝን፣ ትዝታው ሳሙኤልን እና ያሬድ አደመን ይዘው በመጓዝ ቆይተውም ከዐሥር የማያንሱ ሌሎች ቡድኖቻቸውን በማስከተል ከኢየሩሳሌም ጉዞ በፊት እና ከኢየሩሳሌም ቆይታ መልስ በዱባይ እንደሚያካሂዱት የተነገረው ጉባኤ ነው፡፡ በዱባይ በቅዱስ ሚካኤል ስም የተሠራው ቤተ ክርስቲያን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ያልተባረከ እና በርካታ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ የድፍረት ተግባራት የሚፈጸሙበት በመሆኑ በብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ መወገዙን ከዚህ ቀደም መግለጻችን ይታወሳል፡፡ አሁንም በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ምእመናነ ክርስቶስ በቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን መምህራን የተሰበከላቸውን የቀደመ እምነታቸውን እና ስፍራቸውን በማጽናት አቋማቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡


   ትብብርን የማጠናከር እና የአዲስ ስትራቴጂ ዝግጅት ጥያቄ

   አቡነ ጳውሎስ ከኅዳር ወር አንሥቶ በተጠናከረ አኳኋን በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ንቅናቄ በዋናነት በወጣቶች ሞተርነት ከተፋፋመው የዐረቡ ዓለም ሕዝባዊ ተናሥኦት ጋራ በማመሳሰል በሃይማኖት ሽፋን ለሚከናወኑ ድርጊቶች ትኩረት ሰጥቶ በሚንቀሳቀሰው መንግሥት ለማስመታት ጥረት ያድርጉ እንጂ ጥረቱ ፍጹም ሰላማዊ መሆኑን መንግሥት እና መላው ምእመን በውል ይረዳዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በባሕርይውም ጥፋቷን የሚሹ አካላት በአገልግሎት እና የአስተዳደር መዋቅሮቿ ውስጥ ተሰግስገው በሚፈጽሙት ደባ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኦርቶዶክሳዊ ማንነት እንዳይጠፋ የማስጠበቅ እንጂ ሌሎች በራሳቸው ጊዜ እና ቦታ የሚያራምዱትን የእምነት ነጻነት መጋፋት አልያም መተናኮስ ሊሆን አይችልም፡፡

   የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ለመቋቋም በምናደርገው መንፈሳዊ ተጋድሎ በአሐቲነቷ ጸንታ የምትቀጥል እንጂ የሰሜን እና የደቡብ በሚል ለሁለት የምትከፈል ቤተ ክርስቲያን አትኖርም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳ በቅርቡ ከውጭ አገር ጋዜጠኞች ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከ1997 ዓ.ም በኋላ በአገሪቱ የተሟሟቀ ፖለቲካዊ ክርክር አለመታየቱ እና ፍርሃት የነገሠ መስሎ መታየቱ ይገዳቸው እንደሆነ ተጠይቀው ከሰጡት ምላሽ፣ ጎሰኝነት እስከ አሁን ዋና ጉዳይ ቢሆንም እየከሰመ ያለና በእርሱ ፈንታ ሃይማኖታዊ ልዩነት አወያይ እና አከራካሪ ሆኖ መውጣት መጀመሩን እንዲህ ሲሉ አመልክተዋል። [. . .While ethnicity is still a major issue, it is sort of dying down and religious differences are beginning to be the main debated issues.]
   ከዚህ ጋራ በተያያዘ “በሃይማኖት ሽፋን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚቃጡ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል /በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ እንደተዘጋጀው/ ያስችላሉ” የተባሉ ዕቅዶች ወጥተው በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡  

   የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ወጥመድ አስመልክቶ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ መምህራን ገለጻ በተደረገበት ወቅት መምህራኑ የችግሩን አያያዝ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ማኅበረ ቅዱሳን የሸመገለበት እና ምራቅ መዋጡን /ማስተዋሉን/ ያረጋገጠበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ መምህራኑ በገለጻው የሰሟቸውን የወጥመዱን መገለጫዎች ሁሉ ለአገልግሎት በተሠማሩባቸው ቦታዎች መታዘባቸውን በማረጋገጥ ድርጊቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ ሃይማኖት ተቋም የሚያፈርስ የወንጀል ተግባር በመሆኑ ተጠርጣሪዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ አሳስበዋል፤ እነርሱም መረጃውን ለተቋሙ ማኅበረሰብ በሙሉ የሚደርስበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ አሳውቀዋል፡፡

   ከ150 በላይ ሰባክያነ ወንጌል በተገኙበት እና በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ጸሎት ቤት በተካሄደው ተመሳሳይ የገለጻ እና ውይይት መርሐ ግብርም የሰባክያኑ ተባብሮ አለመሥራት ለችግሩ አስተዋፅኦ ማድረጉ በድክመት ታይቷል፡፡ ከእንግዲህ “በሰም እና ወርቅ መነጋገሩ” ቀርቶ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን በስሙ እና በግብሩ ፊት ለፊት የማጋለጡ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ምእመኑ አፍራሽ ትምህርቶችን ተሟግቶ በሚረታበት እና ኅሊናው በሚማረክበት የመሠረተ እምነት ትምህርቶች ላይ ማተኮር፣ የኑፋቄ አቀንቃኞቹ በአስተዳደራዊ መዋቅር ውስንነት እና የመረጃ እጥረት ላይ ተመሥርተው የሚፈጽሟቸውን እንከኖች ያለማሳለስ ማጋለጥ፣ ይህንንም ቤተ ክርስቲያኒቱን አዳክሞ ለመውረስ አልያም ከፍሎ ለመረከብ ከዘረጉት ወጥመድ ጋራ ማስተሳሰር፤ በቪሲዲ፣ በኅትመት እና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በኑፋቄ አቀንቃኞቹ መሠረታዊ ባሕርይ ላይ ተመሥርተው ሙሉ ሥዕል የሚሰጡ ሥራዎችን በማውጣት የተግባር ምላሽ መስጠት፣ በምእመኑ መካከል የሚኖረውን መተሳሰብ ማጎልበት፣ የሰባክያነ ወንጌል እጥረት ባለባቸው እና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በሠለጠኑባቸው አህጉረ ስብከት የተቀናጀ ስምሪት ማካሄድ ንቅናቄው በቀጣይ ምዕራፎቹ እንዲያተኩርባቸው የሚመከሩ አካሄዶች ናቸው፡፡

   አሁን ከሚታዩት የቅራኔዎች መባባስ ጋራ ብዙዎች ፓትርያርኩ መጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚጠመድበትን አጀንዳ የማቆየት የማስቀየሻ ስልት አድርገው ወስደውታል፡፡ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከተላለፉት ውሳኔዎች አንዳቸውም (ወ/ሮ እጅጋየሁ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ እንዳይገቡ የተወሰነውን ጨምሮ) አለመፈጸማቸው በግንቦቱ ሲኖዶስ ከፍተኛ የውዝግብ ጉዳይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል - በተለይም የአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ ካለበት ስፍራ በ20 ቀናት ውስጥ ተነሥቶ በመንበረ ፓትርያርኩ አለመቀመጥ፡፡ ያም ሆነ ይህ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉት የአገልግሎት አካላት ፓትርያርኩ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ወጥመድ ለመሥበር ለሚደረገው የጋራ ጥረት እየሰጡ ያሉትን አውዳሚ ምላሽ የተገነዘበ እና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ የገመገመ፣ አደጋው ከሚጠይቀው ተግባር ጋራ የተመጣጠነ አዲስ የአገልግሎት አቅም እና የአገልግሎት ዝግጁነት ስትራቴጂ እንዲያወጣ እየተጠየቀ ነው።

   ቸር ወሬ ያሰማን!!!!!    Post a Comment

   Blog Archive

   የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

   ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)