March 19, 2011

በጅማ በሃይማኖት ሽፋን ጉዳት ያደረሱ ወገኖች በቁጥጥር ሥር ባለመዋላቸው ቅሬታ እየቀረበ ነው


  • መንግሥት በግጭቱ “የአልሸባብ እጅ አለበት” ይላል:: ነዋሪዎች አልተቀበሉትም
(ሰንደቅ፣ በጋዜጣው ሪፖርተር፣ መጋቢት 7 ቀን 2003 ዓ.ም)፤ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በሊሙ ኮሳ ወረዳ ከሳምንት በፊት በተከሠተው የሃይማኖት ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ባለመዋላቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ነዋሪዎቹ ገለጹ፡፡ የጅማ ኢሚግሬሽን እና ደኅንነት ጽ/ቤት ያወጣው ደብዳቤ በበኩሉ፣ መንግሥት ባለው መረጃ የድርጊቱ ቀስቃሽ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ሳይሆኑ ከሶማልያ የመጡ የአልሸባብ አባላት መሆናቸውን፣ ስድስት የአልሸባብ አባላት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ሌላ ሃያ ተጠርጣሪ ተጨማሪ የአልሸባብ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ዐማኑኤል ዮናስ የጅማ አብያተ ክርስቲያን ሠራተኛ እና የቴዎሎጂ ኮሚቴ ሰብሳቢ በበኩላቸው፣ “የወረዳው መምህራን ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያኑን ሲያቃጥሉ ‹ተመልሰን ስንመጣ እናንተን ነው የምናቃጥላችሁ› ብለው ስለዛቱባቸው ከመንግሥታዊ አካል ዋስትና ይፈልጋሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያኑ እንዲቃጠል ካደረጉ ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከአካባቢው ሸሽተው ሄደዋል፡፡ ይህን ድርጊት ለመፈጸም ያበረታታቸው በውረዳው ውስጥ ያለው የአመራር አካል በቤተሰብ የተሳሰረ በመሆኑ ነው፤” ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሊሙ ኮሳ የፕሮቴስታንት እምነት አገልጋይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጹት፣ “በወረዳችን መጥታችሁ ኅብረተሰቡን ብትጠይቁ መንግሥት የለም ነው የሚላችሁ፡፡ በአካባቢው ያለው አመራር የችግሩ አንድ አካል ሲሆን አስፈላጊ ከሆነ እነማን እንዳደረጉ ስማቸውን በግልጽ መስጠት እንችላለን፡፡ በመሸፋፈን ከችግሩ መውጣት አንችልም፡፡ ከዋናው አመራር እስከ ሥራ አስፈጻሚው ድረስ የተያያዙ ናቸው፡፡ የትኞቹ አክራሪዎች መሆናቸውን እና እነማን በገጠር ውስጥ እየዞሩ እንደሚቀሰቅሱ እናውቃለን፤ ያላቸውን ጥላቻ ጭምር እናውቃለን፡፡ ከዚህ በላይ በችግሩ ውስጥ ለመቆየት ያለን ዋስትና ምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ የወረዳው ሓላፊዎች ሕገ መንግሥቱ ነው እያሉ ያሾፉብናል፤ ያፌዙብናል፡፡ የሚገርመው ግን የት ቦታ እንደሚሰበሰቡና እንደሚደራጁ እያወቅን መቆጣጠርም እየተቻለ ግፍ ተፈጽሞብናል፡፡” ብለዋል፡፡

አያይዘውም ግጭቱን ያሥነሳው “አልሸባብ ነው” የሚባለው ፍጹም ውሸት ነው፡፡ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት እስከ ነጋዴው ኅብረተሰብ ድረስ በአክራሪነት የተሳሰሩ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱን ስም ስጡ ተብለን ከተጠየቅን መስጠት እንችላለን፡፡ በአካባቢያችን ነዋሪ የሆኑ ከመስጊድ አስከ ወረዳ አመራር ተደራጅተው ራሳቸው የፈጸሙት ችግር እንጂ ሌላ ሦስተኛ ወገን ወደ አካባቢያችን መጥቶ የፈጸመው ድርጊት አይደለም፡፡ እሑድ የካቲት 26 ቀን 2003 ዓ.ም ሁለት ሺሕ የአክራሪ ሠራዊት ተደራጅቶ ሊያጠፋን ሞክሮ በሰዓቱ መከላከያ ሰራዊት በሄሊኮፕተር እየታገዘ ባይደርስልን ኖሮ ሁላችንም ጠፍተን፣ አልቀን ነበር፡፡ አሁንም የት እና ለማን መናገር እንዳለብን አናውቅም፡፡ የተደራጁ ሰዎች ተለቅመው ለሕግ አልቀረቡም፤ አሁንም በስጋት ላይ ነን፤” ብለዋል ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ለሰንደቅ እንደገለጹት፡፡

የሊሙ ኮሳ ወረዳ የጸጥታ ሓላፊ የሆኑት አቶ አሕመድ ሙሳ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ሰዓት በሊሙ ኮሳ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በየካቲት 26 ቀን 2003 ዓ.ም የተቃጠሉትን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “ችግሩን የፈጠሩት የአልሸባብ ቡድን አባላት ናቸው እየተባለ ነው፤ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?” ተብለው ለተጠየቁት አቶ አሕመድ ሲመልሱ፣ “ከአልሸባብ ጋራ የተያያዘ ጉዳይ አይደለም፡፡ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪ ሰዎች ናቸው ከአክራሪነት ጋራ በተያያዘ ችግሩን የፈጠሩት፡፡ በርግጥ ወደ ሐረር ተጉዘው የመጡ ሰዎች አሉበት ይባላል” ብለዋል፡፡

በአካባቢው ላይ የተፈጠረው የአክራሪነት ምንጩ ምክንያት ምንድን ነው ብለው ያስባሉ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፣ “ነገሩ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ሆኖም የሃይማኖት ሂደት ነው ብለው የሚያነሡ አሉ፡፡ በሌላ መልኩ ከዚህ በፊት ኦነግ የነበሩ ኀይሎች እንዲሁም በጠባብነት እና በትምክህት ውስጥ ያሉ ኀይሎች በነዋሪዎቹ ውስጥ በመገኘታቸው ይህን ግጭት ለዓላማቸው አውለውታል፤” ሲሉ አቶ አሕመድ ለሰንደቅ ገልጸዋል፡፡
 ++++++++++++++++++++++

(ሰንደቅ፣ መስከረም አያሌው፣ የካቲት 30 ቀን 2003 ዓ.ም)፤ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን አሰንዳቦ ወረዳ ሰሞኑን ተቀስቅሶ በነበረው የሃይማኖት ግጭት የተሳተፉትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እና ኮሚቴ መዋቀሩ ተገለጸ፡፡ የኦሮሞያ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንደገለጸው፣ ባለፉት ሳምንታት በእስልምና እና ፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች መካከል ተፈጥሮ በነበረው የሃይማኖት ግጭት ላይ በመሳተፍ ጸጥታን ሲያውኩ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እና ለፍርድ ለማቅረብ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች አብያተ እምነት እና መኖሪያ ቤቶቻቸው መቃጠላቸውን ያመለከተው የቢሮው መግለጫ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በንጹሐን ዜጎች ላይ በደል ያደረሱት እና ሌላ ተልእኮ ይዘው የተነሡ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)