March 13, 2011

ማን ለእስራኤል መድኃኒትን ከጽዮን ይሰጣል?

(በኤርሚያስ ኅሩይ በተለይ "ለደጀ ሰላም"):- ዓለምና በዓለም ያለው ማንኛውም ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ነገር ሁሉ የፍጥረታት በኹር የሆነውን የሰውን ልጅና ደመ-ነፍስ ያላቸውን እንስሳት አራዊት ጨምሮ ከሰው አእምሮ በላይ በሆነ ፍጹምና ረቂቅ አምላካዊ ጥበብ የሚያልፍ መሆኑ ማስረጃ የማይሻ እውነታ ቢሆንም ሰው በዚህች ምድር ላይ ሲኖር እያንዳንዷን የዕድሜውን ሽራፊ ደቂቃ በሚፈልገው ሁኔታና መጠን ተደስቶና ረክቶ ለመኖር ከሚያስችሉት እጅግ አስፈላጊ ነገሮች አንዱና ዋነኛው የሀገር ደህንነት ነው።

በርግጥ የበሽታ ጥሩ የደዌ  ደግ የለም ማንኛውም ሕመም ሥቃይ አለው፤ ታማሚውን ያሰቃያል፤ ቀጥሎም ቤተሰቡን ከዚያም ዘመድ ያስጨንቃል። ደግነቱ አባወራ ሲታመም እማወራ ወይም ወንድም ሲታመም እህት አብረው የመታመም የተፈጥሮ ግዳጅ ወይም ርግማን የለም፤ አንዱ ሌላውን እያስታመሙ እያከሙ መኖር ይቻላል። ይህ በሰው ልጆች እንጂ በእንስሳትና በአራዊት ሥርዓተ-ማኅበር ውስጥ ያልተለመደ የማኅበራዊ ኑሮ ሥርዓት ወይም ልምድ የምድራዊ ኑሮን ደስታና ርካታ የሚቃረነውን የጤና (ደህንነት) ቀውስ ለመቋቋም ተስፋ ሰጭ ኃይል ነው። ሀገር ከታመመ ሀገር በጽኑ ደዌ ከተያዘ ግን ተያይዞ ወደ መቃብር ከማምራት በቀር ማን አስታማሚ ማን አካሚ ሆኖ በጠበልም ይሁን በክኒን ሥቃይን አስወግዶ ወደ ደህንነት መመለስ እንደምን ይቻላል? አዎን ሀገር ከታመመ ወርቅና ብር ርባና የለውም ዕውቀትና ቁሳቁስም አንዳች አይፈይዱም እናም እንደገና ወደ ሀልዎት ለመመለስ ብቸኛው አማራጭ እንደ ቅዱስ ዳዊት "ማን ለእስራኤል መድኃኒትን ከጽዮን ይሰጣል?" እያሉ ወደ ታመነው ባለመድኃት ወደ እግዚአብሔር ማንጋጠጥ ብቻ ነው።

ለብዙ መቶ ዓመታት እስራኤላውያንን በአሕዛብ ሰይፍ ያስመታው የእስራኤል በፍቅረ-ጣዖት ደዌ መያዝ አስጨንቆት ነቢዩ ስለ ሀገሩ ደህንነት የጸለየውን ይህን ጸሎት ቃል በቃል ተቀብለን ስንዘምረው ስንጸልየው ኖረናል። ከዚህ በኃላ ግን ወደ ህልውናዋ ለተመለሰችው እስራኤል ሳይሆን ምናልባት በድህነትና በበሽታ አለንጋ የምትገረፈው ሳያንሳት የሃይማኖት ትንኮሳና ጥቃት ህልውናዋን ሊያሳጣት ዳር ዳር እያላት ላለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ "ማን ለኢትዮጵያ መድኃኒትን ከጽዮን ይሰጣል?" ብለን ወደራሳችን አምጥተን ልንጸልየው ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል።

ይህንን ለማለት ያስደፈረኝ "ትኩስ ሬሳ የኖረውን ያስነሳ" እንዲሉ ሰሞኑን አክራሪ ሙስሊሞች በጅማ እና በአካባቢው የፕሮቴስታንት ጸሎት ቤቶችና በተከታዮቻቸው ላይ ያደረሱት ጥቃት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጅማን ጨምሮ በሐረርና በአርሲ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ካህናትና በምእመናን ላይ የተፈጸመውን ታሪክ-የማይረሳው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እንዳስታውስ ግድ ስላለኝና በአጥፊዎች ላይ ርምጃ ተወሰደ ቢባልም የጥቃቱ አለመቆም እንደውም በኢኮኖሚና በአስተዳደራዊ ጉዳዮችም ጭምር በረቀቀና በተጠና ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉ መጻኢውን ጊዜ እጅግ አሳሳቢና አስፈሪ እንዳያደርገው ያሳደረብኝ ስጋት ነው።

በርግጥ አክራሪ እስልምና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ደህንነት ሥጋት ከሆነ ሰነባብቷል። ጽንፈኞቹም ጥቃታቸውን ቀጥለዋል መንግሥታቱም ከምንም በላይ ትኩረት ሰጥተውት የቤት ሥራቸውን ያለመዘናጋት እየሠሩ ይገኛሉ። በሀገራችን ግን ጥቃቱ በተወሰነ ጊዜ ልዩነት እያዘናጋ ድንገት የሚወርድ መቅሰፍት ሆኗል። ምናልባት ጥቃቱ በኛ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ ባለመሆኑ ወይም ደግሞ አጥቂም ተጠቂም የዚህች ጥንታዊት ቤ/ክ ህልውና ተፃራሪዎች ናቸው ብለን ጉዳዩን በቸልታ ልናልፈው አንችልም። ወደ እግዚአብሔርና ወደ ፍትሕ አካላት በአንድነት የሚያስጮኸን አጀንዳ ነው። ምክንያቱም የመግደል ሱስ የተጠናወተው ሲያመቸው ከመግደል ወደኃላ አይልም እናም ነገ እንዳለፉት ጊዜያት አንድ ሰሞን ተወርቶ ይረሳል ወይም የዘር የቋንቋ የፖለቲካ ስም እንዳይሰጠው ተፈርቶ ተዳፍኖ ይቀራል ብለው ጽንፈኞቹ ደም የጠማው ሰይፋቸውን በእኛም ቤ/ክ ላይ በድጋሚ ማንሳታቸው አይቀሬ ነው። ትልቁ አጀንዳቸውስ ምን ሆነና!

እውነት ነው ቀደም ብሎ ሁለቴ ሦስቴ ኦርቶዶክሳውያን ሲጨፈጨፉ የዛሬዎቹ ተጠቂዎች ከንፈር እንኳ አልመጠጡልንም። ሳንጠላቸው ጠልተውን "እሰይ!" ያሉም አይታጡም። ይሁን እንጂ አሁን ባለጽዋዎቹ እነርሱ ናቸው ብለን በተራችን እሰይ አንልም ይልቁንም ተባብሮ ተከባብሮ የመኖርን ባህል የሚያጠፉ የሀገርን ሰላምና አንድነት የሚያናግ ሰይጣናዊ እኩይ ተግባር ነው ብለን እንደ ቀዳሚነታችን ቀድመን እናወግዛለን። በዚህ አጋጣሚ የኢ/እ/ም/ቤት ኃላፊዎች ጥቃቱን ማውገዛቸውንና  አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቃቸውን አደንቃለሁ። ኃላፊነታቸው ግን ማውገዝ ወይም ጋዜጣዊ መግልጫ መስጠት ብቻ ነው ብዪ አላምንም። ምክንያቱም ጽንፈኞቹ ከየትም የመጡ አይደሉም ከሕዝቡ መካከል የወጡ እንጂ። እናም የአሁኖቹ ተይዘዋል ቢባልም ነገ ከተከታዮቻቸው ውስጥ ሌሎች ላለመነሣታቸው ማረጋገጫ የለም። ክርስቲያኑም ሕዝብ ምንም እንኳ ክርስትና ለሃይማኖት መሞትን እንጂ መግደልን የማታስተምር "ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው" ብላ የምትሰብክ የፍጹምነት ሕግ መስካሪ ብትሆንም የእናት የአባቱ የወንድም የእህቱ ደም ሲፈስ አካላቸው በሰይፍ ሲከተፍ ወገን ከቀዬው ተፈናቅሎ ዱር ለዱር ሲንከራተት እያየ ሕመሙን ሥቃዩን አፍኖ መኖር ተስኖት ያመረረ ዕለት ደዌው የሀገር ደዌ የሀገር ሕመም ይሆንና ለቤትም ለጎረቤትም ምጥ እንዳይሆን የዚህን ክፉ ደዌ አማጭ ቫይረሶች አጋልጦ ለሕግ በማቅረብና ወጣቱን ትውልድ በማስተማርና በቅርብ በመከታተል ሀገራዊና ሃይማኖታዊ አደራቸውን ከክርስትያኑ ጋር በመተባበር ጠንክረው ሊሠሩ እንደሚገባ ይሰማኛል።

ይህን ማለቴ ኢትዮጵያ ሀገራችን ትታወቅበት ከነበረው የሕዝቦች ተባብሮና ተከባብሮ የመኖር የረጅም ጊዜ ባህል በጽንፈኞች ጥቃት ምክንያት እየሻከረ መጥቶ አሁን በዓይነ-ቁራኛ እየተጠባበቁ ለመኖር ግድ የሚሉ ሁኔታዎች መከሰታቸው ለነገይቱ ኢትዮጵያ ህልውና ስላሰጋኝ እንጂ ለመተንበይ ወይም ለማስፈራራት አይደለም። አዲሱ ትውልድ "ለምንድነው ግን የሚገድሏቸው? መሬቱን የፈጠሩት እነሱ ናቸው እንዴ? ሕጉስ ቢሆን የክርስቲያኖችን የእምነት ነፃነት አያስከብርም እንዴ?" ወዘተ ብሎ እየጠየቀ ነው። መልሱ ግን አሁን ከሚያየው እውነታ ጋር አልተጣጣመለትም። እናም  "ዳሩ ሲፈታ መሀሉ ይፈታ" እንደሚባለው ትናንት ሐረር፣ ጅማ እና አርሲ ዛሬ በድጋሚ ጅማ እና አካባቢው ነገ ናዝሬት፣ አዲስ አበባ... ትናንት ኦርቶዶክስ ዛሬ ፕሮቴስታንት ነገ ካቶሊክ ወይም በድጋሚ ኦርቶዶክስ! የሚል ጥርጣሬ በዚሁ አዲሱ ትውልድ ላይ አሳድሮበታል።  እና እንግዲህ ለዚህች ሀገር የሚበጀው ሰላም፣ ልማት፣ አንድነት ነው ወይስ እያታለሉ ወይም በሰይፍ እያስፈራሩ ሰውን ከአንዱ እምነት ወደ ሌላው እምነት ማፍለስና በዚህ ሳቢያ በሚከሠት ግብግብ መተላለቅ? ለአዲሱስ ትውልድ የምናወርሰው ፍቅር አንድነትን ወይስ የደም ዕዳ?

በመሆኑም አብያተ ክርስቲያናት የዶግማ ልዩነታቸውን በጉያቸው ይዘው እርስ በእርስ ከመተነኳኮል ይልቅ ይህን የሀገር ደዌ የሆነ የጽንፈኞች እብሪትና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በጋራ ማውገዝና ከመንግሥትና ሰላማውያን ከሆኑት የእምነቱ ተከታዮች ጋር ጭምር በመሆን የአክራሪነት ጥቃት ሥጋት ተወግዶ ሕዝቡ እንደ ጥንቱ ተባብሮና ተከባብሮ የሚኖርበትን ሁኔታ በትምህርትና በቅርብ ክትትል ለማስፈን ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት ፈተና ሊታደጓት በጸሎትም ጭምር ሊተጉ ይገባል።   

መንግሥትም ቢሆን ጉዳዩን ከፈጠረው ውጥረትና ካደረሰው ጉዳት ባሻገር ወደፊት ሊያስከትል የሚችለውን የጥፋት ማዕበል ተመልክቶ ከወዲሁ የሚጠበቅበትን ተግባር ሊፈጽም ይገባል። "የሃይማኖት መቻቻል" ብሎ ችግር ሲፈጠር ብቻ በሚድያ መተንተኑ በቂ አለመሆኑን የአሁኑ ጥቃት የሚያስገነዝብ ይመስለኛል። እንደውም እኮ ይህ መሪ ቃል ሚናውን ያልለየ ለሚመለከተው ሁሉ በትክክል የተላለፈ አለመሆኑ እብሪተኞቹ እንኳን ሳይነኩ ቢነኩ እንኳን ወደ ሕግ አቤት ሊሉ ሲገባቸው እንደ ፊልም አክተር በጠራራ ፀሐይ እየተኮሱ ሰይፍ እየመዘዙ ንፁሀንን ለመጨፍጨፍ አቅም የፈጠረላቸው ይመስላል። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ የሰዎችን የእምነት ነፃነት እና መብት ብቻ ሳይሆን  በጠቅላላው የሰብአዊ መብትንና ሕገመንግስትንም መተላልፍ ጭምር ነው። እንደሚባለው የቁርአ ገጾች ሽንት ቤት ተገኝተው ቢሆን እንኳን ይህንን አሳፋሪ ድርጊት የፈጸመውን ሰው ሥርዓት በሚፈቅደው ሁኔታ በሕግ መጠየቅ ነው እንጂ ሆ! ብሎ ሀገር ማወክ ግን ሕጋዊ አካሄድ አይደለም። ተገቢ ቢሆንማ በየቀኑ ከክርስትያናዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ከተገነጠሉ ገፆች ሸቀጥ ጠቅልለው ከሚሸጡልን የመንደር ሱቆች ጀምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገዙ እስከሚያቃጥሉት ቡድኖች ድረስ ከዓመታት በፊት ጦርነት ልንከፍት በተገባን ነበር። ነገር ግን ዜጋ የዜግነት መብትና ግዴታውን የሚያገኘው በጉልበቱ ሳይሆን በሕግ መሆኑን ስለሚያምን ክርስቲይኑ ሕዝብ እስካሁን በእድር፣ በማህበር ተባብሮ ከመኖር በቀር በሙስሊም ወገኖቹ ላይ ጥቃት አድርሶ አያውቅም። በመሆኑም ይህ መንፈስ በሁሉም እምነት ተከታዮች ዘንድ እንዲሰፍን መንግስት ጉዳዩን ለሃይማኖት መሪዎች ብቻ ሳይተው በባለቤትነት ሊከታተለውና በተያዙት ወንጀለኞችም ላይ አስተማሪ የሆነ ሕጋዊ ርምጃ ሊውስድ ይገባል።

የሰላም አምላክ ለሀገራችን ሰላምን ይስጥልን!
         

Be'seme Selassie,
Selam Deje Selamoch,
kezih debdabe gar abari adrege bewektawi guday lay yemetatekur tsehuf lekelachehwalehu. le metomeriya getsachehu yemetmeten kehone leanbabi adresulegn. Selame Egizabher kenante gar yehun,
Ermias Heruy
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)